ካለፈው ሐሙስ አንስቶ የተካሄዱ የ7ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ በተከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ተደምድመዋል። በዚህ ሳምንት ጨዋታዎች የደረጃ ሰንጠረዡ መሪዎች የተቀያየሩበት ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን ያልተጠበቁ አበይት ክስተቶችም ተስተናግደዋል።
የአምናው ቻምፒዮን ፋሲል ከነማ (አፄዎቹ) ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ሲዳማ ቡናን በሰፊ ውጤት ያሸነፉበት ጨዋታ የሳምንቱ ትልቅ ክስተት ነው። አጼዎቹ በመጀመሪያዎቹ 18 ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው 3 ግቦችና ከእረፍት መልስ በ47ኛ ደቂቃ በተቆጠሩ ግቦች 4 ለ 0 በማሸነፍ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።
ገና 3ኛው ደቂቃ ግብ ባስተናገደው ጨዋታ ዓለምብርሀን ይግዛው አፄዎቹን መሪ ያደረገ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በ16ኛውና 18ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን እንዲሁም ኦኪኪ አፎላቢ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ግቦች ፋሲል ከነማን ወደ አሸናፊነት አንደርድረዋል። ገና በጊዜ ሶስት ግቦችን ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ኳስ ይዘው በቀላሉ ወደ ፋሲል ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረዋል።
በአንፃሩ አፄዎቹ በፍጥነት ወደ ግብ ይዘዋቸው የሚሄዱ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩ እንደሚችሉ አመላካች ነበሩ። የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ገና በጊዜ ነበር ግብ ያስተናገደው። በረከት ደስታ የአፄዎቹን መሪነት ወደ 4 ለ 0 ከፍ ማድረግ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎም ፋሲል ከተማ ነጥቡን 15 በማድረስ የሊጉ አናት ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና በነበረው 7 ነጥብ የሚቆይ ቢሆንም በተቆጠሩበት ግቦች ምክንያት ከ11ኛ ወደ 13ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። በ7ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ ባህርዳር ከተማን ከወላይታ ድቻ አገናኝቶ በባህርዳር ከተማ የ3 ለ 1 ድል ጨዋታው ተጠናቋል።
ባህርዳር ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን አድርገዋል።
በ18ኛ ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማዎች ቀዳሚ መሆን የሚችሉበትን ግብ በፍፁም አለሙ አማካኝነት ማግኘት ችለዋል። በ38ኛ ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ የጣና ሞገዶቹን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ ማድረግ ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀርም ምንይሉ ወንድሙ ለጦና ንቦች ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል።
ባህርዳር ከተማ ጅማ አባጅፋርን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለቱንም ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው ኤርትራዊው አሊ ሱሌማን 65ኛው ደቂቃ ላይ ከፍፁም አለሙ የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ግብ በማድረግ የጣና ሞገዶቹን ሶስተኛ ግብ አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎም ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 13 በማድረስ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ቢያሸንፍ ኖሮ መሪነቱን ድጋሚ መያዝ ይችል የነበረው ወላይታ ድቻ በእኩል 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ወደ 3ኛ ደረጃ ተንሸራቷል።
በአዳማ ከተማና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የተደረገው የ7ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው አዳማ ከተማዎች የፈጠሯቸውን በርካታ ዕድሎች በአጨራረስ ድክመት ምክንያት ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል የነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ደካማ ሆኖ ታይቷል፡፡
ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ በ8 ነጥብ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ፈረሰኞቹ በ11 ነጥብ በነበሩበት 5ኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጡ ችለዋል፡፡ በ7ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ በአቡበከር ናስር ሁለት ግቦች ቡናማዎቹ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። አቡበከር ናስር ሁለቱን ግቦች ከመረብ ያሳረፈውም በፍጹም ቅጣት ምት ነው።
ይህም ሊጉ ከተጀመረ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች ከግብ ርቆ የነበረው አቡበከር ናስር በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ተርታ መመደብ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 11 በማድረስ ደረጃውን ወደ 6ኛ ያሳደገ ሲሆን ሽንፈት ያስተናገደው ድሬደዋ ከተማ በ8 ነጥብ ወደ 10ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። በ7ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቅድሚያ የተገናኙት አርባምንጭ ከተማና ጅማ አባጅፋር ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ አጠናቀዋል።
ውጤቱን ተከትሎም ነጥቡን 10 ማድረስ የቻለው አርባምንጭ ከተማ በግብ ክፍያ በልጦ ደረጃውን ወደ 8ኛ ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ በዓመቱ የመጀመሪያ ነጥቡን ያገኘው ጅማ አባጅፋር በ1 ነጥብ ሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ጥሩ ፉክክር በታየበት የሐዋሳ ከተማና የሰበታ ከተማ ጨዋታ ገና በ10ኛው ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ በግንባሩ ባስቆጠረው ግብ ሰበታ ከተማን መሪ ያደረገ ሲሆን፣ ከግቡ መቆጠር በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች መልስ ለመስጠት ሶስት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁባቸው። በ13ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ሐዋሳን አቻ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል።
35ኛ ደቂቃ ብሩክ በየነ ሀዋሳ ከተማን መሪ ያደረገ ግብ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ መስፍን ታፈሰ የሀዋሳ ከተማን መሪነት ከፍ ያደረገ ግብ አስቆጠረ። በዚህም ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 10 በማድረስ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ በውድድር ዓመቱ እስካሁን ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው ሰበታ ከተማ በ4 ነጥብ ባለበት 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።
በውድድር ዓመቱ 3 አቻ ተለያይቶ 3 የተሸነፈውና ምንም ማሸነፍ ያልቻለው ሀድያ ሆሳዕና በሀብታሙ ታደሰ ሁለት ግቦች መከላከያን አሸንፏል። 22ኛ ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ በሀብታሙ አማካኝነት ሲያስቆጥሩ ይኸው ተጫዋች በሁለተኛው አጋማሽ ሁለተኛ ግቡን በማስቆጠር ሃዲያ ሆሳዕና ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል። ውጤቱን ተከትሎም አሸናፊው ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 6 በማድረስ ወደ 14ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መከላከያ ባለበት 10 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2014