በዛሬው አዲስ ዘመን ዱሮ እትማችን ጋዜጣው ከ1950 እስከ 1970ዎቹ ይዟቸው ከወጣ ዘገባዎች መካከል የውጭ ሀይሎች በኢትዮጵያ ላይ ያደርጉ የነበረውን ጣልቃ ገብነት እንዲሁም አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም የሚያሰራጩዋቸው ሀሰተኛ መረጃዎች ተገቢነት የሌላቸው መሆናቸውን የሚመለከቱ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡ ዘገባዎቹ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ላይ ከሚስተዋለው ጣልቃ ገብነት እና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ጋር የሚመሳሰሉ መሆናቸው የዛሬው የአምዳችን ምርጫ አርገናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ታይም መጽሔት ካልታረመ በኢትዮጵያ አይፈለግም
ታይም ማጋዚን የተባለው አሜሪካዊ መጽሔት ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እየደጋገመ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰጠው አስተያየት ከእውነት የራቀ አድርባይነት ያለው ከአግባብ የወጣ የፈጠራ ወሬ ያለበት በመሆኑ ለአስተዳዳሪዎቹ ተደጋግሞ ማሳሰቢያ እንዲደርሳቸው ሳይደረግ አልቀረም ነበር፡፡ እንዲሁም ለተጻፉት ስሕተቶችና ዘለፋዎች ማስተባበያና ማስተካከያ ያወጡ ዘንድ በየጊዜው ተጽፎላቸው ሳለ ነገር ግን እንደተጠየቀው አልፈጸሙም በነሱ በኩል አንድም ፈቃድ አላሳዩም፡፡
ይኅ የተባለው መጽሔት ዘገባውን በማጋነን በማወላገድ በማሳሳትና በማሽሟጠጥ የሚያደርገውን ምን እንኳን እውነተኛውን ነገር ለመለወጥና እውነት ፈላጊዎችን ለማሳሳት የማይቻለው መሆኑ ቢታወቅም፤ ይኸን እየደጋገመ የሚሠነዝረውን የተንኮል ሥራ እያዩ ቸል ብሎ መተው የማይገባ በመሆኑ፤ ከሰኔ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ እንዳይገባ ይከለከል ዘንድ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ውሳኔ አድርጓል፡፡ (ሰኔ 12 ቀን 19 55)
የሊባኖስ ጋዜጣ የፀረ ኢትዮጵያ ዘመቻ
ስምምነት መደረጉን ገለጠከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) አልከሩ አል አረቢ የተባለው የሊባኖስ ጋዜጣ፤ በቅርቡ ባወጣው እትሙ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የግብፅ ፕሬዚዳንትና የአድኃሪ የአረብ መንግሥታት መሪዎች ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ዘመቻቸውን ለማፋፋም መስማማታቸውን ገልጧል፡፡ ጋዜጣው በዚህ ጽሑፉ በዋሽንግተን ዕቅድ መሠረት እነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ አካባቢዎች ሱዳንና ግብፅ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ፍላጎታቸው መሆኑን አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካና የአድኃሪ ገዥ መደቦች ለዚሁ ፀረ ኢትየጵያ ሠፈር መሪ እንዲሆን በየመን ዓረብ ሪፑብሊክ የቀድሞው የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበረው መታጨቱን ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡ ይኸው ፀረ ኢትዮጵያ አድኃሪ ሠፈር በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ላይ ለሚያካሂዱት ሤራ ከአሜሪካና ከምዕራብ ጀርመን ርዳታ የሚያገኝ መሆኑን አልከሩህ አል አረቢ በፅሑፉ ጨምሮ አመልክቷል፡፡ (ጥር 4 ቀን 1970 ዓ.ም)
የምዕራባውያንን የምሥራቅ አፍሪካ ጣልቃ ገብነት ጋዳፊ አወገዙ
ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በምታካሂድበት የአፍሪካ ቀንድ ክፍል የምዕራብ አውሮፓውያን ጣልቃ መግባት ይዞታው የበለጠ እንደሚያባብሰውና የመላው አፍሪካውያንንም ፀጥታ እንደሚያሰጋ የሊቢያ ጀማሂሪያ መሪ ኰሎኔል ሞዋመር ጋዳፊ የገለጡ መሆናቸውን ከኒዠር ዋና ከተማ ኒያሚ የደረሰን ዜና አስረዳ፡፡ ኰሎኔል ሞዋመር ጋዳፊ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በተለይም ፈረንሳይ በአፍሪካ የውስጥ ጣልቃ መግባትን አደገኛነት በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል፡፡
የሊቢያ ጀማሂሪያ መሪ በኒዠር ጉብኝታቸው ወቅት ባሰሙት ንግግር አፍሪካ ራሷን በኢኮኖሚና በፖለቲካ መንገዶች ነፃ ካላወጣች ትርጉም ሊኖረው እንደማይችል ገልጠዋል፡፡ ኰሎኔል ሞዋመር ጋዳፊ በምስራቅ አፍሪካ አገሮች የሚደረገው ጣልቃ ገብነት መወገድ ያለበት መሆኑን ጨምረው ገልጠዋል፡፡ (ጥር 17 ቀን 1970 ዓ.ም )
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ሴራ ፕራቭዳ በጥብቅ አወገዘ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና አካባቢዋ ላይ በመካድ ላይ ያለው ሁኔታ በአፍሪካ አህጉር በማደግ ላይ የሚገኙትን አገሮች ክብርና ነፃነት ለማዳከም በኢምፔሪያሊዝምና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የታቀደ አደገኛና አዲስ ሁኔታ መሆኑን ፕራቭዳ የተባለው የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ልሳን ትናንት ገለጠ፡፡
ፕራቭዳ ትናንት ባወጣው አስተያየት ይኸው በኢምፔሪያሊዝምና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የሚደረገው ሤራ በእሳት እንደ መጫወት የሚቆጠር መሆኑን አስመልክቶ ይህንኑ ሤራ በአፍሪካ በመላው ዓለም ሕዝቦች ላይ የሚውጠነጥኑት ክፍሎች ሁሉ በኃላፊነት የሚጠየቁ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
የሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፕራቭዳ በዚሁ አስተያየቱ ኢምፔሪያሊስቶችና አድኃሪ የዓረብ አገር ገዥ መደቦችና ደጋፊዎቻቸው ሌላ አገር ኅብረተሰባዊነትን የዕድገቱ መመሪያ አድርጎ የመምረጡን ሁኔታ ማቆም እንደማይችሉ ገልጧል፡፡
ቀጥሎም አዲስ የሶሻልና የኢኮኖሚ ሥርዓት ፕሮግራም ያወጀው አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር ተራማጅ ለውጦች በማድረግ ላይ መሆኑንና ከመላው ዓለም ተራማጅ ኃይሎችና ሶሻሊስት አገሮች ጋር የመረዳዳት አቋሙን በማጠናከር ላይ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ፕራቭዳ ከዚሁ በማያያዝ በኢትዮጵያ የሚካሄደው አብዮት በጣም እየገፋ መሔዱንና ይህም ርምጃው ኢምፔሪያሊስቶችንና አድኃሪያንን ያስደነገጣቸው መሆኑን ገልጧል፡፡ ስለዚህም የውስጥ ፀረ አብዮትን ከመደገፋቸውም ሌላ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ግጭት እንድትጀምር በመገፋፋትና ተገንጣዮችን በማደፋፈር አገሪቱን በመገነጣጠል አሁን በመካሔድ ላይ ያለውን አብዮት ለማዳከም ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድቷል፡፡
ቀጥሎም ኢምፔሪያሊዝ በአፍሪካ አህጉር የብሔሮች ነፃነት ንቅናቄዎችና ተራማጅ እንቅስቃሴን ለመግታት እንዲችል በምስራቅ አፍሪካ (በአፍሪካ ቀንድ) ክፍል ዋና ሠፈር የማዘጋጀት ተስፋ ያለ መሆኑን ገልጧል፡፡ የዓለም ኅብረተሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው የኢምፔሪያሊስት ሤራ በጥብቅ እንደሚያወግዘው ፕራቭዳ አመልክቶ ቀና መንፈስ ያላቸው ሕዝቦች ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሙሉ አባል በሆነች አገር የውስጥ ጉዳይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልጧል፡፡ (ሰኔ 13 ቀን 19 55ዓ.ም)
የሞቃዲሾ ሬዲዮ ውሸት አይታክተውም
ባለፈው ሀሙስ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ወሰን ላይ ተኩስ የተከፈተው የኢትዮጵያ ጸጥታ አስከባሪ ወታደሮች ምግብ ስለአለቀባቸው ነው ሲል የሞቃዲሾ ሬዲዮ የሰጠው ሀተታ ፈጽሞ ከእውነት የራቀና መሰረት የሌለው መሆኑን አንድ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡ ቃል አቀባዩ ንግግሩን በመቀጠል የሞቃዲሾ ሬዲዮ ይህን የመሰለ የኢትዮጵያ ወታደሮች ያላቸውን የመልካም ስም ሬኮርድ ለማጉደፍ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች ያለእንዳች ችግር የእናት አገራቸውን ግዛት መብት ለማስከበርና ጸጥታ ለመጠበቅ የሚስችላቸው በቂ ምግብ ያላቸው መሆኑንና ወታደሮቹም በመልካም ስነ ስርአት ስራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ማንኛውም ሰው ቢሆን ወሰ ወሰኑ አካባቢ ሄዶ ሊመለከት ይችላል ካለ በሁዋላ የሶማሊያ ወታደሮች የዳሬሰላሙን ስምምነት በመጣስ ባለፈው እሁድ ከአስር ሰአት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 3 ሰአት ድረስ ዶሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ተኩስ ከፍተዋል በማለት ቃል አቀባዩ ንግግሩን ፈጽሟል፡፡ (መጋቢት 2 ቀን 1956 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5/2014