በዓለም አደባባይ የአትሌቲክስ ስፖርት ክብርና ዝናን የደረበችው ኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የስፖርቱ እምቅ አቅም ያላቸው ባለ ተሰጥኦ ወጣቶች በስፋት ይገኙባታል። የአየር ሁኔታን፣ የቦታ አቀማመጥን እንዲሁም የአኗኗር ሁኔታን ተከትሎ ብዙዎችን ገና በታዳጊነታቸው የሚስበው የአትሌቲክስ ስፖርት፤ በብቃታቸው የተመሰከረላቸውን ተተኪ አትሌቶች ከማሰልጠኛ ማዕከላትና ጣቢያዎች ለክለቦች ያቀብላል።
በርካቶችም በክለቦች ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገር አቀፍ እስከ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተካፍለው ድልና ዝናን ይጎናጸፋሉ።
በመሆኑም ክለቦች የአትሌቶችን አቅምና ተሰጥኦ በተጨባጭ ወደ ውጤታማነት የሚያሸጋግሩ መሆናቸው አያከራክርም። በኢትዮጵያ አንጋፋና በርካታ የስፖርቱን ከዋክብት ያፈሩ የአትሌቲክስ ስፖርት ስመጥር ክለቦች አብዛኛው መቀመጫም በአዲስ አበባ ነው። ከተማዋ አንደኛ ዲቪዚዮን ሰባት ክለቦች እንዲሁም በሁለተኛ ዲቪዚዮን 15 ክለቦችን በመያዝ ከቀዳሚዎቹ መካከል ብትሰለፍም በአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ ግን ስሟ የሚነሳው በደረጃ ሰንጠረዦች ቀዳሚ ስፍራ ላይ አይደለም።
ዓለም ያደነቃቸው ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ያቀፉ ክለቦች መናገሻ የሆነችው አዲስ አበባ በአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ውጤት ማጣቷ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ጥያቄ ያስነሳል። የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራሁ ገብሬ፤ ፌዴሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ እየሰራ መሆኑን ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት አዲስ አበባን በአትሌቲክስ ውጤታማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ቃለምልልስ ጠቁመዋል። ከተማዋ በርካታ አትሌቶችን በስሯ እንደመያዟ ውጤታማ ያልሆነችበት ምክንያት በዋናነት በክለቦችና ማናጀሮች መካከል ባለው ክፍተት መሆኑን የገለፁት ሃላፊዋ፣ በተለይም ውጤታማ የሚባሉት አትሌቶች ክለብ እያላቸውም በማናጀር ውድድሮች ላይ መሳተፋቸው ለከተማዋ ውጤት ማጣት አንዱ ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ።
በዚህም አትሌቶች ጉዳት በማስተናገድና በሌሎች ምክንያቶች ክለቦቻቸውንም ጭምር በተገቢው መልኩ ሲያስተናግዱ አይታይም። በመሆኑም ክለቦችንና ማናጀሮችን ለማነጋገር በፌዴሬሽኑ በኩል መታቀዱን ያስረዳሉ። እንደ ሃላፊዋ ገለፃ፣ በሌሎች ክልሎች ያሉ ክለቦች ውድድሮች ሲኖሩ አትሌቶቻቸው ክልሉን እንዲወክሉ ይደረጋል፤ በከተማዋ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ይለያል። በመመሪያው ላይ ክለቦች ለከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው የሚጠቁም አሰራር አለ፤ ነገር ግን ፈቃደኛ አይደሉም።
ይህንን ችግር ለመፍታትም ፌዴሬሽኑ በሕጉ መሰረት እንደሚሰራ ክለቦችም ይህንኑ እንደሚተገብሩት ንግግር ተደርጓል። የአገሪቷን የአትሌቲክስ ስፖርት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ቢቻል ክልሎችን ከክልሎች፤ ክለቦችንም ከክለቦች በማወዳደር ከሁለቱ የተውጣጡ ምርጥ አትሌቶችን ከሁለቱ በማውጣጣት አወዳድሮ አገርን የሚወክሉ አትሌቶችን ማፍራት የሚቻልበት አሰራር እንዲፈጠር ማድረግ ይገባል ይላሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት በእቅድ ይዞ ነገር ግን ያላከናወናቸውን እንዲሁም በዓመቱ የታቀዱ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዋ ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ተግባራት መካከል ቀዳሚው የማዘውተሪያ ስፍራ ጥገና ሲሆን፤ በጃንሜዳ ለሩጫ አመቺ እንዲሆን ሥራዎች ተከናውነናል።
ጃንሜዳ በተለይም ከኮቪድ 19 ስርጭት ጋር ተያይዞ ለከተማዋ የአትክልትና ፍራፍሬ መገበያያ ሆኖ በመቆየቱ የተነሳ ሜዳው እንደቀድሞ ለልምምድ እንዲሁም በቀጣይ ለሚካሄደው አገር አቋራጭ ውድድር አመቺ አልነበረም። በመሆኑም አትሌቶች ከከተማዋ ለመውጣትና በተሻለ ሜዳ ከፍለው ስልጠናቸውን ለመቀጠል ተገደው ነበር። ይህን የተመለከተው ፌዴሬሽንም በማጸዳትና ጥርጊያ በማድረግ አትሌቶች እንዳይቸገሩ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል።
በቀጣይም በቦታው የሚኖሩ ቀሪ ሥራዎች በፌዴሬሽኑ በኩል እንደሚሰሩ አስረድተዋል። አዲስ ዘመን ስሰኞ ፖርት ይህ ቦታ ለማስታወቂያ ክፍት ነው! የታዳጊ ወጣቶችን ከማፍራትና ሥልጠና ጣቢያዎችን ከመደገፍ አንጻርም የሕጻናት ልዩ ሥልጠና ጣቢያዎችን በመክፈት ፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች (ስብስቴ እና ወንዲራድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች) የሕጻናት የሥልጠና ፕሮግራም የተከፈተ ሲሆን፤ በእነዚህ ማሰልጠኛዎች ሜዳና አስፈላጊ ነገሮችን ለማመቻቸት ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫም አንድ የሥልጠና ጣቢያ በገንዘብ ለመደገፍ በማሰብ ከፌዴሬሽኑ ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል። ይህ ጅምር መሆኑን የሚጠቅሱት ኃላፊዋ በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅም ይገልጻሉ።
ውድድርን ጨምሮ በማሰልጠኛ ማዕከላትና ክለቦች ሥልጠናም በቀጣይ በመደገፍ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር ላይ አተኩሮ ፌዴሬሽኑ ሥራዎቹን እንደሚያከናውን ኃላፊዋ ይጠቁማሉ። ከመደበኛው ስራ ጎን ለጎንም ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ በአጠቃላይ ለመከላከያ እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን 700ሺ ብር የሚደርስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ፌዴሬሽኑ ሲሰራ መቆየቱን አያይዘው ገልጸዋል።
ይሁንና ፌዴሬሽኑ ለሚከውናቸው ሥራዎች እንቅፋት የሆነው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በኮሚሽኑ በኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። ሌሎች ስፖርቶች እንደሚሰሩት ማዘውተሪያዎች ሁሉ አትሌቲክስም ቢታሰብና በየአካባቢው ጥርጊያ ሜዳዎች ቢስፋፉ እንዲሁም ከተማዋን የሚወክል ክለብ እንዲኖር ፌዴሬሽኑ እያደረገ ላለው ጥረት ድጋፍ እንዲደረግለትም ኃላፊዋ አክለዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014