የምንኖርበት ዘመን ጦርነት የቀነሰበት እና ዲፕሎማሲ የገነነበት ነው፡፡ አገራት ጦርነት ውድ እንደሆነ ተገንዝበው ዲፕሎማሲን እንደ ብቸኛ አማራጭ ለመውሰድ እየመረጡ ነው፡፡
በዚህም የተነሳ የዲፕሎማሲ ሥራ ዋጋ ቀን በቀን እየጨመረ ነው፡፡ መሪዎች እና እነሱ የሚልኳቸው ዲፕሎማቶች ጥቁር ሱፋቸውን ለብሰው ከአንዱ ስብሰባ ወደ ሌላው ስብሰባ ሲሮጡ ፤ ከአንዱ አውሮፕላን ወርደው ወደ ሌላው ሲሳፈሩ ፤ ከአንዱ ሆቴል ወደ ሌላው ሲሽከረከሩ ነው የሚውሉት፡፡
በጠረጴዛ ዙሪያ ለሚያደርጉት ዋነኛ ትግል ግን ይዘው የሚቀርቡት የመደራደሪ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን አጀንዳቸውን ቅቡልነት እንዲያገኝ ማድረግ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ ነው፡፡ ከነዚህ መሀከል አንዱ ደግሞ ፋሽን ነው፡፡ ተንታኞች እንደሚሉት፤ አሁን ላይ በተለይ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ መሪዎች እና ዲፕሎማቶች በፋሽን በኩል በቃል ሊነገሩ የማይችሉ መልእክቶችን ማስተላለፍ ላይ በርተትዋል፡፡
በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ተሹሞ ከ2013 እስክ 2017 እ.ኤ.አ ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ዋነኛ የፕሮቶኮል ሃላፊ የነበረው ፒተር ሰልፍሪጅ እንደሚለው ከሆነ ፋሽን ለዲፕሎማሲው ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ ዋሽንግተን ዲፕሎማት የተባለ ገጸ ድር በኖቬምበር 29 ቀን 2016 እ.ኤ.አ ‘Diplomacy By Design’ Examines What Clothes Say About Us በሚል ርእስ ባወጣው ዘገባ ሰልፍሪጅ የሚከተለውን ማለቱን ዘግቧል፡፡ “ፋሽን ሁሉም ቦታ አለ፡፡ ፋሽን ቋንቋ እና ባህልን ይሻገራል፡፡
በፋሽን አንዲትም ቃል ሳታወጣ ብዙ ነገር መናገር ትችላለህ፡፡ የአንድ አገር ባህል እና ቅርስ ለመረዳትም ከፋሽን የተሻለ መንገድ የለም፡፡” በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ጆን ኬሪም በአንድ ዝግጅት ላይ እንደተናገሩት ፋሽን የአሜሪካ የዲፕሎማሲ ሥራ አንድ አካል ነው፡፡ “የምንፈጥራቸው አልባሳት ፤ የምንመገበው ምግብ ፤ የምንጫወታቸው ስፖርቶች እና የምናከብራቸው በዓላት የአንድ አገር ማንነት መገለጫ ናቸው፡፡ ስለዚህም የአገራት
ግንኙነት አንድ አካል ናቸው፡፡ ሁላችንም እንደመናውቀው አሜሪካ በዓለም ያላት ቁመና የሚገለጸው በፖለቲካ እና ጸጥታ ፖሊሲዎቻችን ብቻ አይደለም፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች እንዳየነው ፋሽን በመደበኛው ዲፕሎማሲ ስራ ሊሳኩ ያልቻሉ ጉዳዮች በባህል ዲፕሎማሲ እንዲሳኩልን አድርጓል” ብለው ነበር፡፡
ባለሥልጣናት በአብዛኛው የሚለብሱት ልብስ የተለመደውን ሱፍ ነው፡፡ ልብሱ በአብዛኛው ጥንቁቅነትን፤ ሃይልን እና ብቃትን ያሳያል የሚል እምነት ስላለ ነው ፖለቲከኞች የሚያዘወትሩት፡፡ ነገር ግን ይህ አለባበስ በራሱ በሕዝቡም ሆነ በፋሽን ሀያሲያን ብዙ ትንታኔ የሚሰጥበት ነው፡፡
በዚህም የተነሳ ፖለቲከኞች የተለመደውን ሱፍ ሲለብሱ እንኳን ለቀለም ምርጫቸው ይጠነቀቃሉ፡፡ የትኛው ቀለም ያለው ኮት ከየትኛው ሸሚዝ እና ከረባት ጋር ይሄዳል የሚለው ይተነተናል፡፡ ለምሳሌ ያህል የፌስቡኩ ባለቤት ማርክ ዙከርበርሀግ ባለፈው አመት በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርቦ ስለ ድርጅቱ የግለሰቦችን ግላዊ መረጃ ለሌሎች ማሾለክ ክስ ለሴነተሮች ምላሽ በሰጠበት ወቅት ለብሶት የነበረው ደማቅ ሰማያዊ ከረባት “ይቅርታ አድርጉልኝ” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው በሚል በኒውዮርክ ታይምስ ሀያስያን ተተርጉሟል፡፡ አለባበሱንም አድንቀውለታል፡፡
በሌላ በኩል ዴድሬ ክሌመንት የተባለ የፋሽን ታሪክ ተመራማሪ እና አጥኚ አለባበሱን ተችቷል፡፡ “ሁልጊዜ የሚለብሰው ባለሹራብ ኮፍያ ለብሶ ቢመጣ የበለጠ አደንቀው ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔ ማለት ይሄው ነኝ የሚለውን መልእክት ለማስተላለፍ ያስችለው ነበር” ብሏል፡፡ እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚያመለክተው አለባበስ ሰውነትን ከመሸፈን ያለፈ መልእክት ማስተላለፍ እንደሚችል ነው። በዚህም የተነሳ መሪዎች የት ቦታ ምን ለበሱ የሚለው በስፋት ይተነተናል፡፡
ይሄን ቢለብሱ ወይም ያንን ባያደርጉ ይሻላል የሚል ውይይት እና ክርክርም ይነሳል፡፡ የመሪዎች መነጽር ማጥለቅ ወይም አለማጥለቅ ፤ ከረባት ማሰር ወይም አለማሰር ፤ በሱሪ መውጣት ወይም በቁምጣ መታየት ፤ ስካርፍ ጣል ማድረግ ወይም አለማድረግ ብቻ ሁሉም ነገር ስለ አለባበሳቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ፖለቲካ አቋማቸው እና ወቅታዊ ሁኔታቸው መገለጫ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ታዋቂው የፋሽን መጽሄት ቮግ ባለፈው ዓመት ኖቬምበር 17 ቀን 2020 እ.ኤ.አ Politicians Are The New Fashion Influencers በሚል ርእስ ባስነበበው ጽሁፍ አሁን ላይ እንዲያውም ፖለቲከኞች የሚለብሱት ልብስ በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ በመሆኑ ራሳቸው የፋሽን ሞዴል ወደ መሆን እየተቃረቡ እንደሆነም ይገልጻል። ለዚህም የቀድሞዋን ቀዳማዊ እመቤት ሚሼል ኦባማ እና የአሁኗን ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሀሪስ አለባበስ ይጠቅሳል፡
ወደ እኛ አገር ስንመጣ ሹማምንት ስለሚለብሱት አለባበስ ብዙም የሚጨነቁ ባይመስሉም በቅርብ ጊዜያት ግን ለውጦች እየታዩ መጥተዋል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚሾሙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በሄዱባቸው አገራት የሹመት ደብዳቤያቸው ሲያቀርቡ የሚለብሷቸው አልባሳትም እንዲሁ በብዙዎች ዘንድ የተወደዱ ነበሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ልዩ ስብሰባዎች ሲኖሯቸው ለብሰው የሚመጡት የወከሉትን ሕዝብ የሚገልጽ አለባበስ የምክር ቤቱን ግቢ ደንበኛ የፋሽን ኤክስፖ ስፍራ የሚያስመስለው ሲሆን ብዙዎቹ በስብሰባው ላይ እጅ አውጥተው ሳይናገሩ ማንነነታቸውን እና ከየት እንደሆኑ የሚገልጽ መልእክት እንዲያስተላለፉ አድርጓቸዋል፡፡
ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል የሚለብሷቸው አልባሳት ባህላቸውን እና ሃይማኖታቸውን አዋህደው የሚቀርቡ በመሆናቸው እንዲሁ ተደናቂ ናቸው፡፡ ሰሞኑን በፖላንድ ለሥራ ጉዳይ ተገኝተው የነበሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታዋ ሁሪያ አሊ ለብሰው የነበረው አለባበስም እንዲሁ ተደናቂ የሚባል ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚለብሷቸው ዘመናዊም ሆነ ባህላዊ አልባሳት ለየት ያሉ ናቸው፡፡ የፕሬዚዳንቷ ሁሉም አለባበስ ሊባል በሚችል መልኩ በሕዝብ ዘንድ የሚወደድላቸው ነው፡፡
ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከቀናት በፊት በተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ለብሰውት የነበረው ቀለል ያለ የአገር ልብስ እጅጉን አይነ ግቡ ነበር፡፡ እነዚህ አለባበሶች መበረታታት አለባቸው፡፡
በተለይም ከሌሎች አገራት ሰዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት ውስጥ እነዚህ አልባሳት በተጠና ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፡፡
ሹማምንት የሚለብሱት ልብስ በአንድ ጎን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ መሆን አለበት ፤ በሌላ መልኩ የኢትዮጵያን ብዝሀ ባህል እና ሃይማኖትነት ብሎም ልእልና ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኛ ሹማምንት ለውይይትም ይሁን ለድርድር ከሌሎች ጋር በሚቀመጡበት ጊዜ ከቃል በላይ የሆኑ መልእክቶችን ለማስተላለፍ የሚያስችላቸው መሆን አለበት፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 4/2014