ኖቤል ሲባል አስቀድሞ የሚታሰበን ሽልማቱ ነው። ሽልማቱ በየአመቱ የሚሰጥ ሲሆን፣ ከተጀመረም 120 ዓመታትን አስቆጥሯል። ሽልማት መስጠት የተጀመረውም በፈረንጆቹ በ1901 በኢትዮጵያ ታኅሳስ 1 ቀን 1894 ዓ.ም የአልፍሬድ ኖቤል አምስተኛው ሙት አመት በተዘከረበት ነው።
የመጀመሪያዎቹ ሽልማቶችም የተሰጡት በስዊድን ስቶክሆልም ሲሆን፣ ሽልማቶቹ የተሰጡባቸው መስኮችም ፊዚክስ፣ኬሚስትሪ፣ ህክምና፣ ስነጽሁፍና ሰላም ናቸው። ቆይቶም ምጣኔ ሀብት ተጨምሮበታል። ኖቤል በ1895 ባረቀቀው መመሪያ መሠረት ሽልማቱ እየተሰጠ ይገኛል።
በስማድናዊው አልፍሬድ ኖቤል ስም የተዘጋጀው ይህ ሽልማት ለሰው ልጅ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ተግባሮች ላከናወኑ እንዲሰጥ በሚል ኖቤል በተናዘዘው መሰረት የሚሰጥ ነው። ተሸላሚው የወርቅ ሜዳሊያ፣ ዲፕሎማ እና የገንዘብ ሽልማት ይሰጠዋል። ሎሬት በመባልም እንዲጠራ ይደረጋል። በመላው አለም እስከ አሁን 603 የኖቤል ሽልማቶች ለ962 ሎሬቶች እና ለ25 ድርጅቶች ተሰጥተዋል።
ኖቤል በምርምር ያገኛቸው የፈጠራ ስራዎች የሰው ልጅን የሚጎዱ በሚል በማህበረሰቡ ዘንድ ይሰነዘርበት የነበረው ነቀፌታ አሳስቦት ሽልማቱን ማዘጋጀቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሽልማቱ እጅግ በጣም የተከበረ በሚል የሚታሰብና በዓለም ላይ ትልቅ ስኬታማ ሥራ በመሥራት ውጤታማ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ይሰጣል። ኖቤል ከኢንቨስተመንቶቹ ከሚያገኘው ሀብት አብዛኛውም ለዚህ ሽልማት አንዲውልም ተናዟል።
በቅድሚያ ለተለያዩ የግንባታ ስራዎች / ለሲቪል ስራ/ የሚጠቅመውን ድማሚት የፈጠረው አልፍሬድ ኖቤል፣ ምርምሩ እየሰፋ ሄዶ ለጦር መሳሪያ የሚውሉ የተለያዩ አይነት ፈንጂዎችንና በርካታ የጦር መሳሪያ ተቀጣጣዮችን ፈጥሯል። 355 የፈጠራ ስራዎች የባለቤትነት ባለመብትም ነው። ኖቤል በዚህ ሽልማት ይበልጥ ቢታወቅም፣ ኬሚስት፣ ኢንጂነር፣ የፈጠራ ስራዎች ባለቤትና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሰው እንዲሁም በበጎ አድራጎት ስራውም ይታወቃል።
በእሱ ፈቃድ አራት የተለያዩ ተቋማት ተመስርተውም ነው ሽልማቱ እየተካሄደ ያለው። በዚህ መሠረት ሦስት ስዊድናውያንና አንድ ኖርዌያዊ ሽልማቱን ይሰጣሉ። ከስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የስዊድን ዘውዳዊ ሳይንስ አካዳሚ ለፊዚክስ ፣ለኬሚስትሪ እና ምጣኔ ሀብት ሽልማት ለመስጠት ሲወስኑ፤የካርሎኒስካ ኢንስቲትዩት በፊዚዮሎጂ ወይም በሕክምና ዘርፍ እና የስዊድን አካዳሚ በስነጽሑፍ ዘርፍ ሽልማት ለመስጠት ይወስናሉ ።
በኦስሎ መቀመጫውን ያደረገው የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ በሰላም ዘርፍ ለሚሰጠው ሽልማት ይወስናል። የኖቤል ፋውንዴሽን ሕጋዊ ባለመብትና የፈንዶቹ ተግባራዊ አስተዳዳሪ በመሆን በመሥራትና የሽልማት ሰጪው ተቋሞች የጋራ አስተዳደራዊ ሚናው በመወጣት ያገለግላል። በሽልማቱ ዙሪያ መመካከርና መወሰን ግን አይችልም። ሽልማቱ የሚገባቸውን ሰዎች የሚወስኑት አራቱ ተቋማት ብቻ ናቸው።
አልፍሬድ በርንሀርድ ኖቤል የተወለደው እ.ኤ.አ በ1833 በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ነው። ኖቤል ከተወለደ ከአራት ዓመት በኋላ ቤተሰቦቹ ወደ ሩሲያ ሄዱ። አባቱ በሴንት ፒተስበርግ ከተማ የሚገኝ ፈንጂዎችን እና ሌሎች የጦር መሣሪዎችን የሚያመርት ስኬታማ ፋብሪካን ያስተዳድር ነበር። ይህም ሁኔታ ለኖቤል መልካም አጋጣሚ ሳይፈጥርለት እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኖቤል ፈጠራዎቹን በየጊዜው እያሻሻለ ያወጣም ነበር። የተሻሻለ ፈንጂን በምርምር ማግኘት ችሏል። ይህም በዘመናዊ መልኩ ከፍተኛ ፍንዳታዎችን ማድረግ የሚያስችል ሆነለት። ፈጠራው በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን የሚጨርስና አካባቢዎችን የሚያወድም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ነበር። ይህ የኖቤል ናይትሮግሎሲሪን ፋብሪካ እአአ በ1964 ፍንዳታ ይደርስበትና ታላቅ ወንድሙንና ሌሎች በርካታ ሰዎችን ይገድላል።
አልፍሬድ አሁንም ሌላ የተሻሻለ ፈንጂ ለማምረት ምርምሩን ቀጠለ። አአአ በ1867 ለአያያዝ ለአጠቃቀም የማያስቸግር ከፍተኛ ፍንዳታ ማድረስ የሚችል ‹‹ኪሴልጉር›› የተሰኘ ቅይጥ የፍንዳታ ፈጠራን እውን አደረገ። ይህ ለፈጠራ የተፈጠረ ሰው በቃኝ አላለም። በ1875 ትልቅ አቅም ያለው ጌላቲን የተሰኘ ድማሚት ፣ በ1887 ባሊሲታይትን አገኘ።
በዚህ ወቅት ሌላ ወንድሙ ፈረንሳይ ውስጥ ይሞታል። ጋዜጠኞች የሞተው አልፍሬድ ኖቤል ይመስላቸዋል። ጋዜጠኞቹ የኖቤልን ፈጠራ በጥሩ አይመለከቱትም ነበርና ይህን በሚመጥን መልኩም አንድ ጋዜጣ ‹‹ የሞት ነጋዴው ኖቤል ከዚህ አለም በሞት ተለየ›› በሚል ርእስ ዘገባውን አቀረበ። ኖቤል ግን ይችን አለም የተሰናበተው እአአ በ1896 ነው።
ዜናውን ያነበበው ሁሉ « የማታ የማታ እውነት ይረታ» እንደሚባለው ዘግይቶ ኖቤል አለመሞቱን ቢረዳውም ዜናውን ያነበበውን ኖቤል ግን ምቾትና ሰላም ነሳው። እውነትም ብሞት እንዲህ ተብሎ ነው የሚፃፍልኝ ብሎ ራሱን ጠየቀ። የኔ ብቸኛ ዝናዬ ሞትን ማከፋፈል ማለት ነው ሲል ተፀፀተ።
ያገኘውን ዝናና ዕውቅና በወንድሙ ሞት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር ቆረጠ። በስሙ ፋውንዴሽን በመመሥረት በሥራው ከሚያገኘው ገቢ አብዛኛውን ለዚህ ሽልማት ድርጅት በመስጠት ተሸላሚዎች እንዲውል የወሰነውም ከዚህ በኋላ ነው።
ጥቁር አሜሪካዊው የሰብአዊ መብት ዋና ተሟጋችና ሰማዕት ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የኖቤል ሰላም ሽልማት ከተቀበሉት መካከል ይገኙበታል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናኽም ቤጊን እና የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት የኖቤል የሰላም ሽልማት ተካፋዮች ሽልማቱን ተቀብለዋል። የፍልስጤም መሪ ያሲር አራፋት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሐቅ ራቢን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሺሞን ፔሬዝ በጋራ የተሰጣቸውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተቀበሉት መካከል ይገኙበታል። የናይጄሪያው ወሌ ሶይንካ፣ የግብፁ ናጂብ ማህፉዝ እና የደቡብ አፍሪካው ናዲን ጎርዲመር በስነጽሑፍ ሽልማትን ተቀብለዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ዓመት በፊት የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ሽልማት የበቁት ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገራቸው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው እርምጃዎችና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ‹‹ በኖርዌይ ኮሚቴ ውሳኔ ተደስቻለሁ፤ ለሰላም ለሚሰሩ እና ለሚተጉ በሙሉ የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤ ይህ ሽልማት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ነው ሲሉ አስፍረዋል››።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2014