በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ አምዳችን በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ቦታ ከነበራቸው ድንቅ ኢትዮጵያዊ መሪ መካከል አንዱን ልናነሳ ብዕራችንን ከአፎቱ መዘዝን።እኚህ መሪ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው።እኚህ ታላቅ መሪ ያረፉት ታህሳስ 3 ቀን 1906 በዚህ ሳምንት በዛሬው እለት ነበርና የእሳቸውን የህይወት ታሪክና ለኢትዮጵያ ካበረከቷቸው መካከል ታላቁን ማንሳት ወደድን። ይህም ጉዳይ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲነሱ የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያዊያን ድል አድዋ አብሮ ይነሳል።
ከአባታቸው ንጉስ ሐይለመለኮት ሣህለስላሴ ከእናታቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ ለማ ነሃሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም በዛሬው የአማራ ክልል በቀድሞ የሸዋ ክፍለ አገር አንኮበር ተወለዱ።ምኒልክ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ መንዝ ውስጥ ጠምቄ በሚባል አምባ ከእናታቸው ዘንድ አደጉ። የሸዋ ንጉስ ሆነው አገልግለዋል።
አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የሆኑት ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም ሲሆን፣ በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተው ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለው በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ነገሱ።ዳግማዊ ምንሊክ የተባሉትም የንግሰተ ሳባና የሰለሞን ልጅ ምኒልክ ቀድሞ ነግሶ ስለነበር ነው።
በሶስተኛውም ቀን ባለቤታቸው ወ/ሮ ጣይቱ ብጡል በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ የሚገባቸውን ዘውድ ደፍተዉ እቴጌ ተባሉ።
ከዊኪፒዲያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን በመሩበት ዘመን አገራቸው የዘመናዊ አስተዳደር ስርዓትና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ በብርቱ ሰርተዋል።
በተለይም አዳዲስ ነገር በማስተዋወቅም ይታወቃሉ።በንጉሱ ከተዋወቁ ቴክኖሊጂዎች መካከል፡-ባቡር(1893)፣ ስልክ(1882)፣ ፖስታ(1886)፣ ኤሌክትሪክ(1889)፣ አዉቶሞቢል(1900) ፤ የዉሃ ቧንቧ(1886)፣ ዘመናዊ ህክምና(1889)፣ ሆስፒታል(1890)፣ ፋርማሲ(1904)፣ ባንክ(1898)፣ ገንዘብ(1886)፣ ማተሚያ(1898)፣ ጋዜጣ(1900)፣ ሆቴል(1898)፣ ፖሊስ(1901)፣ የፅህፈት መኪና(1887)፣ ሲኒማ(1889)፣ ወፍጮ(1891)፣ መንገድ(1896)፣ ቀይመስቀል(1889)፣ የሚኒስትሮች ሹመት (1900) ይጠቀሳሉ።
አፄ ምኒልክና አድዋ
አፄ ምኒልክ ከውጪ አገሮች ጋር ለሚኖራቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጣሊያን ጋር የጀመሩት ስምምነት በውጫሌው ውል አንቀፅ 17 ትርጉም መጣረስ ምክንያት ወደ ጦርነት አመራ።ጣልያን የሀገሪቱን ዳር ድንበር በመጣስ በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የተለያዩ ቦታዎችን ተቆጣጠረች።በሁኔታው የተቆጡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጣልያንን ለመወጋት ወሰኑ።ዙፋናቸውን ለአጎታቸው ለራስ ዳርጌ አደራ ብለው ለዘመቻ ከመነሳታቸው በፊት ተከታዩን አዋጅ ለህዝቡ አስተላለፉ።
“ልዑል እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አኖረኝ፤እኔም እስካሁንበልዑል እግዚአብሄር ቸርነት ገዛሁ፤ እንግዲህም ከሞት ሞት የሁሉ ነውና ለኔ ሞት አላዝንም።ደግሞ እግዚአብሄር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠራጠርም።አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሀይማኖት የሚለውጥ ልዑል እግዚአብሄር የወሰነልኝን ባህር አልፎ መጥቷል።እኔም የአገሬን ከብት ማለቅና የሰውን መድከም አይቼ እስከአሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።አሁን ግን በልዑል እግዚአብሄር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።
የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካአሁን አላስቀየምከኝም።አሁን ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህለ ልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በፀሎት እርዳኝ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም’፤ እግዝዕትነ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻየም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከትመህ ላግኝህ ።
መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም
ንጉሱ አዋጁን እንዳስነገሩም ህዝቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊዳፈር የመጣውን ጠላት በወኔ ለመፋለም የንጉሱን ጥሪ ተቀበለ። ንጉሱ ከአርበኞች ጋር ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሲነሱ፤ እቴጌ ጣይቱም አብረው ተነሱ።
ራስ መኮንን የጦር አበጋዝ ሆነው ራስ ወሌን፣ ራስ ሚካኤልን፣ ራስ መንገሻን የመሳሰሉ የጦር አበጋዞችን ይዘው ተጉዘው ጣሊያኖች መሽገው በተቀመጡበት አምባላጌ ተራራ አጠገብ ሰፈሩ።በንጉሱ የእርቅ መልዕክት ተላከ ነገር ግን በጣሊያን በኩል አልተሳካም።
ህዳር 28 ቀን 1988 ዓ.ም የተደረገው የአምባላጌ ጦርነት 2 ሰአት ፈጅቶ ራስ መኮንን በመሩት ክፍል የኢጣሊያ ጦር ሸሽቶ ወደ መቀሌ ሄደ።ከአምባላጌና ከመቀሌ ጦርነት በኋላ ዋናው የጦር አዝማች ባራቴሪ የቀረውን ሰራዊት በ4 ከፍሎና የጦር ካርታ አዘጋጅቶ በአራቱም አቅጣጫ አሰለፋቸው።
በአጠቃላይ የጣሊያን ጦር ከ20ሺህ በላይ የነበረ ሲሆን ሁሉም ዘመናዊ መሳሪያ ከበቂ ጥይቶች ጋር እንዲሁም 60 መድፎችን ታጥቀው ነበር።በአድዋው ጦርነት የኢትዮጵያዊያን የጦር አደረጃጀትና አሰላለፍም እንዲህ ይገለፃል።
አፄ ምኒልክ አድዋ አጠገብ አድማህለያ በተባለው ስፍራ ከ30ሺህ ጦር ጋር ፣ እቴጌ ጣይቱ ከ3ሺህ ወታደር ጋር፣ ፊታዉራሪ ገበየሁ ከ6ሺህ ወታደር ጋር፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት ከ3ሺህ ወታደር ጋር በመሆን በአጠቃላይ ከ70ሺህ ወታደር በላይ ተሰልፎ ነበር።
በዚህ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ጀብዱ በተፈፀመበትና የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ፋና ወጊ የሆነ ድል የተመዘገበበት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የአድዋው ጦርነት በኢትዮጵያውያን ጀግኖች በድል ተጠናቀቀ።
የአፄ ምኒልክ ዘመን ፍጻሜ
ተክለጻድቅ መኩሪያ ስለ አፄ ምኒልክ ዜና ዕረፍት፤ “አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፍ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ በ1900 ዓ/ም የጀመራቸው በሽታ እየፀናባቸው ሔዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎና አንደበታቸው ተዘግቶ እንደቆየ በታኅሣሥ 3 ቀን 1906 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ሲል ያትታል።
የሸዋ ንጉሥ በኋላም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ዘመን ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይሆን፣ ክፉውን በደግነት እየመለሱ ጥፋትን ሁሉ በትዕግሥት እያሸነፉ፣ አገሪቱን በጥበብ መርተዋል።ዘመናዊ ትጥቅ ይዞ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የጣሊያን ጦር በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅም አድርገዋል። በዚህም የዓድዋው ድል ፈርጥ መሆን ችለዋል፡፡
አገራችን ዛሬም የገጠማት የሉዓላዊነት ፈተና በልጆችዋ ጀግንነት ዳግመ-አድዋ ድልን እየተቀዳጀች ወደፊት እየተራመደች ነው፤ የምእራባውያን ተላላኪ በመሆን ሉአላዊነቷን ለማስደፈር የአማራና የአፋር የተለያዩ አካባቢዎችን የወረረውን የትህነግ ግብአተ መሬት ለመፈጸም ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ/ዶ/ር/ የክተት ጥሪ ተቀበለው ግንባር ዘምተው የአድዋን ድል ለመደግም እየተዋደቁ ናቸው።በአሁኑ ወቅትም በርካታ ድሎች ተመዝገበዋል። በትህነግና ተባባሪዎቹ ላይ የተጀመረው ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ እየተመኘን የያኔ አድዋ ጦርነት መሪ የሆኑትን ንጉስ አፄ ምኒሊክን በዚህ መልክ ዘከርናቸው።
ይህን ፅሁፍ ስናዘጋጅ በመረጃ ምንጭነት የተክለፃዲቅ መኩሪያ “አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት”፣ ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ”የተሰኙ መፅሀፍትና ልዩ ልዩ ድህረ ገፆች ተጠቅመናል።
ቸር ያሰማን!
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2014