አብዛኛዎቹን የጤና እክሎች በሰውነት ላይ የከፋ ጉዳት ከማሳከተላቸው በፊት በቀላል መንገድ አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይመክራሉ:: ለዚህም ሰውነትን ሊጎዱ ከሚችሉ ነገሮች ማራቅ፣ አመጋገብና መጠጥን ማስተካከል ብሎም ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቁልፉ መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ:: ከዚህ ባለፈ ቢያንስ በዓመት አንድ ግዜ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ማካሄድ የሰውነት የጤና ሁኔታን ለመረዳት እንደሚያስችል ያመለክታሉ::
ይህ ሁሉ ተደርጎ ታዲያ ሰዎች ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የደም ብዛት፣ ስኳር፣ ኩላሊትና ሌሎችም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቢይዛቸው ቢያንስ ሕመማቸው ተባብሶ የከፋ የጤና ችግር ውስጥ እንዳይከታቸው በየግዜው የሕክምና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባቸው የጤና ባለሙያዎቹ ያሳስባሉ:: ከሕክምናው ክትትል በዘለለም የሕክምና ምክሮችን በልዩ ልዩ መንገድ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸውም ይጠቁማሉ::
በርግጥ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሰዎች ለከፋ የጤና ችግር ከመጋለጣቸው በፊት የአመጋገብ ሥርዓታቸውን አስቀድመው በማስተካከልና መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በመሥራት የጤናቸውን ሁኔታ የመጠበቅ እድል ቢኖራቸውም ለበሽታ ከተዳረጉ በኋላ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኞቹ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አይችሉም::
በርግጥ ዘመኑ በዲጂታል መንገድ ሰዎች ጤና ተቋማት መሄድ ሳይጠበቅባቸው እቤታቸው ሆነው የሕክምና ምክሮችን የሚያገኙበት ሁኔታዎች እየተመቻቹ የመጡበት ቢሆን ከኢኮኖሚ አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ይህንኑ አገልግሎት የሚያገኙትም ውስን ናቸው:: ምንም እንኳን ገንዘብ ከፍሎ ሕክምና ማግኘት አንዱ አማራጭ ቢሆንም ሰዎች ቢያንስ ስለሕመማቸው በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማድረግም ሌላኛው አማራጭ ሊሆን ይችላል:: ከዚህ አንፃር ታዲያ ‹‹አይ ጤና ሄልዝ ኬር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ›› አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ክፍለ ከተሞችና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አዲስ ነገር ይዤ ብቅ ብያለሁ ይላል::
የአይ ጤና ሄልዝ ኬር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር እየሩሳሌም ማሞ እንደሚገልፁት ‹‹አይ ጤና›› መጀመሪያ የጀመረው ፕሮጀክት የሕክምና የጥሪ ማዕከል ሲሆን ሰዎች እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ቀጥታ ከሐኪሞች ጋር ተገናኝተው አስፈላጊ የጤና መረጃና ምክር የሚያገኙበትን መንገድ ፈጥሯል::
ይህም በተለይ የጤና ተቋማት በአቅራቢያቸው ለሌለ፣ መለስተኛና አነስተኛ የጤና እክሎች ለሚያጋጥማቸው፣ በጨቅላ ህፃናት አስተዳደግ ላይ ምክሮችን ለሚፈልጉ፣ የስነተዋልዶና የቤተሰብ ምጣኔ ምክርና መረጃዎች ለሚሹ እንዲሁም ከስነ አእምሮ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችና በተለያዩ ምክንያቶች ለታካሚዎች ሀፍረትን የፈጠሩ የጤና እክሎችን ምስጢራዊ በሆነ መንገድ መወያየት ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል::
በሁለተኛውና በቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት ፕሮጀክት በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት ኅብረተሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ የማይደፍር በመሆኑ ይህን ክፍተት በማየት ‹‹አይ ጤና›› ከሕመም የማገገም ሂደት ላይ ታካሚው ከጤና ተቋማት ከወጣ በኋላ የማገገም እርዳታ አገልግሎት ይሰጣል::
በዚህም አገልግሎቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከአልጋ መውረድ ለማይችሉ ታካሚዎች ጥሩ መፍትሔ ሲሆን ታይቷል:: ካለመንቀሳቀስ ጋር በተያያዘ ውስብስብ የጤና እክሎች እንዳይመጡ ለመከላከለም አግዟል:: በሶስተኛው የ‹‹አይ ጤና›› የተቋማት ተኮር ፕሮጀክት 100 እና ከዛ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያስተዳድሩ ኩባንያዎች፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ቋሚ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት የሚኖርበት መንገድ ተዘርግቷል::
ሠራተኞች ሲታመሙ ብቻ ሳይሆን ጤናማም ሆነው ቋሚ የጤና ትምህርት እንዲያገኙም ይደረጋል:: ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸውም የተለያዩ የጤና መረጃዎችና ምክሮች ይሰጣቸዋል:: ከተቋሙ ውጪ ለሚያወጧቸው የሕክምና ወጪዎችም አገልግሎቱ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል:: አራተኛው ፕሮጀክት ደግሞ የማገገሚያ ማዕከል ሲሆን በተለያዩ በሽታዎች ለተጠቁና በማገገም ሂደት ላይ ላሉ ታካሚዎች ምቹና ሁሉን አቀፍ የማገገም እርዳታ የሚሰጥ ነው::
ማዕከሉ ከነርስ እንክብካቤ ጀምሮ በባለሙያ የተመረጡ የአመጋገብ ሥርዓትና የውስጥ ፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ይሰጣል:: ወዳጅ ዘመድን በማስታመም ሂደት ከሚኖሩ ክፍተቶችና ጭንቀቶችም ኅብረተሰቡን ይገላግላል ተብሎ ይታሰባል:: እንደ ዋና ሥራ አስኪያጇ ገለፃ ‹‹አይ ጤና›› አዲስ ያስጀመረው ፕሮጀክት ‹‹የጤና ትምህርት ለሁሉም›› በሚል ኅብረተሰቡ መሠረታዊ የጤና ትምህርትን በነፃ የሚያገኝበት ማዕከል ሲሆን በአገሪቱ የመጀመሪያውና በኅብረተሰቡ በኩል የሚታየውን የጤና ዕውቀት ክፍተት በማየት የተጀመረ ነው:: በዚህ የማኅበረሰብ የጤና ስልጠና ማዕከል ኅብረተሰቡ ውስብስብ ባልሆኑና አሳታፊ በሆኑ መንገዶች የጤና እውቀት ማስጨበጫ እንዲያገኝ ይደረጋል::
አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም የጤና ባለሙያ መሆን ለሚፈልጉ ብቻ ሲሰጥ የነበረውን የጤና ትምህርትም ያስቀራል:: በማዕከሉ ወሳኝ ተብለው የሚታሰቡ የጤና ትምህርቶች፣ ጤናማ አመጋገብ ሥርዓቶች፣ የስነ ተዋልዶና የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርቶች፣ እንደ ስኳርና ደም ግፊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና እንደ ኮቪድ ያሉ ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ::
ከበሽታ መከላከያ ትምህርቶች ባሻገር በተለያዩ በሽታዎች ለተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሽታው የባሰ ጉዳት እንዳያደርስባቸው ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችና ባጠቃላይ ማንቃት ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችም ይሰጣሉ:: ይህም በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ሕይወታቸው የሚያልፍ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል:: ይህ ማዕከል የመጀመሪያ ቢሆንም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ በአንድ ክፍለ ከተማ አንድ የስልጠና ማዕከል ለመክፈት እቅድ ተይዟል::
በዚህ ዓመትም 5 ሺ ሰዎችን በጤና ትምህርት ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት ታቅዷል:: ለፕሮጀክቱም ከጤና ሚኒስቴር በኩል ሙሉ እውቅና ተሰጥቷል:: ለዚህም ማዕከሉ ከሚገኝበት ክፍለ ከተማ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤትና ከበጎ ፍቃደኛ ሠራተኞች ጋር በመሆን ስልጠናው መወሰድ የሚፈልጉ ሰዎች ተመልምለው በሚወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት ወደ ማዕከሉ መጥተው ስልጠናውን በነፃ እንዲያገኙ ይደረጋል:: በጥሪ ማዕከሉም አማካኝነት ስልጠናውን ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለመሆንም ጥረት ይደረጋል::
ወይዘሮ ፍቅርተ ሹመት በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሴቶች ማኅበር የፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት ማኅበሩ በስድስት ሴት አካል ጉዳተኞች በ1995 ተመስርቷል:: ዋነኛ ዓላማውም አካል ጉዳተኛ ሴቶች በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተጠቃሚ ሲሆኑና ለአገራቸው እድገትም አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ማየት ነው:: ትምህርት፣ ጤናና ሌሎችም ማኅበራዊ ግልጋሎት መስጫ ተቋማት እንደሌሎች ዜጎች በእኩል መልኩ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አይደሉም:: በተለይ ከጤናና ከስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ በሚታዩ ችግሮች እንደሌሎች ዜጎች አግብተው ለመውለድ እንኳን ሲቸገሩ ይታያል::
በጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ አገልግሎቶችን የአካል ጉዳተኞች ይጠቀሙባቸዋል ተብሎ ስለማይታሰብ አካል ጉዳተኞች ተኮር ሥራዎች እምብዛም አይገኙም:: አገልግሎቱ እንኳን ቢኖር ምስጢራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ ላያገኙ ይችላሉ::
እንደ አስተባባሪዋ ገለፃ አንዳንድ ግዜ ደግሞ በተለይ የጤና እንክብካቤ ፈልገው ለሚመጡ አይነስውራን በሚገባቸው መንገድ በረዳቶቻቸው አማካኝነት የሚፈልጉትን የጤና ምክርም ሆነ የሕክምና አገልግሎት ያለመንገር ችግሮችም ይታያሉ:: አካባቢያዊ ነባራዊነቱን አካል ጉዳተኞች ቢችሉትም አመለካከቱን መቋቋም የማያስችላቸው በርካታ ችግሮች አሉባቸው:: ከዚህ የተነሳም በተለይ ከጤና ጋር የተያያዙ በሬዲዮና በየጤና ተቋማት የሚሰጡ ትምህርቶቹ በጥቅሉ የአካል ጉዳተኛ ሴቶችን ጉዳይ ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይደለም::
ከነዚሁ ችግሮች የተነሳ በአዲስ አበባ ያሉ 1,700 ያህል የማኅበሩ አባላት አብዛኛቹ በፅኑ ካልታመሙ በስተቀር ወደ ጤና ተቋማት አይሄዱም:: እነዚህን ችግሮችን ለመቅረፍና አገልግሎቶቹን ተደራሽ ለማድረግ ማህበሩ ከ ‹‹አይ ጤና›› ጋር የጀመረው አገልግሎት ወሳኝ ነው::
የተጀመረው አገልግሎትም ተቋም ተኮርና ‹‹አይ ጤና›› በማኅበሩ ማእከል በመገኘት አካል ጉዳተኞቹ የጤና ትምህርቱንም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ የማኅበሩ አባላት ስለ አካል ጉዳት በሚያውቁ ሰዎች የጤና ትምህርትና ምክር አገልግሎት ያገኛሉ::
የአካል ጉዳተኞቹን ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ የመፍራት ችግሮቻቸውንም ይቀርፋል ተብሎ ይታሰባል:: ከጤና አገልግሎት አለመመቸት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ያልተፈለጉ እርግዝናዎችን እና ውርጃዎችን ለማስወገድም ይረዳል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 2/2014