አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ደሴ ቅርንጫፍ በሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን መዘረፉንና ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት ተቋሙ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አወል ሁሴን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በየሄደበት ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ማፈናቀልና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸም ልዩ ባህሪው የሆነው ወራሪውና ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን በደሴ ቅርንጫፍ መድኃኒትና ሌሎችንም የህክምና ግብዓቶችን የቻለውን በመዝረፍ ያልቻለውን ደግሞ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡
ቅርንጫፉ በከፍተኛ መሰረተ ልማት የተደራጀ እና በአካባቢው ለ27 ሆስፒታሎች፣ ለ303 ጤና ጣቢያዎች፣ ለ60 ወረዳዎች እንዲሁም ከሕግ ማስከበር ዘመቻው እስከ የህልውና ዘመቻው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የመድኃኒትና ሌሎችም የህክምና ግብዓቶችን በማቅረብ አገልግሎት እየሰጠ እንደነበርም አቶ አወል ተናግረዋል።
አቶ አወል አክለውም፤ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ክምችት ክፍል ከነበሩ የተወሰኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መድኃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁስ እና ሁሉንም የድርጅቱ ተሽከርካሪዎች ከጥፋት ቡድኑ ማዳን ቢቻልም የተቀሩት መድኃኒቶች እና የህክምና ግብዓቶችን ግን በሽብር ቡድኑ ተዘርፈዋል፡፡
እንደ አቶ አወል ገለጻ፣ ውድመቱ በከፍተኛ መዋዕለንዋይ የተገነቡ ግዙፍ የእናቶችና ህጻናት ክትባት ግብዓት ማከማቻ፣ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዘን፣ የቅርንጫፉ ዋናው መጋዘን፣ ቢሮዎች፣ የማከማቻ መሰረተ ልማት፣ ፎርክሊፍቶች፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሥርዓቶች፣ የቢሮ መሳሪያዎች እና ሌሎች ንብረቶችን ያካትታል፡፡
አጠቃላይ በቅርንጫፉ ላይ የተፈጸመውን ውድመት በጥልቀት በማጥናት በአይነትና በገንዘብ የደረሰውን የጉዳት መጠን በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግም አቶ አወል አስታውቀዋል።
አብዱረዛቅ መሐመድ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም