– ከመኸር አዝመራ ከ337 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በመኸር አዝመራ በተለያየ ሰብሎች ከለማው 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የሚገኝ ሰብል መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በአጠቃላይ ከመኸር አዝመራ ከ337 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ተመላክቷል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር አዝመራ ከ11 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የለማ ሰብል ተሰብስቧል፡፡
እንደ አቶ በሪሶ ገለጻ፤ ከአንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚገኝ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀው ዝናብ እንዳይበላሹ በደቦና በቤተሰብ እንዲሁም ኮምባይነሮችን በስፋት በማሠማራት መሰብሰብ ተችሏል።
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችን የሰው ሃይል እና ኮምባይነር በመጠቀም እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሰባሰቡ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሰብሎቹ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሰው ሃይልን በማሳተፍና ኮምባይነርን በመጠቀም እየተሰበሰበ እንደሚገኝና ሥራው በሚቀጥሉት ቀናትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
እስካሁንም ስንዴ፣ ሩዝ፣ በቆሎና የቅባት እህል የተሰበሰበ ሲሆን ከተሰበሰቡ ሰብሎችም 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
በመኸር አዝመራ ከለማው ሰብል ውስጥ ስንዴ፣ በገብስ፣ በጤፍ፣ በቆሎ፣ በሩዝ፣ ማሽላና የተለያዩ ሰብሎች እንደሚገኙበት እንደሆነ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ ከመኸር አዝመራ ከ337 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ የምርት ብክነትን በሚቀንስ መልኩ ሰብል የመሰብሰብ ሥራው መጠናከሩን ተናግረዋል።
የዝናብ ስርጭቱ ከቦታ ቦታ የተለያየ በመሆኑ የሰብል አሰባሰቡ የአየር ሁኔታውን መሠረት ባደረገ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ ሰብል በሚሰበስብበት ወቅት ዝናቡን በመፍራት ያልደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንደሌለበት አቶ በሪሶ ተናግረዋል፡፡ የሰብል ብክነት እንዳያጋጥም በሰብል አሰባሰብ ሥራው ሁሉም ባለድርሻ አካል መሳተፍ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም