ሕገወጥ የምግብና መድኃኒት ምርቶችን ለመቆጣጠር የተጠናከረ ትብብር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- ሕገወጥ የምግብና መድኃኒት ምርቶችን ለመቆጣጠር የተጠናከረ ትብብር እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ ምግብ መድኃኒት ባለሥልጣን ገለፁ፡፡

ተቋሙ ትናንትና ባዘጋጀው ከተማ አቀፍ ፎረም ምሥረታ ላይ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት በዳዳ እንደተናገሩት፤ ሕገወጥ የምግብና መድኃኒት ምርቶች በጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ትብብሮችን ማጎልበት ይገባል፡፡

በርካታ ሕገወጦች ባሉበት ሁኔታ ውስጥ እስካለን ድረስ ችግሩን መቶ በመቶ ማጥፋት ባንችልም ህብረተሰቡ፣ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በጋራ ከሠራን ችግሩን መቀነስ እንችላለን ብለዋል፡፡

ሕገወጥ ምርቶች የሚሠሩት በየጓዳውና በድብቅ ቦታዎች ውስጥ ነው ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጇ፤ እኔም ለጤናዬ ባለሥልጣን ነኝ ብለን ሁላችንም ከተንቀሳቀስን ሕገወጥነት ከስር መሠረቱ መከላከል እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የምግብ ደህንነቱ መጠበቁን ማረጋገጥና የጤና ተቋማትን አገልግሎት በተመለከተ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት እንዲሁም መቆጣጠር የባለሥልጣኑ ኃላፊነት ቢሆንም ችግሩ እያንዳንዱን ሰው ስለሚነካ በመሆኑ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር መብራቶም ጣዕመ በበኩላቸው፤ “እኔም ለጤናዬ ባለሥልጣን ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ የጤና ቁጥጥር ፎርም መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የፎረሙ አላማ ለከተማው ነዋሪ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ መፍጠር፣ ሕገወጥ ምርቶችን መቆጣጠር፣ የተፋጠነና የማይቆራረጥ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት መገንባት፣ በሕገወጦች ላይ ስለተወሰዱ ርምጃዎች ማሳወቅን እንደሚያጠቃልል ገልፀዋል፡፡

ውስብስብ ባህሪ ያለውን ሕገወጥነት ለመከላከል የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑም ለፎረሙ አስፈላጊነት እንደ አንድ ምክንያት መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

የቁጥጥር ፎረም ሰነዱ ህብረተሰቡን በባለቤትነት ስሜት ሕገወጥ የምግብና መድኃኒት ምርቶችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያጎለብት ይረዳል ብለዋል፡፡

የፎረሙ አባላት ባለሥልጣኑን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ የንግድ ማህበረሰብ አደረጃጀቶች፣ የጤና ባለሙያዎች ማህበር፣ የሕዝብ አደረጃጀቶች፣ የመንግሥት አካላት፣ የምክር ቤት ተወካዮች፣ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን እንዲሁም የሲቪክና በጎ አድራጎት ማህበራትን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2017 ዓ.ም

Recommended For You