አዲስ አበባ፡- አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ውድመትና ጉዳት በአፋጣኝ ጠግኖ ትምህርት ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ መሀመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል ወረራ ባደረገባቸው አከባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችን በከባድ መሳሪያ መትቷል፤ የትምህርት ቤቶቹን መስኮቶች፣ ወንበሮች፣ በሮችና የትምህርት መገልገያ መሳሪያዎችን ሰባብሯል፤ አውድሟል፡፡ ይህ አሸባሪ ቡድን በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ የሚባል እና የአሸባሪውን እኩይ ባህሪ በግልጽ ያሳየ ነው፡፡
አቶ አሊ መሀመድ እንደተናገሩት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ጠግኖ በአፋጣኝ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥትም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት እየሠራበት ነው፡፡ በተለይ መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ጥቁር ሰሌዳዎችንና ወንበሮችን የማስገባት ሥራ ተጀምሯል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ጠግኖ ሥራ ለማስጀመር ከፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ጋርም ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ ትምህርት ቤቶቹ ተጠግነው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ትልቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ቤቶቹ ጥገናው እንደተጠናቀቀም በክልሉ ትምህርት ተቋርጦባቸው በነበሩ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡
የአፋር ማኅበረሰብ በሽብር ቡድኑ ሕወሓት አገዛዝ ዘመን ለ27 ዓመታት ትልቅ በደል ሲደርስበት እንደነበር አውስተው፤ አሁንም ያንን ጊዜ ለመመለስ አሸባሪው ሕወሓት የቻለውን ያህል ቢሞክርም የአፋር ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በሠራው ታላቅ ጀብዱ ወደ መጣበት መልሶታል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ አሁን አፋር ከአሸባሪው ሃይል ነጻ ስለወጣ በትኩረት እያከናወንን ያለነው የተጎዱትን የመጠገን እና ወደ ልማት ሥራዎች መግባት ነው ብለዋል፡፡
አቶ አሊ መሀመድ እንደገለጹት፤ ሁሉም ክልሎች ለአፋር ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት ሰመራ ድረስ በመምጣት እያሳዩ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አፋር ላይ ያለው ችግር የእኔ ነው ብለው ከአፋር ሕዝብ ጎን በመቆም እገዛ እያደረጉ ነው፡፡
እየተደረገ ላለው ድጋፍ እና እገዛም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በአፋር ክልል በአንድ ዞንና በተጨማሪ በሁለት ወረዳዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውድመትና ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም