ላሊበላ፡- የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በላልይበላ ከተማና አካባቢዋ በሚገኙ የገጠር ከተሞች ከፍተኛ የአስገድዶ መድፈር እንዲሁም ዘረፋ መፈጸሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ካነጋገራቸው የላልይበላና በዙሪያዋ ከሚገኙ የገጠር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ሙሴ በየነ እንደገለጸው፤ የሽብር ቡድኑ በላልይበላና ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ የሆነችው ገለሶት ከተማን በወረራ ይዞ በነበረብት ወቅት ከፍተኛ የአስገድ መድፈር ወንጀል ፈጽሟል፤ በተጨማሪ የንብረት ውድመት አድርሷል፡፡
እንደ ወጣት ሙሴ ገለጻ፤ እናቶችን ከልጆቻቸው፣ ሚስቶችን ከባሎቻቸው፣ ሕጻናት ሴቶችን ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው እየነጠለ በመውሰድ ለሳምንትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ቀናት አግቶ በቡድን ደፍሯል፡፡
የሽብር ቡድኑ ያደረጋቸው እያንዳንዱ ተግባራት ለአማራ ያለውን ጥላቻ አሳይቷል። ጥላቻውን ለመግለጽና ሕዝብን ለመጉዳት በላልይበላ፣ በሹምሻህ ፣ በገለሶትና በኩል መስክ ይገኙ የነበሩ ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት ንብረት ዘርፎ ወስዷል፡፡ መውስድ ያልቻለውንም በሚያሳዝን ሁኔታ አውድሟል ብሏል።
የሽብር ቡድኑ ዕድል ካገኘ አገሪቱ ልትወጣው ወደማትችለው የጥፋት አዘቅት እንደሚከታት የኢትዮጵያ ሕዝብ መገንዘብ ይኖርበታል ያለው ወጣት ሙሴ ፤ አገሪቱን ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለመታደግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድ ሴት ሳይል በመከላከያና በልዩ ሃይሉ ተመዝግቦ ሊፋለመው እንደሚገባ ገልጿል።
ሌላኛው የላልበላና አካባቢው ነዋሪ አቶ ሃብታሙ አከለ በበኩላቸው፤ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ባልና ልጆች ፊት እናቶችን መድፈሩ እንዲሁም ልጆች ፊት አባትን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ አውሬ እንኳን የማያደርገውን ዘግናኝ ግፍ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ ከሰውም ከአውሬም ውጪ የሆነ እንግዳ ምግባር በማሳየቱ ለጥፋት የተላከ ልዩ ፍጥረት መባል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪ የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች የላልይበላ ኤርፖርት በሚገኝበት የሹምሻህ ከተማ የነበሩ ሰዎችን እኛ ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም እያሉ ሲያታልሉ ቆይተዋል። አካባቢውን የወገን ጦር ሊቆጣጠረው ሲቃረብ ግን የሕዝቡን ንብረት በአጠቃላይ በመዝረፍ ከውሃ መጠጫ ብርጭቆ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ንብረቶች ድረስ ጭነው ወስደዋል ብለዋል፡፡
የሹምሻህ ከተማ ጤና ጣቢያ የሕክምና ባለሙያው አቶ ስለሺ ፋንታሁ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማት ንብረቶች ከሚሱን በመዝረፍ ገሚሱን መልሶ ጥቅም ላይ እንዳይውል በማውደም ሸሽቷል።
እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፤ ጤና ጣቢያው ቀድሞም ከላልይበላ ሆስፒታል በትብብር መድኃኒቶችንና አንዳንድ ግብአቶችን ይወስድ ነበር። በትብብር የመጡ በርካታ መድኃኒቶችና ግብዓቶቹ ተዘርፈዋል። አራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒቶች፤ አምቡላንሶች ፣ የሞተር ብስክሌቶች ፣ ፍሪጆች ፣ ማሞቂያዎች፣ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ ውድ የሆኑ አልጋዎች ፣ የቀዶ ጥገናና የማዋለጃ መሣሪያዎች በአሸባሪው ቡድን ተዘርፈዋል።
ጤና ጣቢያው በደረሰበት ጥፋት አገልግሎት በማቆሙ በርካታ እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ ተገደዋል፡፡ በዚህም በርካታ እናቶችና ሕጻናት ለሞት እየተዳረጉ ይገኛል። የደም ግፊት ፣ የስኳርና መሰል የቀን ተቀን ክትትል የሚያስፈልጋቸው ህመምተኞች ተገቢውን ሕክምና እንዲሁም ምርመራ በማጣታቸው ለህልፈት ተዳርገዋል ብለዋል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም