አዲስ አበባ፡- ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በአማራ ክልል ቆቦና ጭና የፈጸማቸውን የጅምላ ግድያዎች አጋለጠ።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ቆቦና ጭና በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ መግደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ግድያዎቹ ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም በነበሩት 10 ተከታታይ ቀናት ውስጥ መፈጸሙን አጣርቻለሁ ብሏል።
ሂውማን ራይትስ ዋች በመስከረምና ጥቅምት ወራት በጭና ተክለሃይማኖት መንደር እንዲሁም በቆቦ ከተማና አካባቢው ስለተፈጸሙ ግድያዎች የዓይን እማኞችን፣ የተጎጂ ዘመዶችና ጎረቤቶች፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ለ36 ሰዎች ቃለ መጠይቅ ማድረጉን አስታውቋል። በአጠቃላይም 49 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ምስክሮቹም የ44ቱን ሰዎች ስም መዘርዘራቸውን ገልጿል።
የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ጭና መንደር በመግባት በ 5 ቀናት በ15 የተለያዩ ስፍራዎች ላይ 26 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ሂዩማን ራይትስ ዋች ገልጿል። በተመሳሳይ በቆቦ ከተማ ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም በአራት የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ 23 ሰዎችን እንደገደሉ ከዓይን እማኞች ማጣራቱን ድርጅቱ አስታውቋል።
ሁለት የሕወሓት ታጣቂዎች የ23 ዓመት ልጃቸውን የ24 ዓመት የወንድማቸውን ልጅ የተገደለባቸውን አንድ የ70 ዓመት አዛውንት ማነጋገሩን የገለጸው ድርጅቱ፤ የአዛውንቱን እማኝነት በሪፖርቱ አስፍሯል።
አዛውንቱም ጭና አጎሽ ማዶ አቅራቢያ በሚገኘው በቤታቸው እንዳሉ እኩለ ቀን ላይ ሁለት የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ወደ ጊቢዬ መጡና መታወቂያ ካርዶቻችን ጠየቁን። ከዚያም የአካባቢው ሚሊሻ አባላት ናችሁ በማለት ወነጀሉን። ከዚያም ልጄንና የወንድሜን ልጅ እጆቻቸውን ወደኋላ አስረው በጊቢዬ በር አውጥተው በጥይት ገደሏቸው። ከዚያም ወደ እኔ ዞረው ሊተኩሱ ሲሉ ለመንኳቸው በማለት ሁኔታውን መግለጻቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
እማኞች የሕወሓት ታጣቂዎች የንጹሃን መኖሪያዎችን እንደመሸሸጊያ በመጠቀም መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ይፈጽሙ እንደነበር ተናግረዋል። ይህም ንጹሃንን ለውጊያ ከለላ በማድረግ የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።
በድርጅቱ ሪፖርት መሰረት፤ የሕወሓት ቡድን ከጭና ባለፈ የሰሜን ወሎ ንጹሃንን ገድለዋል። በተለይ የቆቦና አካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ጳጉሜ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ በቆቦ አጎራባች መንደሮች አርሶአደሮችን ጨምሮ 23 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
የቆቦ ሰኞ ገበያ መንደር ነዋሪ ለሂዩማን ራይትስ ዋች በሰጡት ምስክርነት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ የሕወሓት ታጣቂዎች አራት ሰዎችን ሲገድሉ በቤታቸው መስኮት መመልከታቸውን ተናግረዋል። በርካታ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎችን በምንጭነት የጠቀሰው ድርጅቱ የሕወሓት ታጣቂዎች ንጹሃንን በተለይም ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸውን በግፍ እንደገደለባቸው መናገራቸውን ገልጿል።
የሂውማን ራይትስ ዋች የቀውስና የግጭት ጉዳዮች (crisis and conflict) ዳይሬክተር ላማ ፋኪህ ስለግድያዎቹ ሲናገሩ፤ የሕወሓት ታጣቂዎች ንጹሃንን በመግደል ለሰው ልጅ ሕይወትና ለጦር ሕግጋት መከበር ያላቸውን ቸልተኝነት አሳይተዋል። እነዚህ ግድያዎችና ተያያዥ የጦር ወንጀሎችን በገለልተኛ አካል ማጣራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ከትግራይ ክልል ተነስቶ ወደ አጎራባች አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት የተፈጸመውን በደል በአስቸኳይ ለማጣራት ራሱን የቻለ ዓለምአቀፍ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታውቋል።
ምርመራው በትግራይ ኃይሎች የተፈጸመውን የንጹሃን ግድያና ሌሎች ከባድ የጦርነት ሕግ የጣሱ ወንጀሎችን ማካተት አለበት። በተለይም በየደረጃው ያሉ ተጠያቂዎችን መለየትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማቆየት እንዳለበት ሂውማን ራይትስ ዋች አሳስቧል።
የአሸባሪው ሕወሓት ሰዎችና በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት ዓለምአቀፍ የሰብአዊ ሕግን ማክበርና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሕገወጥ ጥቃት በአስቸኳይ ማቆም አለባቸው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዋች፤ በደል የፈጸሙ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል ብሏል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም