አዲስ አበባ፡- እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ አቶ እሸቴ ሞገስና ሌሎችም ጀግኖች የፈጸሙት ጀብዱና ያደረጉት ተጋድሎ የአማራ ሕዝብም ሆነ የመላው ኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ የሚያመላክት መሆኑን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለጹ።
አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እየተካሄደ ባለው የህልውና ጦርነት በየግንባሩ በእሳት ተፈትነው የወጡ በርካታ ጀግኖች አሉ። አቶ እሸቴ ሞገስና ልጃቸው እንዲሁም በየግንባሩ እየተዋደቁ ያሉ ሌሎችም ጀግኖች የፈጸሙት ጀብዱና ያደረጉት ተጋድሎ የአማራ ሕዝብም ሆነ የመላው ኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ታሪክ የሚያመላክት ነው።
ከባንዳዎችና ከሕወሓት በስተቀር በዚህ ጦርነት በተለያየ መልኩ ተሳትፎ ያላደረገ ኢትዮጵያዊ የለም ያሉት አቶ ግዛቸው፤ በጀግንነት የተሰዋው አቶ እሸቴ ሞገስ ትግሉን ለማስቀጠል ባለው ፍላጎት ምክንያት ለሚያውቃቸው ሰዎች መረጃውን በመስጠቱ ተጋድሎው በሚዲያ እንዲወጣ ተደረገ እንጂ በየግንባሩ ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸሙና ተጋድሎ ያደረጉ የበርካቶች ታሪክ ወደፊት ይገለጻል ብለዋል።
የእነ አቶ እሸቴ ተጋድሎ ኢትዮጵያ ማንም ጠላት መጥቶ የሚያፈርሳትና የሚበትናት ሳትሆን በአይበገሬነት የሚታገልላት ትውልድ የነበራት የጀግና አገር መሆኗን የሚያሳይ ነው።
አገር በቅኝ ግዛት እንዳትገዛ ከማድረግ ጀምሮ አሁንም እየታየ ያለውን ጀግንነት ስንመለከት ይህ ጀግንነት እንዲሁ የመጣ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ መሆኑን ትውልዱ እንዲማር የሚያደርግ መሆኑንም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ጠላቶች የስበት ማዕከል እንደመሆኗ አገሪቱ ከፍ እንዳትል የሚደረግ ትግል ከፊታችን አለ ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የእነ አቶ እሸቴ ተግባር ይህንን ሰባብሮ ለመውጣት የሚያስችል ትልቅ ሞራላዊና ሥነልቦናዊ ግንባታ የሚሰጥ ነው። እስከታገልን ድረስም ሁሉንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ግዛቸው ገለጻ፤ ሁኔታው በኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ አንድ የትግል ምዕራፍ ሆኖ የሚቀመጥና ትውልዱም ሲዘክረው የሚኖር ትልቅ የጀግንነት ስለሆነ በተለያየ መልኩ ተሰንዶ ለትውልድ መተላለፍ አለበት። በታሪክ ጥናት ውስጥም ተካቶ መጠናት ያለበትና የቀጣይም ሆነ ያለፉ ታሪኮችን ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅና ጀግኖችን እየፈጠሩ ለመሄድ ትልቅ ድርሻ ያለው የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።
ስለሆነም መረጃዎችን በአግባቡ ማጠናቀርና መሰነድ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የታሪክ ጸሐፊዎችና ምሁራንም በዚህ ሂደት መሳተፍ አለባቸው። ምሁራን በስፋት እንዲሠሩበት ለማድረግ ደግሞ ተሰንዶ መያዝ ስላለበት የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ መዋቅሩ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
በጦርነቱ ሂደት የነበረውን ጉዳት ጀብዱና ዳራውንም ያካተተ የመሰነድ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
በተጋድሎ ሂደት ውስጥ የተሰው ሌሎች ጀግኖች እንደ አቶ አቶ እሸቴ እድሉን አግኝተው በስልክ ባይገልጹትም ሁሉም ወደ ትግል የሚገቡት ቤተሰቦቻቸውን ለመንግሥት፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አደራ ብለው ነው።
የአማራ ሕዝብም ሆነ መላው ኢትዮጵያውያን የጀግኖችን አደራ ይቀበላሉ፤ የአማራ ክልል መንግሥትም ማኅበረሰቡንና ባለሀብቶችን በማስተባበር በጀግንነት የተሰው ቤተሰቦችን ሁሉ ለማገዝ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም