አዲስ አበባ፡- የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በደሃው ገበሬ ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግፍ የፈጸመው መላውን የአገሪቱን ሕዝብ አንገት ለማስደፋትና ዘላቂ የሥነ ልቦና ጉዳት ለማድረስ በማሰብ መሆኑን የቀድሞ አየር ሃይል አባልና የቦስተን ግብረ ሃይል የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ መቶ አለቃ እዮብ ሽባባው አስታወቁ፡፡
መቶ አለቃ እዮብ ሽባባው ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በዓለም የጦርነት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፊት ለፊት የገጠመውን ሠራዊት በመተው ደሃ ገበሬዎች ላይ የፈጸመው ግፍ የሕዝቡን አንገት ለማስደፋትና የራሳቸውን በእብሪት የተሞላ የበላይነት ስሜት ለማስረጽ ያለመ ነው፡፡ የተፈጸመው ግፍ ለህሊና የሚከብድና ለመቀበል አስቸጋሪ ቢሆንም ሕዝቡ የዚህን ጨካኝ ቡድን ማንነት በሚገባ ተገንዝቦ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሕብረት በመነሳት ታሪካዊ ጠላቱን ለማጥፋት እንዲነሳ አቅም ሰጥቶታል፡፡
በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን የዚህን አውሬ ቡድን በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመከላከያም ሆነ በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ በንቃት ሲከታተሉና ሲቃወሙ መቆየታቸውን አስታውሰው ‹‹ብዙዎቻችን በምንሰማውና በምናየው ነገር እንቅልፍ አልነበረንም፤ ይህን አረመኔያዊ ቡድን እስከወዲያኛው ድረስ ለማስወገድ ከሕዝባችን ጎን ሆነን ስንታገል ቆይተናል›› ብለዋል፡፡
‹‹ይህ እርኩስ የሆነ ቡድን እና ጨካኝ የሆነ ስብስብ የሚፈጽመው በደልና ግፍ በእርግጥ ከጤነኛ ሰው ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ሕጻናት እና መነኩሴዎች ሳይቀሩ ነው እየተደፈሩ ያሉት፡፡ እንደዚህ አይነት የበቀል ስሜት የያዘ ሃይል ሰውም ሆነ ኢትዮጵያዊ ነው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ በጣም የሚረብሽ ፤ ለአዕምሮ ሁሌም እረፍት የሚነሳ ነው›› በማለትም ገልጸዋል፡፡
በተለይ ምንም ይሄ ነው የሚባል ቅርስ የሌለው የሰሜኑ ገበሬን በዚህ ደረጃ እያንገላቱ፤ እየገደሉ፤ ልጆቹን እየፈጁ እያዋረዱት መቆየታቸው ሕወሓት ከመጀመሪያው አንስቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት መሆናቸውን ያረጋገጠ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ሠራዊት እያለ ሕዝብን ማሰቃየት በሰውም በፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ያንን የጦር አካሄድ ስልት ቀይረው ሕዝባዊ ማዕበል በመጠቀም ሰውን በማንገላታት፤ በማሸማቀቅና ከፍተኛ የስነልቦና ተጽዕኖ በመፍጠር ይህንን ጦርነት ለማሸነፍ ነበር ዓላማቸው›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በተቃራኒው ግን ከፍተኛ የሆነ ጥንካሬ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ ከዳር እስከዳር በቁጣ ተነስቶ ይህንን አረመኔያዊና ግፈኛ ስብስብ ዋጋውን እየሰጠው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ማህሌት አብዱል