አንዳንዶች መላው ጥፍት ሲላቸው አያደርጉት የለም። አብዝተው ይዘባርቃሉ፤ ማርሽ ይቀይራሉ፣ ዘዴ ይቀይሳሉ፣ ዕቅድ ከመላ ያበዛሉ ። ይህ ብቻ አይደለም። ወሬ እና ልፍለፋቸው አይጣል ነው። ‹‹ስሙኝ›› ባይነታቸው ከሌሎች ሁሉ ይለያል።
ዓለም ዓይንና ጆሮ እንዲሰጣቸው ይሻሉ። ዕድሉን አግኝተው ‹‹ እህ…›› ከተባሉ ደግሞ የሚያወሩት፣ የሚዘበዝቡት ‹‹እጅ እግር የለሽ›› ይሉት አይነት ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ የእንዲህ አይነቶችን መላ ቢሶች ማንነት እናጢን ከተባለ ታሪካቸው ከበርካታ ክፋቶች ይብሳል። የድርጊታቸው አሻራ በወጉ እንደማይጸዳ ጥላሸት ያደርሳል።
ንጋት ከማይገፈው የጨለማ ታሪክ ያገናኛል። ለነገሩ እውነታው እንዲህ ቢሆን አያስደንቅም። የክፋት ድርጊትን መድረሻ ለማወቅ የመነሻ መስመሩን ጫፍ መፈለጉ ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ ይህ ከታወቀ የሰውየው ልዩ ምልክትና የፎቶግራፍ ምስል አያስፈልግም። ጎረቤት መጠየቅ፣ አካባቢን ማሰስ አይሻም። የኋላ ታሪክ መነሻ ማንነትን ሲያሳይ ልክ እንደ መስታወት ነው። ነጥብ በነጥብ ፣ መልክ በመልክ እየለየ ከባህርይ ያገናኛል፤ ከአሁኑ ድርጊት፣ ከክፋቱ ምርጊት ያዛምዳል፡፡ እንግዲህ የማንነት ስር ሲመዘዝ እንዲህ ነው።
ልክ እንደ መድረሻው መነሻውን አይስትም። ይህ በሆነ ጊዜ ችግሩን ለመደበቅ ወሬ ያበዛል፣ አማራጮችን ፍለጋ ከውሸት ጋር ውሎ ያድራል። የማንነት መነሻው ከክፋት የሚመዘዝ ፍጡር ሞትና ጭካኔ ግብሩ ነው። ቅጥፈትና ጩኸት ስሙ ነው፡፡
ለነገሩ ጭራው የተረገጠ አውሬ አብዝቶ ቢጮህና ቢያንቋርር ፈጽሞ አይደንቅም። ጭራ ሲረገጥ እኮ ወገብ ይለመጣል፣ የልብ ስር ይዞራል። ጭራ ሲረገጥ መላ ቅጥ ይጠፋል፣ ዓለም ሁሉ ይጨልማል። አዎ! ጭራ ሲረገጥ አከርካሪ ይዛነፋል፤ ሁለመና ስቃይ ይሆናል። ይህን ስሜት ለማወቅ ደግሞ የአውሬን ፣ አልያም የሰው በላን ስሜት ማወቅ ያስፈልጋል። ሰው በላው አውሬ ጭራው ሲረገጥበት አፉ ሊከፈት ግድ ነው። አፍ ሲከፈት የስቃይ ድምጽ ይበረታል። ልክ እንደሰሞኑ ማለት ነው።
የጭንቅላት ምስጢር ይጋለጣል። የማንነት አቅም ይፈተናል። ጭራ ተረግጦ አፍ በተከፈተ ጊዜ ልፍለፋ ጩኸቱ አያድርስ ነው። የአውሬው ጭራ መረገጥ የድምጹን ስልት ይቀይራል። ማምለጫ ለማግኘት፣ ሮጦ ለመፈርጠጥ ፣ ጉድጓድ ሜዳውን ያስሳል፡፡ አውሬው ከአዳኙ እጅ ከገባ ወዲህ ግን በዋዛ አያመልጥም። ትርፉ መላላጥ ብቻ ይሆናል። መፍጨርጨሩ ውጤት አልባ ነው። ሙከራው ከመንፈራገጥ አያልፍም። መንጨርጨሩ ከአስቀያሚ ጩኸቱ አይዘልም።
ጥቂት ቆይቶ ደግሞ በተስፋ መቁረጥ ማንቋረር ይጀምራል። ስልት ነው ምናምን እያለ ይዘባርቃል፡፡ የስቃይ ድምጹን የሚሰሙ አንዳንዶች ቀርበው ያዋዩት ይሆናል። ያም ሆኖ ፈጽሞ ሊያምኑት አይችሉም። ትናንት ሰው በላ እንደነበር ያውቃሉና በሩቁ ይሸሹታል። አውሬው ቀድሞ ‹‹እመኑኝ፣ አለሁላችሁ›› ያላቸውን እልፎች ቀርጥፎ መብላቱን የተረዱም ከዳር ቆመው ያጤኑታል፣ የትናንት ክፋቱን እያሰቡ ከአሁን ውድቀቱ ይለኩታል፡፡
ሰው በላው አውሬ እስካሁን ከየቤታቸው እየለቀመ በእሳት የማገዳቸው ነፍሶች አሳዝነውት አያውቅም። እሱ ሁሌም አልጠግብ ባይ ነው። የበላውን አላምጦ ሳይውጥ ዳግመኛ ይርበዋል። የእጁን እየጎረሰም ሌላ ሙዳ ያሰኘዋል፡፡ ዛሬ ጉሮሮው ተፈጥርቆ ሳይያዝ በፊት ብዙ መናገሩን ብዙዎች ያውቃሉ። ሁሌም በጉልበት ማደር ያዋጣው መስሎት አይታመኔ ግፎች ፈጽሟል።
ዓመታት ከቆየበት ጫካው ወጥቶ ሰው ልምሰል ባለ ጊዜ በርካቶች አምነውት፣ ቀርበውት ነበር። የአውሬ ለምዱን አውልቆ በጎች መሀል በገባ ጊዜም ምስኪን የመሰላቸው ንጹሐን ሲታረዱለት ቆይተዋል። አውሬው ለዓመታት ከገዢነት መንበሩ ተፈናጦ ሲቆይ እውነቱ ያልገባቸው ብዙዎች በአታላይ አንደበቱ ሲሞኙ ኖረዋል። የዛኔ ሰው ለመምሰል ጭራውን ቆልፎ፣ ንግግሩን አሳምሮ ነበር። የዛኔ እንደ መልካም ወዳጅ ራስ እየዳሰሰ ፍቅር ላሳያችሁ ይል ነበር።
የዛሬን አያድርገውና በጣቶቹ መሀል የበቀሉት የአውሬው እሾሀማ ጥፍሮች ፍጹም ስውራን ነበሩ። እያከኩ ሲያደሙ፣ እየዳሰሱ ሲቧጭሩ ማንም አላያቸውም፡፡ ጥፍሮቹ አሁን ላይ ደም እስኪተፉ ተመድምደዋል። እድሜ እና ጤና ለአገር ወዳዶቹ፤ አሁንማ የአውሬዎቹ ቆዳቸው እስኪላቀቅ ውስጣቸው እስኪጋለጥ መሰረታቸው ተነቅሏል።
የዛኔ ግን በስለታማ ጥፍሮቻቸው ዕልፎችን ቧጠው አድምተዋል። መርዛሞች ናቸውና በርካቶችን አጥፍተዋል። ትተው የሚያልፉት ጠባሳ ደግሞ በቀላሉ አይሽርም። ቂም ከጥላቻ ያወርሳል። ክፉ ታሪክን ይተክላል። የትውልድን መሰረት ይፍቃል። አንዳንዴ የእዚህን ፍጥረት መልክና ገጽታ መግለፅ ይቸግራል። በርካቶች እንደሚስማሙት የአውሬው ማንነት ልክ እንደ ሲኦሉ ሰይጣን ነው። ሰይጣን ብዘዎች እንደሚገልጹት ያሻውን እስኪያገኝ፣ የሚሽቱን ሁሉ ይሰጣል። የሚሳሳቱ፣ የሚጠለፉ ከወጥመዱ እስኪገቡም መልካም ሆኖ ይቀርባል።
አክባሪ ወዳጆቹ አንድ ቀን ቢያጎድሉ ግን ፈጽሞ አይምራቸውም። ቀርጥፎ ይበላቸዋል፤ አዋርዶ ያሰጣቸዋል፡፡ አጅሬ አውሬው የልቡ ሞልቶ ትዕዛዙ ካልተፈጸመ የበቀል አርጩሜው ይከፋል። ልክ እንደዛሬ ዓመቱ የሰጠውን ሊያስከፍል፣ ያታለለበትን ሊያስመልስ ግብሩን በክፋት ይገልጻል። ይህኔ ትናንት በሌላ ገጽታ የሚያውቁት ሁሉ ከባድ ዋጋን ይከፍላሉ። አምነው እንደተከዱት የኛዎቹ ወገኖች በስለታማ ጥርሶቹ፤ በሹል ጥፍሮቹ ተወግተው፤ ተዘንጥለው ክፉኛ ይጎዳሉ።
ይህ ተግባሩ በግልፅ ታይቷል፡፡ የአውሬው ጭራ እስኪረገጥ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ያልተፈጸመ ግፍና መከራ የለም። እሱ በሰው መሳይ ባህሪው ዕልፎችን አሳዷል። እያሰቃየ፣ በጭካኔ ህይወታቸውን ነጥቋል። ራሱን አክብሮ ሌሎችን አዋርዷል። ሸሽጎ ያቆየውን ትልቅ የክፉት ማንነቱን ለዓለም አሳይቷል፡፡ የሰው በላው ድብቅ ባህርይ ሲገለጥ መልከ ብዙ ሚስጥራቱ ይጋለጣል። የጭካኔው ጥግ ወደር የለሽ ነው። ማንነቱን ደብቆ የሌሎችን ውስጠት ለማጋየት የሚቀድመው አይገኝም።
ከጫካ ህይወቱ ወጥቶ በሰዎች መሀል በቆየባቸው ዓመታት የብዙዎችን ህይወት ሲያመሳቅል ኖሯል፡፡ እርሱን መሰሎች ተሰባስበው ባሴሩት ድብቅ ሴራ የሰው ልጆች መሰረት የሆነች አገር ተዘርፋለች። ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ በአጓጉል የቃላት ሽንገላ የተሞኘው ህዝብ በጠራራ ጸሀይ ተበዝብዟል። የዛኔ ጭብጥ ቆሎ አስጨብጦ ኩንታሉን ለማፈስ መላና ዘዴው የረቀቀ፣ የተራቀቀ ነበር፡፡
አውሬው አንገቱን ደፍቶ፣ ጭራውን ቆልፎ አንደበቱን ሲያሳምር በርካቶች አምነውታል። አውሬነቱን የዘነጉ ፣ ሳሩን እንጂ ገደሉን ያላዩ ብዙኃን በጥርሱ ተቀርጥፈው ወድቀዋል። ዓመታት አልፈው ዓመታት ሲተኩ ግን የግፍ፣ የጭካኔ ህይወት ‹‹ይብቃን›› ያሉ የአውሬውን ስለታማ ጥርስ ሊነቅሉ ቆረጡ። የዛኔ የአውሬው እግሮች ስር ይዘዋል። ዓይኖቹም አርቀው፣ ሰርስረው ያያሉ።
ድምጹ በሩቅ ይጣራል፤ ስምና ዝናው የገነነ ነውና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው። በቃን ባዮቹ ግን እጅ አልሰጡም ። ጥቂት ሆነው ዕልፎችን አስከተሉ። ዓላማቸውን ያወቁ ሚሊዮኖች ከኋላቸው ቆሙ። ደጀን ሆነውም መሪዎቻቸውን ደገፉ፡፡ የታሰበው አልቀረም። የታቀደው ሁሉ ዕውን ሆነ። ሁሉም አስትንፋስ ከአውሬው ጥብቅ አስራት ነፃ ወጣ። ከግፍና በደል ከግድያና ዝርፊያ የተላቀቁት ነፍሶች የሰላም አየር ሊተነፍሱ ፣ በነጻነት ዓለም ሊኖሩ የተስፋን መንገድ ጀመሩ፡፡ አውሬው ይህን ድንገቴ ለውጥ ማመን አልተቻለውም። ሳያስበው በሆነበት ነገር ሁሉ ጭንቀት ያዘው።
በዋዛ ከግፍ መንበሩ የመፈንገሉ ዕውነት ዕንቅልፍና ሰላም ነሳው። የሆነውን ሁሉ ባለማመን አማራጮችን ፈለገ። አሁንም ቀንዱ እስከዳርቻ መቆፈር ይችላል። መርዛም ጥፍሩ ጓዳ ጎድጓዳውን ለመቧጠጥ የሰላ ነው። ላንቃው እስኪላቀቅ ቢጮህ ሰሚ አላጣም ሲል አሰበ። ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ዙሪያ ገባውን እየቃኘ የቀደሙ ጎረቤቶቹን ፈለጋቸው። የትናንት ወዳጆች የቀደመ ውለታቸውን አልረሱም። እሱ ያሻውን ለማግኘት ያሻቸውን ሲሰጣቸው ኖሯል። በእንካ ለእንካ ዘዴያቸው ፣ በእከክልኝ ልከክልህ መርሐቸው በአንድ ሲቋደሱ ኖረዋል።
ለጋራ ዓላማ በእኩል ተሰልፈዋል። እናም ጆሯቸውን አስፍተው ሰጡት፡፡ አሁን ወዳጃሞቹ አውሬዎች በአንድ መምከር ይዘዋል። የሚወድመውን እየለዩ ፣ የሚጋጠውን እያመቻቹ፣ የሚጠበስ የሚዘለዘለውን ቆጥረው ጨርሰዋል። ለጥፋት ዓላማ የሚውለውን ሁሉ አስቀምጠው ቀንና ቦታውን ለይተዋል። ይህ ጉዳይ ለአንዱ ብቻ አይደለም።
ትርፉ ሲገኝ ጠቀሜታው ለሁለቱም ነው፡፡ ከጎረቤት የዘለቀው የአገር ቤቱ አውሬ በዚህ ብቻ ‹‹በቃኝ›› ሊል አልፈለገም። ባህር ማዶ ተሻግሮ፣ አድማስ ሰንጥቆ ታላላቆቹን ነጫጭ አውሬዎች ሊያማክራቸው ወደደ። ታላላቆቹ አውሬዎች በራቸውን አልዘጉበትም። በይሁንታ በፍላጎት ተቀበሉት። ዛሬ ላይ የትናንትናው ጥቅም ቀርቶባቸዋል። ሁሉም አንድ በአንድ አድምጠው በዕቅዱ ተስማሙ፡፡ አውሬ ለአውሬዎች ልባቸው በእኩል ተናበበ። የውስጡን ሃሳብ፣ የወደፊቱን ዕቅድ አመኑለት። እነሱም ቢሆኑ የትናንት ውለታቸውን አልዘነጉም፡፡ትንሹ አውሬ ከቆመበት ምድር ያገኘውን ጸጋና በረከት ሲያጋራቸው ነበር።
ከበላው ከዘነጠለው፣ ሁሉ ሲያቃምሳቸው ኖሯል። እናም ውለታ መመለስ አለባቸው። ቀን ሲወጣ ከሚመጣው ጸጋ ተካፋይ ናቸው። የተጋረጠውን ፈተና በጋራ ካለፉት ከትናንቱ ዓለም ይመለሳሉ፡፡ ሁሉም ቢሆኑ የቀደመውንና የተጋሩትን የጥፍጥና ጣዕም አይዘነጉትም። አውሬው ለእነሱና ለራሱ ጥቅም ሲባል የጠየቁትን አድርጓል። ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ሲሳይ እንደዋዛ ቀርቷል። ይብቃን ያሉ ባለ ራዕዮች ከመንገዱ ከሰፊው ዕቅዳቸው አደናቅፈው ጥለዋቸዋል፡፡
ነጫጮቹ አውሬዎች ከትንንሾቹ አውሬዎች ጋር በደም ማህተም የጠነከረው ውላቸው ዘመን ቆጥሮ እንደሚከፈል ያውቃሉ። የሚያደርጓት፣ የሚፈጽሟት ነጥብ ጉዳይ ሁሉ ያለአንዳች ምክንያት እንደማትባክን ልቦናቸው ያውቃል። ለዚህ ዓላማቸው ዱላ በትር የሚሆኑላቸውን ትናንሽ አውሬዎች ሲያሰማሩ ሁሉንም በእጥፍ እንደሚቀበሉት እርግጠኞች ሆነው ነው። ይህ ቀን እስኪደርስ ሁሉም በእኩል ገበታ ተቀምጠው የአውሬውን ውለታ ያስታውሳሉ፡፡ አሁን የአውሬው የክፋት ልብ መነሳሳት ጀምሯል።
ትናንት የነበረበት የምቾት ዓለም እንደማይዘልቅ ሲገባው ጋሻ የሆኑለትን አጋሮች አጣምሮ ጦሩን ሰብቋል። የአውሬነት ባህሪው፣ የማንነት መልኩ በእጥፍ ጨምሮም የሚያርዳቸውን፣ የሚበላቸውን በጎች መርጦ ጨርሷል፡፡ አንድ ቀን ሌሊት ብዙ ንጹሐን ካሉበት ስፍራ ደረሰ። አብዛኞቹን አሳምሮ ያውቃቸዋል። ማንነቱን ሸሽጎ፣ ጭራውን ቆልፎ በአብሮነት ዓመታትን ዘልቋል።
አውሬው አሁን የትናንቱን እያሰበ አይደለም። አስብቶ የሚያርድበት ጊዜው ደርሷልና ቢላውን ስሎ ፣ ገመዱን ሸክፎ ከበጎች መሀል ተገኝቷል። ክፉው አውሬ የማንነቱን ጥግ፣ የጭካኔውን ሀ ሁ በግድያና በጭፍጨፋ ጀምሮታል። ደም የለመደው ሆዱ በዚህ ብቻ አላበቃም። በተላላኪዎቹ ታግዞ ፣ በአይዞህ ባዮቹ ተደግፎ የራሱን ወሰን ተሻግሯል። መሰሎቹን አሰልጥኖ ፣ እኩዮቹን አመቻችቶ ጥርሱን ስሎ ተነስቷል። ትናንት አብሯቸው ኖሮ ፣ ክፉ ደጉን ከተጋራባቸው መንደሮች ሲቃረብ የስልጣን መንበሩን አሰበው።
የምቾት ዓለሙን አስታወሰው ፤አሁን በቆመበት መሬት የትናንቱን ገዢነት ማሳየት አይችልም። የግፍ ድርጊቱን ፣ የጭካኔውን ዓለም ተነጥቋል። የአውሬው ማንነት አልተቀየረም። በቀደመው ባህሪው፣ በሰዎች መሀል ገብቶ አጨዳውን ጀምሯል። ደም አፍስሶ፣ ህይወት ነጥቋል። ንብረት አውድሞ አገር አፍርሷል፡፡ የአውሬው ክፉ ድርጊት በደጋፊዎቹ ታጅቦ በጥፋት መንገዱ እየተጓዘ ነው። በየደረሰበት የሚያሳርፈው ክፉ አሻራ ዘመን አይሽሬ ሆኗል። ድርጊቱ ሁሉ ከቃላት በላይ ነው።
የትናንት ወዳጆቹ ‹‹አለንልህ›› እያሉት ፣ ጆሮና ዓይኖች ቢያገኝ፣ በክፋት መንገዱ ቀጥሏል፡፡ አሁንም ማንነቱን የተረዱ ጀግኖች ዳግማዊ ትግል ይዘዋል። የአውሬውን የክፋት ቀንዶች ሊሰብሩ፤ መርዛማ ጥፍሮቹን ሊያነክቱ የአንድነት ክንዳቸው ተጣምሯል። አሁንም አውሬው ተስፋን ሰንቋል። ከወደቀበት አንስተው ከአልጋው ሊመልሱት ያሰቡ ነጫጭ አውሬዎች ‹‹አለንህ›› ይሉት ይዘዋል።
የተነሳበትን ዓላማ ሊያኮላሹ ቁርጠት የሆኑበት ጀግኖች ደግሞ መፈናፈኛ እያሳጡት ነው። ዕድሜውን ለማርዘም የሚጠቀምባቸው ግልገል አውሬዎች ስልጣኑን ይመልሱለት ዘንድ ከእሳት ሲማግዳቸው አይደነግጥም። ከእናታቸው ጉያ እየነጠቀ ለሞት ሲዳርጋቸውም ስለነገው የስልጣን ጥማቱ እያሰበ ነው፡፡ የአውሬዎቹ ፍልፈሎች በየደረሱበት ጎጆ ያገኙትን ይገድላሉ። ከእጃቸው የገባውን ይነጥቃሉ፤ ጸያፍ ድርጊቶችን እንዲከውኑ ከአባታቸው ትዕዛዝ አግኝተዋል። በውርስ ካገኙት ጭካኔ ያሻቸውን ይፈጽማሉ። ንብረት አውድመው ፤ በእሳት አጋይተው ፤ ነፍሶችን ይነጥቁ ዘንድ ተልከዋል፡፡ ዳግማዊ ትግሉ ተቀጣጥሏል። የአውሬው ጥርሶች እየረገፉ ነው።
የሾለው ቀንዱ ቄጤማ ሆኗል። ብራቅ ድምጹ ከጉሮሮው ደርቋል። መርዛማ ጥፍሮቹ ተነቅለው ደም ማዝነብ ይዘዋል። ርሀብ ያጠወለገው አካሉ ርቆ እየተራመደ አይደለም። ትናንት ‹‹አለንህ›› ያሉት ዘመዳሞቹ አውሬዎች በሰው ልጆች ኃያል ድምጽ ተውጠዋል። ዓለም በተቃውሞ ጩኸት ተሸፍናለች፡፡ አሁን የአውሬው ጭራ ተረግጧል። መላ ቅጡ ጠፍቶታል። በየአጋጣሚው የሚጮህበት ጉሮሮው እንደቀድሞው አልሆነም። ማስተባበያዎቹ አልቀውበታል። የማታለያ ቃላቶቹ ፣ እያሳመኑ አይደሉም። ባህር ተሸጋሪዎቹ ተንከባላይ የአውሬው ዘመዶች እንደቀድሞው አላገዙትም። ዱላው በዝቶበታል። በለኮሰው እሳት፣ በጫረው ክብሪት በየደረሰበት እየጋየ፤ እየተቃጠለ ነው፡፡ የአውሬው ግልገሎች ቃል እንደተገባላቸው ካሰቡት አልደረሱም። የትናንቱ የተስፋ ስንቅ አብሯቸው አይደለም። ከእናቶቻቸው ተነጥቀው ከበርሀው ወድቀዋል። ከባልንጀሮቻቸው ተለይተው የአሞራ ሲሳይ ሆነዋል። ዕልፎች እጃቸውን እየሰጡ ምህረት ይለምናሉ።
የፈጸሙትን እየተረኩ፤ ያደረጉትን እያስረዱ፣ የአውሬውን ሥራ ይኮንናሉ። አውሬው የተማመነባቸው ግልገሎቹ ከታለመው ግብ አልደረሱም። በያሉበት ታድነው ለምርኮ ተዳርገዋል። ዝረፉ የተባሉትን ይዘው። ርቀው አልተራመዱም። ከገቡበት ከበባ ከተያዙበት ፈርጣማ ክንድ በቀላሉ አላመለጡም። እስካሁን የፈጸሙት ግፍና መከራ ‹‹ይብቃችሁ›› ተብለዋል። ‹‹እንብላ›› ሲሉ ተበልተዋል። እንውጣ ሲሉ ተይዘዋል፡፡ አሁን የጨካኙ አውሬው ጭራ ላይለቀቅ ተረግጧል። አንዳች ምርጫ የለውም። አከርካሪው ታንቋል። ተንኮል መጥመቂያ ጭንቅላቱ አዙሮ ማየት ተስኖታል። የሰለለ ድምጹ የጉሮሮው ቃላት ለማንም እያሳመነ አይደለም።
አርቆ እንዳይጮህ በለመደው ስልት እንዳይዋሽ ሆኖ ተወጥሯል። ‹‹ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም›› እንዲሉ ሆኖ መግቢያ መድረሻው ጠፍቶታል፡፡ ጭራው የተረገጠው አውሬ በቀረችው ሰላላ ድምጽ አሁንም ‹‹ስሙልኝ›› ማለቱን ቀጥሏል። ዛሬም ‹‹አለሁ፣ አልተሸነፍኩም›› ለማለት ዓለምን በቅጥፈት ፣ ራሱን በቅሌት አሳምኗል። ከበባውን በማፈግፈግ ፣ ሲተካው አንዳች እፍረት የለውም ።
የየዕለቱን ሞት መልካም ዕንቅልፍ አድርጎ፣ እንደቅጠል በሚረግፉት ነፍሶች መቀልድ ማፌዙን ቀጥሏል፡፡ ለነገሩ ጭራ ሲረገጥ ነፍስ ትድረስበት ታጣለች። ጭራ ሲረገጥ የእግር መቆሚያው፣ የጭንቅላት ማደሪያው አይታወቅም። ናላ ይዞራል፤ ውሸት ውሸቱን ያዘላብዳል። ሀቁን እውነቱን ያስክዳል። ጭራ ሲረገጥ ሁሌም ቢሆን እንዲህ ነው። የእጅ መላ ይወድቃል፤ የአንደበት ቃላት ይጠፋል፤ የያዙት ተስፋ ይጨልማል። አሁን ማምለጥ፣ መፈርጠጥ ይሉት የለም። ሊጥ የጠማቸው የአውሬው ጭፍራዎች በውርደት ታድነዋል። የተጀመረው በከባድ ጫማ ጭራን የመርገጥ ተልዕኮ በየቦታው ተቀጣጥሏል። የተያዘው አውሬ ፣ የተረገጠው ጭራ ከስሩ ተጎምዷል።
መልካም ሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 30/2014