የምንኖርበት ዘመን ዓለም በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ሰላም ያገኘችበት ወቅት እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። ይህን ከሚናገሩት ምሁራን መሀከል ደግሞ ዋነኛው እስራኤላዊው የዘመኑ ሊቅ ፕሮፌሰር ዩቫል ሀራሪ ናቸው።
ሀራሪ ‹‹ሆሞ ዲየስ›› በተሰኘ በዓለም ከፍተኛ ተነባቢነት ባገኘ (በአማርኛም ተተርጉሟል) መጽሀፋቸው ስለ ዘመናዊው ዓለም እና ጦርነት ሲያነሱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ብዙሃኑ የዓለም መንግሥታት ጦርነት በጣም ውድ እና ጭራሽ የማያዋጣ መሆኑን በመገንዘባቸው ጦርነትን ከማሰብ በጣም መራቃቸውን አስፍረዋል።
በተቃራኒው ጦርነት በዲፕሎማሲ እየተተካ መምጣቱን እና ውጊያ ግድ ከሆነም የሚከናወነው በሳይበር በኩል እንደሆነ ይጠቁማል። በዋነኝነት ግን ጦርነት ከኢኮኖሚያዊ አዋጪነቱ ማነስ በተጨማሪ በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ ሕይወት በሚሰጠው ከፍ ያለ ዋጋ የተነሳ የጦርነት ስልቶች መቀየራቸውን ይገልጻል።
በዚህም የተነሳ ዛሬ ላይ ጦርነት ሲካሄድ ተዋጊዎች ሙሉ ትኩረታቸው የተዋጊውን ሠራዊት ጨፍጭፎ መጨረስ ላይ ሳይሆን የጠላትን የማድረግ አቅም በማዳከም ላይ ነው። ለዚህም የጦር ጀቶችን አንስቶ እንዳያበርር የአየር ማረፊያውን ይመታሉ ፤ የማጥቃት ጉልበቱን ለማዳከም ታንኮቹን እና መድፎቹን ያጋያሉ ፤ ሚሳይል መተኮስ እንዳይችል የሚሳይሉን መቆጣጠሪያ በቴክኖሎጂ ወይም በሃይል ከጥቅም ውጭ ያደርጋሉ ወዘተ…። ዋና ግባቸውም ጠላት ማድረግ ያሰበውን እንዳያከናውን ማድረግ ብቻ ነው።
በዚህም መንገድ በከፍተኛ ደረጃ በጦርነት ወቅት የሚያልቀውን የሰው ልጅ ሕይወት ማዳን ተችሏል። ፕሮፌሰር ሀራሪ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ረሃብን፣ ጦርነትን እና በሽታን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ በመቻሉ አሁን ላይ በረሃብ ከሚሞተው ይልቅ ውፍረትን ተከትለው በሚመጡ በስኳር እና ደም ግፊት የሚሞተው በልጧል። በጦር ሜዳ ከሚሞተው ይልቅ በድንገተኛ የመኪና አደጋ የሚሞተው ይበልጣል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ የዓለም ሂደት የማይገባው እና ከዓለም በተቃራኒ አቅጣጫ የሚሄድ ሃይል አለ።
እሱም ሕወሓት ነው። ሕወሓት ዛሬም በሰው ልጅ ሕይወት የሚቆምር እና ለሰብአዊነት ዋጋ የማይሰጥ ቡድን ነው። ቡድኑ የአማራ እና አፋር ክልሎችን በመውረር በንጹሀን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ለሰው ልጅ ሕይወት ግድ የሌለው መሆኑ የተገለጸበት አንድ ወንጀለኝነቱ ነው፤ በእዚህ ወንጀል የዘር ማጥፋት ፈጽሟል አልፈጸመም የሚለው በሚመለከታቸው አካላት ታይቷል፤ እየታየም ነው። እኔ ዛሬ ለማንሳት የወደድኩት ግን የገዛ ሕዝቤ በሚለው የትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን ጅምላ ጭፍጨፋ ነው።
ይህን ለማየት ደግሞ ቀላሉ መንገድ ሕወሓት አሁን የሚከተለውን የጦርነት ስልት መመልከት ነው። በጦሩ ሜዳ ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩት እና መንግስትም በተደጋጋሚ እንዳስታወቀው ሕወሓት ሕጻን ሳይል አዋቂ ከየቤቱ በግዴታ ሰዎችን ሰብስቦ ወደ ጦር ግንባር ይልካል።
የሕወሓት ሰዎች ይህን ስልት “ጦርነቱን ሕዝባዊ ማድረግ” የሚል የዳቦ ስም ይሰጡታል። በትክክለኛ የጦር ሜዳ ስሙ ግን የህዝብ ማእበል (human wave) ነው የሚባለው። የሕዝባዊ ማእበል ሙያዊ ብያኔን ስንመልከት የሕዝብ ማእበል ጥቃት ወይም የሕዝብ ባህር/ማእበል/ ጥቃት ማለት ሲሆን፣ እግረኛ ወታደርን ያለምንም ከለላ በጠላት ላይ ፊትለፊት በማጉረፍ ጠላትን ማጥለቅለቅ ነው። ልብ አድርጉ! ይህ የውጊያ ስልት በአሁኑ ወቅት ብዙም ተቀባይነት የሌለው እና አዋጪነት የጎደለው ነው።
ሕወሓት ግን ይህን ነው የሚከተለው። ሊያውም ምንም አይነት ወታደራዊ ልምድ እና እውቀት የሌላቸው ሲቪሎችን ከፊት በማድረግ። አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው። በዚህ አይነት የውጊያ ስልት እና በውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው ከመቀሌ ጣርማ በር የተደረሰው። ነገር ግን በሂደቱ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የትግራይ ልጆች አልቀዋል።
ሕወሓቶች ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ ግን የተረፈውን እጁን እንዲሰጥ ከማድረግ ይልቅ በተቃራኒው ድሮ ጦርነቱን ሲቀምሩ የተነሱትን ፎቶ በመለጠፍ ለተጨማሪ ጥፋት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። ልብ አድርጉ እንግዲህ! ዋኖቹ መቀሌ ተቀምጠው የእርዳታ እህል እየበሉ ነው የድሃ ትግራዋይን ልጅ “በዚህ በኩል ይህን ያህል ሺ ብናዘምት” “በዚያ በኩል ይህን ያህል ሺ ብናሰማራ” እያሉ ለሕዝብ ማእበል ታክቲካቸው የሚጠቀሙበት።
በፈረንጆቹ 1984 ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ Human Waves በሚል በሰራው አንድ አጭር ዘገባ ላይ በአንደኛው ዓለም ጦርነት በሶሜ ጦርነት ይህ ታክቲክ ትግበራ ላይ እንደዋለ አመልክቷል። በወቅቱ ጦርነቱ በተጀመረ በግማሽ ሰአት ውስጥ 40ሺ ብሪታንያውያን ያለቁት በዚህ ካልሆነ በሌላ በምን ይመስላችኋል ይላል ጸሀፊው።
በእርግጥም ይህ በዓለም ታሪክ እጅግ አስከፊ የተባለው እና ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በአንድ ወገን ጀርመን በሌላ ወገን ሆነው ያደረጉት ውጊያ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሰው የተሳተፈበት ሲሆን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሞቷል ወይም ቆስሏል። በዚህም የተነሳ ጦርነቱ ከተገኘው ድል ይልቅ በጭፍጨፋው መጠን ማየል ይታወሳል። ዛሬ ላይ ሶስቱም አገራት እንኳን ይህን መሰል
ታክቲክ ሊጠቀሙ ስለ ጦርነት እንኳን ለማሰብ አይፈቅዱም። እርማቸውን አንድ ወታደር ቢሞትባቸው ዓለምን ያናውጡታል። ነገር ግን ማገናዘብ የተነፈጋቸው የሕወሓት ሰዎች ይህን ያረጀ ያፈጀ የጦርነት ስልት ሲጠቀሙ እና ከአንድ በላይ የትግራይ ትውልድ በየሜዳው እንደ ቅጠል ረግፎ እንዲቀር ሲያደርጉ የስንቅ፤ የፕሮፓጋንዳ ፤ የዲፕሎማሲ እና የሞራል ድጋፍ ያደርጉለታል።
ከዚያም አልፎ በሳተላይት ድጋፍ እየተሰጠው በዚህ ግባ በዚያ ውጣ እየተባለ ትውልድ ማስጨፍጨፉን እንዲቀጥል ያበረታቱታል። እብዱን ጻድቃን ገብረ ትንሳይንም “ታላቁ የጦር ስትራቴጂስት” እያሉ በሚዲያቸው ያሞካሹታል። በእውነቱ ያልሰለጠኑ ወጣቶችን ፤ ሴቶችን ፤ እናቶችን እና እድሜያቸው ያልደረሰ ሕጻናትን ማሰለፍ የጦር ስትራቴጂስት ካስባለ የእነሱ ጄነራሎች ሊጠቀሙበት ይገባ ነበር። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንዳልኳችሁ እንኳን ይህን የወደቀ የውጊያ ስልት መጠቀም ቀርቶ ስለጦርነት ማሰብ እንኳን ነውር ሆኖ እንዲታይ አድርገው አገራቸውን እየመሩ ነው።
የሆነ ሆኖ ጦርነቱ ወደ መገባደዱ ላይ ነው። አንድ ሀቅ ግን ልብ ሊባል ይገባል። እሱም ሕወሓት እና አጋሮቹ የትግራይ ሕዝብም እንዲጨፈጨፍ ማግደውታል። ስለዚህም በዘር ማጥፋት / በጄኖሳይድ/ የሚጠየቁ ሕወሓት እና ጀሌዎቹ ብቻ ናቸው።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ትህነግና ተባባሪዎቹ የኢትዮጵያ መንግሥትን በዘር ማጥፋት /ጄኖሳይድ/ ሊከሱ መረጃ የሚሉትን እየሰሩ ናቸው፤ ልብ በሉልኝ፣ /መረጃ የሚሉትን እየሰበሰቡ ሳይሆን፣ እየሰሩ ናቸው/። አዎ የኔ የሚሉትን የትግራይ ክልል ሕዝብ ሕጻን አዛውንት ሳይሉ ያለምንም የውትድርና ሥልጠና በጦርነት ማግደው በማስጨረሳቸው በዘር ማጥፋት መጠየቅ ያለባቸው እነሱ ናቸው። እንድ ትውልድ ነው የጨፈጨፉት።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ኅዳር 29/2014