የዛሬው ዓምዳችን በ1970 ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ ያ ወቅት ሶማሊያ ኢትዮጵያን የወረረችበትና ኢትዮጵያውያን ይህን ወረራ ለመመከትና ዳር ድንበራቸውን ለማስጠበቅ ልክ እንዳሁኑ ሉአላዊነታቸውን ለማስጠበቅ እያደረጉ እንዳሉት ሁሉ ሆ ብለው በጦር ግንባር የዘመቱበት ነበር፡፡
ሠራዊቱ በየግንባሩ ዳር ድንበር ለማስከበር ከሚያደርገው ትግል ጎን ለጎን ሕዝቡ ደጀንነቱን ድጋፉን በልዩ ልዩ መልክ ይገልፅ ነበር፡፡ በዚህም የተለያዩ አስተዋፅኦ እያበረከተ ለአገሩ ያለውን ድጋፍና አጋርነት ያሳይ እንደነበር በወቅቱ የወጡት ጋዜጦቻችን ያስረዳሉ፡፡
ያ ተግባር ሕዝቡ አሁን ለሠራዊቱ ደጀን መሆን እንዳለበት ያስገነዝባልና ይህን የሚመለከቱ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡
ከከፍተኛ አንድ ለምርት ሥራ የተሰማሩ 2 ጋሻ ጤፍ ሰበሰቡ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
የኢትዮጵያን አብዮትና አንድነት በተባበረ አብዮታዊ ሕዝባዊ ትግል ለመጠበቅ «እያመረቱ መታገል እየታገሉ ማምረት» የሚለው መርሆ በግብር በመተርጎም ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ የሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ፩ ውስጥ የሚገኙ አብዮታዊያንና አገር ወዳዶች ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ በአድአ ወረዳ ተገኝተው ከሁለት ጋሻ በላይ የአርሶ አደሩን የጤፍ አዝመራ በማጨድ ሰብስበዋል፡፡
በአብዮታዊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደው ብሔራዊ ጦርነትና ወረራ የመደብ ትግል ዘላቂ ድልን ለመጎናጸፍ ሠፊው የከተማው ነዋሪ ከጭቁኑ አርሶ አደሩ ጎን ተሰልፎ ምርትን ለማሳደግ የሚደርገው ትብብር የአብዮቱ ድል ጉዞ አንድ ምዕፍራ መሆኑን በማመን በከፍተኛ አንድ ውስጥ ከሚገኙት ሰባት ቀበሌዎች ውስጥ የተውጣጣው ሕዝብ የመጀመሪያውን ዙር የምርት ዘመቻ ያካሄደው በዋጂቱ፣ በአባይና ደብድቤ በተባሉት ቀበሌዎች ውስጥ ነው፡፡
በዚሁ ምርት አሰባሰብ ዘመቻ ላይ ያካባቢው አርሶ አደሮች ከአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አንድ ኗሪዎች ጎን የተሰለፉ ሲሆን፤ በዚሁ ዘመቻ የከተማው ሕዝብ አብዮታዊ ዲሲፒሊን በተመላበት አኳኋን ጤፉን በማጨድና በመከመር ያበረከቱትን አገልግሎት አርሶ አደሮቹ በማድነቅ ደስታቸውን ገልጠዋል፡፡
የከተማው ኗሪዎች በተለይ ባለፈው ረቡዕ የምርት ስብሰባው ዘመቻ ባካሄደበት ወቅት ጓድ ሻምበል ካሣዬ አራጋው የሸዋ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ ተገኝተው በአጨዳው አገልግሎት ላይ ተካፋይ በመሆን የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች ከጭቁኑ ገበሬ ጎን በመሰለፍ የትግል አንድነታቸውን በግብር በማሳየታቸው በአብዮቱ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ባለ ውለታ መሆናቸውንና ይህም የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አለመሆኑን በማስገንዘብ አድናቆታቸውን ሠፋ ባለ ንግግር ገልጠዋል።
(ታኅሣስ 7 ቀን 1970 ከወጣው አዲስ ዘመን) የሲራሮ ወረዳ ገበሬ ማኅበራት 1703 ኲንታል በቆሎ ለስንቅ ሰጡ አዋሳ(ኢ.ዜ.አ.)
በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ በሲራሮ ወረዳ የ፩፻፲፫ ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት አባሎች ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት አዳራሽ ጠቅላላ ስብሰባ አድርገው በግንባር ቀደም ዘምቶ ከጠላት ጋር በመዋደቅ ላይ ለሚገኘው ጦር ስንቅ የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ለማስገኘት በተስማሙት መሠረት ፩ሺህ ፯፻፫ ኲንታል በቆሎ ሰብስበው ለወረዳው አብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኰሚቴ አስረከቡ፡፡
የወረዳው አርሶ አደሮች ሰሞኑን ባስተላለፉት ውሳኔ መሠረት ወረዳው በስድስት ዞን ሰብሉን እየተቀበሉ ወደ መጋዘን የሚያቀርቡ ከመንግሥት ሠራተኞች ከገበሬ ማኅበራት የተውጣጡ ተወካዮች ከሰንበቴ ገበሬዎች አካባቢ ፩ሺህ፩፻ ኲንታል፣ ከአቡሬ ገበሬዎች አካባቢ ፭፻ ኲንታል፣ ከአቧሬ ገበሬዎች አካባቢ ፩፻፫ ኲንታል በጠቅላላው ፩ሺህ ፯፻፫ ኲንታል በቆሎ ሰብስበው፤ የእህል ቦርድ በውሰት በሰጠው ጆንያ ሞልተው የወረዳው አስተባባሪ ኰሚቴ በአጄ ከተማ ባዘጋጀው መጋዘን አጠራቅመዋል፡፡
የሲራሮ ወረዳ ገበሬ ማኅበራት አስተዳዳሪና የወረዳው የአብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኰሚቴ ሊቀመንበር ከሥፍራው ተገኝቶ ለነበረው ወኪላችን ሲያስረዱ በእህሉ አሰባሰብ ላይ አንዳንድ ቸልተኞችና አሻጥረኞች የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች በወቅቱ ተዘዋውረው ባለማስረከብ ወደ ኋላ ይጎትቱት እንጂ በወረዳው እስካሁን በመዋጮ በኩል እጅግ አስመስጋኝ ይዞታና እውነተኛ የሀገር ወዳድነት ስሜት አሳይቷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሲራሮ ወረዳ ገበሬ ማኅበር 22ሺህ ብር በማዋጣት ሚሊሺያዎችን ለማሰልጠን ምልመላ የጀመሩ መሆኑን የወረዳው ገበሬዎች ሊቀመንበር አረጋግጠዋል፡፡
(ታኅሣስ 28 ቀን 1970 አም) በከፍተኛ 24 ቀበሌ 15 ኗሪዎች ለዘማች ቤተሰቦች አገልግሎት ሰጡ
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ 24 የቀበሌ 15 ነዋሪዎች ከቀበሌው ውስጥ ከየመሥሪያ ቤታቸው ተመርጠው በእናት ሀገራችን ላይ የተቃጣውን የአድኃሪ ወረራን ጦርነት ለመከላከልና ለመደምሰስ በግንባር ቀደምትነት ለዘመቱት ዘማች ቤተሰቦች እንክብካቤ ለማድረግ ባለፈው እሁድ አጥር ያጠሩላቸው መሆኑን የቀበሌው ጽ/ ቤት አስታወቀ፡፡ «የአብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት» በግንባር ቀደምትነት ዘምተው ከጠላት ጋር በመዋደቅ ላይ ለሚገኙት ዘማች ቤተሰብ ሕዝቡ በመተባበር ይህንኑ ሥራ ሊያበረክት የቻለው ቀደም ሲል የቀበሌው ሊቀመንበርና ሌሎች አባሎች ለዘማቾች ቤተሰብ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ባሳሰቡት መሠረት ነው፡፡
በዚሁ መሠረት ከቀበሌው ሕዝብ አንድ ኰሚቴ ተመርጦ ከተቋቋመ በኋላ ሥራው መጀመሩ ታውቋል፡፡ የተመረጠው ኰሚቴም ባወጣው ፕሮግራም መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ የዘማቾቹ ቤተሰቦች ማንኛውንም ዕቃ ከኅብረት ሱቅ በሚገዙበት ወቅት ተራ ሳይጠብቁና ያለአንዳች ውጣ ውረድ እንዲገዙ ሲወሰን፤ እንዲሁም ለሚያጋጥማቸው ችግር ሁሉ ሕዝቡ እንደሚተባበራቸው ተገልጧል፡፡
ከዚህም ሌላ የዘማቾቹን ቤተሰብ ችግር እንዳይገጥመውና ሕዝቡም በየጊዜው ለርዳታ የተዘጋጀ በመሆኑ ነዋሪው ሕዝብ ቃል በገባው መሠረት በተጠቀሰው ዕለት የዘማቹን ቤተሰብ አጥር ሠርቶ ያስረከበ መሆኑ ተገልጧል፡፡
ለዚሁም አጥር ሥራ ቀበሌው ፻፶ ብር ግምት ያለው ዛፍ ከመስጠቱም በላይ ከሕዝቡ ጉልበት ጋር ሲደመር ከ፫፻ ብር በላይ እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡ ለወደፊቱም ነዋሪው ሕዝብ በየሳምንቱ በዚህ ዓይነት በኅብረት በአካባቢው ተመሳሳይ አገልግሎት ለማበርከት መወሰኑን የቀበሌው ጽ/ቤት ጨምሮ ገልጧል፡፡
(ታኅሣስ 1 ቀን 1970 አም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኀዳር 28 / 2014