በጋራ ድምጽ ሀገር ፈጥረን እናውቃለን። በጋራ ክንድ አርነት ወጥተን እናውቃለን፣ በጋራ ተጉዘን ያልወጣነው የመከራ ዳገት የለም፤ ኢትዮጵያዊነትን ለጠየቁን መልሳችን ይሄ ነው። አሁንም እንዲህ ነን፤ ባለአንጸባራቂ ድሉን የአድዋ ታሪክ በጠላቶቻችን ማንቁርት ላይ ቆመን ልንደግመው እየተንደረደርን ነው። ሮጦ የማይደክመው አቦ ሸማኔ ክንድ፣ ታግሎ የማይዝል አንበሳ ትውልድ የበቀለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
ከተስፋችን ወደብ ለመድረስ ሀይሉም፣ አቅሙም ጥበቡም ያለን ህዝቦች ነን። መነሳታችን ያስፈራቸው አሜሪካና ባላንጣ ሀገራት እንደ ሕወሓት የካብ ላይ እባብ ሆነውብን ብንቸገርም የመጨረሻዋን ሳቅ ግን ማንም አይወስድብንም። ጊዜው የኢትዮጵያ ነው። ሀገር ለመፍጠር፣ ጠላት ለመውረር እውነትና ፍትህን አንግቦ ስለሀገሩ ለመሞት የተዘጋጀ ትውልድ መሀል ነን። በዚህ ትውልድ ስር ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፎ መስጠት የማይታሰብ ነው።
የፈተናችንን ያህል የምንስቅበት፣ የዝቅታችንን ያህል ወደ ላይ የምንሰቀልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ሰሞነ ህማማት ላይ ነን፤ ትንሳኤ ልንሰማ፣ ትንሳኤ ልናይ ዋዜዋው ላይ ነን። ሊነጋጋ በከጃጀለው ሰማይ ስር ነን፤ ከፊታችን እንዳይመሹ ሆነው የሚነጉ ቀናቶች እየተፈጠሩ ነው። ሰሞነ ህማማት መከራችንን ረስተን በአዲስ መንፈስና በአዲስ አስተሳሰብ ቀና የምንልበት ማለዳ ነው።
ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሩ በርካታ ድምጾች በአለም ዙሪያ እየተነሱ ነው። የኢትዮጵያዊነትን አለላ መልክ ለማቆሸሽ ከእብሪተኞች ጋር የሚዶልቱ የአሜሪካን መንግስትን መሰል የሀጢያት ጥበበኞች ቢነሱብንም በህዝባችን የጥንካሬ ክንድ ግን የተቃጣብንን የተንኮል ሴራ እየበጣጠስን፣ የተከፈተብንን ዘመቻ በድል እየተወጣን እንገኛለን። በትንሳያችን ማግስት የተነሱ ይሁዳዊ ባንዳዎች ከዚያም ከዚም እያወኩን ቢገኙም በማሸነፍ ርምጃ ውስጥ ነን።
ከዚም ከዛም ድምጻችንን ለምንወዳት ሀገራችን በማሰማት ላይ እንገኛለን። የአሜሪካ መንግስትና ተባባሪዎቹ ሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች መንግስታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነትና የሀሰት መረጃቻውን የሚቃወም ‹ኖ ሞር› የተሰኘ ሰልፍ እየተደረገ ይገኛል።
ይህ ድምጽ በመላ አለም እያስተገባ ነው። ሀገር በልጆቿ ስትኮራ እንዲህ ነው። ድምጻችን ዋጋ እስኪያወጣ ድረስ ገና እንጮሀለን። ስለ ሀገራችን ዝም አንልም። በአሁኑ ሰዓት አለም ስለኢትዮጵያ በአንድ ድምጽ እያወራ ነው። ኢትዮጵያን አትንኩ፣ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ የሚሉ የቁጣ ድምጾች ተበራክተዋል። የዓለም የክፋት ፊታውራሪዋ የአሜሪካ መንግስት ከኋላና ከፊቷ መሰል ባንዳዎችን አሰልፎ የድሀ ሀገራትን ተስፋና ህልም ለማምከን ጎንበስ ቀና ላይ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን በፍጹም እጅ ሳንሰጥ ሀያሏን ሀገር እየተፋለምናት እንገኛለን።
በዳግማዊ አድዋ ዳግማዊቷን አፍሪካ ልንፈጥር በአንድነት ተሰልፈናል። አሜሪካ የብልጽግናዋን መሰረት በድሀ ሀገራት ሞትና ጉስቁልና መስርታ ዘመናዊ አምባገነንነትን ለዓለም ያወጀች ገና ስልጣኔ ምን እንደሆነ ያልገባት ሀገር ናት። ስልጣኔ ምንጩ ሀብት አይደለም፤ ነጻነት ነው፤ በዚህ በያዝንው የህልውና ጦርነት ከላይ ማን ስልጡን እንደሆነ የምናየው ይሆናል።
የአሜሪካ ስልጣኔ የሀይል ስልጣኔ ነው። የምዕራባውያኑ ስልጣኔ በራስ ወዳድነት ተጀምሮ በራስ ወዳድነት የተጠናቀቀ ነው። ዛሬ ላይ ከዓለም ቀዳሚ ነን ብለው የሚመኩበት ስልጣኔና ብልጽግና ልክ እንደ አሁኑ በማያገባቸው እየገቡ ከድሀ ሀገራት ላይ የመዘበሩት የሀይል ውጤት ነው።
ባለፈው ጊዜ የቅኝ ግዛት ዘመን ምዕራባውያኑ በሀይል ከአፍሪካ ብዙ አትርፈዋል። አሁን ላይ የሚያዘባንናቸው የሀይል ሚዛን ትላንት ላይ ከአፍሪካ የሰረቁት እንደሆነ ማን በነገራቸው እላለሁ። ዛሬም ይሄን የሀይል ሚዛን የአፍሪካ ሁሉ ኩራት
ከሆነችው ኢትዮጵያ ነጥቀው ለወንበዴ በመስጠት እርባና ቢስ አፍሪካን መፍጠር ይፈልጋሉ። መነሻቸው ይሄ ነው መድረሻቸው ደግሞ ለምንም የማትሆን፣ ታሪክና መሰረት የሌላትን አፍሪካ መፍጠር ነው። ግን አይሆንላቸውም..ምክንያቱም እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን። ዘመን ዘምኖ በአዲስ የባርነት እሳቤ ዛሬን እንደፈጠረ እናውቃለን፤ አሜሪካም የነጻነት ምድሯን ሀገረ ኢትዮጵያን ደፍራና አስፈራርታ ለሕወሓት አሸባሪ ቡድን እንካችሁ እንዳሻችሁ አድርጓት ብላ ልትሰጥ እንዳማራት ይሄንንም እናውቃለን፤ ግን እንዳማራት ይቀራል።
አሜሪካውያን በኢኮኖሚ ይበልጡን እንደሆነ እንጂ በነጻነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ግን ጥጋችን እንደማይደርሱ ስንናገር በኩራት ነው። አድዋ ላይ የተጻፈው የአንድነት ድል በሀብትና በብልጽግና ሳይሆን በሀገር ፍቅር የሆነ ነው።
በስልጣኔዋ አንቱታን ያገኘችው ጣሊያን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥታ እንደተባረረች ዓለም ያውቀዋል። ይሄ የሆነው ለሀገር ፍቅር በተከፈለ ዋጋ ነው። አሁንም እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው። አሁን እየሮጥን ያለነው አሜሪካንና ምዕራባውያንን አሸንፈን ዳግማዊ አድዋን ለመጻፍ ነው። እንደ እኛ ነጻነት የገባው ሀገርና ህዝብ በዓለም የለም። ልክ እንደትላንቱ ዛሬም ነጻነታችንን አስጠብቀን ለመኖር የሚያዳግተን አንድም ነገር የለም። ምክንያቱም ልክ እንደ ትላንቱ ለሀገሩ የቆመ ትውልድ አለንና ነው።
የአሜሪካ ጭራ ሆነው ከክፋት ወይኗ ለመጎንጨት ቀን የሚቆጥሩ ምዕራባውያን የመኖራቸውን ያህል እውነትን ሽተው የአሜሪካንን የክፋት ሀያልነት በመንቀፍ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ የፍትህ ልቦችም አልጠፉም። እኚህን የቁርጥ ቀን ልጆች ኢትዮጵያ ሁሌም ታስታውሳቸዋለች።
በምጧ ቀን፣ በጭንቀቷ ወራት አጠገቧ ሆነው ደስታዋን ሊያዋልዷት ማርያም..ማርያም ለሚሏት የአብራኳ ክፋዮች ውለታ አላት። እስከዚያው ግን ከጠላቶቿ አንዱን ሳንሆን ቀን ሊያወጧት ከሚታገሉ የቁርጥ ቀን ልጆቿ እንደ አንዱ
እንጠራ። ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንት የጠላቶቻችንን አፍ ለማዘጋት ስለኢትዮጵያ በእጅጉ ጮኸናል። ገና እንጮሀለን፤ በርባንን ፈተው ሊለቁ በሚዶልቱት ላይ፣ እንደ ይሁዳ መልካሙን ሰው አሳልፈው ለመስጠት በሚቆምሩት ላይ እንጮሀለን።
የበግ ለምድ ለብሰው አጠገባችን በቆሙት ተኩላዎች ላይ፣ በውጪም በውስጥም ጠላት በሆኑን ሁሉ ላይ እንጮሀለን። ጩሆታችን ፍሬ አፍርቶ እንደ እያሪኮ የጥላቻን ግንብ እስኪያፈርስ እንጮሀለን። ዓለም ስለኢትዮጵያ እንድትሰማ፣ ፍትህና እውነት ዋጋ እንዲያገኙ እንጮሀለን። በያለንበት የመሰሪዎቹን ሴራ ለማክሸፍ ስለ ሀገራችን እንናገራለን። አዎን እኔም መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ነው ብያችኋለሁ፤ በተቃውሞ ዘመቻው ላይ የኢትዮጵያን እውነትና የሀያላኖቹን ያልተገባ አካሄድ በማጋለጥ ወገንተኝነታቸውን ያሳዩን የውጪ ሀገራት ዜጎች ነበሩ።
በርካታ የውጪ ዜጎች ስለኢትዮጵያ ድምጽ ሆነው ሀያላኖቹን ሲቃወሙ ነበር። የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ ዌንቢንና ረዳት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሁዋን ቹኒንግ እንዲሁም ሴኔጋላዊው ዓለም አቀፍ ሙዚቀኛ ኤኮን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ ሀያላኖቹ እየፈጸሙ ያሉትን ደባ ከተቃወሙት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ገና ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን በመቃወም ዓለም በአንድ ድምጽ ከኢትዮጵያ ጎን የምትቆምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ባይ ነኝ።
ሰሞኑን የምንሰማው ዓለም አቀፍ የንቅናቄ ድምጽ የኢትዮጵያን የፍትህ ጥያቄ እውን የማድረጉን ተግባር የሚያፋጥን ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። አሜሪካና ግብራበሮቿ በዓለም አደባባይ የሚዋረዱበት የኢትዮጵያ ከፍታ ደግሞ የሚታወጅበት ሰሞነ ፍሰሀ ከፊታችን እየመጣ ነው። እኛ ኢትዮጵያን ይዘን ከእውነታችን ጋር ወደ ፊት እንቀጥላለን፤ ያኔ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል። ያኔ ሁሉም ነገር መልስ ያገኛል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014