ሕወሓት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የፈላጭ ቆራጭነት ዘመኑ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ካደረጋቸው ዘርፎች አንዱ ትምህርት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች የህልውና አደጋ ላይ እንድትወድቅ አስተዋጽኦ ያበረከተው የትምህርት ሥርዓቱና ፖሊሲው ሀገር ወዳድና ምክንያታዊ ትውልድን ማፍራት ባለመቻሉ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ።
በትውልድ መካከል መራራቅ እንዲፈጠር የሚያደርግ የትምህርት ይዘትና ትርክት ያለበት፤ ከአካዳሚክ ጉዳይነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ ላይ ያተኮረ፤ ተማሪዎችን አንጥሮ የማውጣት ክፍተት የነበረበት፤ ከጥራት ይልቅ ተደራሽነት ላይ ያተኮረ የትምህርት ሥርዓት እንደነበርም ይገልጻሉ። ትምህርት ቤቶች የእውቀት መገበያያ ቦታዎች መሆናቸው ቀርቶ የፖለቲካ ፍላጎት ማስተናገጃ እየሆኑ በተማሪዎች መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩ ሂደት ሲስተጓጎል፤ አንዳንዴም ግጭቶቹ እየተባባሱ የጨቅላ ተማሪዎችን ህይወት ሲቀጥፉ ተመልክተናል። የዚህ ሁሉ መንስዔዎች ታዲያ ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር በማጋጨት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ሲል የሚነዛቸው የሀሰት ትርክቶች መሆናቸው ግልጽ ነው። ትውልዱ ከኢትዮጵያዊነቱ ይልቅ ለብሄር ማንነቱ ትኩረት እንዲሰጥ ተደርጎ የተቀረጸ በመሆኑ በተነገረው የተዛባ ትርክት ላይ እየተንጠለጠለ ሁሉም በየፊናው ራሱን የብሄሩ ተቆርቋሪ፤ የብሄሩ ተሟጋች አድርጎ ዋናውን የኢትዮጵያዊነት ምስል እንዳያይ ሆኗል።
ባስ ያለበትም ነጻ አውጪ ነኝ እያለ ንጹኋንን እየገደለ፣ ንብረት እያወደመ ኢትዮጵያን የማተራመስ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በተማሪዎች ላይ በተሠራው ብሄር ተኮር አስተምህሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት እርከን ላይ ናቸው፤ ክፉና ደጉን ያውቃሉ፤ ያመዛዝናሉ የተባሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ የሕወሓት የጥፋት ወጥመድ ሰለባ ሆነው የትምህርትን ዋጋ ያሳጡ ተግባራትም ሲፈጸሙ ታዝበናል።
ራሳቸው የሚማሩበትን ትምህርት ቤት የሚያወድሙ፤ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸውን ተቋማት የሚያወድሙ ተማሪዎችን ያየንበት መጥፎ የታሪክ አጋጣሚ አልፏል። ዛሬ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ የትምህርት ሥርዓቱ ያሉበትን ክፍተቶች አርሞ በእውቀትና በሥነምግባር የታነጸ ትውልድን ለማፍራት እንቅስቃሴዎችን መጀመሩ አይዘነጋም። ይሁንና ያለፈው ሥርዓት ቅሪት አሁንም ዘርፉን እየተፈታተነ ወደፊት አላራምድ ብሎታል።
በተለይም በሰሜን የሀገሪቱ ክፍሎች የመማር ማስተማር ሂደቶች መስተጓጎላቸው ሳያንስ በርካታ ትምህርት ቤቶች በፍጥነት እንዳያገግሙ ተደርገው በአሸባሪ ቡድኑ ጉዳት ተፈጽሞባቸዋል።
ይህም ትምህርት ሚኒስቴር ዘርፉን ከወደቀበት ለማንሳት እያደረገ ያለውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትት እንደሚሆን ይገመታል። የትምህርት ሚኒስቴር ከሰሞኑ ‹‹ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ›› በሚል የተጀመረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በተለያዩ መንገዶች በመደገፍ ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ በፍጥነት በማውጣት የተጎዳውን የትምርት ዘርፍ የማከም እቅድ እንዳለው ገልጿል። በእለቱ በነበረው መርሃ ግብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማትና ከሰራተኞች ያሰባሰበውን ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሰራዊትና ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ ለግሷል። ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች ደም የመለገስና ሌሎች ድጋፎችንም አድርገዋል።
ቁጥራቸው 34 የሚሆን የመስሪያ ቤት ሠራተኞችም መከላከያ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ወደ ግንባር ተሸኝተዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጉዳዩን አስመልክተው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ጦርነቱ የህልውና ጦርነት እንደሆነና ይቺ ሀገር እንደሀገር የመቀጠልና አለመቀጠሏ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ወቅት ላይ አንደምንገኝ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ከውስጧ የወጣ እኩይ ጠላት ገጥሟት አያውቅም ያሉት
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ይህ አሁን የተፈጸመው ክህደት ለሰላሳ ዓመት እርስ በእርስ እንደጠላት የተያየንበት ጊዜ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አብቅቶ አዲስ ዘመን ለማስፈን ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል። የዚህ ጦርነት በፍጥነት መጠናቀቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ ዋናው ጉዳዩ ገብቶ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጦችን ለማምጣት እንደሚስችለውም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።
ዛሬ የገባንበት ጦርነት የአርባ አምስት ዓመት የትምህርት ውድቀት ውጤት መሆኑን በዘርፉ የተሠማሩ ሙያተኞችን ያስማማ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት በወደቀ የትምህርት ፖሊሲ የተማሩና በወጥመዱ የተያዙ ወጣቶች ሀገርን አደጋ ላይ እንድትወድቅ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በወጥመዱ ያልተያዙት ግን ከገባችበት መቀመቅ ሊያወጧት የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል። እየተደረገ ካለው የህልውና ጦርነት በተጨማሪ የወደቀውንና የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ለማስተካከል ከፊት ለፊት ሌላ ጦርነት መኖሩንም ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትምህርትን ከዚህ ቀደም ከነበረበት አዘቅት አውጥቶ ጠንካራና ጥራት ያለው ትምህርት በሁሉም ቦታ ተደራሽ የማድረግ ሃላፊነት አለበት ብለዋል። የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ለጦርነቱ ከሰጡት ደም በተጨማሪ ሌላ ደም በመስጠት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የትምህርት ተቋማት ትክክለኛ የተማረ ሃይል የሚፈራባቸው ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንዲህ አይነት ጦርነት ውስጥ የከተተን ድንቁርና እና ድህነት መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከእንዲህ አይነት ችግሮች በዘላቂነት ለመላቀቅ በአግባቡ የተማረ ዜጋን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህ ጦርነት በኋላ ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ሌላው ከፊታችን የሚጠብቀን ጦርነት እንደሆነም ገልጸዋል። ይህንን እቅድ በፍጥነት ለመተግበር ጦርነቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ ስለሚያስፈልግ ትምህርት ሚኒስቴር ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በህልውና ጦርነቱ ላይ ለሚሳተፉት ወገኖች አለንላችሁ ከጎናችሁ ነን የሚለው ማበረታታት በገንዘብ ድጋፍና ደምበመለገስ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ግንባር ሄዶ እስከመፋለም የደረሰ መሆኑም በተግባር የታየ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የዘማች ቤተሰቦችን ማገዝም ሌላው የህልውና ዘመቻውን ግብ መምታት የሚያፋጥኑ ተግባራት አንደሆኑ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበው አደጋ ተወግዶ ሀገሪቱ ወደ ሰላሟና ወደ ቀደመ ክብሯ እስክትመለስ ድረስ ድጋፉ የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ አሁን ወዳለችበት ችግር እንድትገባ ያደረጋት የትምህርት እጥረት እንደሆነና ከችግር የሚያስወጣት ብቸኛው መፍትሄም ትምህርት በመሆኑ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በትምህት ዘርፍ ዘመቻ እንደሚደረግ ተናግረዋል። እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰን ሀገርን መጥላት፣ ህዝብን መጥላት፣ ራስን መውደድ ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ይህ በተሳሳተ መንገድ የተገነባው ስብዕና በትምህርት መስተካካል እንዳለበት ገልጸዋል። አስተሳሰብን መለወጥ የሚቻለው በትምህርት በመሆኑ በቀጣይ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር፤ ትልቅ ሀገር እንድትሆን፤ ህዝቦቿ ተከባብረውና ተፈቃቅረው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን በትምህርት ሥራ ላይ የምናደርገው ርብርብ ከዚህ ጦርነት ያልተናነሰ ትግል የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ቀበቶውን ማጥበቅ እንደሚገባው ጥሪ አስተላልፈዋል። ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች አንዱ ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3፣ 2014 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የዘማች ቤተሰቦች ሰብል እንዲሰበሰቡ የሚል ነው። የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫው እንደተናገሩት ሀገርን በጋራ ማቆም የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት እንደሆነና የትምህርት ዘርፉም ማህበረሰቡን የማገዝ ሃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል። መምህራንና ተማሪዎች ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ ያሉ አርሷደሮችን ሰብል በመሰብሰብ ህግ በማስከበሩ ሂደት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ያልተሰበሰቡ የዘማች ሰብሎችን መሰብሰብና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል። እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ እያንዳንዱ የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ገንዘብ በመሰብሰብ፣ ደም በመለገስ፣ ስንቅ በማዘጋጀትና በሌሎችም ድጋፎች ሁሉ እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል። የደረሱ ሰብሎች በወቅቱ እንዲሰበሰቡ ማድረግ የሀገር ኢኮኖሚን ከመደጎም አንጻር ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ሀገሪቱን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የምርትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዳይዳከም ያግዛል፤ ይህን በማድረግ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተማሪ ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰበሰብ ታክስ የሚማር እንደመሆኑ ተማሪዎች ይህን ለሚያደርግላቸው ማህበረሰብ እንዲህ አይነት ድጋፍ ማድረግ ጦርነቱን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ውስጥ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እድል የሚሰጣቸው ነው። ከዚህ በኋላ የትምህርት ሥርዓቱ ለሁሉም ዜጋ እኩል ሀገራዊ ስሜት ያለው ሆኖ እንደሚቀጥል የገለጹት ሚኒስትሩ እንዲህ አይነቱ ሀገራዊ ተሳትፎም ይመጣል ተብሎ የታሰበውን ሀገራዊ ስሜት ያሳድገዋል ብለዋል። ለሳምንት ያህል የሚቋረጠው የትምህርት ጊዜም በልዩ ፕሮግራም የሚካካስ መሆኑን ገልጸዋል።
በመግለጫው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ እና የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው መምህራንና ተማሪዎች እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ የሀገሪቱን ወቅታዊ ችግር ከግምት ያስገባ ድጋፍ በማድረግ በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል። ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ አንድ አራተኛው በትምህርት ዘርፍ ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶክተር ቶላ በሪሶ ይህ ሃይል ከተባበረ ሀገሪቱን ከገባችበት ችግር ለማውጣት ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በየትምህርት ቤቱ ብሄራዊ ጀግንነትናን ክብርን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራት መኖራቸውን በመጥቀስ የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰቦች በተዘጋጁት ፕሮግራሞች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አምስት የአማራ ክልል ዞኖች ብቻ ከአንድ ሺ ስድስት መቶ በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያየ መጠን ያላቸው ጉዳቶች መድረሳቸውን ገልጸዋል። ከነዚህ ውስጥ ሶስት መቶ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን አስታውቀዋል።
ጉዳቶቹን ያስተናገዱ ዞኖች የዋግ ልዩ ዞን፣ የሰሜን ወሎ ዞን፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ ዞን እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ከትግራይ ክልል ውጭ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች በላይ ትምህርታቸው ተስተጓጉሏል። ወደ አርባ ሺ የሚደርሱ መምህራን ከትምህርት ሥራ ውጭ መሆናቸውም ተገልጿል። መረጃው ከሳምንት ወዲህ የተከሰቱ ጥፋቶች የሚያካትት ከሆነ ደግሞ የጉዳቱ ደረጃ ከዚህም በላይ ሊያድግ እንደሚችል ገልጸዋል። በአስራ አምስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይም በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የትግራይ ክልልን ጨምሮ ከሰባት ዩኒቨርሲቲዎች አስራ አምስት ካምፓስ በሙሉ ወይም በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በእነዚህ ጉዳት በደረሰባቸው ካምፓሶች የሚማሩ ተማሪዎችን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማዛወሩ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014