አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም መዲና ናት። ይህም የሆነው አንድም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫውን አዲስ አበባ በማድረጉ ብሎም ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን የነጻነት ጉዞ ውስጥ ከነበራት ታሪክ አንጻር ነው። አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ሌላ አፍሪካዊ የሚያደርጋትን ነገር እየለመደች ነው፤ የአፍሪካ አልባሳት።
የፋሽን ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የአፍሪካ አልባሳት ገበያ በአዲስ አበባ እየደራ ነው። ባለደማቅ ቀለም የአፍሪካ አልባሳትን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል።
የዛሬ የፋሽን ጉዳያችንም ይሄው ነው። ወደ እዚህ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ግን እስኪ በጥቂቱ ስለ አፍሪካ አልባሳት እናውጋ። የአፍሪካ አልባሳት እንደ ሌላው አለም በጥጥ እና መሰል ግብአቶች የሚሰሩ ቢሆኑም፣ ከአውሮፓውያኑ የተለየ ግብአት አላቸው።
የተመድ ገጸ ድር በፈረንጆቹ መስከረም 2020 African history told through fashionable printed clothing በሚል ርእስ ባወጣው ጽሁፍ የአፍሪካ አልባሳትን ባህሪ ሲተነትን፤ ”የአፍሪካ አልባሳት በደማቅ ቀለሞች የተዋቡ፤ የተጠጋጋ ቅጥ (ፓተርን) እና ሊካድ የማይቻል ውበት ያላቸው ናቸው” ብሏል።
የእነዚህ ደማቅ ቀለሞች የታተሙባቸው አልባሳት ጥቅም ላይ የመዋል ታሪክ ሶሰት መቶ ዓመታት ወደኋላ ይሄዳል። በአሁኑ ወቅት ቪስኮ እየተባለ የሚጠራ የሆላንዶች ፋብሪካ ነበር በወቅቱ ይህን ልብስ ለአፍሪካውያን ያስተዋወቀው። ከዚያ በኋላም ልብሱ አፍሪካዊ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን የዚህ ልብስ ዝና ሰፍቶ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ እና ጥቁር አሜሪካውያን በስፋት እየለበሱት ነው። ከነዚህ መካከል ታዋቂው ደግሞ አንጀሊና የሚባለው ልብስ ነው።
የተመድ ገጽ እንዳመለከተው፤ የዚህ ልብስ መነሻ ሀሳብ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት ናቸው። ሆኖም አሁን በመላው አፍሪካ ተወዳጁ ልብስ በቅቷል። በቀለም ያጌጠው ይህ ልብስ በአንገት የሚጠለቅ እና ሲያስፈልግ ቲሸርት ከተፈለገም ቀሚስ መሆን ይችላል።
ስያሜው የመጣው ልብሱ መለበስ በተጀመረበት ወቅት ዝነኛ ከነበረ የጋና የሙዚቃ ባንድ ነው። በኮፊ አናን፤ በሚሼል ኦባማ እና ሌሎችም ስም የተሰየሙ ዝነኛ አልባሳትም አሉ። እነዚህ አልባሳት በየሀገሩ የየራሳቸው መጠሪያም አላቸው። ለምሳሌ ያህል አንጀሊና በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊኮች ዘንድ ያ ማዶ በመባል ይጠራል። የሆነ ሆኖ ተመሳሳይ ልብስ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ይለበሳል።
በዚህም የተነሳ ተቺዎች ልብሱን ለአፍሪካ ያስተዋወቀው ድርጅት አፍሪካዊ አይደለም ቢሉም እንኳ አፍሪካውያን ዲዛይነሮች ግን ልብሱ የኛ ነው ይላሉ። አልባሳቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዝና ቢያተርፉም እንኳ በአፍሪካውያን የእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ እና በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ከ200 ዓመታት በላይ እንደቆዩ እና በዚህም የተነሳ የአፍሪካ አልባሳት መባል እንደሚችሉ ይሞግታሉ።
የሆነ ሆኖ ይህ ልብስ ነው እንግዲህ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ ገበያ ውስጥም መታየት የጀመረው። ተፈላጊነቱም እየጨመረ ስለመሆኑ ዲዛይነሮች እና ነጋዴዎች ይናገራሉ። የልብሱ ፍላጎት ጨምሯል ከሚሉት መካከል አንዷ ደግሞ ዲዛይነር ፌቨን አሸብር ናት። ”የአፍሪካ አልባሳት በብዛት እየተለመዱ እንደመጡ አያለሁ” ትላለች ፌቨን:: ምክንያቱንም ስታስረዳ “የአፍሪካ ጨርቅ ትንሽ እኛ ከምናውቃቸው ጨርቆች ለየት ያለ ሲሆን፣ ኦርጅናል የተባለው ጨርቅ 100 በመቶ ጥጥ ይሆንና በጣም ጠንካራ ነው። እንዲሁም በቀላሉ ሰው አይን ውስጥ የሚገባም ነው። በተለያየ አይነት ደማማቅ ቀለሞችና ፓተርኖች ይገኛል” ትላለች።
ከውበት ባለፈም ግን የዋጋ ጉዳይ ልብሱን ተመራጭ እንዳደረገው ነው ዲዛይነሯ የምትናገረው። ”በአብዛኛው አንዱ የአፍሪካ ጨርቅ 5 ተኩል ሜትር ሲሆን፣ ገበያ ላይ ከ800 እስከ 1500 ብር ድረስ ይገኛል። አንድ ጊዜ የሚገዛው 5 ተኩል ሜትሩ ጨርቅ ለቤተሰብ ማለትም ለባልና ሚስት እንዲሁም ለሁለት ልጆች በቂ ስለሆነ ብዙዎች የቤተሰብ ፎቶ ሲፈልጉ ይመርጡታል፤ ከዚህም በተጨማሪ ለልደት ለበአላት፣ ለሙሽሮች የመስክ ፎቶ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።
”በማለት ታስረዳለች። ከዲዛይነሮች አንጻር ያለውን እየታ ስታስረዳም “ይሄንን የአፍሪካ ጨርቅ ከተለያዩ የጨርቅ አይነቶች ጋር እየቀላቀሉ መስራት ስለሚቻል ብዙ ዲዛይነሮች ይመርጡታል፤ የሀገራችንን ጨርቅም ከአፍሪካ ጨርቅ ጋር ተቀላቅሎ ሲሰራ የተለየ ውበት አለው›› ነው የምትለው። ከውበቱም በተጨማሪ የሀገራችንን ጨርቅ ለሌሎች ሀገሮች ለማስተዋወቅ በእጅጉ አንደሚረዳም ትጠቁማለች።
የአፍሪካ ጨርቅም በማንኛውም ቦታ እንዲለበስ ተደርጎ መሰራት እንደሚቻልም ትገልጸለች። ለቢሮ፣ በኮት፣ በሸሚዝ፣ በጉርድ ወይም በቀሚስ፣ በቲሸርት መልክ በተፈለገው አይነት በተፈለገው ዲዛይን ከሌላ ጨርቅ ጋር ተቀላቅሎም ሳይቀላቀልም በጥሩ ሁኔታ ተሰርቶ ሊለበስ እንደሚችልም ታብራራለች። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የታይምለስ ክሎዚንግ እና አክሰሰሪ ባለቤት ዲዛይነር ካሌብ ነው።
ዲዛይነር ካሌብ እንደሚለው፤ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አልባሳት ገበያ እየጦፈ ነው። ”እኔ ከምሸጣቸው አልባሳት አብዛኞቹ የአፍሪካ አልባሳት እየሆኑ ናቸው። በተለይ ሰዎች የሰርግ ፎቶ ለመነሳትና መሰል ፕሮግራሞች አሁን ላይ በጣም ጥቅም ላይ እየዋለ ነው “ይላል። እሱ አንደሚለው፤ ለመወደዱ ምክንያት ውበቱ እና ዋጋው ነው። በአፍሪካ ጨርቅ የምትሰራው ልብስ ላይ የምታወጣው ዋጋ ከሌሎች ልብሶች አንጻር ሲተያይ በጣም ሰፊ ልዩነት አለው። በተለይ ከኛ የባህል አልባሳት አንጻር በጣም ዋጋው ርካሽ ነው። አንድ ሀበሻ ቀሚስ ለመግዛት የምታወጣው ወጪ በአፍሪካ ጨርቅ አንድ ሙሉ ቤተሰብን ያለብሳል።
የአፍሪካ ልብስ ለመስራት የሚያገለግለው ጨርቅ የሚመጣው ከጎረቤት ሀገራት በተለይም ከኬንያ ነው። ሀገር ውስጥ ካሉ አምራቾች አይገኝም። ይህ ሁኔታን በበጎ ጎኑ ስናየው ለቀጠናዊ የንግድ ትብብር በር የሚከፍት ቢሆንም፣ በሌላ መልኩ እንዲህ አይነት ቀላል ምርቶችን በራሳችን ፋብሪካዎች በብዛት ማምረት አለመቻላችን አሳሳቢ ነው ሲል ያብራራል።
በጥቅሉ ሲታይ ግን አዲስ አበባ በተለይ የአፍሪካ አልባሳትን እየተለማመደች ነው። ባለ ደማቅ ቀለሞቹ የአፍሪካ አልባሳት ከሌሎች አልባሳት ጋር እየተዋሀዱ አዳዲስ ፋሽን እየፈጠሩ ነው። ይህ ሁኔታ ይበል ያሰኛል። የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እና የአፍሪካ ኩራት የሆነችው ኢትዮጵያ በአለባበስም አፍሪካዊያንን መምሰሏ አግባብነት አለው።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ኀዳር 27 / 2014