የዓለማችንን ከ35 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል:: ልጆችን ያላሳዳጊ ፣ አባቶችንና እናቶችን ያለ ጧርና ቀባሪ አስቀርቷል:: የበርካታ ሚሊዮኖችን የማምረት አቅም አዳክሟል፤ ቤተሰብ በትኗል:: የቤተሰብን፣ የአገርን የዓለም ሀብት ተቀራምቷል:: በሽታው ከዓለማችን ገዳይ በሽታዎች ግንባር ቀደም እስከመባልም ደርሷል:: እሱ በዚህች ምድር ላይ ያላሳደረው ችግር የለም:: የዓለም ጤና ድርጅትና አገሮች እያደረጉ ባሉት ርብርብ በጀመረው ፍጥነት መጓዝ ባይችልም ዛሬም የዓለም ጤና ጠንቅ ሆኖ ቀጥሏል:: ኤችአይቪ/ ኤድስ::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የኤችአይቪ እንደ በሽታ ታውቆ የመጀመሪያው ተጠቂ ሪፖርት ከተደረገ ከ35 ዓመት በኋላ በዓለም 78 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ ተጠቂዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚሁ ውስጥ ግማሽ የሚጠጉት ማለትም 35 ሚሊየን ሰዎች ከኤድስ ጋር በተያያዘ ህመሞች ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል::
ሳይንቲስቶች እንደሚያምኑት ይህ የሰውነት መከላከል ብቃትን የሚያመነምን፣ ለተለያዩ በሽታዎች በቀላሉ የሚያጋልጥና ለሞት የሚዳርግ በሽታ፣ ከቺምፓንዚዎች ወደ ሰዎች የተላለፈ ነው ይላሉ:: ከየትም ይምጣ ከየት በምንም ይምጣ በምንም በሽታው ግን የሰው ልጅ የጤና ጠንቅ ነው::
በሽታው የሰዎችን የተፈጥሮ መከላከል አቅም ቀስ በቀስ በማዳከም በበሽታዎች በቀላሉ የሚጠቁበትና የሚሞቱበትን ሁኔታ የሚፈጥር በዋናነት በልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት በቀላሉ የሚተላለፍ ነው:: በዓለም ገዳይ በመባል ከሚታወቁት በሽታዎች መካከልም ሲጠቀስ እንደነበርም ይታወቃል::
የዓለም ጤና ድርጅትም ይህን በሽታ ለመዋጋት ዩኤን ኤድስን አቋቁሞ መሥራት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል:: የዓለም ጤና ድርጅትና ሀገሮች ይህን ትልቅ የጤና ስጋት ለመዋጋት ከፍተኛ ሀብት መድበው ባለሙያ አሰማርተው በበሽታው ላይ ዘምተዋል፤ ይህን ተከትሎም ብዙ ድል አግኝተዋል፤ ገና ብዙ የሚቀራቸውም አለ::
የዓለም ጤና ድርጅት ኤችአይቪ ኤድስ ላይ የያዘውን ትኩረት በማጠናከርም በበሽታው ላይ ግንዛቤ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ የዓለም ኤድስ ቀን በየዓመቱ ህዳር 22 ቀን እንዲከበር አድርጓል:: በዚህም ቀደም ሲል በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይከናወኑ የነበሩ ተግባሮችን አጠናክሮ ለመቀጠል ፣ አዳዲስ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ሲሠራ ቆይቷል::
ዘንድሮም ይህ ቀን በዚህ ሳምንት ህዳር 22 ቀን ‹‹ልዩነቶች ሲወገዱ ኤድስም ይወገዳል›› በሚል መሪ ሃሳብ በመላ ዓለም ተከብሯል:: የዛሬው የሳምንቱ በታሪኩ ዓምዳችን ርዕሰ ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይሆናል::
የዓለም ኤድስ ቀን መከበር የጀመረው በ1981 ዓ.ም ኅዳር 22 በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር ዲሴምበር 1 ቀን 1988 ነበር:: ቀኑ ላለፉት 32 ዓመታት ተከብሯል:: በየዓመቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች መንግሥታት እና የሲቪል ማኅበረሰብ አካላት በአንድ ላይ ተባብረው ከኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ መሪ ቃል በማውጣት ቀኑን እየዘከሩ ግንዛቤ ለመስጠት ይረባረባሉ::
ሀገሮችም የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ቀኑን ያከብሩትል:: በዚህም በሽታውን በመከላከል፣ የህክምና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን ተደራሽ በማድረግ፣ ወዘተ ግንዛቤ የመስጠት ሥራዎች ይካሄዳሉ:: ሰዎች እንደ «ጸ» የምትመስል ቀይ ሪቫን ኮታቸው፣ ሸሚዛቸውና ቀሚሳቸው ላይ ያደርጋሉ:: ሪባኑ ለኤችአይቪ እንደ ዓለም አቀፍ ምልክት በመሆን የሚያገለግል፣ ግንዛቤ ለመስጠትም የሚረዳ፣ ከኤች አይቪ ጋር ለሚኖሩት ኅብረተሰቡ ያለውን ድጋፍና ትብብር ለማሳየት የሚጠቀምበት ነው::
የአሜሪካን ሳይኮሎጂ አሶሴሽን የተሰኘ ድረገጽ መረጃ እንደሚያብራራው:: ቀኑ መከበር የጀመረበት ወቅት ኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በጣም የከፋበትና ቀውስ የተፈጠረበት ነበር:: ዘመቻው የተጀመረው የዓለም ጤና ድርጅት ከያዛቸው ዓለም አቀፍ ዘመቻዎች ዘጠነኛው ተደረጎም ነው:: በፈረንጆቹ ታህሳስ አንድ ቀን ከመላ ዓለም የተሳሰቡ ሰዎች በሚገኙበት ቀኑ ይከበራል:: በዚህ ቀን ኤችአይቪን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የተቀመጡ አቅጣጫዎችና የተያዙ እቅዶች ያመጡት ለውጥ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ይገመገማሉ:: በዚያውም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተያዘው ጥረትን አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል ይገባል::
በየዓመቱ ኅዳር 22 ቀን ዓለም የዓለም ኤች አይ ቪ ቀን በሚል ሀገሮች በዓውድ ጥናት በስብሰባ፣ በሰልፍ በመሳሰሉ ቀኑን ያከብሩታል ፤ ለህዝቡ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በመገናኛ ብዙሃን ፣ ወዘተ እንዳይዘናጋ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሠራል::
የቀኑ መከበር ህዝቡና መንግሥታት ከኤች አይ ቪ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ፣ የህክምና አገልግሎት የሚያስፋልጋቸው ተደራሽ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ፣በበሽታው ያልተጠቁ ሰዎች እና በበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ እና እንዲጠነቀቁ ግንዛቤ ለመስጠትም ጭምር ይጠቅማል:: ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ሰዎች በሕይወታቸው ጉዳዮች ዙሪያ ድምፃቸው እንዲሰማ ይረዳል ፤ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ቡድኖች እና ሌሎች በኤድስ ላይ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምላሹም ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ እንዲያገለግሉና ገንዘብን ጨምሮ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ሚና ይኖረዋል::
የተባበሩት መንግሥታት የኤድስ መርጃ ድርጅት (UNAIDS) በፈረንጆቹ 1996 ለመመስረቱም የበሽታው አሳሳቢ እየሆነ መምጣት ምክንያት ነበር:: ድርጅቱ ዓለም አቀፋዊ ክፍለ አህጉራዊና ብሔራዊ እንዲሁም ቀጣናዊ በሆኑ ኤድስ ጉዳዮች ላይ አመራር በመስጠት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚረዱ ፈጠራዎችን በማበረታታትና እስከ መጨረሻው ኤችአይቪ ታሪክ ሆኖ እንዲቀር እንደሚሠራ ሰነዶች ያሳያሉ::
እአአ በ2019 የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በየዓመቱ ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር በተያያዘ አንድ ሚሊየን ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ:: ኤድስ በአንዳንድ ሀገሮች የሰው ልጅን ሕይወት ከሚቀጥፉ በሽታዎች በመሪነት ስፍራ ላይ ይገኛል:: በተለይ ከሰሐራ በታች የሚገኙ ሀገሮች ዋና የጤና ችግር በመሆን ይታወቃል:: በእነዚህ ሀገሮች በሽታው በጤና በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር እንዲሁም በህይወት የመቆያ ጊዜን በማሳጠር የሚታወቅ ነው::
እንደ ግሎባል በርደን ኦፍ ዲዚዝ ስተዲ ጥናት አአአ በ2017 ብቻ 954 ሺ ሰዎች በእዚህ በሽታ ህይወታቸውን አጥተዋል:: ይህም ወባ ከሚያስከትለው የሞት መጠን 50 በመቶ ብልጫ ያለው የሞት መጠን ሆኖ ተገኝቶም ነበር::
አሁንም በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ አያሌ ሰዎችን በመግደል ከሚታወቁት በሽታዎች አንዱ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ ከሰሐራ በታች በሆኑት አገራት ደግሞ ዋና ገዳይ በሽታ በመባል ይታወቃል:: የግሎባል በርደን መረጃ አያይዞ እንዳመለከተው፤ ኤድስ የሚያስከትለው ሞት የልብ በሽታ ከሚያስከትለው የሞት መጠን 50 በመቶ ብልጫ ያለው የሞት መጠን የሚያስከትል ሲሆን፣ ካንሰር ከሚያስከትለው የሞት መጠን ደግሞ ከሁለት አጥፍ በላይ የሞት መጠን የሚያስከትል ተብሎም ነበር::
በሽታው በአገራችን መገኘቱ ይፋ የተደረገው 1984 ዓ.ም ነው:: ችግሩ አሳሳቢ ሆኖ በመገኘቱ በሀገራችን በዓመቱ ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ አተኩሮ የሚሠራና ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ኃይል ተመሠረተ:: ሆኖም ግን በነበረው የፀጥታ ችግር የፖለቲካ ግርግርና በሥልጣን ሽግግር ምክንያት ( በወቅቱ ደርግ ወድቆ የወያኔ የሽግግር መንግሥት እየተመሠረተ ነበር ) በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት አልተቻለም ነበር:: ይህም በሽታው እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታን ፈጠረለት::
ኤች አይቪ ኤድስ የአባለዘር በሽታ እንደመሆኑ ብዙዎች እንዲጠቁ ምክንያት ነው፤ በተለይ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ራቅ ያለሥፍራ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች ተጋላጮች መሆናቸውን የጥናት ሰነዶች ያሳያሉ:: በመጠጥና በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የሆኑትም ሴሰኛ የሚሆኑበት ዕድል ሠፊ ነው:: ይህም ለኤች አይቪ በሽታ እንዲጋለጡና ተጠቂ እንዲሆኑ ያደርጋል:: በአጠቃላይ ልቅ የወሲብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ለበሽታው የመጋለጥ ዕድላቸው ሠፊ ነው::
በሽታው ይፋ ከተደረገ ከሁለት ዓመት በኋላ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር የኤድስ ቁጥጥር መምሪያ ሲመሠረት ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሔራዊ ፕሮግራሙን ቀረጸ:: በእነዚህ እንቅስቃሴዎቹ በሀገሪቱ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድና በሽታው ተሰራጭቶባቸዋል በተባሉባቸው አካባቢዎች ካርታ በማውጣት በቅኝት ይከታተል ነበር::
ከመጀመሪያዎቹ መረጃዎች የኤችአይቪ ኤድስ የተጠቁና የሟቾች ቁጥር የሚያስደነግጡ ሆኑ:: የህዝቡ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ለደረሰበት ጉዳትም ልዩ ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልጉትን ሁኔታዎች እና በሽታው እያስከተለ ያለው ተጨባጭ ተፅዕኖም ከአቅም በላይ እየሆነ መጣ::
በኢትዮጵያ የኤድስ ጉዳዮች የግድ ሪፖርት መደረግ የጀመሩት በ1979 ዓ.ም ሲሆን፤ በወቅቱ ሁለት ሰዎች ተጠቂዎች እንደነበሩ ሰነዶች ያሳያሉ፤ ይህ አኀዝ 1994 ዓ.ም 107 ሺህ 575 ተጠቂዎች ሪፖርት መደረጉን በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያሳያል:: በ2002 ከሀገሪቱ ሕዝብ 6 ነጥብ 6 በላይ የሚሆነው ጎልማሳ የኤች አይቪ ፖዘቲቭ ተብሎ ይታሰብ ነበር:: በወቅቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሕዝብ የቫይረሱ ተጠቂ ይሆናል ተብሎ ተገምቶም ነበር::
በኢትዮጵያ ስርጭቱን ለመግታት ጥረቶች ቢደረጉም፣ ያለው ድህነት፣ የመደበኛ ትምህርት እጥረት እና ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ጉዳቶች መኖራቸው፣ ኤች አይቪ ኤድስ ዕረፍት አልባ ሆኖ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነዋል:: መንግሥት በ1988 በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ብሔራዊ ፖሊሲ አረቀቀ:: በመጋቢት 2000 ብሔራዊ የኤችኤይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪ ጽህፈት ቤት ተቋቋመ:: ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ተከትለው የክልል ጤና ቢሮዎችም ባለ ብዙ ዘርፍ የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ አውጥተው ነበር::
በ1988 በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ብሔራዊ ፖሊሲ ተረቀቀ:: በመጋቢት 2000 ብሔራዊ የኤችኤይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪ ጽህፈት ቤት ተቋቋመ:: ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ተከትለው የክልል ጤና ቢሮዎችም ባለ ብዙ ዘርፍ የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ አውጥተው ነበር::
ስርጭቱን ለመግታት የተደረጉ ጥረቶችን ተከትሎ ለውጦችም ቢታዩም፣ ለውጦቹን ተከትሎ በተፈጠረ መዘናጋት ደግሞ በሽታው ያንሰራራባቸው ወቅቶችም ነበሩ:: በአጠቃላይ በሚፈለገው ልክ ለውጥ ላለማምጣት ድህነት፣ የመደበኛ ትምህርት እጥረት መዘናጋት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ::
በፈረንረጆቹ 2016 በኢትዮጵያ ከሕዝቡ 67% በመቶ የራሱን ሁኔታ ማወቅ ችሎ ነበር:: በዚሁ ዓመት ከአጠቃላይ ሕዝቡ 710 ሺህ የሚሆነው ከኤች አይቪ ጋር የሚኖር ነበር:: ከእነዚህ ውስጥ 650 ሺህ የሚሆኑት በጎልማሳ ዕድሜ ያሉ ናቸው:: ቀሪው 62 ሺህ ደግሞ ሕፃናቶች ነበሩ:: ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ግን በየዓመቱ በኢትዮጵያ በኤች አይቪ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር 35 በመቶ እየቀነሱ የመጡ ሲሆን፣ በሁሉም ዕድሜ የተጠቂዎች ከፍተኛ ጣሪያው ግን 1 ነጥብ 1 ሚሊየን እንደነበር ሰነዶች ያሳያሉ:: በኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 1995 ጀምሮ አዲስ ተጠቂዎች በሀገራችን በ81 በመቶ እየቀነሰ መሆኑና ከ2002 ጀምሮ ደግሞ ተጠቂዎች 35 መውረዱን የተመድ ኤድስ መረጃዎች ያስረዳል::
ከ2008 ወዲህ ግን የኤችአይቪ መጠነ ክስተቱ በ10 በመቶ መጨመር ጀመረ:: እናም የተጠቂዎች ቁጥር በሁሉም የዕድሜ ክልል እና በጎልማሶች ደግሞ በእጥፍ ጨምሮ በየዓመቱ አዲስ ኤችአይቪ ተጠቂዎች 36 በመቶ እየጨመረ ነው::
የፀረ ኤች አይቪ ህክምና ሽፋን በሁሉም የዕድሜ ክልሎች 90 በመቶ የጨመረ ሲሆን፤ በነፍሰ ጡር ሴቶችንም በ6 ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ ማሳደግ ተችሏል:: በብሔራዊ ደረጃ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሁኔታ የሚያውቁ ሲሆን፤ 86 በመቶው ሕክምናውን ይጠቀማሉ:: በ2020 ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ 79 በመቶ ሰዎች የራሳቸውን ደረጃ እንደሚያውቁ ሰነዶች ያስረዳሉ::
በኢትዮጵያ ኤችአይቪ እየቀነሰ ከመጣ ከተወሰነ ዓመት በኋላ አገርሽቶ እንደገና ሕመሙ በጎልማሶች ላይ መጨመር ጀምሯል:: ኢትዮጵያ ባካሄደችው የኤችአይቪ ሦስት ግቦች የመጀመሪያው ባይሳካም 2ኛው እና 3ኛው 90% የኤችአይቪ ግቦች ስኬታማ መሆን ችለዋል፤ በዚህም የበሽታውን ስርጭት መከላከል ተችሏል:: በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ግብ ባለመሳካቱ ግቡን በድጋሚ ከልሶ በማርቀቅ ቀሪዎች እንደመሳካታቸው አሁንም ትኩረት ተሰጥቶት ወጣቱን የሚቀጥፈውን ቫይረስ ለመቀልበስና ለመግታት መታሰብ አለበት ሲል ሰነዱ ያስረዳል::
በዓለም አቀፍ ደረጃም ኤችአይቪ ኤድስ አሁንም ስጋት መሆኑን ሰሞኑን በተከበረው የዓለም የኤድስ ቀን የወጡ መረጃዎች ያስገነዝባሉ:: መረጃዎቹ አንደሚያመለክቱት፤ ኤች አይቪ ኤድስ አሁንም በዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብን የሚጎዳ የሕዝብ ጤና ጉዳይ ሆኖ መሆኑ ቀጥሏል:: ዓለም በዚህ የጤና ጠንቅ ላይ ታላላቅ ለውጦችን ማሳየት ብትችልም፣ በእአአ 2020 በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንዲቻል ከተቀመጡ ወሳኝ ግቦች ያልተሳኩ እንደተገኙ ተመልክቷል:: ልዩነትና ለሰው ልጅ ክብር አለመስጠት በሽታው አሁን ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሆኖ እንዲቀጥል ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቅሰዋል::
ላለፉት ሁለት ዓመታት ዓለምን ያስጨነቃት ኮቪድ 19 ደግሞ ሌላው ችግሩን ያባባሰ ሆኖ ተገኝቷል:: ኮቪድ ያስከተለው ኢፍትሐዊነት እና ልዩነት የህክምና አገልግሎት እስከ ማቋረጥ የተደረሰበት ሁኔታ እንዲፈጠር አርጓል:: ይህም የጤና ችግሩ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ አያሌ ሰዎችን ህይወት በእጅጉ ፈታኝ አድርጎታል:: ‹‹ልዩነቶች ሲወገዱ ኤድስም ይወገዳል›› የሚለው የዚህ ዓመቱ የዓለም ኤድስ ቀን መርህ ጭብጥም ይህንኑ ችግር መፍታትንና የተረሱ ሰዎችን መድረስን ያለመ ነው:: ለዛሬ አበቃን::
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 26/2014