እአአ 2017 በኬንያ በተካሄደው የፕሬዚዳንት ምርጫ ተጭበርብሯል በመባሉ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምርጫ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገውን ውጤት ባስገራሚ ሁኔታ መሻሩ ይታወሳል፡፡ በኬንያ በተካሄደው ምርጫ ውጤቱ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ እያሰራጩ ባለው የምርጫ ውጤት መሰረት በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋን እየመሩ መሆኑ ተነግሮ ነበር።
ይሁንና ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል ማለታቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፎች አድርገዋል። እንደተፈራውም በኬንያ ምርጫ ማግስት የተለመደው ብጥብጥ ተነሳ፤ በብጥብጡም ብዙ ሰዎች ሞተዋል።
ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ መገደላቸውን ተከትሎም፤ ከተቃዋሚው ኦዲንጋ ደጋፊዎች ሲደመጥ የነበረው ሃሳብ የምርጫ ቦርድ ሃላፊው የተገደሉት ምርጫው እንዳይጭበረበር በያዙት አቋም ነው። በወቅቱ የተፎካካሪ ፓርቲ ጠበቃዎች 19 ነጥብ 2 ሚሊዮን የተመዘገቡ መራጮች ድምፅ ኮሚሽኑ መቁጠሩን ተናግረዋል፡፡ የኮሚሽኑ ጠበቃዎች በበኩላቸው የተመዘገቡ መራጮች ድምፅ ተቆጥሮ ያላለቀው ሰርቨሩ በመበላሸቱ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በዚህ ምርጫ የሚሊዮን ኬንያውያን የግል መረጃ ለረጅም ጊዜ እንዲሰበሰብ ተደርጓል፡፡ የተወሰደው መረጃ በጣም አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤት ባሳወቀበት ወቅት ግን አልተገለፀም ነበር፡፡ የግል መረጃዎቹን ሰብስቦ የነበረው የፈረንሳይ ድርጅት የሆነው ኦቶ ሳፍራንሞርፖ ሲሆን፤ የኬንያ መንግስት መረጃዎቹን እንዲያቀርብ ጠይቆት ማቅረብ አልቻለም፡፡
እአአ የካቲት 2019 ላይ ደግሞ የኬንያ መንግስት ሁዱማ ቁጥር የተባለ የዜጎች መረጃ ማሰባሰብ ዘመቻ ጀምሯል፡፡ ዘመቻው ለወር የሚቆይ ሲሆን መንግስት የእያንዳንዱ ዜጋ የግል መረጃ፣ የመታውቂያ ቁጥር እንዲሁም የሚኖሩበት አድራሻ የመመዝገብ ስራን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም የኬንያ መንግስት የዜጎቹን ጠለቅ ያለ የግል መረጃ ለመሰብሰብ ከማስተር ካርድ ድርጅት ጋር የተዋዋለ ሲሆን፤ የሁዱማ ቁጥር ያለበት ካርድ እንዲዘጋጅ በማድረግ ዜጎች የመንግስት አገልግሎት ሲያገኙ እንዲከፍሉ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ የኬንያ መንግስት ሁለቱ ስራዎች ማለትም የሁዱማ እና የማስተር ካርድ ስራው ተመጋጋቢነት ያላቸውና በሌሎች አገሮች በተለይ በናይጄሪያ ሁለቱ ስራዎች ውጤት ያመጡ በመሆናው ተግባር ላይ እንደሚውሉ ተናግሯል፡፡ የሁንዱማ መርሃ ግብር ተጨማሪ ቁጥርና ካርድ የሚይዝ ሲሆን ካርዱ የዜግነት መገለጫዎችን እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡
የሁንዱማ ካርድ የዜግነት መታውቂያ፣ ፓስፖርት፣ መንጃ ፈቃድ፣ የልደት ወረቀት፣ የብሄራዊ ደህንነት ፈንድ ካርድ፣ የጤና መድህን ካርድ እንዲሁም የታክስ ከፋይነት ካርድ ያካተተ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ምዝገባው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በሁንዱማ መርሃ ግብር ያልተመዘገበ ዜጋ የመንግስት አገልግሎት ማግኘት አይችልም፡፡ በመርሃ ግብሩ የተሳሳቱና አደገኛ የሆኑ ህጎች ተካተውበታል፡፡
ዜጎችን የፋይናንስ አቅርቦቶችን እንዲገዙ ለማድረግ መሰረታዊ የሆኑ የመንግስት አገልግሎቶችን ትከለከላላችሁ ማለት፤ መንግስትነት ሳይሆን ሰዎችን ማስገደድ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ተናረዋል፡፡ የኬንያ ህገመንግስት እንደሚለው ማንኛውም ህግ ሲወጣ የህዝቡ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሰረት መንግስት ያወጣው መርሃ ግብር በህገ መንግስቱ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ መርሃ ግብሩ ዜጎች መሰረታዊ የተባሉ አገልግሎቶችን የያዘ ቢሆንም፤ ከህዝቡ ይሁንታ እንዲያገኝ ለውይይት ሊቀርብ ይገባል፡፡
መንግስት ስለ መርሃ ግብሩ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሚድያና መገናኛ ብዙሀንን እያወያየ ይገኛል፡፡ በማህበራዊ ሚድያና በመገናኛ ብዙኃን በኩል ቀድሞ መረጃ መልቀቅ በአሁን ወቅት የተለመደ የህግ ማወጃ መንገድ ሆኗል፡፡ በሚገርም ሁኔታ ኬንያ እስካሁን መረጃ መጠበቂያ ህግ አላወጣችም፡፡ ይህ ማለት የአጠቃላይ የዜጎች መረጃ ማለትም የበጀት መጠን፣ የጣት አሻራ እና ወሳኝ የሆኑ የዜጎች መረጃ የሚቀመጠው ያለምንም ህጋዊ ጥበቃ ነው፡፡
ማስታወስ የሚገባው የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን እስካሁን የተያዘው በኦቶ ሳፍራን ሞርፖ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም የፈረንሳይ መንግስት አሁንም ድረስ የኬንያን ዜጋ መረጃ የመበርበር አጋጣሚ አለው ማለት ነው፡፡ በአሁን ወቅት ህጋዊ ማዕቀፎች ባለመኖራቸው ማንኛውም የህዝብ መረጃ በኦቶ ሳፍራን ሞርፖ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ የኬንያን የዴሞክራሲ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ‹‹ዲጅታል ዴሞክራሲ አናሎግ ፖለቲክስ›› የሚለው መፅሀፍ ላይ ይህን ሁኔታ ዲጅታል ቅኝ ግዛት ብሎ ይጠረዋል፡፡ የግል ኩባንያ ከዜጎች በበለጠ የፖለቲካ ስልጣን አግኝቶ ለራሱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የኬንያ ምርጫ የመረጃ ቋት ለማንኛውም ጉዳይ ክፍት የተደረገ አደለም፡፡ ዋናው አስፈላጊው ጉዳይ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ኬንያ ቅድሚያ ሰጥታ መስራት አለባት፡፡ የኬንያ ምርጫ መረጃ እንደ ምርት ከመሸጡ በፊት ህግ አውጥቶ መታደግ ይገባል፡፡ በምን አይነት ሁኔታ ነው አንድ አገር ነፃ ናት የሚባለው፡፡ አገር የሚመራ መንግስት የህዝብ መረጃ ለግል ድርጅት እንደ ንግድ ለውውጥ ሲጠቀምበት ምን አይነት መንግስት ሊባል ይችላል፡፡ የኬንያ መንግስት የህዝቡን መረጃ ጠብቆ ይዛል ተብሎ እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ መንግስትም በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡
ከቴክኒካል ቴክኖሎጂ ቡድኖች የወጣው ሪፖርት እንደሚሳየው ከሆነ እአአ 2017 ምርጫ ወቅት የተፈጠረው የመረጃ መደበቅ ስራ የግል መረጃ ጠባቂ ህግ ባለመኖሩ ነው፡፡ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ለሽያጭ ያቀረበ ሲሆን፤ ፖለቲከኞች በፅሁፍ መልዕክቶች እና በድረገፅ በኩል ያልተገባ መልዕክት ከማስተላለፍ በዘለለ ለመራጮች ስልክ ይደውሉ እንደነበር ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ የፓርቲ አባላት ስም ዝርዝር ከሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የተሰበሰበ ሲሆን ስም ዝርዝሩ ላይ የሚገኙ የግል መረጃዎች በሚስጥር ለመያዝ የተሞከረ መንገድ አልነበረም፡፡
ከምርጫው ውጪ አለም አቀፉ የመረጃ አያያዝ ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ የኬናውያን የሞባይል መረጃ በፖሊስና በፀጥታ አካላት እጅ በመግባቱ ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዜጎች እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ ኬንያውያን የሞባይል መረጃዎቻቸው ያለነሱ ፈቃድ ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ በመሰጠቱ ተቃውሞ አንስቷል፡፡ በዚህም ያለፍላጎታቸው ያልተገቡ የፅሁፍ መልዕክቶችና ለሚያገኙት የተለየ አገልግሎት እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡
ሴቶች በደህንነት ጥበቃዎች ፆታዊ ትንኮሳ እየደረሰባቸው እንደሚኝ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ የደህንነት ጥበቃዎቹ ወሳኝ የተባሉ የግል መረጃዎች ስላሏቸው የግልና የመንግስት ህንፃዎችን እየበረበሩ ይገኛሉ፡፡ የኬንያ ዜጋ የሆኑ ሁሉ የግል መረጃዎቻቸው የጠበቀ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ መንግስት የህግ ማዕቀፍ አውጥቶ ዜጎች ከሰብዓዊ ጥሰት የመታደግ ፍላጎት እያሳየ አደለም፡፡ ሁዱማ ቁጥር የተባለው መርሃ ግብር ባልሆነ ሰዓት የመጣ በመሆኑ ማንኛውም የህዝብ ተሳትፎ እንዳይኖር ያግዳል፡፡
ኬንያ በአሁኑ ወቅት የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን እያደረሰ ያለው የሽብር ጥቃት በአፍሪቃ ቀንድ ያለውን ተፅዕኖ ለማሳየት ምስክር ነች። «ታዋዊዛ» የተባለው የምስራቅ አፍሪቃ የጥናት ድርጅት እንዳመለከተው በኬንያና በሶማሌ የድንበር አቅራቢያ ቦታዎች ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ብቻ ከ50 በላይ የፖሊስ መኮንኖች በአልሸባብ መገደላቸውን አመልክቷል።
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከአልሸባብ የሽብር ጥቃት በተጨማሪ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች የሀገሬውን ሰውም ይሁን የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ስጋት ላይ ጥሏል። ስለ ደህንነት ሲወራ_ምርጫን ተከትሎ በመንግስትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረዉው ውዝግብና ግጭትም ሌላው ለሀገሪቱ ዜጎች አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ነበር። በተለይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች «ራይላ ኦዲንጋ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ» ብለው _በነበረበት ወቅት የህዝቡ ጭንቀት ከፍተኛ ነበር።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2011
መርድ ክፍሉ