የባስማ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ላይ እየተተገበረ ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶች ያረቀቁት ፕሮጀክት ነው።ከዚህ ቀደም በቻይና ተሞክሮ በቻይናውያን ጠንካራ ሥራ ከሽፏል።በሶሪያ በተወሰነ ደረጃ ተሞክሮ ውጤት ቢያመጣም በአብዛኛው ግን ከሽፏል።አሁን ሶስተኛዋ የትግበራ ቦታ ኢትዮጵያ ተደርጋለች። ትግበራው ገና ከመጀመሩ ከአሁኑ እየከሸፈ ይገኛል።
ለመሆኑ የባስማ ፕሮጀክት ምንድን ነው የሚለውን በጨረፍታ እንይ። ፕሮጀክቱ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ምእራባውያን የማይመቻቸውን አገዛዝ ከስልጣን ለማስወገድ እና ተላላኪያቸውን ወደ ወንበሩ ለማምጣት የሚጠቀሙበት ድብልቅ የጦርነት ስልት (hybrid war) ነው።
ይህ የጦርነት ስልት የዲፕሎማሲ ጦርነት ፤ ኢኮኖሚያዊ ጦርነት ፤ የፕሮፓጋንዳ ጦርነትን ፤ የሳይበር ጦርነትን፤ እና ሌሎችንም አደባልቆ በመጠቀም በምእራባውያኑ የማይፈለገው መንግሥት እንዲንገዳገድ እና ከዚያም በህዝብ ተቃውሞ እና በአማጽያን ትብብር እንዲወድቅ የሚደረግበት ነው።
ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዘጋጀው ይህ እቅድ ከዓመት በፊት በፈረንጆቹ ህዳር 10 ቀን 2020 የወጣ ሲሆን፣ ይህን እቅድ እንዲያስተገብርም C2FC የተባለ ቡድን ለንደን ላይ ተቋቁሞ እንዲሰራው ተደርጓል።የዚህ ቡድን አላማ ማማከር ፤ ማስተባበር ፤ አቅም መፍጠር እና መሰለል ነው።ለዚህም ሥራ ከሚዲያዎች ፤ ከታዋቂ ሰዎች ፤ ከምሁራን ፤ ከማህበረሰብ አንቂዎች ፤ ከእርዳታ ድርጅቶች ፤ መንግሥታዊ ካልሆኑ የበጎ አድራጎት ተቋማት እና ከስለላ ተቋማት የተውጣጡ አካላት እንዲሰባሰቡ ተደርጓል፡፡
ይህን መሰል ስብስብ ከዚህ ቀደም ሶሪያ ላይ የመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች የትርክት የበላይነት እንዲወስዱ ለማድረግ ያገለገለ ሲሆን፣ በተለይም አማጽያኑ በህዝብ ዘንድ እንዲታዘንላቸው እና ተወዳጅ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።እንዲያም ሆኖ ግን እንደ ተፈለገው የበሽር አልአሳድን መንግሥት ከስልጣን ማውረድ አልተቻለም።
ምእራባውያኑ አሁን ደግሞ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዙረዋል።ኢትዮጵያ ላይም የተከናወነው ተመሳሳዩ ነው ።በሚዲያዎቻቸው በተቻለ መጠን የጁንታውን ድል ለማጉላት መሞከር ፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በሁሉም መንገድ ማጣጣል ፤ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ኃይሎችን ማፈን እና የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶቻቸው እንዲዘጉ ማድረግ እና መሰል ተግባራት ተከናውነዋል።
ዘገባዎቹ በአማራ እና አፋር የተደረጉ የሕወሓት የውንብድና ሥራዎች እንዳይነገሩ በማድረግ ፤ በተቃራኒው የሕወሓት ጦር ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ እንደሆነ እና አዲስ አበባ ትልቅ ስጋት ውስጥ እንዳለች በተደጋጋሚ በማስነገር ፤ የኢትዮጵያን መንግሥት በዘር ማጥፋት በመክሰስ ፣ እርዳታ በመከልከል እና በሌሎችም ዙሪያ ያጠነጠኑ ነበሩ።
እነዚህ በፕሮፓጋንዳው በኩል የሚደረጉ ጦርነቶች በጦር ግንባሩ ለሕወሓት ከሚደረገው የሳተላይት ድጋፍ ፤ በጸጥታው ምክር ቤት እና በምእራባውያኑ የውጭ ጉዳይ ቢሮዎች ለጁንታው ከሚደረገው የፖለቲካ ድጋፍ ፤ በኢኮኖሚው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከሚደረገው የማእቀብ ጫና ፤ በእርዳታ ድርጅቶች በኩል ለሕወሓት ተዋጊዎች ከሚደረገው የስንቅ ድጋፍ እንዲሁም ሌሎች ድጋፎች ጋር ሲዳመር ሕወሓት አዲስ አበባ እስካሁን መግባት ነበረበት፡፡
ነገሩ ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆኗል።ሕወሓት መፈራረስ ይዟል። ሽንፈቱ የተጀመረውም በቅርቡ በቅድሚያ በአፋር ግንባር ነው።ከዚያም በአማራ ክልል የተለያዩ ግንባሮች ቀጥሏል።
አፋሮች ይህን የባስማ ፕሮጀክት እንዴት ረቱት? የሳተላይት ድጋፍ ስለነበራቸው ነው ? ወይም የምእራቡ ሚዲያ ለአፋር ህዝብ ሰቆቃ እና ትግል የተለየ ሽፋን ስለሰጠ? ወይስ ለአፋር ሀዝብ ስንቅ እና መሳሪያ ያቀበለ የውጭ ኃይል ነበር ? አልያም በዲፕሎማሲው መድረክ ለአፋር ህዝብ የተለየ ድጋፍ ስለተደረገለት ነው?
አይደለም። አፋሮች የባስማ ፕሮጀክትን የረቱት በዳጉ ባህላቸው ፤ በኢትዮጵያዊ ወኔያቸው ፤ እና ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር መናበብ እና መደጋገፍ በመቻላቸው ነው።እነዚህን ሶስቱን ነገሮች ደግሞ የባስማ ፕሮጀክትም ሆነ ሌላ የሴራ ፕሮጀክት አይረታቸውም፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አወል አርባ የሚሉትም ይህንን ነው። ርእሰ መስተዳድሩ ከሁለት ሳምንት በፊት ለኢቢሲ በሰጡት መግለጫ የአፋር ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ‘ዳጉ’ የሕወሓት የሀሰት ፕሮፓጋንዳን ከመመከት አልፎ የጠላትን እንቅስቃሴ በማክሸፍ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል። የሽብር ቡድኑ በጦር ግንባር የደረሰበትን ኪሳራ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለማደናገር የተለያዩ የውዥንብር መረጃዎችን ለመልቀቅ ቢሞክርም፣ ዳጉን የመሠለ የጠራ አስተማማኝ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ባለቤት የሆነው የአፋር ህዝብ ለዚህ ቦታ እንደሌለው በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
በእርግጥም እውነታቸውን ነው።የዳጉ የመረጃ ልውውጥ መንገድ ሀገር በቀል እና ባህላዊ ነው።ስለዚህም በየትኛውም የምእራባውያን የሳተላይት እና የስለላ መስመሮች ሊጠለፍ አይችልም።አፋሮች ማህበራዊ ሚዲያ ቢጠቀሙም ነገር ግን ተአማኒ የመረጃ ምንጫቸው የራሳቸው ባህላዊ የተግባቦት መስመር ነው።
ስለዚህም የባስማ ፕሮጀክት ተግባሪዎች በምሁር ስም ሺ የማስፈራሪያ ትንታኔ ቢሰጡ ፤ እነ ሲ ኤን ኤን እና ቢቢሲ ሕወሓት እዚህ ደረሰ ቢሉ ፤ የሕወሓት ደጋፊ አክቲቪስቶች የፈለጉትን አይነት ፎቶ ሾፕ ቢያዘጋጁ በአፋር ጀግኖች ጆሮ ውስጥ ግን ምንም ትርጉም አልነበረውም።የድሉ ምንጭም ይሄ ነው።አሜሪካኖች በሳተላይታቸው የሕወሓትን ጦር በዚህ ግባ በዚያ ውጣ እያሉ ቢመሩትም አፋሮች ግን በዳጉ የተጋባቦት መስመራቸው ይህን የአሜሪካኖች የስምሪት መረጃ ዋጋ ቢስ አድርገውታል። ሕወሓትም በአፋር በረሀ አሸዋ ውስጥ ሰምጣ ቀርታለች፡፡
አሁን እንዳረጋገጥነው ፕሮጀክት ባስማ የሚከሽፈው በመሰል ሀገር በቀል እውቀቶች እና ባህሎች ነው። በብዙ ሚሊዮን ዶላሮች በምእራባውያኑ ሀገራት የሚተገበረውን ፕሮጀክት ባስማ በአፋር በኩል መና ያስቀረው ዳጉ ነው። አፋሮች በዳጉ ባህላቸው እርስ በራሳቸው ይግባባሉ ፤ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ደግሞ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ይነጋገራሉ። ይህን ማንም የምእራብ ዓለም ፕሮጀክት አያስቆመውም፡፡
አማራ ክልልም አሁን ፕሮጀክት ባስማን የሚያከስምበት የራሱን ፕሮጀክት መጠቀም ጀምሯል። ይህ ፕሮጀክት ደግሞ በዘመናት የዳበረው ፕሮጀክት ፋኖ ነው። ይህም ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊ ፕሮጀክት ነው። ይህም ፕሮጀክት በፕሮፓጋንዳ ጦርነት ፤ በሳይበር ዘመቻ፤ በኢኮኖሚያዊ ጫና ፤ በዲፕሎማሲያዊ ግርግር ብዙም የማይደነግጥ ነው።
ይህን ፕሮጀክት ለማስተግበር የሚያስፈልገው የተለየ በጀትም ሆነ ቴክኖሎጂ ሳይሆን ወኔ እና እምቢ ባይነት ነው። የሚከናወነውም መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ እና ባንዳነትን በመጸየፍ ነው።ከዚህ ቀደም ወያኔን ከአዲስ አበባ ለማባረር ከፕሮጀክት ቄሮ ጋር በጋራ ተተግብሮ ውጤታማነቱ ተመስክሮለታል።ባለፉት ቀናትም ይህ ፕሮጀክት ፋኖ ውጤታማነቱን እያሳየ ነው፡፡
አሁን የሚያስፈልገን እንደ ፕሮጀክት ዳጉ ፤ ፕሮጀክት ፋኖ እና ፕሮጀክት ቄሮ ያሉ የድል ፕሮጀክቶችን ከአንድ ክልል ሀብትነት በማውጣት የመላው ኢትዮጵያውያን ሀብት ማድረግ ነው።በዚህ መልኩ ለከርሞውም ቢሆን ጠላት በኢትዮጵያ ላይ የሚሸርበውን ሴራ ማክሸፍ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014