ኩላሊት ከሰውነትዎ የጀርባ የጎድን አጥንቶችዎ በታች ከአከርካሪዎ ጎንና ጎን የሚገኝ አነስተኛ የሰውነት አካል ነው:: አላስፈላጊ ቆሻሻዎችን ከሰውነት ውስጥ በማስወገድ፣ በሰውነትዎ ውስጥ የሚገኙ እንደ ካልሺየም፣ ሶዲምና ፖታሺየም የመሰሉ ንጥረ ነገሮችን በማመጣጠንና ሆርሞን እንዲመረት በማድረግ ረገድም የኩላሊትዎ ሚና የጎላ ነው::
በሽታ ካላጋጠመዎ በስተቀር የተመጣጠነ ምግብ መመገብና በቂ ውሃ መጠጣት የኩላሊትዎን ጤንነት ለመጠበቅ በቂ ነው:: ይሁን እንጂ አንዳንድ ምግቦች በተለየ ሁኔታ የኩላሊትዎን ጤና ከፍ እንደሚያደርጉ የስነ ምግብ ባለሙያዎች ይናገራሉ::
የኩላሊትዎን ጤንነት ለመጠበቅ ሁሉም ነገር የሚጀምረው ገና በማለዳ ንፁህ ውሃ ተጎንጭተው ጤናማ ምግብ ተመግበው ቀንዎን ሲያሳልፉ ነው::
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አራት ምግቦች ደግሞ ኩላሊትዎ ንፁና ጤናማ ሆኖ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ የሚያስችሉ በመሆናቸው ‹‹ግድ የለም ይጠቀሟቸው›› ይልዎታል የስነ ምግብ ጤና ባለሙያዎቹ::
1ኛ፡- ወይን
ወይን በኦቾሎኒና በእንጆሬ ውስጥ ብቻ የሚገኘውንና ለሰውነት ጠቃሚ የሆነውን ‹‹ሪዘርቬራቶል›› የተሰኘ ንጥረ ነገር በውስጡ ይዟል:: ተመራማሪዎች የኩላሊት በሽታ ባለባቸው አይጦች ባደረጉት ምርምር ንጥረ ነገሩ የኩላሊት እብጠትን እንደሚቀንስ አረጋግጠዋል:: በተለይ ቀይ የወይን ፍሬ ከተቻለ ዘወትር ከልተቻለ ደግሞ አልፎ አልፎ መመገብ የኩላሊትዎን ጤና ከመጠበቅ በዘለለ የተሟላ የሰውነት ጤና እንዲኖርዎት ያደርጋል:: ከዚህ አኳያ ወይንን ቢመገቡ ብዙ የጤና በረከት ይኖረዋልና ይመገቡት::
2ኛ፡-የፍራፍሬ ጭማቂ
ሲትሪክ አሲድ በሎሚ፣በብርቱካንና በሃባብ ፍራፍሬዎች ውስጥ በብዛት ይገኛል:: ይህ አሲድ በሽንትዎ ውስጥ ያለውን ካልሺየም በማስወገድ በኩላሊትዎ ውስጥ ጠጠር እንዳይፈጠር ይረዳል:: ይህም ለኩላሊት ጠጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የካልሲየም ክሪስታሎች መፈጠርን ይቀንሳል:: በተጨማሪም፣ በየቀኑ አንድ ኩባያ
ንፁህ የሎሚ፣ የብርቱካን አልያም ደግሞ የሀባብ ጭማቂ መውሰድ የዕለት ተዕለት ፈሳሽ ፍላጎትዎን ለማሟላት ይረዳዎታል።
3ኛ፡- በቪታሚን ቢ-6 የበለፀጉ ምግቦች
በሰውነት ውስጥ ምግብን ወደ ኃይል በመለወጥ ሂደት የቪታሚን ቢ-6 ሚና የጎላ ነው:: ይህ ሂደትም ቪታሚን ቢ-6ን ይፈልጋል:: ከዚህ አንፃር ዘወትር በሚመገቡት ምግብ ውስጥ ቢያንስ 50 ሚሊግራም ቪታሚን ቢ- 6 መጨመር የግድ ይልዎታል:: ይህ ደግሞ በኩላሊትዎ ውስጥ ጠጠር እንዳይፈጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል:: ሆኖም በጤና አጠባበቅ ኤክስፐርት ቁጥጥር ስር ያለ የሕክምና ቴራፒ አካል ካልሆነ በስተቀር አዋቂዎች በቀን ከ 100 ሚሊ ግራም ቫይታሚን ቢ- 6 በላይ መውሰድ እንደሌለባቸው የስነ ምግብ ጤና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ::
4ኛ፡-ውሃ
አንድ አዋቂ ሰው 60 ከመቶው የሰውነቱ ክፍል ውሃ ነው:: ከዚህ አንፃር ርጥብ ሆኖ መቆየቱ ወሳኝ እንደሆነ ይነገራል:: ውሃ ከአእምሮ እስከ ጉበት ድረስ እያንዳንዱ
የሰውነት አካል በአግባቡ ሥራውን እንዲያከናውን እጅግ አስፈላጊ ነው:: ከዚህ አንፃር ኩላሊት በሰውነትዎ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ የሚያጣራ በመሆኑ ለኩላሊትዎ ከምንም በላይ ወሳኝ ነው::
ኩላሊት በሰውነት ውስጥ ያለውን ፈሳሽ በማጣራት በሽንት አማካኝነት አላስፈላጊ ቆሻሻዎችን በሽንት አማካኝነት ያስወግዳል:: ከዚህ አኳያ የሚጠቀሙት የውሃ መጠን አነስተኛ ከሆነ የሽንትዎ መጠንም አነስተኛ ይሆናል:: ኩላሊትዎ ሥራውን የሚያቆመውና በኩላሊትዎ ውስጥም ጠጠር የሚፈጠረው በአነስተኛ የሽንት መጠን ነው:: አነስተኛ ሽንት ሊኖር የሚችለው ደግሞ ውሃን በብዛት ካለመጠታት ጋር ተያይዞ ነው::
ከዚህ አንፃር በቂ ውሃ መጠጣት ኩላሊቶችዎ ከመጠን ያለፈ ቆሻሻን በበቂ ሁኔታ ከሰውነትዎ ውስጥ እንዲያፀዱ ያስችልዎታል:: ታዲያ ምን ይጠብቃሉ! ውሃን እንደልብ ያገኙታል:: በየእለቱ ቢጎነጩት የኩላሊትዎን እድሜ ያረዝማሉ:: እናም ውሃን ይጠጡ::
ምንጭ፡- ናሽናል ዴይሊ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014