በአንድ ወቅት አንድ ፖለቲከኛ ‹‹የአገራችን የፖለቲካ ችግር የውይይት ጥራት አለመኖር ነው›› ሲል ሰምቻለሁ:: ተራ አሉቧልታዎችና ብሽሽቆች ከሚነዙባቸው ማህበራዊ ገጾች ጀምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ፈቃድ እስካላቸው ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ድረስ በቋሚነት የመደገፍ እና በቋሚነት የመቃወም አባዜ የተጠናወታቸው መሆኑን እንታዘበለን::
እርግጥ ነው በቋሚነት የምንደግፈው እና በቋሚነት የምንቃወመው ሊኖር ይችላል:: ይህ የሚሆነው ግን ያ የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው ነገር እኛ ከምናምንበት ወይም ለአገር ይጠቅማል ብለን ከምናስበው ጉዳይ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ ሲገኝ ነው:: አለበለዚያ ግን ገና ለገና ‹‹ተቃዋሚው ነበር፤ አሁን ለምን ደገፈው?›› ይሉኛል፤ ወይም ‹‹ደጋፊው ነበር፤ አሁን ለምን ተቃወመው?›› ይሉኛል በሚል ጥፋቱ ላይ አብሮ ሙጭጭ ማለት አቋም ሳይሆን ከንቱ ግትርነት ነው::
ነገሬን ግልጽ እንዲያደርግልኝ፤ በመጀመሪያ ለዚህ ጽሑፍ ያነሳሳኝን ምክንያት ልጥቀስ:: በቅርቡ ስድስት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን እና የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮችን ጨምሮ የኢትዮጵያን መንግሥት አደጋ ላይ የሚጥል ሴራ ላይ የዙም ውይይት ማድረጋቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቶ መነጋገሪያ ሆኖ ተመልክተናል:: ከእነዚህ ደግሞ በስፋት መነጋገሪያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ እና ዶክተር እሌኒ ገብረመድኅን ናቸው:: በተለይም ዶክተር እሌኒ ደግሞ በቲውተር ገጻቸው ማስተባበያ የሚመስል ነገር መጻፋቸው አጀንዳነታቸውን ይበልጥ አጉልቶታል::
ለአሁኑ ግን የእኔ ትዝብት እነዚህ ሰዎች ላይ አይደለም:: የእነዚህን ሰዎች ድርጊት ተከትሎ ባስተዋልኩት የሌሎች ሰዎች ክርክር ላይ ነው:: በተለይም ዶክተር እሌኒ ብዙ አድናቂዎች እና አክባሪዎች ስለነበሯቸው አሁን እንዴት አድርገን እንወቅሳቸዋለን ብለው አንዳንዶች ሲወዛገቡ ነበር:: ዶክተር እሌኒን የወቀሷቸውንም ‹‹ስታደንቋቸው
አልነበር እንዴ፤ በአንድ ጊዜ ወደ ወቀሳው ዘላችሁ እንዴት ገባችሁ!›› እያሉ አንዳንዶች ዶክተሯን ተችተው የተናገሩትን ለማብጠልጠል ሲሞክሩም ተስተውሏል::
ይህንን መነሻ አድርገን አጠቃላይ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ሕይወታችንን ስንመለከተው እንዲህ የተወዛገበ እየሆነ መምጣቱን እንገነዘባለን:: በቃ፤ ቋሚ ደጋፊ እና ቋሚ ተቃዋሚ የሚባል ነገር መኖር የለበትም::
ቋሚ ደጋፊ ወይም ቋሚ ተቃዋሚ ሆንን ማለት እኮ እያደነቅን ያለነው ወይም እየተቃወምን ያለነው ድርጊቱን ሳይሆን ግለሰቡን ነው ማለት ነው:: የእኔ ሃይማኖት ወይም የእኔ ብሔር ሰው ስለሆነ በቋሚነት ማድነቅ የለብኝም:: በሆነ አጋጣሚ ስላስቀየመኝም ዕድሜ ዘላለሜን ስወቅሰው አልኖርም፤ ጥሩ ያደረገ ዕለት ደረቴን ነፍቼ አመሰግነዋለሁ::
ለምሳሌ፤ ዶክተር እሌኒን ለረጅም ዓመታት ስናመሰግናቸው ኖረናል፤ ያኔ ጥሩ ሰርተው ነበር ማለት ነው:: ዛሬ ለአገር የማይጠቅም ነገር ስላደረጉ ምንም ሳላፍር፣ ማንንም ሳልፈራ፣ ግጥም አድርጌ እወቅሳቸዋለሁ:: ነገ ሀሳባቸውን አስተካክለው ለአገር የሚጠቅም ሥራ ከሰሩ ደግሞ አፌን ሞልቼ አደንቃቸዋለሁ፤ አመሰግናቸዋለሁ! ምክንያቱም የማየው ሀሳባቸውን እና ድርጊታቸውን እንጂ ግለሰባዊ ማንነታቸውን አይደለም::
በግለሰቦች ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርና መንግሥት ያለን የፖለቲካ ባህልም /ልማድም/ ተመሳሳይ ነው:: አንድ ሰው መንግሥትን በፈጸመው ተግባር ካመሰገነ ‹‹የመንግሥት ደጋፊ ነህ›› ይባላል:: ሌላ ጊዜ ደግሞ በመንግሥት ላይ የጎደለ ነገር ተመልክቶ መንግሥትን ሲወቅስ ‹‹ ፀረ መንግሥት፣ ወላዋይ፣ አቋም የለሽ!›› ተብሎ ይሰደባል:: ‹‹ትናንት ስታደገድግ አልነበር?›› ሲባል ሰምተናል:: ይሄንንም በተለይም በተፎካካሪ ፓርቲ አባልነት ውስጥ ባሉ ሰዎች ዘንድ በስፋት ስናስተውለው ቆይተናል:: የመንግሥትን ጥሩ ጎን አይተው ያመሰገኑም ባልዋሉበት ‹‹ተለጣፊ›› የሚል ታርጋ ሊለጠፍባቸው ይችላል:: በግለሰቦችም ላይ እንደዚሁ ነው::
መንግሥትን በቋሚነት ላመሰግነው ወይም በቋሚነት ልወቅሰው አልችልም፤ የማመሰግነውም የምወቅሰውም በሰራው ላይ ተመርኩዤ ነው:: ጥሩ ሲሰራ አመሰግነዋለሁ፤ መጥፎ ሲሰራ አወቅሳለሁ:: እንዲህ ማድረጉ ያስመሰግነዋል፣ በዚሁ ይቀጥልበት እንዳልኩት ሁሉ፤ እንዲህ ማድረግ ልክ አይደለም ብዬ እንደ ዜጋ ለአገሬ ይበጃል ያልኩትን አስተያየት እሰጣለሁ:: መንግሥት ካልተመሰገነም ሆነ ካልተወቀሰ ለራሱ ለመንግሥትም አይጠቅመውም:: አድናቆት ብቻ ሊያጠነክረው አይችልም፤ ወቀሳ ብቻም ሊያስተካክለው አይችልም፤ ዜጎችም መንግሥትን በነጻነት መመስገን ባለበት ማመስገን፣ መተቸት ካለበትም መተቸት ይኖርባቸዋል::
ይህንን ስል ግን ወላዋይ አቋም ያለው የለም እያልኩም አይደለም:: በወላዋይ አቋማቸው ብዙ የምንታዘባቸው ሰዎች ሞልተዋል:: ትናንት ያሉትን ዛሬ የሚቀይሩ:: ይሄ ማለት ያ የተቃወሙት ወይም የደገፉት አካል ምንም አቋሙን ሳይቀር ራሳቸው የሚቀየሩ ማለት ነው::
ወላዋይ ከተባሉም እንዲህ አይነት ሰዎች ናቸው ወላዋይ መባል ያለባቸው:: ያ የተቃወሙት ወይም የደገፉት አካል ሀሳቡን ሲቀይር የማያደንቁበት ወይም የማይወቅሱበት ምክንያት የለም:: ትናንት እንዲህ በማለትህ ወቅሼህ ነበር፤ ዛሬ በማስተካከልህ አመሰግንሃለሁ፤ ወይም ትናንት እንዲህ በማለትህ አመስግኜህ ነበር፣ ዛሬ ግን እንዲህ በማለትህ ተቀይሜሃለሁ ማለት አቋም ያለው ሰው ባህሪ ነው::
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፤ ያ የምንደግፈው ወይም የምንቃወመውን አካል ብቻ ሳይሆን እኛም አቋም ልንቀይርና ልናስተካክል እንችላለን:: እንደ ዘመኑና እንዳለው ነባራዊ ሁኔታ ሰዎች ሀሳባቸውን ቢያስተካክሉ ምንም ችግር የለውም:: አንድ ነገር ላይ ሙዝዝ ከማለት ይሻላል:: በሰዎች ምክር ወይም በማንበብ ወይም የጊዜውን ባህሪ በመረዳት አቋምን ማስተካከል ምክንያታዊና የሚያስኬድም ነው::
ከምንም በላይ ግን አስቸጋሪውና የፖለቲካ ባህላችንንም የብሽሽቅ ያደረገው፤ ቋሚ ደጋፊ እና ቋሚ ተቃዋሚ መሆን ነው:: ሰዎችን በሀሳባቸው ወይም በድርጊታቸው ሳይሆን በግለሰባዊ ማንነታቸው መፈረጁ ነው ለእዚህ የዳረገን::
ትናንት አገር ሲያተራምስ የነበረ አሸባሪ ‹‹በሥራዬ ተፀፅቻለሁ፤ ከዚህ በኋላ ለአገር የሚጠቅም ነገር እሰራለሁ›› ከማለትም አልፎ ባለው መሠረት ሲሰራ ከታየ እንዲሁም ምጡቅ ተመራማሪ ቢሆን ላናደንቀው ነው? ጨረቃ ላይ ቢወጣ ‹‹ትናንት ይህን ስላደረገ…›› በሚል ይህን አስገራሚ ብቃቱን ላናደንቀው ነው? በአንፃሩ፤ ትናንት የህዋ ተመራማሪ የነበረ ሰው ድንገት ተነስቶ አገር ካላሸበርኩ ቢል፣ ዘራፊ ካልሆንኩ ቢል ‹‹ትናንት እንዲህ አይነት ሰው ነበር እኮ›› በሚል ዝም ሊባል ነው ወይ? ጥሩ ሥራ መደበቂያ ሊሆን አይችልምና በጥፋቱ ልክ ይወቃሳል፤ ይተቻል::
በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን በየካፌው እና በየትራንስፖርት ቦታው የምንሰማው ይሄው የፍረጃ እና የግትርነት አባዜ ነው:: እገሌ ትናንት የእገሌ ተቃዋሚ ነበር፤ ዛሬ ለምን አመሰገነ፤ ወይም ትናንት ሲያሽቃብጥለት ነበር ዛሬ ለምን ተቃወመ! እንደዚያ ብሎ ነገር የለም:: የምናደንቀውም የምንወቅሰውም ዛሬ ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ነው:: ትናንት በሠራው ሥራ ተገቢውን ምስጋና እና አድነቆት አግኝቷል፤ ያ ግን ዛሬ ለሚፈጽመው ጥፋት መሸፈኛ ሊሆን አይችልም::
አንዳንዶቻችን ደግሞ ለራሳችን የሚሆነውን ብቻ መርጠን እናደንቃለን፤ ወይም እንወቅሳለን:: ከተናገረ ብዙ ነገር ውስጥ አንዷን ብቻ መዞ መውቀስ ወይም ማድነቅ ለምዶብናል:: ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ታዋቂ ሰዎች ‹‹ከዓውድ ውጭ ተተርጉሞብኛል›› የሚል ማስተባበያ ሲያቀርቡ የሚሰማው:: ምንም እንኳን እነርሱ ራሳቸውን ከወቀሳ ለማዳን እንደዚያ ቢሉም፤ የሚተነትነው ሰውም ሙሉ ይዘቱን በጥሞና መረዳት ይኖርበታል::
በአጠቃላይ ግለሰቦችንም ሆነ መንግሥትን በቋሚነት ልንደግፍ ወይም ልንቃወም አይገባም! የምንቃወመውም ሆነ የምንደግፈው ዛሬ ላይ በሚፈጽሙት ተግባር መሆን አለበት::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 /2014