በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን የውጭ ኃይሎች በተለይ የሶማሊያ መንግሥት ሰርጎ ገቦችና ወታደሮች በ1970 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ ዘልቀው በመግባት ሲወጓት የነበረበትንና የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ይህን ወረራ ለመቀልበስ ያደርጉ የነበረውን ግብግብ የተመለከቱ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል።
በዚህ ግብግብ ከኢትዮጵየ ወታደሮች ጎን ለጎን አርሶ አደሩም ጭምር መሣሪያ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በጦርና በዱላ እየተዋጋ ጠላትን ድል ያደርግ የነበረበትን ሁኔታ የሚያመለክቱ ዘገባዎችንም ይዘናል፡፡
የሐረር ዙሪያ ገበሬዎች ወራሪን ለመከላል ወሰኑ
ሐረር(ኢ.ዜ.አ)፡- በሐረር ዙሪያ አውራጃ በአወዳይ ከተማ በሸሪፍ ካሌድ ቀበሌ የሚገኙት ከ፩ ሺ በላይ አርሶ አደሮች በአለፈው ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ስብሰባ አድርገው የአድኃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት መደበኛ ወታደሮች የሚፈጽሙትን ግልጽ ወረራ ለመከላከልና ለመደምሰስ መስማማታቸው ተገለጸ፡፡
አርሶ አደሮቹ ይህንኑ ስምምነት ያደረጉት የአካባቢው ጦር አዛዦች የምሥራቅ እዝና የ፫ኛ ክፍለ ጦር ወታደራዊ የፖለቲካ ካድሬዎች ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ስለ ፀጥታ አጠባባቅ፣ ስለ ሰብል አሰባሰብ ሁኔታ ሰፊ ገለጣና ማብራሪያ ካደረጉላቸው በኋላ መሆኑ ታውቋል።የአውዳይ ከተማና የሸሪፍ ካሌድ ቀበሌ የሚገኙት በሐረር ዙሪያ አውራጃ በዓለማያ ወረዳ ነው።
(ጥር 21 ቀን 1970 ዓ.ም )
70 የሶማሊያ ወታደሮች ተገደሉ
ሐረር (ኢ.ዜ.አ)፡- በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በበደኖ ከተማ አካባቢ ደደሳቦና ደነባ በተባሉት ቀበሌዎች የሚገኙት መለዮ ለባሾች ወዛደሩና አባት ጦረኞች በመተባበር ባደረጉት አሰሳ 70 የሶማሌ መደበኛ ወታደሮችን ሲገድሉ ከመቶ ሃምሳ በላይ ማቁሰላቸው ተገለጠ፡፡
በዚሁ ጊዜ በተካሄደው ጀብዱ የጠላትን ምሽግ ሠፈር እንዳልነበረ አድርገው መደምሰሳቸውን አንድ የክፍለ ሀገሩ ቃል አቀባይ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በጋራ ሙለታ አውራጃ አስተዳደር ውስጥ ጫካ ገብተው የነበሩ አምስት አርሶ አደሮች ከነሙሉ ትጥቃቸው መንግሥት በሰጠው ምህረት በመጠቀም እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጥፋታቸው ተፀጽተው ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው የተመለሱት የገበሬ ማኅበራት አባላት በጋራ ሙለታ አውራጃ አስተዳደር ቀበሌዎች አርሶ አደሮች መሆናቸው ታውቋል።አርሶ አደሮቹ በአሁኑ ጊዜ ፈርሶ የነበረውን ማኅበራቸውን መልሶ ለማቋቋም በየገበሬ ማኅበራቸው እየቀረቡ መመዝገባቸውን የክፍለ ሀገሩ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡
(ጥር 28 ቀን 19 70 ዓ.ም)
በሶማሊያ ፕሮፓጋንዳ ተወናብደው የነበሩ 124 ሰዎች በምህረት ገቡ
ጎባ(ኢ.ዜ.አ)፡- በአድኃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት ከንቱ ፕሮፓጋንዳ ተሰብከው ጫካ በመግባት ፀረ ሕዝብ ተግባር ሲፈጽሙ የቆዩ 124 ሰዎች በተለያዩ ቦታዎችና ቀኖች ከነማሣሪያቸው እጃቸውን እየሰጡ ምህረት በመጠየቅ የገቡ መሆናቸውን የመንደዮ አውራጃ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ባለፈው ቅዳሜ በላከው ዜና አስታውቋል፡፡
እነዚህ ሰዎች በአድራጎታቸው ተጸጽተው ምህረት በመጠየቅ በመንደዮ አውራጃ በሚገኙት ስድስት ወረዳዎች ውስጥ እጃቸውን የሰጡት ካለፈው መስከረም ወር ፸ ዓ/ም/ ጀምሮ ባለው ጊዜ መሆኑ ተገልጧል፡፡
ምህረት ጠያቂዎቹ አብረዋቸው ሔደው ከነበሩት ቤተሰቦቻቸው ጋር ተመልሰው ለየወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት እጃቸውን በሰጡበት ወቅት አድኃሪው የሞቃዲሾ መንግሥት እናት ሀገራቸውን እንዲወጉበት ያስታጠቃቸውን 120 ልዩ ልዩ አውቶማቲክ ጠብመንጃዎች ፩ ሺህ ፭፻፹፭ ልዩ ልዩ ጥይቶች ሦስት ሽጉጦችና አንድ የእጅ ቦምብ አስረክበዋል፡፡
የስድስቱ ወረዳ አስተዳዳሪዎችም በየበኩላቸው ለነዚሁ ሰዎች ስለ አብዮቱ ሂደትና ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሰፊ ገለጻ ከማድረጋቸውም ሌላ ሙሉ ምህረት የተደረገላቸው ስለሆነ ወደ ቀድሞው ቀበሌያቸው እንዲመለሱ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲመሠርቱ ያስገነዘቡዋቸው መሆኑን ያውራጃው አስተዳደር ጽ/ቤት ጨምሮ ገልጧል፡፡
(ጥር 9 ቀን 1970 ዓ.ም)
ለመሰላና ደደር ገበሬዎች ትጥቅ ተሰጠ
አሰበተፈሪ(ኢ.ዜ.አ)፡- በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በጨርጨር አደላ ጋራ ጉራቻና በወበራ አውራጃ ለሚገኙ የመሰላና የደደር ወረዳ ገበሬዎች ሰሞኑን የመሣሪያ ትጥቅ ተሰጥቷል፡፡
ታኅሳስ ፳ና ፳፩ ቀን ፸ ዓ/ም/ በመሰላና በሐረዋጫ ከተሞች ተገኝተው ትጥቅ የሰጡት የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ አባል ናቸው።ጓድ ሻምበል ባሻ ደመቀ ባንጃው በዚሁ ጊዜ በመሰላ ወረዳ ቆላማ ክፍል ውስጥ ሰርገው የገቡትን የሶማ ወታደሮች በጦርና በዱላ ዘምተው በመደምሰስ ጀብዱ ለፈጸሙት ሁለት ገበሬዎች የማረኩትን አንድ ክላሽንኮቭ አውቶማቲክ ጠመንጃ አንድ መውዜር ከነጥይታቸው የመረቁላቸው ከመሆኑም በላይ ሌሎች አሥራ አንድ ሰዎች ደግሞ ልዩ ልዩ ሽልማት በመስጠት መሣሪያ አስታጥቀዋቸዋል፡፡
የትጥቅ አሰጣጡ ሥነ ስርዓት ከተፈጸመ በኋላ ጓድ ሻምበል ባሻ ደመቀ ባደረጉት ንግግር «ይህ የተሰጠው መሣሪያ ለሰፊው ሕዝብ መጠበቂያና ለአገራቸው ዳር ድንበር ማስከበሪያ እንጂ በሌላ ቂም በቀል አፈሙዙን ወደ ጭቁኖች ለመመለስ አለመሆኑን የታጠቁትን ገበሬዎች አስጠንቅቀዋቸዋል፡፡»
ቀጥለውም በተለይ የመሰላ ወረዳ ገበሬዎችና የከተማው ሕዝብ በመተባበር ከወረዳው መለዮ ለባሾች ጎን ተሰልፎ በወረዳው ውስጥ ሠርገው ገብተው አደጋ ለመጣል የሞከሩትን የሶማሌ ገዥ መደብ ወታደሮች በመደምሰሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
(ታኅሳስ 21 ቀን 1970 ዓ.ም)
በአዶላ የሶማሌ ወታደሮች ተደመሰሱ
አዋሳ(ኢ.ዜ.አ)፡- በሲዳሞ ክፍለ ሀገር በአዶላ ወረዳ ባለፈው ረቡዕ ቀንቱ ሙራ በተባለው ቀበሌ ገበሬ ማኅበር አባሎች ላይ የሶማሌ መደበኛ ወታደሮች አደጋ ለመጣል ሲሞክሩ በክብረ መንግሥት ከተማ ውስጥ የሚገኙ መለዮ ለባሾች አባት ጦረኞችና የመንግሥት ሠራተኞች በፍጥነት ደርሰው በወሰዱት አፋጣኝ ርምጃ ፯ቱን ገድለው በርከት ያሉትን ማቁሰላቸውን የክፍለ ሀገሩ አስተዳደር ጽ/ቤት ትናንት አስታወቁ፡፡
በዚሁ የመከላከል ርምጃ ከወገን በኩል ጉዳት አለመድረሱን ጽህፈት ቤቱ ገልጦ በእብሪት የመጡትን የሶማሊያ መደበኛ ወታደሮች ከአካባቢው ፈጽሞ ለመደምሰስ ከክብረ መንግሥት ከተማ የተውጣጣ አሳሽ ቡድን ክትትሉን መቀጠሉን ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጧል፡፡
ታኅሳስ 18 ቀን 1970 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2014