አርበኝነት ዘርፈ ብዙ ነው። ወታደር በጦር ሜዳ፤ አትሌቱ በመሮጫ መሙ፤ ከያኒው በመድረክ፤ ነጋዴው በግብሩ፤ ምሁሩ በምርምሩ ሌላውም በየዘርፉ ሊገልጸው ይችላል። የአንዱ አርበኝነት ከሌላው ጋር ካልተሳሰረ አርበኝነቱ ፍሬ አይኖረውም። የወታደሩ የአርበኝነት ገድል በነጋዴው የግብር መክፈል አርበኝነት ካልታገዘ ዋጋ አይኖረውም። የዘፋኙ አርበኝነት አትሌቱን ለማሞገስ ካልሆነ ጥቅም የለውም።
የትኛውም አገር በዚህ መልኩ በየሙያው ውስጥ ያሉ አርበኞች ሲተባበሩ ብቻ ነው ወደ ስኬት ማማ መውጣት የምትችለው። ልክ እንደዚያ ሁሉ ፋሽኑ እና ሞዴሊንጉም የራሱ የሆነ የአርበኝነት ሚና አለው። እንዴት ዓይነት ሚና ከማለታችን በፊት ታሪክን ወደኋላ እንመልከት።
በዓለም በርካታ አገሮች እንደታየው፣ በዘመነ ደርግ እንደተስተዋለውም መንግሥታት የአለባበስ ፋሽንን ለአርበኝነት መገለጫ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ዜጎች አንድ ዓይነት ዲዛይን ያላቸው አልባሳትን እንዲለብሱ በማድረግ ለአገራቸው ያላቸውን ስሜት እንዲገልጹ ብሎም የተጻራሪ ወገንን እንዲያወግዙበት ተደርጓል። ለምሳሌ ያህል በአለባበስ ረገድ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ዜጎች የሚለብሱት ልብስ የምዕራባውያን እንዳይመስል አድርጋ ነበር። የሚሠሩ የአልባሳት ፋሽኖች ቀላል፤ ንጹህ እና ለሥራ የሚመቹ ሆነው እንዲሠሩ ይደረግም ነበር። በሌሎች ኮሚኒስት አገራትም ተመሳሳይ የአለባበስ እና የፋሽን መንገዶችን ይከተሉ የነበረ ሲሆን፣ በተለይም ዋናው አላማ በአለባበስ ውስጥ ለአገር ያለ ፍቅርን እና አርበኝነትን ብሎም ለአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ያለን ተቃውሞ ለማሳየት ነበር።
ዛሬ መንግሥት በዜጎች አለባበስ ላይ ውሳኔ መስጠት የሚችልበት ዘመን አይደለም። ስለዚህም ዜጎች የራሳቸውን የልብስ ምርጫ መወሰን ይችላሉ። እንዲያም ቢሆን ግን አገራት ይህን የአርበኝነት መንፈስ በአልባሳት ውስጥ ማስኬድ የሚችሉበትን መላ አላጡም። ለዚህም የፋሽን ኢንዱስትሪውን በአግባቡ ይጠቀሙበታል። ለዚህም ማሳያዎች ማንሳት ይቻላል።
የአሜሪካን እንመልከት። አሜሪካውያን በየዓመቱ ጁላይ 4 ቀንን የነፃነት ቀን ብለው ያከብሩታል። ይህ በዓል አሜሪካውያን ከእንግሊዙ ንጉሥ ጆርጅ ሳልሳዊ አገዛዝ ነፃ መሆናቸውን እና የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች (united states of America) የመሠረቱበት ቀን ነው። በዓሉ በፖለቲካ ውይይቶች፣ በሙዚቃ፣ በድግስ፣ በጭፈራ ወዘተ የሚከበር ሲሆን፤ ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘ ፋሽንም የራሱ የሆነ ቦታ አለው።
በበዓሉ ቀን የሚለበሱ አልባሳት አሜሪካዊነትን እና አርበኝነትን የሚገልጹ ሆነው ይሠራሉ። በዓሉ የሚውለው በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ፀሐይ ጎልታ በምትታይበት ወቅት በመሆኑ ብዙዎች ቀለል ያለ ልብስ ይለብሳሉ፤ እነዚያ አልባሳት ግን ብዙውን ጊዜ ቀይ ሰማያዊ እና ነጭ ቀለሞች ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ይበረታታል። እነዚህ ቀለማት የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ ቀለማት ናቸው። የፋሽን ዲዛይነሮችም ለዚያ ቀን ብለው አዳዲስ ዲዛይኖችን የሚያዘጋጁ ሲሆን፣ የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ ያለባቸው ወይም የሰንደቁን ቀለም የያዙ አልባሳት በተለየ ሁኔታ ይመረታሉ።
በሩሲያም ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታያሉ። በርካታ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሩሲያውያን የፋሽን ዲዛይነሮች በሚሰሯቸው አዳዲስ የፋሽን ፈጠራዎች ውስጥ የሩሲያ የአርበኝነት ስሜት አይሎ ይታያል። ዓለም አቀፉ የፋሽን ኢንዱስትሪ በርካታ ታዋቂ ሞዴሎችን እና ምርቶችን የምታበረክተው ሩሲያ በፋሽን ረገድ ግን የምዕራቡን ከመቅዳት ባለፈ የራሷን ቀለም የምትገልጥ ሆናለች። በተወሰነ መልኩም የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለሩሲያዊ አርበኝነት መገለጫ ሆኖ እንዲሠራ አድርጋለች።
ወደ እኛ ስንመጣ ፋሽን ለአርበኝነት እና አገራዊ ስሜትን ለማዳበር ሊያግዝ እንደሚችል ምልክቶች መታየት ጀምረዋል። በአንድ ጎን የባህል አልባሳት በአዳዲስ ዲዛይን እና አሠራር እየተመረቱ በብዛት መቅረብ የጀመሩ ሲሆን፣ በተለይም በከተማ ያለው ሕዝብ በበዓል ቀናት ቢያንስ የባህል አልባሳትን ለመልበስ ፍላጎት እንዳለው እየታየ ነው። ለዚህም ጥምቀትን እና ኢሬቻን ማየት እንችላለን። በእነዚህ በዓላት ላይ በባህል አልባሳት ደምቆ መታየት ራሱን የቻለ አርበኝነት ነው።
በሌላ መልኩ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በሰንደቅ አላማው ቀለም የተሠሩ አልባሳት ቁጥር እየጨመረ ነው። ይህም ሊበረታታ የሚገባው ነው። ነገር ግን እነዚህን አልባሳት በአዘቦት ቀን ሊለበሱ በሚችልበት ሁኔታ እና የሰንደቁን ክብር ባልነካ ሁኔታ እንዴት ማዘጋጀት ይቻላል የሚለውን ከግንዛቤ መክተት ያስፈልጋል።
በሰንደቁ ቀለም የተሠሩ ቦርሳዎች፣ ቲቨርቶች፣ መነጽሮች እና ሌሎችም መመረት አለባቸው። በሌላ መልኩ አርበኝነት የሚገለጸው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ቀለም በመጠቀም ብቻ አይደለም። የብሔር ብሔረሰቦችን መገለጫ ቀለሞች በአልባሳት ዲዛይን ውስጥ በማስገባት ብዝሀነትን ማሳየትም ይቻላል። ይህ በቅርቡ በተካሄደ አንድ የኪነጥበብ ሽልማት መርሀ ግብር ላይ ታዳሚዎች የአገር ባህል ልብስ ለብሰው እንዲመጡ መጠየቁም በፋሽን ውስጥ ሊገለጥ ለሚገባው አርበኝነት ጥሩ ማሳያ ነው።
በጥቅሉ ፋሽንን የአርበኝነት ስሜት ማንጸባረቂያ አድርጎ መጠቀም ይቻላል። እያንዳንዱ ብሔር የራሱ የሆነ መገለጫ ልብስ እንዳለው ሁሉ ኢትዮጵያም እንደ አገር በዓለም መድረክ መገለጫዋ የሚሆን የአለባበስ ስልት ሊኖራት ይገባል። አልያም ሁላችንም የምናስታውሰው በቅርቡ በኦሎምፒክ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተፈጠረው ዓይነት አሳፋሪ ክስተት ይፈጠራል። በወቅቱ ቡድኑ በመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ አርፍዶ ከመምጣቱ በላይ ለቦታው የሚመጥን እና አገሪቱን መወከል የሚችል አለባበስ ሳይኖረው በቦታው መገኘቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
ያ አጋጣሚ የሚያሳየን በፋሽን እና ሞዴሊንግ ዘርፉ፤ አልባሳትን አገርን እና ለእሷ ያለንን የአርበኝነት ስሜት በሚገልጽ መልኩ ከማዘጋጀት አንጻር ገና ወደኋላ እንደቀረን ነው። ይህን ክፍተት መሙላት አለብን። የአሜሪካ ከተሞች ስሞች የተጻፉባቸው፤ የእኛ ያልሆኑ ሀሳቦች የሰፈሩባቸው፤ በእኛ ፍልስፍና ያልተቃኙ አልባሳትን እየለበስን ኢትዮጵያዊ አርበኝነትን ማምጣት አይቻልም።
ኢትዮጵያዊ አርበኝነትን መፍጠር ካልቻልን ደግሞ የምንመኘውን ከነጮች ጥገኝነት የመላቀቅ መንገድ ልናሳካ አንችልም። ስለዚህም የፋሽን ባለሙያዎች በዚህ ዙሪያ አበክረው ሊሰሩበት ይገባል የሚል መልዕክት ልናስተላልፍ እንወዳለን።
አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2014