እንደ ሕዝብ በየዘመኑ ስለአገራችን ከፍ ያሉ ህልሞችን አልመናል፤ ትውልድ ተሻጋሪ የተስፋ ቃሎችን አምጠናል። እነዚህን ህልሞች ተጨባጭ ተስፋ፤ የተስፋ ቃሎቹን አምጠን ለመውለድ የሄድንባቸው እልህ አስጨራሽ መንገዶች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። ይህም እውነታ እስከዛሬ ድረስ ያልተሻገርነው ትልቁ አገራዊ ተግዳሮት ሆኖብናል።
በአንድ በኩል እንደ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን አለመረዳታችን፤ እነዚሁ ጠላቶቻችን በላያችን ላይ የጫኑብንን እና ያጎበጠንን ሸክም በአግባብ አለመረዳታችን፤ ለመረዳት የሚሆን መነቃቃት እንደ ሕዝብ ፈጥረን መንቀሳቀስ አለመቻላችን በየዘመኑ እየከፈልን ላለነው ያልተገባ ዋጋ ተጠቃሽ ምክንያቶች እንደሆኑ ይታመናል።
በተለይም እንደ ሕዝብ ሕልሞቻችንን እና የተስፋ ቃሎቻችንን የጋራ አድርገን በአንድ መንፈስና ከዚህ በሚመነጭ ቁርጠኝነት እንዳንንቀሳቀስ ጠላቶቻችን በየዘመኑ ባንዳዎችን በማሰለፍ ህልማችንን ሲያመክኑ፤ የተስፋ ቃሎቻችንን አምጠን እንዳንወልድ ሾተላይ ሲ ሆኑብን በስፋት ተስተውሏል።
ዛሬም እንደ አገር ያጋጠመን የህልውና ፈተና ይኸው የባንዳነት ችግር ነው። ይህ ከስግብግነት ስሪት የሚመነጭ አገራዊ እርግማን በየዘመኑ መልኩንና ቋንቋውን እየቀየረ ትውልዶች የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖሩ፤ የተመኙትን እንዳይሆኑ፤ ህልማቸውን እንዳይጨብጡ አድርጓቸዋል።
ከራስ ወዳድነትና ከጥገኛ አስተሳሰብ የሚመነጨው ይህ አገራዊ እርግማን በአሸባሪው ሕወሓት ዘመን የመጨረሻ የሚባለው ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለብዙዎች ግልጽ ነው። አሸባሪው ሕወሓት ለባንዳነት ተልዕኮው ስኬት እስከ ሲኦል መውረድ የሚፈልግ ኃይል ሆኖ ተከስቷል። ይህንንም በአደባባይ ከማወጅ ጀምሮ በተጨባጭ እየተገበረ ይገኛል።
ይህ የመጨረሻ በሚባል ከፍ ባለ የሞራል ዝቅጠት በአሸባሪው ሕወሓት በአገራችን የተከሰተው ባንዳነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢሆን ከዚህ በፊት ስለመከሰቱ እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይደለም። ለዚህ ደግሞ የአስተሳሰቡ ተሸካሚዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት አገር የመምራት ዕድል ተሰጥቷቸው፤ እንደ መንግሥት ራሳቸውን ቆጥረው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸው ነው።
ያስተዳደራትንና እንደ አገር የመራትን አገር እስከ ማፍረስ የሚዘልቀው የቡድኑ የባንዳነት ጥግ በዓለም ተወዳዳሪና አቻ የማይገኝለት እንደሚሆን ይታመናል፤ ለተቀበለው የባንዳነት ተልዕኮ አገርና ሕዝብን እያስከፈለው ያለው ዋጋም በአረመኔያዊ የጭካኔ ተግባር መታጀቡ ልዩ መገለጫው ነው።
ከፍጥረቱ ጀምሮ በባንዳነት የአስተሳሰብ ርግማን ውስጥ የሚቅበዘበዘው ይህ ቡድን በቀደመው ዘመንም ቢሆን በነፃነት ስም የታሪካዊ ጠላቶቻችንን አገርን የመከፋፈልና የማፍረስ ተልዕኮ ተቀብሎ፤ የቱን ያህል መራራ ዋጋ እንዳስከፈለን የአደባባይ ምስጢር ነው።
«ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይተውም» እንደሚባለው ቡድኑን ከፍጥረቱ የተጠናወተው ይህ የአስተሳሰብ ርግማን፤ በዘመኑ ሁሉ እየተከተለው ተቅበዝባዥ አድርጎታል። ከርሱም አልፎ እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ የቀደመ የአገር ወዳድነት ታሪክ እያጠለሸ፤ የገዛ ታሪኩ ጠላት እንዲሆን እያደረገው ይገኛል። ትውልዱንም በውሸት ትርክቶች የማንነት መደበላለቅ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ጨምሮታል።
ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ የዚህ ቡድን የዘመኑ የባንዳነት ተልዕኮ ከፍጥረቱ ጀምሮ አገር ለማፍረስ የሄደበትን ረጅም ርቀት መካስ በሚያስችል ሁኔታ መላውን ሕዝባችንን አንድ የማድረጉ፤ ከዚህም ባለፈ የጋራ ህልሙን እውን ለማድረግ፤ የተስፋ ቃሉን አምጦ ለመውለድ የሚያስችል አንድነት የማምጣቱ እውነታ ነው።
ይህም ከቡድኑ ከፍ ያለ የባንዳነት ተልዕኮ እንደ ሕዝብ ያተረፍነው ታሪካዊ ትሩፋት ነው። በዚህም ቡድኑ ባንዳነትን እንደአስተሳሰብ ቀብረን ለመሄድ የሚያስችለንን አቅም ፈጥሮልናል። ባንዳነት በየትኛውም መልኩ ቢገለጽ የምንጠየፍበትን ማንነት መገንባት የሚያስችል ዕድልም ሰጥቶናል።
ከሁሉም በላይ እንደ ሕዝብ ያለምናቸውን ሕልሞች፤ እንደ አገር የተቀበልናቸውን የተስፋ ቃሎች በጋራ አምጠን ለመውለድ የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም ፈጥሮልናል። የቱንም ያህል ምጡ አስጨናቂ ቢሆንም፤ የምጡ ጊዜ የቱንም ያህል ቢራዘም የፈጠርነው አንድነት የተስፋ ቃላችንን አምጦ ለመውለድ በቂና ከበቂ በላይ ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2014