በንጉሡ የአገዛዝ ዘመን የቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ እየተቀጣጠለ መቀጠሉን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ ሥልጣናቸውን ለቀቁ። ልጅ እንዳልካቸው መኮንንም በጠቅላይ ሚኒስትርነት በንጉሡ ተሾሙ።
በዚሁ ጊዜ የአየር ወለድ ጦር አዛዥ በነበሩት ኮሎኔል የዓለም ዘውድ ተሰማ የሚመሩና የአዲስ አበባና የአካባቢዋን የጦር ክፍሎች እንወክላለን የሚሉ መሥመራዊ መኮንኖችና የበታች ሹሞች «የጦር ኃይሎች ኮሚቴ» የተሰኘ ቡድን ፈጥረው፣ በአራተኛ ክፍለ ጦር ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ ድርጅታቸውን መሠረቱ። ኮሚቴው ሥራውን የጀመረው «አገርና ሕዝብ በድለዋል፤ ፍትሕ አዛብተዋል» የተባሉ የቀድሞ ካቢኔ አባላት በጥበቃ ሥር ሆነው እንዲመረመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልካቸውን በመጠየቅ እንደነበር ሰነዶች ያሳያሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው የወታደሮቹን ጥያቄ መቀበል ውጥረቱን የሚያረግብ ስለመሰላቸው፣ ንጉሡን በማግባባት ለወታደሮቹ አዎንታዊ መልስ እንዲሰጥ አደረጉ። ሚያዝያ 18 ቀን 1966 ዓ.ም ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተ ወልድ እና በቅርብ የተገኙ የቀድሞ ሚኒስትሮች፤ ከንጉሠ ነገሥቱ ፊት እንዲቀርቡ ተደርጎ ለጥቂት ጊዜ በጦሩ ጥበቃ ሥር እንዲቆዩ መወሰኑ፣ በመከላከያ ሚኒስትሩ በጀነራል አቢይ አበበ አማካይነት ተነገራቸውና ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሠፈር ተወሰዱ።
ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ከመላው ሠራዊት በተውጣጡ 109 ወታደሮች ደርግ በአራተኛ ክፍለ ጦር መመሥረቱ ተሰማ። ደርግ የአቶ አክሊሉ ካቢኔ አባላትን ያገኛቸው በጎፋ ሠፈር «በጥበቃ ሥር» ሆነው ነው። ከደርግ ምሥረታ ጀምሮም በጥበቃ ሥር የነበሩ የቀድሞ ባለሥልጣናት አያያዝ እየጠበቀና የታሣሪዎችም ቁጥር እየጨመረ መጣ።
እሥረኞች ከነበሩበት የጎፋ ሠፈር ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሠፈር እንዲዘዋወሩ ተደረገ። በሐምሌ አጋማሽ ላይ የልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ ተሽሮ ልጅ ሚካኤል እምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፤ ራሳቸው ልጅ እንዳልካቸውና የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው እየተያዙ ከነባሮቹ እሥረኞች ጋር ታሰሩ።
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረዳቸውን፣ ሕገ መንግሥቱ መሻሩን፣ ፓርላመንት መዘጋቱን፣ አላግባብ በለጸጉ፣ ፍርድ አጎደሉ፣ አስተዳደር በደሉ የተባሉ የቀድሞ ባለሥልጣናት ሁሉ በጦር ፍርድ ቤት የሚዳኙ መሆኑን ደርግ በአዋጅ አስታወቀ። በዚሁ
ዕለት የንጉሡ የልጅ ልጅ እና የባህር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ተይዘው ከእሥረኞቹ ጋር እንዲቀላቀሉ ሆነ። ንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋናቸው ከወረዱ ወዲህ የሚታሰሩ ባለሥልጣናት እየጨመረ ክፍሎች በእሥረኞች ተጣበቡ።
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የበለጸጉና የባለጉ ካሉ ተጣርቶ እውነት ሆኖ ሲገኝ እንዲከሰሱ 33 ኛ ዓመት ቁ14/326 ግንቦት 8 ቀን 1966 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ወጥቶ ነበር፤ አዋጁ ቢወጣም ባለሥልጣናቱ ተይዘው በእስር ቆዩ ።
ባለሥልጣናቱ የተከሰሱበት ጉዳይ ሳይነገራቸው ክስ ሳይመሠረትባቸው እስከ ኅዳር 1967 ዓ.ም ለስምንት ወራት በእስር ቆዩ። ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የደርግ አባላት እና ንዑስ ደርግ በመባል የሚታወቁ በታላቁ ቤተመንግሥት ተሰበሰቡ። በስብሰባው የደርጉ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ጀነራል አማን አንዶም ግን አልተገኙም።
በባለሥልጣናቱ ላይ አንዳችም ክስ ሳይመሠረትባቸው ደርግ ራሱ ከሳሽ ራሱ ፈራጅ ሆኖ ሥልጣኑን ተጠቅሞ በዚሁ ቀን ኅዳር 14 ቀን 1667ዓ.ም በስብሰባ የግድያ ውሳኔ አሳለፈባቸው። በ60ዎቹም የቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ የግድያ እርምጃው የተወሰደው ከርቸሌ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ጊቢ ውስጥ ሲሆን፣ አስከሬናቸውም እዚያው እንዲቀበር ተደርጎ ዘመድም እንዳይጠይቅ ተከልክሏል።
በእዚህ እርምጃ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ አገረ ገዢዎች የካቢኒ ሚኒስትሮች የጦር ጄኔራሎች ያለፍርድ ውሳኔ ተገደሉ። ‹‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› ሲል የነበረው ደርግ በትረ ሥልጣኑን እንደጨበጠ በደም መጨማለቅ እንደጀመረ ሰነዶች ያሳያሉ።
ግድያውን አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በሚል ገነት አየለ በጻፉት መጽሀፍ ላይ የግድያ እርምጃውን ለመውሰድ አስቀድሞ የተያዘ አጀንዳ እንዳልነበር ኮሎኔል መንግሥቱ ገልጸዋል። ‹‹ማንም አመነም አላመነም እኔ የምናገረው እውነቱን ነው፤ በበኩሌ የተወሰደውን እርምጃ አልደገፍኩትም፤ ሌሎችም የደርግ አባላት በስልሳዎቹ ግድያ ሊጠየቁ አይገባም፤ ምክንያቱም በተቆጡ በተናደዱ የንኡስ ደርግ አባላት ድምጽ ተውጠን በዚያ ውስጥ ተዘፍቀን የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ። እኛ የተነሳንለትና ቆመንለት የነበረው ዓላማ ይሄ አልነበረም። ያንን የመሰለ ውሳኔ ለመወሰን አላሰብንም ነበር።›› ብለዋል።
የዚያን እለት ብቸኛው አጀንዳ የጀነራል አማን ጉዳይ እንደነበረም ጠቅሰው፣ ስለ ኃይለስላሴ መንግሥት ባለሥልጣኖች የሚል ነገር ጨርሶ አልበረም። … ለኃይለስላሴ ሚኒስትሮችና ጀነራሎች ምን ስብሰባ መጥራት ያስፈልጋል፤ መርማሪ ከሚሽኑ ተቋቁሟል። በቃ ይሄ ነው።›› ሲሉ አስታውቀዋል።
በደርግ ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍስሃ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ በሚል መጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ጉባዔውን በሊቀመንበርነት መምራት ብቻ ሳይሆን አጀዳውን አዘጋጅተው አቅርበዋል ሲሉ ጽፈዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፤ ኮሎኔል መንግሥቱ ኅዳር 13 ቀን 1967 ዓ.ም የእስርና የአብዮታዊ ርምጃ ደብዳቤ ጽፈዋል። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ስምና ፊርማ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ በቀድሞ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የተላለፈውን ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ ተግባራዊ ስለማድረግ ይመለከታል በሚል የተጻፈ ነው። በዚህም ደብዳቤ ለ54 ሰዎች መቀበሪያ ጉድጓድ እርምጃው በሚወሰድበት ቦታ በዶዘር እንዲቆፈር ታዟል፤ እርምጃው የሚወሰድባቸው ባለሥልጣናት ዝርዝርም ተለይቷል። ኮሎኔል መንግሥቱ አንዳሉት ሳይሆን በእስረኞቹ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ነው ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ስብሰባ የተካሄደው።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ በመጀመር የካቢኒ ሚኒስትሮች ጠቅላይ ገዥዎች የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረቦች የንጉሡ ባለሥልጣናት ስማቸው ሲጠራ ተሰብሳቢዎቹ በወሬ ወይም ባሉባልታ የሰሙትን እየተናገሩ ድምጽ መስጠቱ ቀጠለ። ሃምሳ ዘጠነኛው ተራ ሲደርስ በቃ የሚል ስለተሰማ ሰብሳቢው ለዛሬ እዚህ ላይ እናበቃለን፤ የቀሩ ካለ ሌላ ጊዜ ይታያል በማለት የድምጽ መስጠት ሂደት ቆመ ሲሉ በመጽሐፋቸው ያትታሉ።
በስብሰባው ደክሟቸው በመሃል ይገደል አይገደል የሚለውን ሲወያዩ የዘመቻ መኮንኑ ሻለቃ ወደ አዳራሽ ገብተው ለተሰብሳቢው ሰላምታ ሰጥተው ጄኔራል አማን እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉ ሪፖርት አቀረቡ። ሰብሳቢው ኮሎኔል መንግሥቱም ከማንም አስተያየት ሳይጠይቁና ሳይጠብቁ በፈቃዳቸው እጃቸውን ከሰጡ ይስጡ ካልሆነ ይደምሰሱ በማለት ትዕዛዝ እንደሰጡ ፍስሐ ደስታ ጠቅሰዋል።
አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ከባድ ተኩስ ስለተሰማ ከጊቢው ታንኮችና ብረት ለበሶች እየወጡ ተኩሱ ወደሚሰማበት አቅጣጫ አመሩ። ታንኮቹ የተነቃነቁት ጄኔራል አማን እጄን አልሰጥም ብለው ሲታኮሱ ሁኔታው ከከበባቸው ጦር በላይ ስለሆነ ተጨማሪ ርዳታ ስለተጠየቀ ነው። በመጨረሻ አንድ ታንክ ቤቱን ደርምሶ ሲገባ ጄኔራሉ ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ ሽጉጣቸውንና ኡዚያቸውን አጠገባቸው አድርገው ራሳቸውን ገድለው ተገኙ ሲል አብዮቱና ትዝታዬ መጽሐፍ ያስረዳል።
በፍርደ ገምድል የአንድ ቀን ስብሰባ ውሳኔ በኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የተገደሉት 59 እሥረኞች ውስጥ ሃምሳ ሁለቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ 5 ወታደሮች እና 2 የደርግ አባላት ይገኙበታል። በመኖሪያ ቤታቸው በዚሁ እለት ሲታኮሱ የተገደሉት ጀነራል አማን አንዶም ሲጨመሩበት የሟቾች ቁጥር 60 ነበሩ።
ኃለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2014