እኛ ኢትዮጵያውያን ውብ ድብልቅ ማንነት ያለን ከቀሪው ዓለም የሚለየን በርካታ ባህላዊ እሴቶች የያዝን ነን። አስተውሎ አገራችንን ለመረዳት የሞከረ ሁሉ በሕዝቦች ሕብረት፣ አመጋገብ፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል፣ የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ አመጋገብና የተለያዩ የኀዘንና የደስታ ጊዜ ሥርዓቶቻችን እጅግ ማራኪና ከእኛ ውጪ በሌላ አገር የማናገኛቸው ናቸው።
የጎዳና ላይ የጥምቀት፣ የጨምበላላ እና ሌሎችም ልዩ ልዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻችን እኛነታችን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ እሴቶቻችን ናቸው። እንደ እድር፣ እቁብና ማሕበር ያሉ እሴቶችም በደስታና በኀዘን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአገር ላይ ችግር ሲያጋጥም አብሮ ለመምከር ፣ አካበቢን ለመጠበቅ እንዲሁም አገርን ለሚከላከል ሠራዊት የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ ለማድረግና ይሄንንም ለማስተባበር ጭምር እያገዙ ናቸው ። አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአገራችን ላይ ጥቃት በከፈተበት በዚህ ወቅትም ባህላዊ እሴቶቻችን ለህልውና ዘመቻው በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
እነዚህን ሀብቶቻችንን ከበርካታ ሺ ዘመናት በላይ ማሕበረሰቡ ሳይበረዙና ሳይጠፉ ጠብቆ ከዘመን ዘመን ለትውልድ ማስተላለፍ ችሏል። በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን ጥቂቶቹን እናንሳ ብንል እንኳን በድምቀት መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የሚያከብሩት የመስቀል ክብረ በዓል “ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች” መካከል ማንሳት እንችላለን። በዚህ ሳንገደብ የጥምቀት በዓል የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል አንዱ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።
ሌላው “የኢሬቻ” ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል ከመላው ዓለም ቱሪስቶች ሊታደሙበት የሚፈልጉት ደማቅ ሥነሥርዓት ነው። የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሒውማኒቲ) መስፈሩ ይፋ የተደረገው ኅዳር 2009 ዓ.ም ነበር። የኦሮሞ ሕዝብ በረጅም ዘመናት ውስጥ ካዳበራቸው የአኗኗር ብልሃቶች እና ሥርዓቶች መካከል አንዱ የገዳ ሥርዓት ነው። የገዳ ሥርዓት በዋናነት የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመምራት የሚረዱ ዕሴቶችን አካትቷል። ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ዋና ምሰሶ የሆነ ሥርዓት ሃይማኖታዊ እና የሕግ ሥርዓቶችን በውስጡ አካቶ ይዟል። በተጨማሪም የገዳ ሥርዓት ከውልደት እስከ ሽምግልና ድረስ በእድሜ በመከፋፈል የተለያዩ የማሕበረሰብ ኃላፊነቶችን እና የሥልጣን ድርሻዎችን ይሰጣል። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ዋቄፈታ እና ኢሬቻ የተሰኙ የዕምነትና ባሕላዊ ሥርዓቶች ይገኙበታል።
አዲሱ መንግሥት በተመሰረተበት እለት የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና አደረጃጀቶችን የመከለስ ሥራ ተሰርቷል። ከዚህ ውስጥ እንደ አዲስ ማሻሻያ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል ደግሞ የባህልና ቱሪዝም የቀድሞው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው። በሂደቱም ለዓመታት ተጣምረው በአንድ አዋጅና ማስፈፀሚያ መመሪያዎች ትግበራ ሲያደርጉ የነበሩት በሁለት ሚኒስቴር መሥሪያቤት ስር እንዲሆኑ ተደርጓል። በዚህም የቱሪዝም ሚኒስቴርና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሚል ለሁለት ተከፍለው የየራሳቸውን ሥልጣንና ተግባራት እንዲወስዱ ተደርጓል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደ ንኡስ ክፍል ይታይና እራሱን የቻለ ሰፊ ትኩረት ይሰጠው ስላልነበር በሚፈለገው መልኩ ባህላዊ እሴቶችን ለመጠበቅ፣ ለማበልፀግ እንዲሁም በሚፈለገው መንገድ ለማስተዋወቅ አልተቻለም ነበር። አሁን ግን መሥሪያቤቶቹ የየራሳቸውን አደረጃጀትና ሥልጣንና ሃላፊነት ቆጥረው በመውሰዳቸው የተሻለ ውጤት ይመዘገባል የሚል እምነት እንዳለ የዘርፉ ባለሙያዎች አንስተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም የነበሩት አሻሽሎ ከማስቀጠል እንዲሁም አዳዲስ አሰራሮችን ዘርግቶ ውጤት ከማምጣት አንፃር ይበል የሚያሰኙ ጅምር ሥራዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል። እነዚህ ተግባራትን በሙሉ አቅም መተግበር የጀመረው በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ መዋቀሩ ይፋ ከተደረገበት እለት አንስቶ ነው። ለመሆኑ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ምን ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክር ። መረጃዎቹን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ አግኝተናል።
የቋንቋ ፖሊሲ
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል የኢትዮጵያውያንን ቋንቋ ማበልፀግ አንዱ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔር ብሐረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎቻቸው በልፅገው ለሁል አቀፍ ልማት ተጠቃሚነት የሚበቁበት ፤ በሕዝቦች መካከል መከባበር ፤ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የጎለበተበት ዴሞክራሲያዊ ሕብረተሰብ ተፈጥሮ ማየትን ራእይ ያደረገው የአገራችን የቋንቋ ፖሊሲ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ መታተሙ ይታወቃል። በፖሊሲውም የአገራችን የሥራ ቋንቋዎች ወደ አምስት እንዳሳደገ ይታወቃል። በመሆኑም በፖሊሲው ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች ለክልል ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተደጋጋሚ እየተሰጠ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።
ከዚህ በተጓዳኝ ፖሊሲው በኦሮሚኛ፤ ሶማልኛ፤ አፋርኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ዝግጅት መጀመሩን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው ይፋ አድርገዋል። በመሆኑም በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ፖሊሲው በሁሉም ቋንቋዎች ደርሶ ለተሻለ እድገት የበኩሉን አስተዋፆ እንደሚያደርግ ይታመናል።
“የመቻቻል” ጥበብ መገንባት
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ካከናወናቸውና አሁንም እየተገበራቸው ከሚገኙ ሁነቶች መካከል በየዓመቱ በኅዳር ወር ላይ የሚከበረውን የዓለም የመቻቻል ቀን አከባበር ነው። ይህን በማስመልከት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ “መቻቻል የሞራል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካዊና የሕግ መስፈርትም ጭምር ነው። መቻቻል በመሰረታዊነት ሰላምን ማውረድ የሚችል በመሆኑ ጦርነትን በሠላም ለመለወጥ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው፤ በተለይም በግጭት ውስጥ የነበሩ የተለያዩ አገራት የመቻቻል ቀንን በማክበር ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ አብሮነታቸውን ያጎለበቱ ወይም በማጎልበት ላይ የሚገኙ ብዙ መሆናቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል። መሥሪያ ቤታቸውም መቻቻል እንዲጎለብት የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በተገቢው ለመወጣት እንደሚሰራ ነው ያሳወቁት።
በአገራችን 12ኛው አገር አቀፍ የመቻቻል ቀን ከኅዳር 16 እስከ 25-2014 ዓ.ም በክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም በየደረጃው በሚገኙ የአስተዳደር እርከኖች በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓቶች “መቻቻል ለሠላም፣ ለአብሮነትና ለጋራ ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ይገኛል። ብዙ ሕዝብን በንቅናቄ ባሳተፈና ወጪን በቆጠበ መልኩ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ከክልል የባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በአዳማ ከተማ ምክክር ተደርጎ ነበር።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24ኛ ጊዜ የተከበረው የመቻቻል ቀን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ያቀረቡት የባህል ዕሴት ቡድን መሪ አቶ ግዛቸው ኪዳኔ ‹‹የመቻቻል ዕሴትን ማጎልበት የተለያዩ ማንነትን፣ ባህልና ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ ሰላማዊ አብሮ የመኖር ግንኙነት ሳይዛነፍ እንዲኖር ያደርጋል›› በማለት አብራርተዋል።
በተጨማሪም ልዩነትን ማስወገጃ፣ የጋራ ዕሴትና አንድነት ማጠናከሪያ የሆነውን የመቻቻል ባህል ማጠናከር የሚጀምረው ብዝኅነትን ከመቀበል ነው። ብዙ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች በአገራችን መኖራቸው የአንድነታችን ጥንካሬ ማሳያ መሆኑን አሳይተዋል።
የምክክር መድረኩን የመሩት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ ‹‹መቻቻል የመልካም ግንኙነት እና ጉርብትና መፍጠሪያ ጥበብ ነው። የበለፀገ ማኅበረሰብ እና ኢኮኖሚ የሚኖረው መቻቻል መሠረት ሲሆን ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ወደድንም ጠላንም አገር የሆነው ብዝኀ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ታሪክ ይዘን መቻቻልንም ማዕከላዊ ማስተሳሰሪያችን አድርገን ነው። የአንድነታችን ጥንካሬ የልዩነታችን ውበት ጎልቶ የሚወጣውና ለዓለም ተምሳሌት የምንሆነው በፈተና የፀና የማቻቻል ባህል ሲኖረን ነውና ዕለቱን ተናበንና ተመካክረን ማክበር አለብን›› ብለዋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ሙሐመድ በበኩላቸው ‹‹አሁን በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እኔን ብቻ ቻሉኝ፣ እኔን ብቻ ስሙኝ፣ እኔ ብቻ አዋቂ ነኝ፣ ካለኔ ምንም አይሆንም በሚል የትህነግ ግትር ሃሳብ የተወለደ ነው። የተጠናከረ የመቻቻል ባህል መኖር የጋራ መተማመን ተፈጥሮ በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ እኩል ኃላፊነት እንዲሰማን ያደርጋልና አጠናክረን ልናከብረው ይገባል›› ብለዋል።
የሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ሌላኛው ሃላፊ አቶ አካሉ አስፋው በበኩላቸው ‹‹በአገራችን የመቻቻል ባህል የተመናመነበት ምክንያት የብሔርና የሃይማኖት ቅራኔ በመስፋፋቱና የተጠና የፖለቲካና የማኅበረሰብ ሽግግር አለማድረጋችን ሲሆን የተሳሳተ የታሪክ ትርክትም የራሱን ጥቁር ነጥብ አኑሯል። የመቻቻል ዕለቱን ማክበር እንድንከባበርና እንድንደማመጥ እንዲሁም እርስ በርሳችን የበለጠ እንድንተዋወቅ ዕድል ስለሚፈጥር ትኩረት ሰጥተን እናከብረዋለን›› ብለዋል።
እነዚህ በክብረ በዓሉ ላይ የተነገሩ መልእክቶችና ተግባራት በቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስፋት በዚህ መሰል አብሮነትን በሚያጠነክሩ ባህላዊ እና ዓለምአቀፋዊ እሴቶች ላይ እንደሚያተኩር የሚያመላክቱ ናቸው።
ሥልጣንና ተግባራት
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከክልል ቢሮ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አድርጎ ነበር። በዚህም በአዋጅ 1263/2014 ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት ላይ ተወያይቷል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ጉዳዩን አስመልክተው ሲገልጹ፤ ‹‹የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም አብሮ የነበረና በተለያዩ ጊዜያት በአዋጅ ተለያይቶ እንደገና የተገናኘ ተቋም ነው። በዋናነት የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር በስፖርት የጎለበተ ጤናማ ማኅበረሰብን መፍጠርና የአገርን ገፅታ መገንባት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ነው›› ብለዋል።
አሁን የተቋቋመበት አዋጅ ከዚህ ቀደም የነበሩትን የሕግ ክፍተቶች መሙላት በሚያስችል ደረጃ ተቆጥሮ የተሰጠ በመሆኑ የወል ተግባራትን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል። የዘርፉ ምሁራንም ይህን ጉዳይ አጥብቀው እየደገፉት ይገኛሉ።
የባህል ዕሴት፣ ቋንቋ፣ ትርጉም፣ የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ እና የፈጠራ ሥራዎች ልማትን ማጥናት፣ መጠበቅና ማልማት ላይ የሚያተኩሩ ስምንት ተግባራት እንዲሁም የማስ ስፖርት፣ የማዘውተሪያ ስፍራ፣ ሥልጠናና ውድድርን ማስፋፋትና ማጠናከር ላይ የሚያተኩሩ ስምንት እንዲሁም ሁለት የጋራ ተግባራት በአጠቃላይ 18 የዘርፍ ተኮር ተግባራት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ 1263 ተሰጥቶታል ሲሉ የሕግ ክፍል ዳይሬክተሩ አቶ በላቸው ድሪባ ገልጸዋል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በቀጣይ 100 ቀናት የሚከወናወኑ ዋና ዋና ተግባርትም በሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ ቀርቦና ውይይት ተካሂዶበት የሥራ ስምሪት ተሰጥቶበታል። ዘርፉም የአደረጃጀት ማሻሻያ ከማድረጉና ልዩ ትኩረት ከማግኘቱ አንፃር በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ባህላዊ እሴቶችን የማበልፀግ፣ የመጠበቅና በተገቢው መንገድ የማስተዋወቅ ትግበራው ውጤታማና ተስፋ ሰጪ እንደሚሆን ይታመናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 19/2014