አገራችን የአገር ውስጥ ከሀዲ ጠላቶቻችንና ታሪካዊ የቅርብና የሩቅ የውጭ ጠላቶቻችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ተቀናጅተው የከፈቱባትን ጦርነት እየመከተች ትገኛለች፡፡ ከሀዲው ሕወሓትና ተባባሪዎቹ የከፈቱትን ይህን ጦርነት በመከላከያ፣ በልዩ ሀይሎች ፣ በፋኖና በሚሊሺያዎች ለመመከት ርብርብ እየተደረገ ነው፤ ጦርነቱ የመላውን ህዝብ ሰፊ ተሳትፎ የሚፈልግ መሆኑ ታምኖበትም ህዝቡን በማነቃነቅ ርብርቡ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የህልውና ዘመቻው በሁሉም አቅጣጫ እየተካሄደና በርካታ ድሎችም እየተመዘገቡ ባሉበት ወቅት ነው እንግዲህ የህልውና ዘመቻውን በቅርበት ለመምራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም መከላከያን ለመምራት ወደ ግንባር የዘመቱት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ጦር ኃይሎች አዛዥነታቸው መከላከያን በበላይነት መምራታቸው እንዳለ ሆኖ ነው ሰራዊቱን ግንባር ላይ ሆነው በቅርበት ለመምራት በመወሰን ነው የዘመቱት፡፡ በአገራችን ላይ የተከፈተውን የተቀናጀ ጦርነት በድል ለመወጣት ከተለመደው አካሄድ ወጣ ያለ መንገድ መሄድን ይጠይቃልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ትክክለኛ፣ ታሪካዊና ወቅታዊም ነው፡፡
ከሀዲውና አሸባሪው ሕወሓት ህጻናትን፣ አዛውንቶችን፣ አካል ጉዳተኞችንና እናቶችን ጭምር ለጦርነት ከፊት እያሰለፈ ባለበት ሁኔታ በመከላከያ ሰራዊት ብቻ የቡድኑን የጥፋት ተልእኮ ማሳካት እንደማይቻል በመንግሥት ታምኖበት መላ ህዝቡ በዘመቻው እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻውን መቀላቀላቸው ከዚህ የሚበልጥ ምንም አይነት አገራዊ ተልዕኮ እንደሌለ አመላክቷል፡፡
ይህንን የሽብር ቡድን ማሸነፍ እንደሚቻል ያለፉት የጦር ግንባር ድሎች ያመለክታሉ፡፡ በህልውና ዘመቻው የትህነግና ተባባሪዎቹን ቅዠት ለማምከን በተካሄዱ የጦር ግንባር ውሎዎች ትህነግ በወረራቸው የአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም አፋር ክልል ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንዲደርስበት በማድረግ በኃይል ወደ ቀድሞ ስልጣኑ ለመመለስ የነበረውን ምኞት ቅዠት ማድረግ ተችሏል፡፡ ቡድኑ ቀደም ሲልም በህግ ማስከበር ዘመቻው አከርካሪው ተሰብሮ ዋሻ ውስጥ ተቀርቅሮ የቀረም ነበር፡፡ መላ ህዝቡን ባሳተፈው ጦርነት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንባር ላይ አመራር ሲታከልበት የጦርነቱን ድል ማፋጠን ይቻላል፡፡
ይህን አሸባሪ ቡድን ጨርሶ መደምሰስ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ኃይሎችም ይህ ቡድን እስከ አለ ድረስ አርፈው እንደማይቀመጡና ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንደማያነሱ ከእስከ አሁኑ ሁኔታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ መንግሥት ይህን ቡድን ለማጥፋት የያዘውን ቁርጠኛ አቋም እና እያካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻ በአጭር ጊዜና በውጤታማ መልኩ ለማሳካት
የጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ተገኝቶ አመራር መስጠት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡
በዓድዋ አጼ ምኒልክና ጣይቱ ጦሩ መሀል ተገኝተው የፈጸሙት ጀብድና በወራሪው የጣልያን ሰራዊት ላይ የተቀዳጁት ድል የሚያስገነዝበውም ይህንኑ ነው፤ ጦርነቱን የገጠምነው ከትህነግ ጋር ሊመስል ቢችልም፣ ጦርነቱ ግን እየተካሄደ ያለው ከውጭ ሀይሎች ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪዎችን ምኞት መና ለማስቀረት ካካሄደቻቸው ጦርነቶች መረዳት የሚቻለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡
ቡድኑ አገሪቱ ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖራት አጥብቀው ከሚሰሩት አሜሪካን ጨምሮ ከምእራባውያን ጋር በግልጽ የተሰለፈ ነው፡፡ ከታሪካዊ ጠላታችን ግብጽና አሻንጉሊቷ ሱዳን ጋር ተሰልፎ አገሩን እየወጋ ያለ ቡድንም ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ጠላት አገርን ሲደፍር ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ መሪያቸውም ተቆጥቶ ጦሩን እንደሚቀላቀል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እንደ አንድ ታሪካዊ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ቡድኑን ጨርሶ ለማጥፋት የመላ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ተሳትፎ፣ የጸጥታ ሀይሎች መስዋእትነት ወሳኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ጦርነቱን በግንባር ሆኖ የሚመራ የአገር መሪ ሲገኝ ለጦሩ ታላቅ ወኔን የሚያላብስ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከመሪያቸው ጎን እንዲሰለፉ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
ደግሞ ድሉ ምን ያህል ፈጣንና ጣፋጭ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ቡድን የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ እንዳይቀጥል፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሰፈሰፉ የውጭ ሀይሎችም የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ቅሌት ዳግም እንዲሸከሙ ለማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰራዊቱ ቆራጥ አመራር ለመስጠት ወደ ግንባር መሄዳቸው ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፤ ጦርነቱንም በብልሃት፣ በቆራጥነት በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በህልውና ዘመቻው ግንባር ላይ የተሰለፉ የመከላከያ፣ የልዩ ኃይሎችና የፋኖ አባላት በሙሉ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር የጀግንነት ገድል እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ አሁን ደግሞ በሌላ ታሪካዊ ወቅት ላይ ተገኝተዋል። የሀገራችን መሪና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መከላከያን በቅርበት ለመምራት ከአጠገባቸው በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ተገኝተዋልና ደስ ሊላቸው ይገባል፡፡ ይህ ሁሌም ሊገኝ የማይችል በዚህ ዘመን እናንተ ብቻ ያገኛችሁት ታላቅ ዕድል ነውና፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦር ኃይሎች አዛዥነታቸው ፊትም ከእናንተው ጋር ቢሆኑም አሁን ደግሞ ይበልጥ አጠገባችሁ ሆነዋል፡፡ ድላችሁን በቅርበት ይመለከታሉ፤ ችግራችሁን በቅርበት ይረዳሉ፤ ለላቀ ሌላ ድል እንድትዘጋጁና እንድታስመዘግቡም ትልቅ አቅም ይሆኗችኋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አንድ ግንባር ላይ አብረን ነበርን ብላችሁ በኩራት የምትናገሩበትን ታሪካዊ አጋጣሚ አግኝታችኋል፡፡ እናንተ ያሰባችሁትን በማሰብና እናንተ የምትፈጽሙትን አብሮ በመፈጸም መሪያችሁ ትግሉን ለመፈጸም አጠገባችሁ ተገኝተዋልና ለድሉ ይበልጥ ልትተጉ ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለታላቅ አገራዊ ተልእኮ ነው አብረዋችሁ የሆኑት፡፡ ይህን ታላቅ አገራዊ ተልእኮ በማሳካት የታሰበውን ድል በፍጥነት በማምጣት ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ የፈለጉ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎችን ከንቱ ምኞት በማምከን አሁንም የኢትዮጵያን አሸናፊነት አረጋግጡ!
አዲስ ዘመን ህዳር 19 ቀን 2014 ዓ.ም