ተከሳሹ ከፖሊሱ ጠረጴዛ ፊት ለፊት ካለው ወንበር ተቀምጦ ጥያቄዎችን ይመልሳል።አሁንም ማስረጃ በቀረበበት ጉዳይ ላይ ክዶ እየተከራከረ ነው።ከሰዓታት በፊት የሕክምና ቀጠሮ ነበረው።በተከሰሰበት የነፍስ ማጥፋት ወንጀልም ችሎት ሲመላለስ ወራት ተቆጥረዋል።
ኪሮስ ኃይሌና እሱን መሰል ተከሳሾች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስካልተባሉ እንደወንጀለኛ አይቆጠሩም።ጉዳያቸው በሕግ ፊት በእኩል ይታያል።ፖሊስ ጣቢያ አልያም ማረሚያ ቤት መሄዳቸው ብቻ ወንጀለኞች አያደርጋቸውም። ያም ቢሆን ሁሌም ከጥርጣሬ ዓይኖች ይወድቃሉ።
በቀጠሮ ቀን ከማረሚያ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ከእጃቸው ካቴና አይታጣም።የሕክምና ቀጠሮ ካላቸውም እውነታው ተመሳሳይ ነው።ከጀርባቸው መሳሪያ ያነገቱ ንቁና ጠንቃቃ ፖሊሶች ይከተሏቸዋል።የፖሊሶቹ ዓይኖች መቼም ማንንም አምነው አያውቁም።ከቅርብና ከሩቅ የሚያዩትን ሁሉ በጥርጣሬ እየቃኙ እስረኞቻቸውን ይከታተላሉ።
ኪሮስ የፍርድ ቤት ቀጠሮ በተያዘለት ቀን በፖሊሶች ታጅቦ ይጓዛል።ችሎት በቀረበ ጊዜ በግፍ ፈጽሞታል የተባለውን ወንጀል ማስተባበል ልማዱ ነው።ስለሆነው ሁሉ የዓይን እማኞች ቀርበው መስክረዋል ፤የሕክምና ማስረጃዎች አረጋግጠዋል።የእሱ አቋም ግን ፈጽሞ አልተለወጠም።ግድያውን አልፈጸምኩም፣ አላደረኩትም ሲል ‹‹ዓይኔን ግንባር ያርገው›› ብሏል።
ኪሮስ አሁን በሕግ ፊት ለጥያቄ የቀረበበት ምክንያት የግድያው ክስ አይደለም።ከደቂቃዎች በፊት ከፖሊሶች እጅ ለማምለጥ ያደረገው ሙከራ እያስጠየቀው ነው።ተከሳሹ ፈጽሞታል በተባለው የግድያ ወንጀል ተከሶ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ቆይቷል።በስፍራው በነበረበት አጋጣሚ ሕመም ላይ መሆኑን አሳውቆም ሕክምና እንዲያገኝ ተፈቅዶለታል።
ኪሮስ ሚያዚያ 6 ቀን 2012 ዓም ማለዳ በፖሊሶች ታጅቦ ወደ ሕክምናው አምርቷል።ከራስ ደስታ ሆስፒታል ደርሶም ተገቢውን ሕክምና አጠናቋል።ጉዳዩን እንደጨረሰ ሁለት ፖሊሶች የእጁን ካቴና መኖር አረጋግጠው ወደነበረበት ማረፊያ ለመመለስ ጉዞ ጀምረዋል።
ፖሊሶች የሕግ ታራሚን መያዛቸው በተለየ ንቁ አድርጓቸዋል።ሰውዬው ከሌሎች እንዳይቀርብ፣ ሌሎችም ከእሱ እንዳይጠጉ በተለመደው ጥንቃቄ ይራመዳሉ። ኪሮስ ዙሪያ ገባውን እየቃኘ አዕምሮውን ያሰራል። በወንጀል ተጠያቂ ሆኖ ለእስር መዳረጉ ያሳሰበው ይመስላል።በውሳኔው ስንት ዓመት እንደሚፈረድበት እርግጠኛ አይደለም ።
ኪሮስ ሁሌም እንዲህ ባሰበ ጊዜ ተስፋ ይቆርጣል። ይናደዳል፣ በየምክንያቱ ይበሳጫል። እየተራመደ የእጁን ካቴና ደጋግሞ አስተዋለው። አንዳች ስሜት ብልጭ ሲል ታወቀው።ካቴናው በቀላሉ እንደሚፈታ ገብቶታል። በውስጡ እየሳቀ፣ አመቺ ሁኔታን ጠበቀ።
የሕግ እስረኛ መሆኑ አልጠፋውም።በአጋጣሚው ተጠቅሞ ማምለጥ ቢችል ግን ታሪክ እንደሚለወጥ ያውቃል።ለአፍታ ውል ያለውን ሀሳብ ዕውን ማድረግ አሰኘው።አሁንም ዙሪያውን ቃኝቶ የአጃቢ ፖሊሶቹን ገጽታ አስተዋለ።ንቃት፣ ቅልጥፍናቸው እንዳለ ነው።
ኪሮስ ከፖሊሶቹ እጅ ቢያመልጥ የሚከፍሉትን ዋጋ አሳምሮ ያውቃል።ለእሱ ምንም ቢሆኑ ደንታው አይደለም።አሁን ዓላማና እቅዱ አንድና አንድ ሆኗል። እንደምንም ከእነሱ አምልጦ ከአካባቢው መሰወር። ሕይወትን ከሥሩ ጀምሮ የሆነውን መርሳት። ዳግም ካቴናውን ነካክቶ አቅሙን ፈተሸው። ዕድል እንዳለው ሲያውቅ ያሰበውን ሊያደርገው ቆረጠ።
አሁን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሆኗል።የቀትር ጸሐይ ‹‹አናት ትበሳለች›› እንዲሏት ሆና አምርራለች።ግለት ቃጠሎዋ መንገደኛውን እያራደ ነው።ኪሮስና ፖሊሶቹ አራዳ ክፍለ ከተማ ጌጅ ኮሌጅ አካባቢ ደርሰዋል።የኪሮስ አዕምሮ አሁንም በፍጥነት ያስባል።የፖሊሶቹ ጠንቃቃ ዓይኖች ከእሱ አልተነቀሉም።
ኪሮስ ድንገት ከመሐላቸው አፈትልኮ ሩጫውን ቀጠለ። ፈጣኖቹ ፖሊሶች ከእሱ ሩጫ ልቀው ከጀርባው ተከተሉት።ፊትና ኋላ ሆነው በአጭር ርቀት ተከታተሉ።በአካባቢው ተኩስ መሰማቱ ጥቂት ግርግር ፈጠረ ።
አጋጣሚውን ተጠቅሞ መሹለክ የሞከረው እስረኛ አልተሳካላትም ።ርቆ ሳይርቅ ከፖሊሶች መዳፍ ወደቀ። በቁጥጥር ስር ሲውል በእጆቹ የገባው ካቴና በስልት መፈታቱ ተረጋገጠ።
ኪሮስ በሁለቱ ፖሊሶች እማኝነት የቀረበበትን ክስ ማስተባበሉን ቀጥሏል።መርማሪው ለዐቃቤ ህግ ክስ የሚያበቃውን በቂ ማስረጃ ሰንዶ እንዳበቃ የሰጠውን ቃል በፊርማው እንዲያረጋግጥ ሰነዱን አስጠጋለት።በተጠረጠረበት የማምለጥ ሙከራ ክስ ተጠያቂ ያለመሆኑን የሚገልጸው የተከሳሹ ቃል በጉልህ ተነበበ።
ቅድመ-ታሪክ…
ኪሮስ ኃይሌ ተወልዶ ያደገው በትግራይ ክልል ነው።የልጅነት ዕድሜውን በትምህርትና ወላጆቹን በመርዳት አሳልፏል።ኪሮስ ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር የትምህርት ዕድል አላጣም።ከአካባቢው ከሚገኝ ትምህርት ቤት ገብቶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ያለማቋረጥ ተምሯል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲቀጥል ኪሮስ በዕድሜው ከፍ ብሎ ነበር።ይህ ወቅት ለእሱና ለእኩዮቹ የጉርምስና ጊዜያቸው ነው።በትንሽ ትልቁ የሚቆጡበት፣ በየምክንያቱ ጠብና ዱላን የሚሽቱበት ፈታኝ የአፍላነት ዕድሜ።
ኪሮስ ዘጠነኛ ክፍልን አልፎ ወደ አስረኛ ተሻግሯል።በያዘው ዓመት ጠንክሮ ከተማረ ለተከታዮቹ ጊዜያት መሠረት ይጥላል።ካሰበው ለመድረስ በርትቶ ማጥናት፣ ይኖርበታል።ይህ ይሆን ዘንድ ለትምህርቱ ጊዜ መስጠት፣ ከጨዋታው መቀነስ ግድ ይለዋል።
አሁንም ያለበት የጉርምስና ዕድሜ ይፈትነው ይዟል። ከእኩዮቹ ከመምህራንና ከሌሎችም እየተስማማ አይደለም። ይህ ዓመሉም ከዓይን አስገብቶታል።አስረኛን ክፍል ማጋመስ እንደያዘ ድንገት የሕይወት መስመሩን የሚያስቀይር ክፉ አጋጣሚ ተፈጠረ ።ተማሪው ኪሮስ ከመምህሩ ባይግባባ ግጭት ተፈጠረ ።ጉዳዩ ቀላል አልሆነም።የትምህርቱ ጉዳይ ጫፍ ሳይደርሰ መሰናክል ሆነበት።በዚሁ ምክንያት ብዙ ያሰበበት ትምህርቱ በዋዛ ተቋረጠ።
ባልንጀሮቹ ካሰቡት ሲዘልቁ እሱ ደብተሩን ዘግቶ ከቤት መዋል ጀመረ።እንዲህ መሆኑ አላዋጣውም።ጥቂት ጊዜያትን ከወላጆቹ እንዳሳለፈ አርቆ ማሰብ ጀመረ።የሀሳቡ ዳርቻ በአጭሩ አልተገታም።ከሩቅ የሚያደርሰው፣ከሰፈር ቀዬው የሚያርቀው ሆነ።አዲስ አበባ ገብቶ ሥራ መያዝ፣ ገንዘብ መቁጠር ዕቅዱ ቢሆን ፈጥኖ ጓዙን ሸከፈ።
ኪሮስ አዲስ አበባ ሲዘልቅ ብዙ አልተቸገረም። ከከተማዋ ጋር በቀላሉ ተግባቡ።በስፍራው አብሮ አደግ ጓደኛው መኖሩ እንግድነት ሳይሰማው ወደሥራ እንዲገባ አገዘው።ኪሮስ መዋያውን ሳሪስ አደይ አበባ አድርጎ መተዳደሪያውን አማረጠ።
አካባቢው የንግድ ሥፍራ መሆኑ ምርጫውን አሰፋለት።ያሻውን ለይቶ ከእንጀራው እንዲገናኝ ምክንያት ሆኖም ሥራውን ጀመረ።
አሁን ኪሮስና ባልንጀራው ጥሩ ነጋዴዎች ሆነዋል።ከመርካቶ የሚያመጡትን ልብስ ደንበኞቻቸው ይገዟቸዋል።ከእጃቸው ያለው ሲጣራም የተሻለውን ገዝተው አትርፈው ይሸጣሉ።
ልብሶቹን ዞረው ለመሸጥ ዘዴና ብልሀት ይጠይቃል።ገበያ ለመሳብ ደንበኞችን ለመማረክ መፍጠን መቀላጠፍ የግድ ነው።ባልንጀሮቹም ቢሆኑ ከሌሎች ልቆ ለመታየት ብዙ ሲጥሩ ይውላሉ።ኪሮስ ብቸኝነቱን የምታስረሳው አጋር ካገኘ ወዲህ ደስተኛ የሆነ ይመስላል።ከእሷ ጋር ፤አብረው መኖራቸው የወደፊቱን ሕይወት እንዲያቅዱ፣በፍቅር እንዲተሳሰቡ ምክንያት ሆኗል።
አንዳንዴ ኪሮስና ጓደኛው ከሥራ መልስ በመዝናናት ያሳልፋሉ። መጠጥ እየተጎነጩ፣ፑል እየተጫወቱ፣ ጊዜን መግፋት ልምዳቸው ሆኗል።የፑል ጨዋታው ከበርካቶች ያገናኛል። በመዝናናቱ የሚሳተፉ፣ በጨዋታው የሚታደሙ ብዙዎች በእኩል ይጋሩታል።
ኪሮስ ብዙ ጊዜ ጨዋታው ላይ ትዕግስት የለውም። ተራን ሰበብ አድርጎ ከአንዳንዶች ይጋጫል። መታገስ የሚያውቁ ብዙዎች በዝምታ ያልፉታል። እንደሱ ችኩል የሆኑ ጥቂቶች የጠብ ዱላ ለማንሳት ይጣደፋሉ። እንዲህ መሆኑን የለመዱት ደግሞ ትዝብትና ዝምታ መለያቸው ነው።
ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም
በዚህ ቀን ኪሮስና ባልንጀሮቹ ከአንድ መዝናኛ ስፍራ ተገኝተዋል።ጥቂት እንደቆዩ ግቢው ውስጥ ከሚገኝ የፑል መጫወቻ ታደሙ።ጨዋታው ቀጥሎ ዙሩ ሲጠናቀቅ መጫወት የፈለጉ ተረኞች ፍላጎት አሳዩ።ከነዚህ መሐል ኪሮስና አንድ ሰው በእኩል ተገናኙ።ሁለቱም መጫወት ፈልገዋል።
ከሰውዬው ቀድሞ ወደመጫወቻ ጠረጴዛው የቀረበው ኪሮስ ዕድሉን መስጠት አልፈለገም።ተራው የእሱ መሆኑን በመናገር ጊዜውን መጠቀም ፈለገ።ይህን ያስተዋለው ሰው መቅደም የሚገባው እሱ እንደሆነ ሊያስረዳው ሞከረ።ሁለቱም በንግግር አልተግባቡም።ተከራከሩ፣ወደጓሮ ዞር ብለው ብዙ ተጨቃጨቁ።አሁንም አልተግባቡም።ይህ አጋጣሚ ያልተመቸው ኪሮስ በውስጡ ቂም እንደያዘ ከአካባቢው ራቀ።
አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሆኗል።የሬስቶራንቱ ግቢ ጥቂት ደንበኞች መዝናናታቸውን ቀጥለዋል።ኪሮስና ባልንጀሮቹ ከአንድ ጠረጴዛ ከበው መጠጥ እየተጎነጩ ነው። ከእነሱ ጋር ባለቤቱ ተቀምጣለች።የኪሮስ ዓይን ከአንድ ስፍራ እያጮለቀ ማየቱን ቀጥሏል።እነሱ ካሉበት ተቃራኒ አቅጣጫ አንድ ሰው መኖሩን ያስተዋለው ኪሮስ ጥርሱን እየነከሰ እጁን በእጁ ያማታል።ሰውዬው ቀን በፑል ጨዋታ ላይ የተጋጨው የሬስቶራንቱ ደንበኛ ነው።ገና እንዳየው ፊቱ መለ ዋወጥ ጀምሯል።
ሰውየው ወደቤቱ ለመሄድ ያሰበ ይመስላል። ያስቀዳውን መጠጥ ጨልጦ የተጠየቀውን ሂሳብ ከፍሎ ከወንበሩ ተነሳ። ይህን ያየው ኪሮስ እጁን ወደ ጀርባው እየሰደደ የያዘው ጩቤ በስፍራው መኖሩን አረጋገጠ።ሰውየው ተነስቶ መንገድ እንደጀመረ ከነበረበት ፈጥኖ ተነሳ።የሚፈልገው ሰው ከግቢው እየወጣ መሆኑን አውቋል።ፈጠን እያለ ተከተለው።
ሁኔታው ያላማረው የኪሮስ ባልንጀራ ቀልጠፍ ብሎ እጁን ያዘና ከመንገዱ እንዲመለስ ጠየቀው።ኪሮስ በጓደኛው ድርጊት በሸቀ።‹‹ተው›› እያለ መለመኑ ከልብ አበሳጨው። እጁን መነጨቀና ሰውዬው ላይ ፈጥኖ ደረሰበት። ጊዜ አልሰጠውም። ከጀርባው የያዘውን ጩቤ አውጥቶ ያሯሩጠው ያዘ። ሰውየው አመጣጡን እንዳየ ራሱን ለማዳን ሞከረ። ማምለጥ አልቻለም።ኪሮስ አጠገቡ ደርሶ አንገቱን አነቀው። ሰውዬው የእሱን አንገትና ኮሌታ ይዞ ጥቂት ታገሉ።
ጓደኛውን ጨምሮ በሰፍራው የነበሩ ለግልግል ተነሱ።ያሰቡትን ከማድረጋቸው በፊት ግን የኪሮስ እጅ ቀደመ። የያዘውን ጩቤ አውጥቶ ወደጠበኛው ሰነዘረ። ስለቱ አቅጣጫውን አልሳተም።ጀርባውን፣ ጎኑንና እጁን ክፉኛ ወጋው።ሰውየው ጉዳቱን መቋቋም አልቻለም። በደም ተነክሮ ከመሬት ተዘረረ።
ኪሮስ ይህን እንዳየ ከግቢው ሮጦ ወጣ ።ልብሱ በላዩ ተቀዶ ነበር ። ደጅ ከቆመው ባጃጅ እየተጣደፈ ሲገባ ሚስቱ ፈጥና ተከተለችው። ወዲያው ለባለ ባጃጁ ትዕዛዝ አስተላለፈ።ሾፌሩ የተባለውን ለመፈጸም አቅጣጫውን ወደ ሃያ ሁለት ጎላጎል አድርጎ ፈጠነ ።ወንጀል የፈጸመበትን ጩቤ አልጣለውም።ባለ ባጃጁ ከደቂቃዎች በፊት ስለተፈጸመው ድርጊት ጠንቅቆ ያውቃል ።ኪሮስ ሰፈሩ ሲደርስ ጩቤውን እንደያዘው መውረዱንም አስተውሏል።
የፖሊስ ምርመራ …
ምሽቱን ጥቆማ ደርሶት ከሬስቶራንቱ ግቢ የደረሰው የፖሊስ ቡድን ከስፍራው ያገኘው የሟችን አስከሬን ነበር።አካባቢውን በጥንቃቄ ከቦ ምርመራውን እንዳጠናቀቅ የሟችን በድን ሆስፒታል ሸኝቶ ምርመራውን ቀጠለ።በዕለቱ የደረሰው የተጠርጣሪነት ጥቆማ ወደ ኪሮስ ሀይሌ የሚያደላ ነበር።
ፖሊስ ያገኛቸውን ጥቆማዎች በማስረጃ አስደግፎ ተጠርጣሪውን ከእጁ አስገባ።ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉትንም ለጥያቄ ጠራ።ሰዎቹ ‹‹አይተናል፣ ሰምተናል›› ያሉትን ሁሉ ተናገሩ።መርማሪው ዋና ኢንስፔክተር ወንደሰን አሕመድ ያገኛቸውን መረጃዎች በዶሴው አስፍሮ ተጠርጣሪውን ስለወንጀሉ እንዲያስረዳው ጠየቀ።
ተጠርጣሪው ኪሮስ ሀይሌ ተፈጽሟል ስለተባለው የግድያ ወንጀል አንዳች የሚያውቀው ጉዳይ እንደሌለ ተናገረ።በወቅቱ ከጓደኞቹ ጋር በቦታው አምሽቶ በጊዜ መመለሱንና ተጠያቂ ሊሆን እንደማይገባ በእርግጠኝነት ተናገረ።ፖሊሱ ያያዛቸውን መረጃዎች በማስረጃዎች በማስደገፍ ክስ እንዲመሰረት ወደ ዐቃቤ ህግ አስተላለፈ።
ውሳኔ…
ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሽ ኪሮስ ኃይሌ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮው ተገኝቷል፡፡ በተከሳሹ ላይ የቀረበውን የነፍስ ማጥፋት የወንጀል ክስ በተገቢው የሰውና የሕክምና ማስረጃዎች አያይዞም ጥፋተኛ ስለመሆኑ አረጋግጧል፡፡
በዕለቱ በሰጠው የፍርድ ውሳኔም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በመወሰን መዝገቡን ዘግቷል፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014