የተወለዱትና ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ራስደስታ ሆስፒታል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው::የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ልዑል መኮንን ትምህርት ተከታትለዋል::አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካልና ኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል ገብተው ለሁለት ዓመት ከተማሩ በኋላ ግን በወቅቱ የነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄ ትደግፋለህ በሚል በመታሰራቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ::ከስድስት ወር የወህኒ ቤት ቆይታ በኋላ በምህረት ሲፈቱ ፈረንሳይ ሃገር በመሄድ በፓሪስ ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ገብተው የጀመሩትን ትምህርት ቀጠሉበት::ሆኖም ልክ መመረቂያቸው ላይ ሲደርሱ የመንግስት ለውጥ በመምጣቱና አብዮቱ በመፈንዳቱ ሀገር ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ:: የዛሬው የዘመን እንግዳችን በአብዮቱ ከመሳተፍም በላይ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ድርጅት አባል ሆነው በድርጅቱ ስር ይታተም በነበረው ‹‹አዲስ ፋና›› የተሰኘውን ህጋዊ መፅሔት ዋና አዘጋጅ በመሆን አገለገሉ::
የመኢሶን ታክቲክና ማፈግፈግ ሳይሳካ ቀርቶ የድርጅቱ በርካታ አባላት በደርግ እጅ የወደቁበት ሰዓት እንግዳችን የዚሁ ፅዋ ቀማሽ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ:: በወህኒ ቤትም በነበራቸው ቆይታ በደረሰባቸው ድብደባና እንግልት ለከፍተኛ የጤና ችግር ተዳርገውም ነበር::ከአምስት ዓመታት እሥራት በኋላ ወደ ስዊዲን በመሄድ ጤንነታቸውን ከማስመለሳቸውም ባሻገር ስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ በመግባት በአንትሮፖሎጂ (Antropology) የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መስራት ችለዋል:: በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በተማሩበት የሙያ መስክ ለአስር ዓመታት ያህል በመምህርነት አገልግለዋል::ለዶክትሬት ዲግሪያቸው የምርምር ስራ በሰሩበት ታይላንድ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት አማካሪ በመሆንም ሰርተዋል::በታይላንድ በቆዩበት ጊዜም በሀገሪቱ ድህነትን ለመቅረፍ፤ የምግብ አቅርቦትንና ተገበያይነትን አስተማማኝ ለማድረግ ብሎም ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ክብካቤ ግጭትን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ሊጣጣም የሚችልባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ ከአስር በላይ የጥናት ውጤቶችን አበርክተዋል::
ቡታን( የሂማልያ ኪንግደም) በምትባል ሀገር የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅትና ዓለም ባንክ በጋራ ይመሩት የነበረው የገጠር ልማት ድርጅት አማካሪ በመሆን የአርሶ አደሩና የአርብቶአደሩ ሕዝብ የውሃ፤ ደንና ግጦሽ ሃብትን ተንከባካቢና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ጥናትና ምርምር በማድረግ ለትምህርትና ስልጠና የሚበጁ ሥራዎችን አበርክተዋል:: ወደ አፍሪካ በመምጣት በኬንያ ፣ ሩዋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ታንዛኒ በመዘዋወር ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የእርሻ ምርምር ተቋማት በከፍተኛ ሳይንቲስትነት ፤ ፕሮጀክት ማኔጀርነትና የእነዚሁ ዓለም ዓቀፍ የእርሻ ምርምር ተቋማት ተወካይ በመሆን ካገለገሉ በኋላ በጤና እክል ምክንያት በጡረታ ራሳቸውን አግልለዋል::
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር አማረ ተግባሩ ከምርምርና ጥናት ስራዎቻቸው ባሻገር ገና በ28 ዓመታቸው በደርግ መንግሥት በታሰሩበት ወቅት በጋዜጣ ጠርዝና በሲጋራ ወረቀት ላይ በመፃፍ ያጠናቀሯትን ‹‹ ያንዲት ምድር ልጆች›› የተሰኘችውን መጽሐፍ ለህትመት አብቅተዋል::በዚህም አልተወሰኑም ‹‹ ሃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ›› ፣ ‹‹አድዋ ከዋዜማ እስከ ድል ቀን›› የተሰኙ መጽሐፍቶችን ለአንባቢያን ያደረሱ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ‹‹ፀሐዩ ዕንቁ ሥላሴ ፀረ ፋሽስት አርበኛና ያገር ባለውለታ›› የተባለ አዲስ መጽሐፍ ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ::ዶክተር አማረ ተግባሩ ለህትመት ባበቋቸው መጽሐፍትና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀር በናል::
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ስለሚያስመርቁት መጽሐፍት አጠቃላይ ይዘት በጥቂቱ ያስረዱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ዶክተር አማረ፡– ይህ ‹‹ ፀረ- ፋሽስት አርበኛና፤ የአገር ባለውለታ›› የተሰኘው መጽሐፌ በዋናነት የሚያጠነጥነው በደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁ ሥላሴ የፀረ – ፋሽስት አርበኝነት ተጋድሎና፤ በቀጣዩ አገር የማረጋጋትና የማስተዳደር ተግባር ላይ ነው::ይሁን እንጂ መጽሐፉ ከደጃዝማቹና ቤተሰቦቻቸው ታሪክ በዘለለ በተለይም ለአሁኑና ለመጭው ትውልድ ሀገራችን ስላለፈችባቸው ውጣ ውረዶች ፤ ቀደምት አባቶቻችን ስለነበራቸው ጥልቅ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ፤ ስላሳለፉት ተጋድሎና አገርን አንድ ለማድረግ ስላፈሰሱት ላብና ደም የሚዘክር ነው:: በመሆኑም በተለይም አሁን ላይ ያለው ትውልድ ከዚህ መጽሐፍ ብዙ ሊማረው የሚገባ ቁምነገር እንዳለ ነው የማምነው::
አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የሃይሌ ፊዳን ታሪክ በመፃፍ ለህትመት አድርሰው ነበር::ይህንን መጽሐፍ ለመፃፍ የፈለጉበት አብይ ምክንያት ምን ነበር?
ዶክተር አማረ፡– ይህንን መጽሐፍ የፃፍኩበት ኃይሌ ፊዳ ጓደኛዬ ስለሆነ አይደለም::ብዙ ጊዜ ጓደኛ ለመጥቀም፤ ሃጥያቱን ለመሸፋፈን አልያም ለዚያ ሰው ጥብቅና ለመቆም ሆን ተብሎ በስሜታዊነት አልያም ለጥቅም ሲባል የተፃፈ መምሰል የለበትም::እኔ እንዳውም ሃይሌ ጓደኛዬ ነው ከማለት አስተማሪዬ ነው ማለት ይቀለኛል::እንደሰው የቀረፀኝ ሰው ነው::እንደታላቅ ወንድሜ የማየው ሰው ነው::መቼም በፖለቲካ ትግል ውስጥ ስትገቢ የዕድሜ ልዩነቱ ይጠብና ጓደኛ ነው የምትሆኚው::በዚህ አጋጣሚ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ በአብዮቱ ጊዜ ከእስር እንደተፈታሁ ለህክምና በሚል ሰበብ ወደ ፈረንሳይ አገር እንድሄድ የነበርኩበት የፖለቲካ ድርጅት አድርጎኝ ነበር::
ይሁንና ፈረንሳይ የሄድኩበት ዋነኛው ምክንያት ለህክምናና ለትምህርት ይባል እንጂ ዋናው ሰበብ ግን አልነበረም::ድርጅቱ ሃይሌ ፊዳን አግኝቼ ከቻይናና ከኩባ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ በፈንጂ አምካኝነት ስልጠና እንድወስድ ተፈልጎ ነበር::ፈረንሳይ ሄጄ ሃይሌን ካገኘሁት በኋላም የመጣሁበትን ምክንያት ስነግረው ነገሩን ተቃወመው ፤ ይልቁን ትምህርቴን እንድማር ነው የመከረኝ::እኔ ከተማርኩ በኋላ ህዝቡን ማንቃትና መደራጀት እንደሚገባኝ፣ ከዚያ ህዝቡ ራሱ የራሱን ውሳኔ ሊወስን ይችላል ብሎ ነገረኝ::በወቅቱ እኔ ቅር ተሰኝቼ ነበር፤ በኋላ ነበር ነገሩ የገባኝ:: በአጠቃላይ ሃይሌ ፊዳ የመርህ ሰው ነበር::ለአገሩና ለህዝቡ ብዙ ዋጋ የከፈለ ብርቱ ታጋይ ቢሆንም ብዙዎች ግን የእሱን ትክክለኛ ስብዕና በቀና መልኩ የተረዱት አይመስለኝም::እኔ ደግሞ እሱን በቅርበት አውቀው ስለነበር በሱ ዙሪያ የተፈጠረውን ውዥንብር ጥርት አድርጎ ያሳይልኛል በሚል ነው ይህንን መጽሐፍ ለመፃፍ የወሰንኩት::
አዲስ ዘመን፡- ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተዘዋወሩ ሲሰሩ ወደ ኢትትዮጵያ ተመልሰው ያፈራዎትን ወገን ማገዝ ያልቻሉበት የተለየ ምክንያት ካለ ቢጠቅሱልን?
ዶክተር አማረ፡- መቼም ማንም ሰው ቢሆን ስደተኛ ሆኖ ከአገር ሲወጣ አንድ ቀን ወደ አገሬ እመለሳለሁ ብሎ ነው የሚያስበው::ግን ደግሞ በተሄደበት አገር ኑሮ ማበጀት አለ፤ ትዳር መመስረት አለ፤ እድሜም ይሄዳል::ይህም ቶሎ ወደ አገር ላለመመለስ ምክንያት ሊሆን ይችላል::ሆኖም የእኔ ዋነኛ ችግር እዛም ሄጄ በፖለቲካው መስክ ተሳትፎ ከማድረግ አለማረፌ ነበር::በተለይም ከደርግ ጋር በዚያ ሁኔታ ከተለያየን በኋላም የተለያዩ ፅሁፎችን እፅፍ ስለነበር ወደዚህ መመለስ የማይታሰብ ነገር ሆነብኝ:: ወያኔዎቹ ከመጡ በኋላ ደግሞ በደርግ የተበደለ ሁሉ እነሱን የሚደግፍ ይመስላቸው ስለነበር ከእኔ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ሞክረው ነበር::ነገር ግን እኔ ፈቃደኛ አልሆንኩም:: ኤርትራን ከኢትዮጵያ የገነጠሉበትን መንገድ በመተቸት በአሌፍ መፅሔት ላይ ፅፌ ስለነበር ከወያኔ ሰዎች ጋር አቃቃረኝ::በዚህ ፅሁፍ ምክንያት መጽሔቱ እንዲዘጋ ተደርጓል::
በተመሳሳይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ሲመጣም የኢትዮጵያውያንን አገር ወዳድነትንና አርበኝነትን አላግባብ ለግል ዓላማ የመጠቀም ፍላጎት አለ፤ በኋላ ችግር ይመጣል የሚል ነገር አንስቼ ነበር::ምክንያቱም ደግሞ ኤርትራ እንድትገነጠል እና አገር እንድትሆን እውቅና የሰጡት እነሱ ሆነው ሳለ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እናስከበር ማለታቸው ከመጀመሪያውም አልጣመኝም ነበር::ይህንኑ ስሜቴን ገልጬ ነበር::ይልቁንስ እናንተ የምትሉት ነገር እውነት ከሆነ አለምአቀፍ ጫና በመፍጠር ወደ ድርድር መምጣት እንዳለበት ነበር የተናገርኩት::ይህንን ተገን በማድረግ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበት ሁኔታ እንዲፈጥሩም የሚመክር ፅሁፍ በዚሁ በእናንተ ጋዜጣ ላይ ፃፍኩ::
በአጠቃላይ የነበረውን መንግሥት አካሄድ እቃወም ስለነበር ወደ አገሬ መመለስ አልቻልኩም ነበር::እንዳውም የግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ሲጀመር በዚያ ላይ በአማካሪነት ብመረጥም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‹‹እሱ የኢትዮጵያ ልምድ የለውም›› ብለው እንዳልቀጠር አደረጉ::በኋላ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የምናገርበትን እድል አገኘሁ::ያም ቢሆን ግን ልክ እንደባይተዋር ሹልክ ብሎ ገብቶ ከመውጣት ባለፈ አገሬን የምደግፍበትን እድል አላገኘሁም::
አዲስ ዘመን፡- እንደእርሶ አገር ወዳድ ዜጎች ከአገራቸውና ከህዝባቸው ተገልለው እንዲኖሩ ያስገደደው የዚህ ስርዓት መወገድ ምን አይነት ስሜት ነው የፈጠረቦት ታዲያ?
ዶክተር አማረ፡- ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው::ብችል እንዳውም ባልመልሰው ነው የምወደው::ግን ከጠየቅሽኝ አንፃር ግን እኔም ሆንኩኝም ማንኛውም የአገር ፍቅር ስሜት ያለው ሰው በትህነግ የሚመራው የኢህአዴግ መንግሥት በታሪካችን አይተነው የማናውቀው ከሃዲ መንግሥት ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም::ምንአልባት በውስጣቸው በቅንነት ጥቂት የብሔረሰብ እኩልነት ጥያቄ ያነሱ ነበሩ ቢባልም እንኳን እኔ አልቀበለውም::ምክንያቱም ደግሞ ቅንነት ብቻውን ከተጠያቂነት አያድንም::ቅንነት የነበራቸው ሰዎች እዛ ውስጥ አሉ እንኳን ብንል የእነሱ የአገር ሀሳቢነት አይዋጥልኝም ነበር::ግን መዘዙ የተረፈው ለእኛው ነው::
ይህም ማለት ሙጀሌ እግርሽ ውስጥ ከገባ ከነሰንኮፉ ተነቅሎ ካልወጣ ላይ ላዩን ስለጠረግሽው ብቻ ጤና አታገኚም::ወይም የተንጋደደን ዛፍ ቅርንጫፉን ስለደገፍሽው ቀጥ ብሎ ያድጋል ተብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው::እናም በአጠቃላይ እኔ ለትህነግ መንግሥት ፍቅር ኖሮኝ አያውቅም፤ በመወገዱም ደግሞ አላዝንም::ግን
ዋናው ነገር ማንኛውም ተራ ሰው ሊመልሰው የሚችለው ጉዳይ እነዚህ ሰዎች ያተረፉልን መዘዝ ለዘመናት የሚቀጥል መሆኑን ነው::ምክንያቱም መዘዙ ትግራይ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ ነው::አሁንም በእነሱ ምክንያት የተቀሰቀሰው ጦርነት ማብቂያና ማለቂያ ከሌለው ምንድን ነው ሊከተለው የሚችለው? የሚለው ነገር ማንንም የሚያሳስብ ነው::እንዳው እዚህ ነገር ውስጥ ብዙ መግባት ስህተት ውስጥ እንዳይጥለኝ እሰጋለሁኝ::ያም ቢሆን ግን የትህነጎች ውሳኔ ፈፅሞ የተሳሳተ እንደነበር መካድ አይቻልም::
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሲሉ ምን ማለቶ ነው?
ዶክተር አማረ፡- በኢህአዴግ መንግሥት መሃል የተፈጠረው ችግር የተወሰነው ሰዎችን ከኩርፊያ እስከ ግጭት ቢያደርስም የሚደገፍ ግን አልነበረም::ግን ተከፍተውስ ቢሆን ወደ ጦርነት መገባት ነበረበት ብዬ አላምንም::የአንዱን መከፋትና ማኩረፍ በመጠቀም ይህችን አገር ለማፍረስ ያሰፈሰፈውን የውጭ ሃይል ጋር መሰለፍ ለእኔ ፈፅሞ የምቀበለው አይደለም::ምንስ ቢሆን አገራችን አይደለም ወይ? በመሆኑም ምንም እንኳን በብልፅግና እና በትህነግ ሰዎች መካከል የነበረው ልዩነት በአግባቡ ሳይዙት ቀርቶ ወደዚህ ሁኔታ ተገብቷል ለማለት እንኳን የማንችልበት ሁኔታ ነው ያለው::ምክንያቱም ዛሬ ቅኝ ገዢዎች በቀጥታ የእኛኑ ሰዎች ተጠቅመው ነው አገራችንን ለማፍረስ እየሞከሩ ያሉት::በተደጋጋሚ እንደሚባለው አሁን እየተፋለምን ያለነው እኮ የትህነግ ጦርነትን አይደለም::ይሄ የውክልና ጦርነት ነው::ምክንያቱም አሁን ዘመኑ ተለውጧል፤ ዛሬ ቅኝ ገዢዎች በቀጥታ ሊወሩን አይችሉም::ግን ገላጋይ መስለው አልያም አንዱን አካል በግልፅ ደግፈው ነው የሚመጡት::
አሁን እየተካሄደ ያለው ከአሸባሪው ሕወሓት ጀርባ ተንጠላጥሎ የሚደረግ የውጭ ወረራ ነው::ግን እንዴት የራሳችን ወገኖች ከገዛ አገራቸው በላይ ራስ ወዳድነታቸው ወይም ‹‹ኢጎአቸው›› በልጦባቸው አገሪቱ የማትወጣው ፈተና ውስጥ የከተቱበትን ሁኔታ ስትመለከቺው ለማመን ይከብድሻል:: እስካሁን በህዝባችን ላይ የፈፀሙት ነገር ሲታሰብ በጣም የሚደንቅ ነው:: ብቻ አባቶቻችን ‹‹የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል!›› እንደሚሉት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም እንደስራው ማግኘቱ አይቀርም::ፈጣሪ አገራችን አንድ ሆና የምትቀጥልበትን ሁኔታ እንዲፈጥር ነው የምፀልየው:: በነገራችን ላይ ግብፅ የምትመራው የአረብ ሊግም ሆነ ምዕራባውያኑ አሸባሪውን ሕወሓት የሚደግፉት የሱ ፍቅር ስላላቸው አይደለም::ኢትዮጵያን ለማፍረስና ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ብቻ ነው::ወያኔዎች ግን ትንሽ እንኳን የአባቶቻቸው ታሪክና ገድል እንዴት ሊቆረቁራቸው እንዳልቻለ በጣም የሚደንቀኝ ነው::የቱንም ያህል ቢገፉ በዚህ ደረጀ አገራቸውን ለመክዳት የሚስችላቸው ሁኔታ የለም ባይ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡- ግን የበደለው ማነው፤ የተገፋውስ ማነው? ይህ አሸባሪ ቡድን ይህንን የመብት ጥያቄ የማንሳት መብትስ አለው እንዴ?
ዶክተር አማረ፡- እሱማ ትህነግ የመብት ጥያቄ ማንሳት ይችላል እያልኩሽ አይደለም:: አሁን ላይ ዋና አጀንዳው እኔና አንቺ የምንስማማበት የትህነግ በዳይነት ጉዳይ አይደለም::ዋናው አጀንዳ ኢትዮጵያን ማንበርከክ ነው::ግን ደግሞስ እንዳው ትህነግ ተበድሏል ቢባል እንኳን አገርን ያህል ነገር ለውጭ ወራሪ ይሰጣል ተብሎ ለማመን ይከብደኛል::የሚገርመው ይህንን ያህል ህዝቡን ገፍተው ሲጠቀሙበትና ሃብት ሲያከማቹ ኖረው በዚያ ላይ ደግሞ በሠላም የሚኖሩበት እድል ተፈጥሮላቸው ሳለ ፀብ መጫራቸው ነው::ይህ በምንም መልኩ አሳማኝ ሊሆን አይችልም::እነሱ እኮ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ቅስምና አከርካሪ ነው የመቱት::ችግሩ ግን ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ጦሱ ረጅም መሆኑ ነው::የሰላም መደፍረስ አንድ ቦታ ብቻ ያለው ህዝብን ብቻ አይደለም የሚጎዳው በአጠቃላይ አገሪቱንም ጭምር እንጂ::መሪዎቻችን ብልሃቱና ቆራጥነቱ ፈጣሪ ከሰጣቸው እኛም እያገዝናቸው ይህንን ነገር መቋጨቱ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ይህ ጦርነት የምዕራባውያን ጭምር ከሆነ ታዲያ ኢትዮጵያን እንደሶሪያና ሊቢያ ከመፍረስ መታደግ የሚቻለው እንዴት ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር አማረ፡- በተለይም አሜሪካኖች ቀይባህርን የመቆጣጠር የቆየ ህልም ስላላቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሉ የማይምሱት ጉድጓድ የለም::እኔ ስለአሜሪካኖች ባለኝ መረጃ በተለይ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ስልጣኑን በተረከበበት ዘመን ሁሉ የውጭ ፖሊሲያቸው በጣም መጥፎ ነው::ምንአለባት ለህዝባቸው የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ::ግን የውጭ ፖሊሲያቸው ተሳክቶላቸው አያውቅም::በገቡበት ሁሉ ማተራመስና አገር ማፍረስ ነው ሴራቸው::በቬትናምና ፈረንሳይ ሽንፈት ሲያጋጥማቸው አልተማሩም::የሚገርመው እስከዛሬ በገቡበት ሁሉ ባያሸንፉም በየአገሩ የፈጠሩት እልቂትና ጉዳት በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም::እኔ በነበርኩበት በታይላንድና ላኦስ ድንበር የአሜሪካኖች ትልቁ የአየር ሃይል እዛ ነበር::ከዚያ ሲመለሱ በአውሮፕላን ደን ሲያቃጥሉ እና መርዝ ሲረጩ ያደረሱት ጉዳት ዛሬም ድረስ የዚያ ውጤት ህፃናቶችና ሴቶች ላይ የዘለቀ ነው::
ከዚያ በኋላ መካከለኛው ምስራቅ ላይ ኢራቅን፤ ሶሪያን እዚህም አፍሪካ ሊቢያ ላይ ያደረሱትን ውድመት አይተናል::አሁንም ቢሆን የአሜሪካን ፍላጎት ለማወቅ አስቸጋሪ ነው::ግን እነሱ ራሳቸው የሚፈልጉትን ያውቃሉ ብዬ አላስብም::አሜሪካኖቹ የሚፈልጉትን ቢያውቁትማ ኖሮ ሉዓላዊ በሆነች አገርና ነፃ በሆነ ህዝብ ላይ ጣታቸውን ለማሳረፍ ባልሞከሩ ነበር::የኢትዮጵያ ህዝብ የፈለገውን መንግሥት የመምረጥም ሆነ የመሾም መብት አለው::ኢትዮጵያ ከሌላው አገር በተለየ ለምንድነው ጫና መፍጠርና መብቷን መጋፋት የሚፈልጉት?::እነሱ ትናንትና የዩጋንዳ ጦር ደቡብ ሱዳን ገብቶ ሲያተራምስ፤ ከዚያ በፊት የታንዛኒያ ጦር ኡጋንዳ ገብቶ አቦቴን እንዲያስወግድ ሲያደርጉ፤ ሰሞኑን እንኳን የሩዋንዳ ጦር ሞዛምቢክ ገብቶ ‹‹እስላማዊ ናቸው›› ያላቸውን ሃይሎች ድራሻቸውን ሲያጠፉ የተናገሩት ነገር የለም:: ታዲያ የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያ ገባ አልገባ ምንድን ነው የሚያገባቸው? እንኳንስ በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ምንአልባት የሁለቱን ህዝቦች የጥሞና ጊዜ ሳይኖራቸው መለያየታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደገና ወደ ሰላምም መምጣታቸው ሊበረታታ ነበር የሚገባው::
ትህነግ ግን ከ20 ዓመታት በኋላ ሠላም የተፈጠረበትን የሁለቱን አገራት ድንበር ለማተራመስ ሲል አስመራ ድረስ ሮኬት ሲተኩስና የኢትዮጵያን ጦር በዚህ መልክ ሲያጠቃ ኢትዮጵያ መብት እንደሌላት የሚታመነውስ ለምንድን ነው? አልፎ ተርፎ እንኳን ኤርትራን ይቅርና ከሩቅም መጋበዝ ትችላለች::በአለም ገለልተኛ ነኝ የምትለው ሲዊድን እንኳን በቅርቡ አሜሪካኖች አይ.ኤስ. ኤስን በደበደቡበት በሶሪያና በኢራቅ አካባቢ አየር ሃይሏን ልካ አግዛለች::ኢትዮጵያ ወዳዶቿን የመምረጥ ሙሉ መብት አላት::ሚዛን ጠብቃ የኖረች አገር ነች::ኢትዮጵያ እኮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራችም ናት::ኢትዮጵያ አትንኩኝ አለች እንጂ ሌላው ላይ አልደረሰችም::ስለሆነም አሜሪካኖች ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል::እኛ ደግሞ አሁን የገጠመን ፈተና የእልህ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው::ይህንን በዲፕሎማሲውም ሆነ በፖለቲካው መስክ እንዲገነዘቡት ማድረግ ይገባናል::ደግሞ የግድ ጦርነት ውስጥ እንደመግባታችን ወታደራዊ የበላይነቱን ከጨበጥን በኋላ ነው ወደ ድርድርና ንግግር መምጣት የምንችለው::
አዲስ ዘመን፡- ይህ አሸባሪ ቡድን ይህንን ያህል በደል ከፈፀመ በኋላ ድርድር ይደረግ ቢባል ምንያህል ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር አማረ፡– በእኔ አቅም በዚህ ጉዳይ ላይ እርግጥ ያለ ሃሳብ መስጠት ይከብደኛል::ግን እንደማንኛው ቅን ኢትዮጵያዊ ምንአልባት ከዚህ ቡድን ውስጥ አፈንግጦ የሚወጣና የአገርን አንድነት ለማስቀጠል የሚፈልግ፤ ብሎም ለድርድር ዝግጁ የሆነ አካል ይኖር ይሆናል ብዬ እመኝ ነበር::በተለይም መጀመሪያ ላይ የትህነግ መስራቾች ሲያዙና በጦር ሜዳ ሲገደሉ ለድርድር ፈቃደኛ የሚሆን ወገን ይኖራል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር::ወይም ደግሞ ጥቃቱ እየከፋባቸው ሲሄድ የግዳቸውን እጅ ይሰጣሉ ብዬ ነበር::ግን ያንን እስካሁን አላየንም::ሆኖም በየትኛውም ጦርነት ቢሆን አሸናፊውም ሆነ ተሸናፊ መጨረሻ ላይ ጠረጴዛ ላይ መቀመጣቸው አይቀሬ ነው::አሜሪካኖች ቬትናም በዚያ መልኩ ደብድበውም ቢሆን እስከመጨረሻው ድረስ ድርድር ነበር::ድርድር ሲባል ግን እነዚህን ሰዎች ዳግመኛ ስልጣን ላይ ማምጣት ማለት አይደለም::ትጥቅ የሚፈቱበትና ጦራቸውን ከወረሩት ክፍል የሚወጡበት፣ የተጠያቂነትን ጉዳይ የሚረጋገጥበት ነው::ምክንያቱም አሁን የተመረጠ መንግሥት አለ፤ ህዝቡ ማንም ሳያስገድደው ወጥቶ አሁን ላለው የኢትዮጵያ መንግሥት ድምፁን ሰጥቷል::ድምፁን ሲሰጠውም የአገሬን ዳር ድንበር ታስከብርልኛለህ ብሎ ነው::ይሄ ምንም ድርድር ውስጥ የሚገባ አይደለም::አሁን አንዱ ጫካ ገብቶ እንደገና ስልጣን የሚይዝበት እድል አብቅቷል::ያንን ምዕራፍ ተሻግረነዋል፤ በምን አይነት አሁን ወደዚያ ልንመለስ አንችልም::
ይሁንና በመጨረሻ ላይ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ ይህንን እውነታ ተቀብለው ለድርድር መቅረባቸው የማይቀር ነው::አሜሪካኖች ከታሊባን ጋር ተደራድረው የለም እንዴ? ስለዚህ ድርድር የነበረና ያለ ነው::ግን ከአሁኑ መተንበይ የለብንም::መንግሥታችንም ቢሆን ህዝበኛ በሆነ መንፈስ የእኛ ምርኮኛ ልናደርገው አይገባም::መንገዱን ልናስተው አይገባም::ይልቁንም በጥበብ ሊመራ ነው የሚገባው::ምክንያቱም ይህች አገር ከምትችለው በላይ የሆነባትን ሸክምና መዘዝ እንዲቀንስ ሁላችንንም የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ አለበት::ህዝቡ የኑሮ ውድነቱ የጫነበትን ቀንበር ረስቶ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ተነስቷል::በመሆኑም የምንችለውን ሁሉ አድርገን ከእነኚህ ሰዎች የምገላገልበትን መንገድ ማበጀት ያስፈልገናል::
አዲስ ዘመን፡- ምዕራብያውያኑ ሚዲያ ኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያሉትን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በምን መልኩ መመከት ይገባል ይላሉ?
ዶክተር አማረ፡- ልክ ነው፤ በውጭ ሚዲያዎች ዘመቻ በራሱ ለዚህች አገር ተጨማሪ ፈተና ሆኖባታል::ለምሳሌ እኔ የሲውዲን ዜጋ ነኝ::በየቀኑ ወደ ሲዊዲን እንድመለስ ተደጋጋሚ የሆነ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ነው የሚደርሰኝ::እኔ ግን ይህች አገር ከዚህም የበለጠ ችግር ያየች በመሆኑ አሁን በገጠማት ነገር እንደማትወድቅ አውቃለሁኝ::እርግጥ ነው ዘመቻቸው የተቀናጀና የተናበበ መሆኑ ከባድ አድርጎታል::ገለልተኛ ነን የሚሉት እንዲሁም ለአሜሪካ ፖሊሲ ምቹ አይደሉም የሚባሉ የአውሮፓ አገራት ሳይቀሩ የሚያሳዩት ባህሪ በቀላሉ የሚታይ አይደለም::ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆነው ዜጋ ላይ ሳይቀር ተፅዕኖ ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ ይህችን አገር ለማፍረስና ህዝቧቿን ለማንበርከክ ምንያህል እንደቋመጡ ነው::በመሆኑም ሁላችንም በያለንበት ‹‹እምቢ!›› ማለት መቻል አለብን::
ምዕራባውያኑ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ወደለየለት ትርምስ ውስጥ ብትገባ እንኳን እኔ ሸሽቼ ሌላው የሚጋፈጥበት ምክንያትስ ምንድን ነው?::እኔ ለብዙ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ነው ኢትዮጵያን መጎብኘት ያለባችሁ ብዬ እየቀሰቀስኳቸው ነው ያለሁት::እኛ ራሳችን በእነሱ አስተሳሰብ ውስጥ ገብተን ነው ባልተፈጠረ ነገር ስጋት ውስጥ እየወደቅን ያለነው::እንደእኔ እምነት እነሱ የሚያስቡትን እኛ ራሳችን እንደነሱ ሆነን የእልቂትና የጥፋት ዘመን እንደመጣ አድርገን በራሳችንና በህዝባችን ላይ የምንናገር ሆነን ስንገኝ ነው የሚያሳዝነው::እርግጥ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ውሳኔ አለው::ግን በተቻለ መጠን የአርበኝነትና የኢትዮጵያዊ ስሜት አለኝ የሚል ሁሉ ለምዕራብውያኑ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በምንም አይነት እጁን መስጠት የለበትም::እንዳውም በመከራው ጊዜ ነው ህብረታችን ሊጠናከር የሚገባው:: ምንአልባት የግድ ሁላችን ወደ ጦር ግንባር መዝመት አይጠበቅብንም ይሆናል::ግን ደግሞ በየአለንበት ለሀገራችን ሉዓላዊነት ዘብ መቆም ይገባናል::
በነገራችን ላይ ደርግ የተሸነፈው በጦርነት ሳይሆን በፕሮፖጋንዳ ነበር፣ አሁንም ያሰቡት ልክ እንደዚያን ጊዜ በፕሮፖጋንዳ ሀገር ለማፍረስ ነው::ግን አሁን ላይ በፕሮፖጋንዳና በወሬ የሚሸነፍ ህዝብ የለም::እናም ለምዕራብውያኑ ያለኝ መልዕክት ኢትዮጵያ በሀሰት ወሬ እንደማትበተን አውቃችሁ አርፋችሁ ብትቀመጡና አፋችሁን ብትዘጉ ይሻላል የሚል ነው::የተመረጠ መንግሥት እያለ አሜሪካ የምትፈልጋቸው ሰዎች መጥተው በምንም አይነት ስልጣን የሚይዙበት ሁኔታ የለም::ይህ እንኳን ቢፈጠር በባዶ መሬት ላይ ብቻ ነው::ምክንያቱም ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለወያኔና ለምዕራብውያኑ እጁን የሚሰጥበትና የዚህችን አገርና የአባቶቻችንን የነፃነት ታሪክ የሚንድ ተግባር አይፈፅምም:: ይህ ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያውያን መቃብር ላይ ብቻ ነው!::
አዲስ ዘመን፡-ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
ዶክተር አማረ፡– እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ አመሰግናለሁኝ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014