‹‹እግዚአብሄር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም።ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።›› ይህ ከ126 ዓመት በፊት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ባህር ተሻግሮ ኢትዮጵያን ለመውረር ቋምጦ በመጣው የፋሽስት ጣሊያን ለመመከት ለመላው ኢትዮጵያዊ የተላለፈ የክተት አዋጅ።
ይህንን አዋጅ ብዙዎቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ እየሰማነው ያደግን ቢሆንም ሁሌም እንደአዲስ ወኔያችንን የሚሸንጥ ዘመን አይሽሬ የንጉስ ጥሪ ነው፡፡
ታሪካችን እንደሚያሳየው አዋጁ በታወጀበት ወቅት ምንም እንኳን የንጉሱ ባላንጣ የሆኑ ሥርዓትን የሚቃወሙ ባላባቶች የበዙበት ቢሆንም ቅሉ የንጉሱን ጥሪ አሻፈረኝ ብሎ የቀረ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ሁሉም ከያለበት ኩርፊያውን፤ ቂሙን ወደጎን ትቶ አገር ላይ ጦር ሰብቆ የመጣውን የባህር ማዶ ወራሪን ለመመከት በአንድ ልብ ተነሳ እንጂ !፡፡ ፈጣሪውን ታምኖ የወጣው ይህ የጥቁሮች አውራ የሆነው ሕዝብ ለብዙዎች በነፃነት መኖር ደሙን አፈሰሰ፤ አጥንቱን ከሰከሰ፤ ሕይወቱንም ገበረ፡፡ በከንቱም አልቀረ ድልን ተቀዳጀ፡፡
ያ የአባቶቻችን ገድል ዛሬም ህያው ሆኖ በልባችን ነግሶ ይኖራል፡፡ አንደበቶቻችን ዛሬም እንደ አዲስ ብስራት ይዘክሩታል፤ ያወድሱታል፡፡ አዎን! አሁንም ድረስ በዓለም አደባባይ ቀና ብለን የመሄዳችን ምክንያት አድዋ ነው! እንደሕዝብ የመቀጠላችንም ሁነኛ ሚስጥር አድዋ ነው!፡፡ ለክብሩ ሟቹ ይህ የአገሬ ሰው በሽንፈቱ ተዋርዶ በቆየው የነጭ ወራሪ በትር ቢያይልበትም ልክ እንደአባቶቹ እጅ አልሰጠም፡ ፡ እርግጥ ነው!፤ ቂም አርግዞ የኖረውን ይህ የባዕድ አገር እንግዳ የወላጆቹን ብድር ሊመልስ ዙሪያችን አድብቶብናል፡፡ የእናት ጡት ነካሽ የሆኑ ባንዳዎቻችንም ተጠቅሞም ሊበትነን ሌት ተቀን ደፋ ቀና ማለቱንም ቀጥለውበታል፡፡
ይሁንና የቱንም ያህል የበቀል ክንዳቸው ቢበረታብን ጀግንነት በሁለት እግሩ ከነነፍሱ ቆሞ በታየበት በዚህች አገር ጎራዴና ጦር ከታንክ ጋር ተጋጥመው የጥቁር ሕዝቦችን ነፃነት ያወጁ ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን አገር ልንደራደርባት አንችልም ብለን ከአራቱም አቅጣጫ ተነስተናል፡፡ የጦርነት ነጋሪት የጎሰመብን ይህንን የታሪክ አተላ ራሱ በማሰው ጉድጓድ ልንቀብረው ልክ እንደአባቶቻችን ከመሪ እስከ ሎሌ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከየጎጣችን ያለንን ይዘን ወጥተናል።ይህ ሕብረ-ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ ወኔ ታዲያ በመላው ዓለም ናኝቶ መታየት ጀምሯል፡፡ በውድቀታችን ለመሳለቅ ለቋመጡት የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችንን አንገት አስደፍቷል፡፡
አሜሪካንም ሆነች ሌሎቹ ምዕራባውያን በማዕቀብና በማስፈራራት በኢትዮጵያ አገራችን ላይ የሚሰሩትን የዘመነ ኒዎ-ኮሎኒያሊዝም ኢምፔሪያሊስታዊ ፕሮጀክት በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ ለማስፈፀም ቢጣጣሩም ልፋቸው መክኖባቸዋል፡፡ እርግጥ ነው፤ አሁንም ቢሆን እጅ ጥምዘዛቸው አልሳካ ቢላቸውም፤ ተስፋ ቆርጠው አልተውንም፡፡ ለዚህ እኩይ ዓላማቸው እውን መሆን አስቀድመው በዘየዱት ማዕቀብ በተጨማሪ መገናኛ አውታሮቻቸውና አፈቀላጤዎቻቸው ሊያሸማቅቁን ተነስተውብናል፡፡ በበሬ ወለደ ዜናዎቻቸው እርስበርስ እንድንባላና እንዳንተማመን ያናውጡን ይዘዋል። እኛ ግን የአባቶቻችንን ቀይ መስመር እንዲያልፉ አንፈቅድላቸውም፡፡
ከእንግዲህ የዘመናዊ ባርነትን ካቴና እጃችን ላይ ሊያጠልቁልንና በነጭ ፕሮፖጋንዳ በየሚዲያቸው በሎቢስቶቹ ታጅበው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲንጫጩብን በተለይም እኛ የሚዲያው ተዋናዮች ገለልተኛ ነን በሚል እሳቤ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም፡፡ ከጦርነቱ እኩል የተከፈተብንን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በብዕር መመከት ያለባቸው በመላው ዓለም የሚገኙት የአገራችን ጋዜጠኞች በመሆናችን ሴራውን ለማክሸፍ ይገባናል፡፡
የተከፈተብንን ሕዝባዊ ጦርነት የምናሸንፈው በመከላከያ ኃይል ብቻ ሳይሆን ከሕዝባዊ አንድነታችን በሚመነጭ አቅም ጭምር ነው።
ጦርነቱን በድል ለመወጣት ይህን አቅም ወደ ሕዝባዊ የጦር ኃይል ግንባታ መቀየር ያስፈልጋል ።ለዚህ የሚሆንም አደረጃጀቶችን መፍጠር ይጠይቃል። ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ገበሬውን፣ የመንግሥት ባለስልጣኖችና ሠራተኛው፣ነጋዴው፣ የሃይማኖት አባቶችና በውጭ አገራት የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዚሁ ኃይል የተሟላ አቅም አድርጎ መሥራትም ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ፡፡
መላው ሕዝባችን ድሉን ለማፋጠን ለመከላከያ ሠራዊት ደጀን በመሆን ያለእረፍት ሌትና ቀን የዘመቻው አካል መሆን ይኖርበታል፡፡ ነጋዴዎችም ሆነ ባለፀጋው፤ የታክሲ አሽከርካሪም ሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ዶክተሮች ነርሶች ሐኪሞችም ሁሉም በየሙያው መስካቸው የመከላከያ ሰራዊቱ አጋር በመሆን መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ይህንን ጦርነት ለማሸነፍ ጦርነቱን ሕዝባዊ ጦርነት ማድረግ ወሳኝ ነው። ከምኞት በዘለለ ለአገራችን የምናስብ ከሆነ አዲሱ ትውልድ በየጫት እና መጠጥ ቤቱ ቁጭ ብሎ ‹‹እዚህ ደረሱ፤ ከዚያ ወጡ›› ከሚል ወሬ ወጥቶ ቦላሌውን ቆርጦ ፤ ሸሚዙን ጠቅልሎ እኔም መከላከያ ነኝ ብሎ ለአገሩ ዘብ መቆም ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ የሞራልም የትውልድም ኃላፊነቱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ሰሞኑን ጦርነቱን በግንባር ሆነው ለመምራት የደረሱበት ውሳኔ ኃላፊነትን ለመወጣት የቱን ያህል ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግ በተጨባጭ ያመላከተ ነው። የሳቸውን ፈለግና ዱካ ተከትሎ መንቀሳቀስ ደግሞ የዜጎች ሁሉ የጋራ ኃላፊነት ነው። ይህን አለማድረግ የታሪክ ተወቃሽነትን የሚያመጣ ፤አባቶቻችን ልጆች ስለመሆናችን ከፍ ያለ ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ለማይቀረው ዘመቻ ሁላችንም ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ሁላችንም የመከላከያ ሠራዊት አባል አድርገን እራሳችንን በመቁጠር ዘመቻውን መቀላቀል ይጠበቅብናል ። ይህም ድላችን በእጃችን እንዳለ ማረጋገጫችን ነው!፡፡
ሜሎዲ
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014