የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ሰላም ከፍ ባለ ድምጽ ከሚያዜሙ የዓለም ሕዝቦች መካከል አንዱ ነው። ችግሮች ወደ ግጭት ከማምራታቸውና ዋጋ ከማስከፈላቸውም በፊት ነገሮችን በሰከነ መንፈስ የማየትና የማረም የቆየ ባህል ባለቤት ነው። በዚህም ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ አንድ ሆኖ እንደ አገር መቀጠል የቻለ ሕዝብም ነው።
ለዚህም ሃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶቹ ከፍ ያለውን ስፍራ ይይዛሉ ፤ እነዚህ እሴቶች ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረጉ፣ ሰውን በሰውነቱ የሚቀበሉ እና አብሮ መኖርን የሚያበረታቱ ናቸው። አገርን እንደ አገር በማስቀጠል ሂደት ውስጥም ወሳኝ አቅም በመሆን አገርን እንደ አገር አጽንተው ማስቆም የቻሉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍትሕ እና ለነጻነት ፤ ስለአገሩና ሉዓላዊ ስብዕናው ቀናዊ እንዲሆን ፤ ሕይወቱንም ለነዚሁ ከፍ ላሉ ማኅበራዊ እሴቶች መስዋዕት ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ የሆነ ቁርጠኝነት እንዲኖረው አስችለውታል። ለዘመናት ነጻነቱን አስከብሮ ለመኖርም ሆነ በነጻነት የተጋድሎ ታሪኮች ለሌሎች ፋና ወጊ እንዲሆን አድርገውታል።
እነዚህ እሴቶች አገራዊ አቅምና የኢትዮጵያዊ ማንነት መሠረት ሆነው ከትውልድ ትውልድ እየተላለፉ ቢመጡም በየዘመኑ ከነዚህ እሴቶች አፈንግጠው ከእውነተኛ ማንነታቸው ጋር የተጣሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በመፈጠራቸው ምክንያት ሕዝባችን የሰላም ሐዋሪያ የመሆኑን ያህል የሰላሙ ባለቤት ሳይሆን ቀርቷል።
በተደቀሉ አስተሳሰቦች ፍጥረታቸው የተሟሸ ግለሰቦች በየዘመኑ በፈጠሯቸው የተዛቡ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ በፈጠሯቸው ግራ መጋባቶች ሕዝባችን ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈልም ተገድዷል ። ዛሬም ሳንፈልግ የገባንበት የህልውና ዘመቻ የዚሁ እውነታ አካል ነው ። እየከፈልነው ያለውም ዋጋ የተዳቀሉ አስተሳሰቦች የወለዱት ግራ መጋባት ነው ።
አሸባሪዎቹ ሕወሓትም ሆነ ሸኔ ለአገሪቱ የህልውና አደጋ እስከ መሆን የደረሱት ገና ከፍጥረታቸው ጀምሮ በአገሪቱ ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ባልተቃኘ ማንነት በተገነቡ፤ በዚህም የማንነት ግራ መጋባት ውስጥ ባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ነው።
እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ግራ መጋባታቸውን የፖለቲካ ዓላማ አድርገው ወደ ሕዝብ ለማጋባት የሄዱበት የሴራ መንገድ፤ ይህንኑ መንገድ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሆ! ብለው የመነሳታቸው እውነታ ወቅታዊ ፈተናውን አክብዶታል ።
ይህ ኢትዮጵያዊ መሠረት የሌለው የቡድኖቹ የፖለቲካ እሳቤ ፈተና ከመሆን ባለፈ መቼም ቢሆን የሕዝባችንን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረስ የመጣ ማኅበረሰባዊ ማንነት/ኢትዮጵያዊነት/ አሸንፎ የመውጣት አቅምም ሆነ ዕድል የለውም፤ሊኖረውም አይችልም። በቃ ሲባል የሚያበቃ ማኅበረሰባዊ መሠረት የሌለው ተራ እውነት ነው።
ለዚህ ደግሞ ዛሬ ላይ እየሆነ ያለው እውነት ተጨባጭ ማሳያ ነው። እንደ ሕዝብ ይህንን የተዳቀለ አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ የወለደውን ሴራ ዛሬ ላይም “በቃ” ብለነው እያበቃለትና ወደ መቃብር እየወረደም ነው። አስተሳሰቡ የወለዳቸው የትናንት እብሪትና መፋነኖች፤ ያዙኝ ልቀቁኝ እና ጉሮ ወሸባዬዎች የጠዋት ጤዛ ሆነዋል። ፈልገን የማናገኛቸው የማለዳ እውነቶች ሆነዋል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2014