ዓለም ስለ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ስለ ዴሞክራሲና ስለሰው ልጆች ቀጣይ እጣ ፈንታ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚህ 21ኛው ክፍለዘመን፤ ከባርነት የሚቀዳ ተጠቃሚነት ያሰከራቸው አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ለክፍለ ዘመኑ አስተሳሰብ ተግዳሮት ሆነው ተሰልፈዋል።
እነዚህ ሀገራት በቀደመው ዘመን አፍሪካውያንን በቅኝ አገዛዝ በመቀራመት ለአህጉሪቱ ህዝቦች እስከ ዛሬ ያልተገፈፈ የህይወት ጽልመት ፈጥረዋል። በዚህም የአህጉሪቱ ህዝቦች እጣ ፈንታቸውን በራሳቸው እንዳይወስኑ አቅምና ድፍረት አጥተዋል። ጽልመቱን ሰብረው እንዳይወጡም እንደ ባሪያ ፍንገላው ዘመን በብረት ሳይሆን በሴራ ሰንሰለቶች እጅ ከወርች ታስረዋል።
ሀገራቱ በዚህ ዘመን አፍሪካውያንን እንደቀደመው ዘመን በሰንሰለት አስረው ለግዞት ሕይወት ከማጋዝ ይልቅ ተስፋቸውን ነጥቀው ፤ በተስፋቸው እየቆመሩ ፤ በነጻነት እና በዴሞክራሲ ስም ከትናንት የከፋ ሕይወት እንዲያሳልፉ እያደረጉ ነው። በዚህም አፍሪካውያን ቤታቸው ሙሉ ሆኖ ሳለ የታሰረ እጃቸውን ይዘው ምጽዋት ጠባቂ ሆነዋል።
ባርነትና ከባርነት የሚቀዳ ተጠቃሚነት አሜሪካንን በውልደቷ ማግስት ለእርስ በርስ ጦርነት የዳረጋት ከፍ ያለ ሀገራዊ ተቃርኖ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህ ተቃርኖ በጦርነቱ አሸናፊ በሆነው ሀይል የተዘጋ የታሪክ ምዕራፍ መስሎ ቢታይም እውነቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል ።
ለችግሩ የአሜሪካ መስራች አባቶች ብዙ ዋጋ ከፍለው፤ ለዓለም አዲስ አስተሳሰብና አስተምህሮ አበርክተው ከፍ ባለ የሞራል ልእልና ቢያልፉም ፤ እነሱን እየተካ የመጣው ዘመናዊው ትውልድ ከቀደሙት አባቶቹ የሞራል እሴቶች እየተፋታ በቀደመው ዘመን ተሸንፎ የነበረው አስተሳሰብ በዚህ ዘመን አፈር ልሶ ፤ ህይወት ዘርቶ ለአብዛኞቹ የአለም ሀገራት ሕዝቦች የስጋት ምንጭ ሆኗል። ተስፋ አልባ እየሆነ ለመጣው የህይወት ጅማሯቸው ምክንያት ሆኗል።
በዴሞክራሲ፤ በሰብአዊ መብቶችና በመልካም አስተዳደር መጋረጃዎች የተገመደው ዘመናዊው የባርነትና ከባርነት የሚቀዳ ተጠቃሚነትን የማስቀጠል ሴራ ከቀደመው ዘመን በከፋ ሁኔታ ሀገራትን ወደ ፍርስራሽነት፤ ህዝቦችን ወደተስፋ ቢስነትና ተመጽዋችነት ለውጧል። ለዚህም ኢራቅን፣ ሶሪያን፣ የመንን ፣ ሶማሊያን እና በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ተስፋ ቢስ ሆነው ሕይወታቸውን የሚመሩ የአፍሪካ ሀገራትን ህዝቦች መጥቀስ ይቻላል።
የተሻለች ዓለም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እየተገዳደረ ያለው ይህ ፍጹም ከሆነ ኢ ሰብአዊነትና ራስ ወዳድነት የሚመነጭ አስተሳሰብ ይብቃ ለማለት አሁን ትክክለኛው ወቅት ነው። ይህ አስተሳሰብ ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መፍቀድ ዓለም አቀፍ አምባገነንነት በከፋ መልኩ እንዲያቆጠቁጥ ዕድል የመስጠት ያህል ነው ።
ይህ አስተሳሰብ ፈጥኖ ካልከሰመ አስተሳሰቡ በሚፈጥረው ጽልመት ተስፋ ቢስ እና ሀገር አልባ የሚሆኑ የዓለም ህዝቦች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱ የማይቀር ነው። በተለይም በቀደመው ዘመን የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆኑት አፍሪካውያን የችግሩ ዋነኛ ሰለባ የመሆናቸው እውነታ የአደባባይ ምስጢር ነው ።
ከዚህ የተነሳም አፍሪካውያን ትናንት ባሪያ ያደረገንን፣ ዛሬ ደግሞ ተስፋችንን ሰርቆ በተስፋችን እያመነዘረ ህይወታችንን በጽልመት የጋረደው አስተሳሰብ እንዲያበቃ ግንባር ቀደም ሆነን መሰለፍ ይጠበቅብናል። የቀደመውንና የዛሬውን ታሪካችንን በሰከነ መንፈስ መርምረን በሁለንተናችን አስተሳሰቡ በዚህ ትውልድ እንዲያበቃ ድምጻችንን ከፍ አድርገን ይብቃ! ልንል፤ በቁርጠኝነት ልንታገለው እና ለዚህም እራሳችንን ለሰማዕትነት ማዘጋጀት ይጠበቅብናል።
ነጻነትና ፍትህ ወዳድ የሆኑ፤ ለመላው የዓለም ህዝብ ቀና አመለካከት ያላቸው የዓለም ሕዝቦችም ባርነትና ከባርነት የሚቀዳ የእልፍ ተጠቃሚነት አስተሳሰብ፤ ዓለምን ለከፋ መከራና ስቃይ የሚዳርግ አለም አቀፍ አምባገነንነት፣ ከሁሉም በላይ የሰው ልጅ አሁን ከደረሰበት አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ ከወለዳቸው የሞራል እሴቶች አፋትቶ ወደ እንስሳነት ደረጃ የሚያወርድን የስግብግብነት መንፈስ ከፍ ባለ ድምጽና ቁርጠኝነት ሊታገሉት፤ ይብቃ ! ሊሉት ይገባል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/2014