አገር ሲወረር የመሪዎች ወደ ግንባር የመዝመት ታሪክ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። እስከ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ድረስ ሳይቋረጥ የነበረ ተግባር ነበር። ግን ተቋረጠ። ይሁን እንጂ የተቋረጠው የመሪዎች የጀግንነት እሴት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተቀጠለ። እነሆ ባለፈው ሰኞ በመንግሥታቸው በተወሰነው መሰረት በማግስቱ እሮብ ጠዋት ዐቢይ ወደ ጦር ግንባር ተጉዘዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው መንግስትን ውሳኔ ተከትሎ ከሕዝብ የተገኘው ምላሽ እጅግ ያልተጠበቀ ሲሆን፤ እሱም በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትራችን አንለይም በሚል ወደ ዘመቻው ማቅናታቸው ሲሆን እሱም ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አቶ ክርስቲያን ታደለ መጀመሩ ታውቋል። ”ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት የምንሰስተው ሕይወት የለምና እኛም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዘምታለን። ሕዝቤ ሆይ ተከተል!” በማለት በማኅበራዊ ድረ-ገፃቸው የገለፁት አቶ ክርስቲያን ከሁሉም በፊት አገር መሆኑንም ተናግረዋል፤ “ድል ለአገራችን!!! ድል ለሕዝባችን!!!” ሲሉም የኢትዮጵያን አሸናፊነት ከወዲሁ አብስረዋል።
ጉዳዩ ከአገርም ባለፈ ዲያስፖራውንም ጎንጦታልና “ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር ወደ ፊት!!!” ለማለትና በአውደ ውጊያው በመሰለፍ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማዳን ከሠራዊቱ ጎን እሰለፋለሁ በማለት ጓዜን ጨርቄን ሳይሉ እየመጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ታማኝ በየነ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ጥሪው እከሌ ከእከሌ አይልምና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ከስፖርቱ ዓለምም መከላከያን እየተቀላቀሉ ያሉ ስለመኖራቸው በመገናኛ ብዙኃን እየተገለፀ ይገኛል።
“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ትክክል ነው። በዚህ ሰዓት በአገራችን ላይ የተቃጣውን ችግር ልክ አባቶቻችን በዓድዋ እንዳደረጉት እኔም በግንባር ሄጄ የሚጠበቅብኝን እወጣለሁ” ያለው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከስፖርቱ ዘርፍ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድን ወደ ግንባር መንቀሳቀስ ተከትሎ ምላሽ ሰጥቷል። ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እንዳለው ከሆነ ወደ ግንባር መሄዱና አገር አፍራሹን ቡድን በመፋለም ሰላምን ማስፈን ብቻ በቂ አይደለም። በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ልክ እንደ አውደ ውጊያው ሁሉ እራሱን የቻለ ዘመቻ ያስፈልጋል። እስከ ዛሬ 8 ሰአት የምንሰራ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ 16 ሰዓት ልንሰራ ይገባል።
ኃይሌ እንደሚለው ድህነታችን ለብዙ ነገር አጋልጦናል። አሁን የእጅ ዙር ጦርነት እያካሄዱብን ያሉት፣ በማእቀብ የሚያስፈራሩን ሁሉ ደሀ በመሆናችን ነው። በመሆኑም ይህ ሁሉ ችግር ሊያስተምረንና በእጥፍ ሰርተን ከድህነት በመውጣት እራሳችንን ማስከበር አለብን። ይህ ጉዳይ በተለይ ወጣቱን ሊያስቆጣው፤ በእልህም ወደ ስራ ሊያስገባው ይገባል።
ከሚዲያው ዘርፍም ከተለመደው ስራ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መዝመት ተከትሎ ወደ ግንባር የተንቀሳቀሱ መኖራቸው የተሰማ ሲሆን፤ በትናንትናው ዜና እወጃ ሰዓትም የኢሳት ጋዜጠኞች እኔ ለሀገሬ እዋጋለሁ በማለት ወደ ግንባር መንቀሳቀሳቸው ተገልጿል።
ጉዳዩን ሰፋ አድርገን በአህጉር ደረጃ ስንመለከተው ደግሞ የምናገኘው የትናንት በስቲያውን “አፍሪካውያን ወደ ዳግም ቅኝ ግዛት እንዳይመለሱ ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው እንዲታገሉ የፓን አፍሪካ አቀንቃኙ ማፖንጋ ጆሹዋ ጠየቁ” የሚለውን የዋልታ ዜና ይሆናል።
ምንም እንኳ የአፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ጎን የመሰለፍ ተግባር በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት፣ አድዋ ካልመጣንና ከጎናችሁ ካልሆንን በማለት በተደራጀ መልኩ በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፤ ያ አፍሪካዊነት ዛሬም እንደ አዲስ አቆጥቁጦና ኃይሉንም አጠናክሮ ከተፍ ብሏል።
“የአፍሪካ የነፃነት እናት የሆነችው ኢትዮጵያ በበረከተባት ጫና ብትዳከም አፍሪካ ያለ ጥርጥር ወደ ዳግም ቅኝ ግዛት ትገባለች ሲሉ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ማፖንጋ ጆሽዋ 3ኛ ገለፁ። [. . .] በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የጣልቃ ገብነት ችግር የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ችግር በመሆኑ አፍሪካዊያን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል።” የሚለው የዜናው መግቢያም የሚነግረን ይህንኑ ሲሆን፤ ማፖንጋ ጆሽዋ 3ኛ “ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ምልክት ነች” ማለታቸውም የኢትዮጵያን ዘላለማዊ አፍሪካዊነትን የሚመሰክር ብቻ ሳይሆን አሜሪካና ግብረ አበሮቿ ምን ያህል ይህንን የኢትዮጵያን ቀንዲልነት ከስሩ ነቅሎ ለመጣል መከራቸውን እያዩ እንደሆነም ጥሩ ማሳያ ነው።
እኝህ እውቅ ደራሲም “በአሜሪካ መሪነት ኢትዮጵያን ወደ ትንንሽ አገራት ለመከፋፈል በምዕራባውያኑ የተሸረበውን ሴራ መታገልና የአፍሪካን በራስ የመወሰን አቅም ማጠናከር” እንደሚገባ ያሳሰቡትም ከዚሁ ከአሜሪካና ተባባሪዎቿ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም በመነሳት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው።
ታሪክ
ምኒልክ አዲስ አበባ ላይ ተከተለኝ ብለው ደብረ ብርሃን ሲደርሱ በመቶ ሺዎች ሕዝብ ቀድሟቸው ማግኘታቸውን ታሪክ በወርቅ ቀለሙ አቅልሞ አስፍሮታል። እቴጌ ጣይቱ ሴቶችን ተከተይኝ ባሉት መሰረት በአንድ ጀምበር ከ60 ሺህ በላይ ሴቶች በዙሪያቸው ከበዋቸው ወደ አድዋ አቅንተዋል። መንግሥቱ ኃይለማሪያም እብሪተኛውና በእነ አሜሪካ ግፊት ሊወረን የቋመጠው ዚአድባሬ በደፈረን ሰዓት “ተነስ!!! ታጠቅ!!! ዝመት!!!” ባሉት መሰረት በአንድ ጊዜ ብቻ 300 ሺህ ሰራዊት ታጠቅ ጦር ሰፈር ከትቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጥሪ ተከትሎ ስንቱ እንደተከተላቸው አሁን ላይ ቁጥሩ ባይታወቅም ዘመኑንና የሕዝብ ቁጥሩን ባገናዘበ መልኩ እንደሚሆን ግን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
• አካባቢህን ጠብቅ፣
• ወደ ግንባር ዝመት፣
• መከላከያን ደግፍ።
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014