በኪነ ጥበብ ብዙ ነገሮች ይገለጣሉ። ኪነ ጥበብን ከሌሎች አገላለጾች የሚለየው ደግሞ ስሜት ውስጥ የሚገባ መሆኑ ነው። በረቂቅ ቋንቋ የሚገለጽ፣ በቅኔ የሚተረጎም፣ በዜማ የሚቃኝ መሆኑ ነው።
የአገር ታሪክ፣ ባህል፣ የማሕበረሰብ ሥነ ልቦና… በአጠቃላይ የአንድ ዘመን ምንነት በኪነ ጥበብ ይገለጻል። ምክንያቱም ኪነ ጥበብ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው። የዘመን ባህሪ የሚታወቀው በዚያን ዘመን በተሰሩ የጥበብ ሥራዎች ነው።
የድሮ ታሪክ ስናነብ በታሪኩ ውስጥ የኪነ ጥበብ ሥራዎች አሉ። በዘመኑ የነበሩ ነገሥታትን ጀግንነት የሚያወድሱ፣ የተሸነፈው አካል ላይ የሚሳለቁ ግጥሞችን እናገኛለን። ግጥሞቹ በአዝማሪ፣ በሕዝብ ዘፈን፣ በለቅሶም ሆነ በሰርግ እንጉርጉሮ የሚባሉ ናቸው። እነዚህ ስንኞች የዚያን ዘመን ምንነት፣ የመንግሥታዊ አስተዳደሩን ባህሪ፣ የሕዝቡን ሥነ ልቦና ያሳዩናል።
በኢትዮጵያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል የክልሉን መንግሥት እያስተዳደረ የነበረው ሕወሓት ሰሜን እዝ ላይ ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ በክልሉ የህግ ማስከበር ዘመቻ ተካሂዶ በድል መጠናቀቁ ይታወቃል። ይህ ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ አንዲት ዶሮ ብቻ ካለቻቸው እናት ጀምሮ እስከ ትልልቅ ባለሀብቶች በገንዘብ፣ ወጣቱ በግንባር፣ ምሁሩ በሃሳብ፣ አርቲስቱ በኪነ ጥበበብ… በአጠቃላይ ሁሉም በየተሰማራበት ታግሏል።
በጦርነቱ ድል የተመታው ትህነግ በርካታ አመራሮቹ ተገድለውበታል፤ ሌሎች ደግሞ ተማርከውበታል፤ ጥቂቶቹ ደግሞ የተወሰኑ ወራትን በተንቤን በረሃ ዋሻ ውስጥ ቆይተው በውጭ ሃይሎች ድጋፍ እንደገና በማንሰራራት አሁንም የጦርነት ቁማር እየተጫወቱ ይገኛሉ። አገራችን አሁንም ይህን ለመቀልበስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።
ይህን ታሪካዊ ክስተት ተክትሎም ሕዝቡ የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ በርካታ የኪነጥበብ ሥራዎች ወጥተዋል። ከአንጋፋዎቹ እነ አለማየሁ እሸቴ ጀምሮ፤ ፀጋዬ እሸቱ፣ ግርማ ተፈራ፣ አብነት አጎናፍር፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ዘቢባ ግርማ፣ አስጌ ዴንደሾ የመሳሰሉት ወጣት እና አንጋፋ ድምጻውያን በህብረትም በተናጠልም በአገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ስሜታቸውን አንጸባርቀዋል። ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ስለኢትዮጵያ የሚለውንና በርካታ ድምጻውያን የተሳተፉበትን አልበም እንዲሁም የቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮን/ አርማሽ ‹‹ቀና በልን›› በዚሁ አምድ መዳሰሳችን ይታወሳል።
በቅርቡ ደግሞ ንዋይ ደበበ እና ወንድወሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) ዜማዎችን አውጥተዋል። ግርማ ተፈራ እና ዘሪቱ ከበደም ለየራሳቸው አውጥተዋል። እስኪ ለዛሬው የንዋይን እና የወንዲ ማክን እናያለን።
አርቲስት ንዋይ ደበበ ‹‹አገሬን አልረሳም›› በሚለው ዘፈኑ በማይረሳት አገሩ ላይ ትልቅ አሻራ አስቀምጧል። አገራዊ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ይህ የንዋይ ዘፈን የሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ፕሮግራም ማስጀመሪያ እስከ መሆን ደርሷል። የመድረክ ዝግጅቶች ማድመቂያ ነው። ሌሎች የፍቅር እና የማሕበራዊ ጉዳዮች ዘፈኖቹ እንዳሉ ሆነው በአገር ጉዳይ ላይ እንኳን ብዙ ዘፍኗል። እነ በላይ ዘለቀን እና ሌሎች አርበኞችንና ጀግኖችንም ታሪካቸውን በሕዝብ ዘንድ ይበልጥ እንዲሰርጽ አድርጓል።
ታሪክ እና ጀግናን ለታሪክ የሚያስቀምጠው ንዋይ፤ አሁን ደግሞ ‹‹የታሪክ መዝገብ›› በሚል አዲስ ነጠላ ዜማ አውጥቷል። የዘፈኑ ጥቅል መልዕክትም አሁን ባለው አገራዊ ጉዳይ ላይ ነው። የዘፈኑ ክሊፕ ላይ ንዋይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለበት የአገር ባህል ጋቢ እና የጀግናውን የመከላከያ ሠራዊት ልብስ ለብሶ የተሰራ ነው።
ዛሬም እንደገና ነገም እንደገና
የቅድመ አያቶቼን የአባቶቼን ዝና
አርማ የሚያስከብር የሚያደርግ ገናና
ይወለዳል ጎበዝ ይወለዳል ጀግና!
እያለ፤ ኢትዮጵያ ጥንትም የጀግኖች አገር እንደሆነች፤ ዛሬም ጀግኖች እንዳሏት ይነግረናል። በዘፈኑ ክሊፕ ላይ የጥንት አርበኞች፣ የጥንት የጦር መሳሪያዎች፣ የአሁኑ የመከላከያ ሠራዊት ዓርማዎችና ትርዒቶች ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቦታዎች ይታዩበታል።
የታሪክ መዝገብ ድልን አበሰረ
የጀግናው ደም አጥንቱ መሰከረ
የነገር ጉንጉን ብሎም ከንቱ ሴራ
ከሸፈ ታሪክ ሰሪው ችቦ አበራ።
አገሬ ሸንተረሩ ወንዜ ዳርዳሯ
ሲዶልት የነበረ ከንቱ ሴራ
ድል እንጂ ማፈግፈግን ያለመደው
ጀግናችን ምሽግ ሰብሮ አዋረደው።
የኢትዮጵያን የድል ታሪክ ማስታወሻ
የአሉላ ዮሐንስን ክቡር ጋሻ
ከሃዲ አገር አፍራሽ ቢያስደፍረው
ዘመተ አዲስ ትውልድ ሊያስከብረው
የእነዚህ ስንኞች መልዕክት፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዶልት የነበረውን ሃይል ሴራ የኢትዮጵያ ልጆች እንዳከሸፉት መመስከር ነው። የእነ ራስ አሉላ አባ ነጋ እና አጼ ዮሐንስ አራተኛን ታሪክ ከሃዲዎች ቢያስደፍሩትም አዲሱ ትውልድ ግን የኢትዮጵያን ክብር እንዳስጠበቀው ይነግረናል።
ንዋይ አንጋፋ ስለሆነ ብዙ ተብሎለታል። ሥራዎቹም ለረጅም ዓመታት (ከ1970ዎቹ ጀምሮ) ተሰምተውለታል።
አርቲስት ወንደወሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) ወጣት አርቲስት ነው። የወንዲ ማክ የዘፈን ግጥሞች ከተለመዱት የዘፈን ግጥሞች ይለያሉ። በብዙ ዘፈኖች ውስጥ እንደምንሰማው የዘፈን ግጥም ብቻውን መቆም አይችልም። ይሄ ማለት ዜማውን ያልሰማ ሰው ግጥሙ ብቻውን ተጽፎ ቢያገኘው ግጥም አይመስለውም።
የወንዲ ማክ ዘፈኖች ግጥሞች ግን ብቻቸውን መቆም የሚችሉ ናቸው። ዜማውን ያልሰማ ሰው ግጥሞቹን ብቻቸውን ቢያገኛቸው ይተነትናቸዋል። ከውስጣቸው የሚወጣ ሃሳብ አላቸው።
ወንዲ ማክ ከሕዝብ ጋር የተዋወቀበት ዘፈኑ ‹‹ሺ 80›› የሚለው ዘፈኑ ነው። በነገራችን ላይ ይህ የወንዲ ማክ ዘፈን የወጣው ከአገራዊ ለውጡ በፊት ነበር። የዘፈኑ መልዕክትም ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊን ማገናኘት ነበር፤ እነሆ ትንቢቱ ሰምሮለት ዛሬ አንድ ሆነዋል።
በመገናኛ በአስመራ መንገድ
በደብረ ሲና ደሴ ላይ መውረድ
መቀሌ አድሬ ነግቶ መሳፈር
በአባ ሻዎል ላይ ካንቺ መንሸርሸር
አባ ሻውል አስመራ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው።
ይሄው አርቲስት በ2009 ዓ.ም ባወጣው ‹‹አባ ዳማ›› በሚለው ዘፈኑ የሕዝብ ለሕዝብን ቅርርብ አስተጋብቷል። ይህ ዘፈኑ በወቅቱ በጣም በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ተሰምቷል። በ ‹‹ዩ ትዩብ›› ከ19 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አይቶታል።
ወደ አሁኑ ሥራው ስንሄድ፤ ባለፈው ሳምንት ‹‹ምን ቢያዩብሽ?›› የሚል ርዕስ ያለው አዲስ ነጠላ ዜማ አውጥቷል። የዘፈኑ ሙሉ መልዕክት አገራችን ያለችበት ወቅታዊ ጉዳይ ይመለከታል። በተለይም የውጭ አገራትን የጣልቃ ገብነት ትኩረት ይታዘባል። ግጥሙ የራሱ ስለሆነ አርቲስ ስለአገርና ታሪክ ያለው አረዳድ የሚደነቅ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ዘፈኑ ክሊፕ ባይሰራለትም በምትኩ የታሪካዊ ቦታዎች ምስል እና የዘፈኖቹ ስንኞች በጽሑፍ ይነበባሉ።
ከዘፈኑ ርዕስ ስንነሳ ‹‹ምን ቢያዩብሽ›› ይላል። የአሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት መንግሥታት ኢትዮጵያ ላይ ቀን ከሌሊት እንቅልፍ አጥተዋል። ከጥንት ጀምሮ ዓይናቸውን ከኢትዮጵያ ላይ አይነቅሉም። ገባ ብለው ለመነካካት የሞከሩት ዋጋቸውን አግኝተው ስለተመለሱ በርቀት ሆነው ነው የሚከታተሏት። እናም፤ ከያኒው ይሄን ያህል ትኩረት ያደረጉብሽ ምን ቢያዩብሽ ነው ማለቱ ነው ።
ምን ቢያዩብሽ
ከበቡሽ
ሲበላ ሲጠጣ ሲቆረጥም ጮማ
ማንም ሳያደርሳት ከደጅ ከርማ እሷማ
አሁን ጊዜው ደርሶ ልጉረስ ብትል በእጇ
ሞፈር ቀንበር ቆርጣ አበጃጅታ ደጇ
አሳላፊው በዝቶ አላስቆርስ ቢሏት
ጠላና ጠጁንም ቀላቅለው ሊግቷት
አስካሪዋ ይስከር እሷ እንደሁ ቋሚ ናት።
‹‹አሁን ጊዜው ደርሶ ልጉረስ ብትል በእጇ›› አዎ! ኢትዮጵያ አሁን ልትነሳ፣ ልትበለጽግ ነው ሲባል፣ አዲስ ለውጥ ልታመጣ ነው ሲባል፤ ምቀኞቿ ሁሉ እንቅልፍ አጥተዋል።
እኔን ያስገረመኝ ሆድ ሆዴን የበላኝ
እኔን ያስገረመኝ የአሳላፊው ተንኮል
ለእሱ ማር ጠጅ ጥሎ ለእሷ ግን በስኳር
ስኳሩስ ባልከፋ የሸንኮራ ነው
በላይ በላይ ቢሉት ማስከሩ ምነው
ያም ከዚያ ያም ከዚያ ጦሩን ቢሰብቅብሽ
መምጫቸው እልፍ ሆኖ በጥብጠው ሊያጠጡሽ
ቃል ኖሮሽ ላትወድቂ ቢሽር እንጂ ኮሶሽ
የዘመናት ትብታብ ሲቆጣጥሩብሽ
አንድ ዓይን ገልጦ እንቅልፍ ምን ያህል ቢፈሩሽ
እነርሱ ገብቷቸው ያልገባን ልጆችሽ
ቆጥረን ያልደረስነው ስንት ነው አቅምሽ?
አዎ! ለራሳቸው የማር ጠጅ እየጣሉ ኢትዮጵያ የስኳር ጠጅ እንድትጠጣ ለማድረግ ያስባሉ። የስኳር ጠጅ ማለት ትክክለኛው ጠጅ ሳይሆን ስኳር በመጨመር ጣፋጭ አስመስሎ ደንበኛን ማጭበርበር ነው። ኃያል የሚባሉ አገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ አጥተዋል። አንድ ዓይናቸውን ብቻ ጨፍነው ነው የሚተኙት።
‹‹እነርሱ ገብቷቸው ያልገባን ልጆችሽ›› የምትለዋ ስንኝ በጣም ብዙ ነገር ትገልጻለች። ምዕራባውያኑ አገራት ኢትዮጵያን በሚገባ ያውቋታል። እነርሱ የሚያውቋትን ያህል እኛ አናውቃትም። ምን ሀብት እንዳላት ያውቃሉ፣ በአፍሪካ በቅኝ ያልተገዛች ገናና አገር መሆኗን ያውቃሉ። የራሷ ያልተበረዘ ባህል እንዳላት፣ የሥልጣኔ አስጀማሪ እንደሆነች ያውቃሉ። እነዚህ ኃያል የሚባሉ አገራት በአፍሪካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር እንድትኖር አይፈልጉም። ዳሩ ግን እነርሱ ያወቋትን ያህል እኛ አላወቅናትም።
መሶብሽ ካረጀ ሰበዙ ተስቦ
እንጀራሽ ከማን ነው የሚኖር ተደራርቦ
ሁሉም የኔ ከኔ ለኔ ያለብሽ
ከራስ ፍቅር ወድቆ ምጥ ቢያበዛብሽ
መውለጃሽ ተቃርቦ ማርያምም ቀርባሽ
ልናይ ነው ኢትዮጵያ ደርሷል ትንሳኤሽ!
‹‹ሁሉም የኔ ከኔ ለኔ ያለብሽ›› ለዜማ ማድመቂያ የገባ ስንኝ አይደለም። በኢትዮጵያ ሥልጣኔ እና ሀብት ላይ ‹‹የኔ፣ ከኔ ለኔ›› ያሉ ብዙ ናቸው። አንዳንዱ፤ ይህ አይነት ሥልጣኔ ወይም ምርት የእኔ ነው ይላል፤ አንዳንዱ ከእኔ ተወስዶ ነው ይላል። አንዳንዱ ደግሞ በዚህ በዚህ ምክንያት አሁን ላይ ለእኔ ነው የሚገባ ይላል። ትንሳኤዋ የመድረሱን ተስፋም ይነግረናል።
ውሃነትሽን አይተው
እርጥብ ተፈጥሮሽን የቅጥርሽን ስሪት
ገራገርነትሽን ሞኝ አድርገው እየሳሉት
ጠላትሽን ሆነና የተፈጥሮ ሀብትሽ
እነርሱ ረስርሰው በጥም ቢያቃጥሉሽ
ንሥር ሆነሽ ውጪ ታድሷል ጉልበትሽ
‹‹ውሃነትሽን አይተው›› የሚለው በብዙ ነገር ሊተረጎም ይችላል። የዋህነትሽን ለማለት ወይም በእማሬያዊ ትርጉሙ የውሃ ማማ መሆኗን ለመግለጽ፣ የዓባይ ወንዝ ባለቤት መሆኗን ለማሳወቅ የተጠቀመው ይሆናል። ቀጥሎ ካሉት ስንኞችም የምንረዳው በአባይ ጉዳይ ላይ የበዪ ተመልካች ሁኚ መባሏን የሚገልጽ ነው።
ነጭ ሽብር ቀይ ሽብር ሁሉንም አየነው
እናሸንፋለን እናቸንፋለን
የቃላት ልውውጥ ስንቱን አጋደለው
የእነርሱን አስይዘው የእኛን እያስጣሉ
ስንቶች ከራስ ርቀው ባዕድ ኮበለሉ
ሶሻሊስት ኮሚኒስት ሁሉንም ቃኘነው
አብዮት ዴሞክራሲ ጨፍነን ሞከርነው
ትምህርቱን ቁሱንም ሁሉንም ቃረምነው
መዘመን መዋስ ነው ብለን ደመደምነው
ተውሰው ቢለብሱት እንዳው ሞገስ የለው
የቀየህን ሰርዶ በቀየህ በሬ ነው
ጠበቅ አድርጎ መያዝ አገር በቀሉን ነው።
የእነዚህ ስንኞች መልዕክት፤ አገር በቀል የሆኑ ነገሮችን አጥብቀን መያዝ እንዳለብን እና በዚህም ኢትዮጵያ ራሷን የቻለችና ሁሉም ነገር ያላት መሆኗን ማሳየት ነው። ከምዕራቡም ከምሥራቁም ዓለም እያመጣን ሞክረነዋል፤ ግን መኮረጅ ብቻውን ለውጥ አላስገኘንም ነው። ስለዚህ አገር በቀል የሆኑ የራሳችን ነገሮችን ማወቅና ማሳወቅ አለብን ይለናል።
በአጠቃላይ በአገራችን የተፈጠረው ክስተት ከመጥፎ ነገር በጎ ነገር እንድናገኝ አድርጎናል። የሕዝብ አንድነት ከመፈጠሩ በተጨማሪ አርቲስቶች እንዲህ አይነት የፈጠራ ሥራዎቻቸውን አውጥተዋል። የአገራቸውን ገናናነት ለአዲሱ ትውልድ አሳውቀዋል። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ተሸርሽሮ የነበረው አገራዊ ስሜት በኪነ ጥበብ ሰዎችም ሆነ በሌሎች እንደ አዲስ ተነቃቅቷል። አርቲስቶች በዚህ ክስተት የአገራቸው ህልውና እንዲጠበቅ ከማድረግ በተጨማሪ ገላልጠው አሳውቀዋልና ሊመሰገኑ ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014