የሰብዓዊ መብት አክባሪነት እና አስከባሪነት የሚገለጸው እንዴት ነው? ሰዎችን ከማረጋጋት ይልቅ በማሸበር ጦርነትን ከማብረድ ይልቅ በማቀጣጠል፤ ሰላማዊ እና ተጎጂውን አካል ከመደገፍ ይልቅ በተፃራሪው ወንጀለኛውን በስውር አይዞህ እያሉ በማባበል ይሆን እንዴ? የሰብዓዊ መብት አክባሪ ነን ባዮቹ እየፈጸሙ ያለው ተግባር ግን ይህ ነው። በተለይ አንደኛዋ የዓለም መንግሥት የሰብዓዊ መብት ዋስ ጠበቃ ነኝ የማለት ያህል በየአገሩ እንደእርጎ ዝንብ ጥልቅ እያለች የምትበጠብጠዋ አሜሪካ ሥራዋ ሁሉ ተቃራኒ ሆኖ ዓለምን እየረበሸ ይገኛል። ድንቄም የዓለም መሪ የዓለም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አሉ የመስፍን እናት!
አሸባሪ አመሉ ነውና በየቦታው የተበታተነ እሳት ያነዳል። ሰዎችን ይማግዳል። ርህራሔ ብሎ ነገር አያውቅም። ወጣት፣ ሽማግሌ እና ሕፃን በየአካባቢው በአሸባሪው ሴራ ይሞታል። የአሸባሪው ጥፋት ፆታ እና ዘር አይለይም። ሴት፣ ወንድ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ … ብቻ ሁሉንም ይፈጃል። የሰብዓዊነት ጭንብል ለባሽዋ ደግሞ ይህንን ተግባር የምትቃወም አትመስልም። ከላይ ከላይ ለሰብዓዊነት ቆሜያለሁ የሰው ነፍስ ያሳሳኛል ትላለች። ነገር ግን ቀድሞም አሸባሪው በተለያዩ ክልሎች በተዘዋዋሪ የሚያስፈጽመውን ተግባር እያየች እንዳላየ እያለፈች ቆይታለች።
ነገሩ ተጧጡፎ ጭራሽ አሸባሪው አገር የማፍረስ ዕቅዱን ለመተግበር ሲንቀሳቀስ ከመቃወም ይልቅ ተቆርቋሪ ሆናለታለች። እያራገበች በየሚዲያው እና በየማሕበራዊ ድረገፁ በሰፊው በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረውን ችግር እያጋጋለች፣ የሳሳውን ተበጠሰ እያለች አንዳንዴም የበሬ ወለደ ዜና እየፈበረከች ወሬውን ታናፍሰው ያዘች። ይሔ ነው እንግዲህ ሰብዓዊነት ድንቄም ሰብዓዊነት!
የሰብዓዊ መብት ሲጣስ ይነዝረኛል የምትለዋ አገር ቀድሞ እንደዛ በየእስር ቤቱ በፒንሳ ጥፍር ሲነቀልና እንደበግ ሰው ተዘቅዝቆ ቆዳው ሲገፈፍ የት ነበረች? በጉዳይ አስፈፃሚዋ ሱዛን ራይስ በኩል መሪውን በዓለም አደባባይ በውግዘት እና በፍትሕ ተጠያቂነት ሳይሆን ቁጥር አንድ የምስራቅ አፍሪካ ሊቅ በማሰኘት ግዴታዋን ስትወጣ አልነበር። የዛን ጊዜ አሜሪካ በኢትዮጵያ የነበረው የሰብዓዊ መብት መጣስ አያሳስባትም ነበር? አሜሪካ ብቻ ሳትሆን የሰብዓዊ መብት ጭንብል ለባሾቹ ቀድሞም አምባገነን እና የሰብዓዊ መብት ገፋፊን ሲደግፉ ከመቆየታቸው አንፃር አሁንም እየፈጸሙ ያለው ተግባር ለምን ያስደንቀናል? በፊትም አሁንም ልምዳቸው ተመሳሳይ ነው። በእርግጥም መደነቅ የለብንም።
አንዲት ግራ የምታጋባ ሚስት የነበረችው አባወራ ሚስቱ ወደ ገበያ ስትሔድ ወራጅ ውሃ ይወስዳታል። አባወራውም ወሬውን ሲሰማ ‹‹ላም እሳት ወለደች እንዳትበላው ፈጃት እንዳትተወው ልጇ ሆነባት›› እንደሚባለው ያችኑ ግራ የምታጋባ ሚስቱን ሊያድን ወደ ወንዝ ወረደ። ሰዎች አጅበውት የት አካባቢ ውሃ እንደወሰዳት አረጋግጦ፤ ሚስቱን ለማፋለግ ለተገኙት ወዳጆቹ ወራጅ ውሃ ወሰዳት ከተባለበት ቦታ በላይኛው በኩል ፈልጉ አላቸው። እርሱም ውሃው ከሚወርድበት በተቃራኒ አቅጣጫ መፈለግ ጀመረ።
ሰዎቹ ግራ ተጋቡ ‹‹ምን ማለትህ ነው? ውሃ የሚወስደው ወደ ታች እኮ ነው።›› አሉት። ሰውየውም እኔ የሚስቴን አመል መች አጣሁት፤ እሷ ሁል ጊዜም የሚቀናት በተቃራኒው ነው አላቸው ይባላል። እነጭንብል ለባሾቹም ለምዶባቸው ድርጊታቸው ከስማቸው እና ከሚናገሩት ተቃራኒ ሆኗል። አሁን አሁን በፍጹም ቀጥተኛ የሰላም አካሔድ ብሎ ነገር አይገባቸውም። ተግባራቸው በተቃራኒው ዓለምን ማመስ ላይ ትኩረት አድርጓል። ለእዚህ ማሳያ አንደኛዋ አፍጋኒስታን ናት። ከአፍጋኒስታን በኋላ እነሊቢያ እና እነሶሪያ በሰብዓዊነት ስም በአገራቸው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው በመፈትፈት አገራቱን ለከፋ ጉዳት እና ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል።
እነኚሁ የሰብዓዊነት ጭንብል ለባሾች አሁን ደግሞ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዙረዋል። አሁን ምን ያህል ራስ ወዳድ መሆናቸውን በደንብ በተግባር ለዓለም አረጋግጠዋል። በተለይ ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊነት ጭንብል ለባሾችን ተግባር በአግባቡ ተረድተውታል። ነገር ግን ጭንብል ለባሾቹ ኢትዮጵያውያን የገባቸው አልመሰላቸውም። ነገሮችን ሁሉ እያዩ ያሉት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ብቻ ነው። ቢያንስ ተነቅቶብናል እዚህ ጋር እናጠምዝዝ አይሉም። በእነርሱ ቤት እየሰሩ ያለው ስውር ወጥመድ የኢትዮጵያ ሕዝብ አያውቀውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዓለም የፖለቲካ ሴራ የማይገባው ሕዝብ ነው። ነገር ግን በተቃራኒው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያልተረዱ፤ የታላቅነት እና የአሸናፊነት ታሪኩን ያልተገነዘቡ እነርሱ ናቸው።
አሸባሪውን፣ ጦርነት ከፋቹን እና ከሃዲውን ሕወሓት ከተደበቀበት ጉድጓድ አውጥተው በጦር ምክር እና በሚስጥር የሳተላይት ድጋፍ በመስጠት ብዙዎች እንዲያልቁ ማድረግ በእርግጥም እነርሱን እውነተኛ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ያደርጋቸዋል። በሚስጥር ከሚሰጡት ድጋፍ በተጨማሪ በእርሱ ብቻ ሳይሆን በአደባባይ ከቀላል የባለሥልጣናት የጉዞ ክልከላ ጀምረው ቀስ በቀስ አሸባሪ ሃይሉን እንደሚደግፉ በአደባባይ በተለያየ መልኩ ማሳየታቸውን ቀጥለዋል።
ከማሳያዎቹ መካከል የተዛቡ መረጃዎችን በሚዲያዎቻቸው ማስለቀቅ አንደኛው ነው። እጅግ በጣም የሚያስቀው የሰብዓዊነት ካባን እንደለበሱ የሚያሳብቅ መረጃን በገዛ ሚዲያቸው ለቀዋል። ሕፃናት ለጦርነት መሠማራታቸው እንደጀግንነት እንዲታይ በፊት ገፃቸው ላይ ለመብታቸው የሚታገሉ ጀግኖች ብለው አስነብበዋል። በየትኛው ዓለም ሕፃናትን በጦርነት ላይ ማሳተፍ ሰብዓዊ እንደሚያሰኝ ግልጽ አይደለም። እንግዲህ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎቹ ስለሰብዓዊነት የሚያስቡት በዚህ ልክ ነው ከተባለ እንዴት የዓለም የሰብዓዊነት ጠበቃ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያጠያይቃል።
አላበቁም በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ለውይይት በማቅረብ ማዕቀብ ለማስጣል የሰብዓዊ መብት ጭንብል ለባሾቹ ቢፍጨረጨሩም እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም። ጭንብል ለባሾቹ በድብቅ ‹‹ነፃ ናቸው›› በሚሏቸው ሚዲያዎቻቸው ከመጠቀም ባሻገር በአደባባይ በራሳቸው በኩል ሊያደርጉት የሚችሉትን ፈጸሙ።
አሜሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራትን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የቀረጸችው ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አገሪቱ የማስገባት የንግድ ዕድል ከ“አግዋ” ኢትዮጵያን አስወጥታታለች። በአርግጥ ለኢትዮጵያውያን “አግዋ” ቢጠቅማትም ከነፃነቷ ጋር ሊነፃፀር የማይችል ተራ ጉዳይ በመሆኑ ብዙዎችን የሚያስጸጽት አልሆነም። ይልቁኑ የሆነው በተቃራኒው ነው። ‹‹ዕቃ አላውስ ያለ ክፉ ጎረቤት ዕቃ ያስገዛል›› እንደሚባለው ኢትዮጵያም በእነርሱ ፍላጎት ላይ የተመሰረተው ዕድል ሲቆም ሌላ ራስን የማውጫ መንገድ መፈጠር ላይ ትኩረት አድርጋለች። ይህ በሌሎች ችሮታ ላይ ያልተመሰረተ መንገድ ደግሞ አስተማማኝ ይሆናል።
የጭንብል ለባሾቹ የግል ሀብት የሆኑት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እና ተሰሚነት ያላቸው ተቋማት የአሸባሪው ሕወሓት ደጋፊ ሆነው የኢትዮጵያ መንግሥትን በተመለከተ ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ ቢገኙም፤ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ፣ አሶሼትድ ፕሬስ፣ ቴሌግራፍ፣ ፍራንስ 24 እና ሌሎች ምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን አሸባሪው ሕወሓትን በመደገፍ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨታቸውን እንዲያቆሙ በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ ከመውጣት ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች እያጋለጡ ነው።
ነገር ግን መገናኛ ብዙኃናቸውን በመጠቀም አሁንም የመንግሥትን ትዕግስት እና የኢትዮጵያውያንን እውነተኛ ፍላጎት እና በአገር ውስጥም ሆነ በአሜሪካ እንዲሁም በተለያዩ አገሮች የሚካሔዱ ትልልቅ ሰልፎችን ለመዘገብ አልፈቀዱም። እንግዲህ ሰብዓዊነት እንዲህ እውነቱን መደበቅንም የሚያካትት ነው። እርግጥ ነው ምዕራባውያን የሚፈልጉት ቢሆን ኖሮ እንኳን በሚሊየን፣ በመቶ ሺህ እና በአስር ሺህ የሚቆጠር ሰው ሰልፍ የወጣባቸው ክስተቶች ቀርተው መቶ ሰው የተሰበሰበበት ሰልፍ እንኳ ይዘገብ ነበር። እንግዲህ የሚዲያ ሚዛናዊነት እዚህ ጋር አፈር በላ ማለት ነው።
ለነገሩ ሚዛናዊነት ሲባል በመስከረም ወር በሲኤንኤን ኒማ በተሰኘች ጋዜጠኛ ተላልፎ የነበረው የሀሰት ዘገባ ምን ያህል ሚዛናዊነት የሚባል ነገርን በጭራሽ ማዕከል እንደማያደርጉ አሳይቷል። በምንጭነት የአሸባሪው ሕወሓት አመራርን እና የቡድኑን አባላት እንዲሁም በማይካድራ ጭፍጨፋ የሚፈለጉ ነፍሰ ገዳዮችን ሳይቀር በመጠቀም ምን ያህል የጋዜጠኝነት ሥነምግባርን ጠብቀው እንደማይሰሩ አረጋግጠዋል። ደግነቱ ይህ ተግባር በማሕበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያውያን ተጋልጧል።
በሚዲያ ሽፋን ሕወሓትን ከማገዝ ባሻገር እነአሜሪካ፣ እንግሊዝና አየር ላንድ የፈጠሩት የዲፕሎማሲ ጫና እና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲሁም ለጁንታው በሳተላይት መረጃ መስጠት እና የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸው ሲታሰብ እውነት እነርሱን ራሳቸውን በዓለም አደባባይ አሸባሪዎች ማለት ሳይሻል አይቀርም። ታዲያ አሸባሪን ማደራጀት እና መደገፍ በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ መሪን እና የተመሰረተ መንግሥትን በሌላ ለመተካት ማሰብ አሸባሪ ካላሰኘ ሌላ ምን አሸባሪ ሊያሰኝ የሚችል ድርጊት ይኖራል?
ሰው መግደል ሕዝብ መጨረስ ንብረት ማውደም ከሆነ አሸባሪ የሚያሰኘው የሰብዓዊነት ጭንብል ለባሾቹ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ድርጊቱን እየፈፀሙት ነው። ስለዚህ በዓለም አደባባይ አሸባሪ ሊሰኙ ይገባል። ይህ ተግባራቸው አሁንም ቀጥሏል። በተለያየ መልኩ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል ብቻ ሳይሆን፤ የዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር በኩል እየፈፀሙት ያለው ተግባርም በጣም የሚያስገርም ነው። ሰብዓዊነት እና ኢትዮጵያን ማፍረስ ኢትዮጵያን ማዳከም ምን እንደሚያገናኘው ግራ ያጋባል።
አሁን ደግሞ ውስጥ ውስጡን የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲወጣ ለማድረግ ግፊት ጀምረዋል የሚል ወሬ እየተናፈሰ ነው። እዚህ ላይ በእርግጥ ጭንብል ለባሾቹን ኢትዮጵያ አስግታቸዋለች ለማለት ያስደፍራል። የአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት የሆነችዋ አገር በኢኮኖሚ ነፃነት እና በዴሞክራሲ ለአፍሪካውያን ምሳሌ በመሆን አፍሪካን ለዘላለም የማደኽየት ዓላማቸው እንዳይሳካላቸው እንደምታደርግባቸው ገምተዋል። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የምትልበት ዕድል የለም። በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ መሪ መሆኗ የማይቀር ነው።
ጦርነት የአንድን አገር ዜጎች ሕይወትና ንብረት ብቻ ሳይሆን የአገር ህልውናን አደጋ ውስጥ የሚከት ክፉ መቅሰፍት መሆኑ አይካድም። ኢኮኖሚውን በማሽመድመድ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ቀውስ የሚፈጥር እንደሚሆን ይታመናል። ነገር ግን ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ከገባችበት ጦርነት በፍጥነት መውጣቷ አይቀርም። ፊቷን ወደ ልማት በማዞር የዕድገት መስመሯም የተቃና እንደሚሆን አያጠራጥርም። ነገር ግን ለዚህ ሁሉ አዛኝ መሳይ ቂቤ አንጓች የሆኑት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች በየትኛውም መልኩ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙልን እንፈልጋለን።
‹‹በቃችሁ! እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ›› ለማለት፤ የተለያዩ ሰልፎች፣ የነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተመንግሥት ዘመቻ እና ሌሎችም የእጃችሁን አንሱልን አቤቱታዎች ቀርበዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደብዳቤ አስገብቷል። ሁሉም በየበኩሉ እባካችሁን ተውን ብሏል። ሰሚ ጠፋ እንጂ!
በኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት እንዲመጣ ከተፈለገ የአሜሪካ መንግሥት ሁሉንም ነገር ለኢትዮጵያውያን ይተወው። የአሜሪካ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ማንኛውም በሰብዓዊነት ስም ጭንብል የለበሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ አገራት እጃቸውን ከኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ማንሳት አለባቸው። እምቢ ካሉ ግን ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ሉዓላዊነት የማይተኙ መሆናቸውን በቅኝ ግዛት አልገዛም ማለታቸውን ማስታወስ ሳያስፈልግ አይቀርም። ሕዝብም ሆነ መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ ለማንበርከክ ለሚንቀሳቀስ ሃይል ትዕግስት የላቸውም። ኢትዮጵያውያን የበላይ እንሁን አይሉም። ፍላጎታቸው ውስን ነው። እርሱም ነፃነት እና እኩልነት ብቻ ነው።
ኢትዮጵያውያን በራሳቸው መንገድ የራሳቸውን ዓላማ አንግበው ነገ የተሻለች ሀገር መሰናክሎችን የምትሻገር፣ የዜጎቿን ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ የምታስጠብቅ፣ ዴሞክራሲ እና ነፃነት ተደጋግፈው በተጨባጭ የሚተገበርባት አገር እንድትኖራቸው አቅደዋል። ዕቅዱን በራሳቸው መንገድ ቀርጸው ለመንደርደር መንገድ ጀምረዋል። አሁን ግን መሰናክል አጋጥሟል። መሰናክሉን ለማለፍ ከባድ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ራስን የማስከበር ችግር የለባቸውም። ስለዚህ ይህንንም መሰናክል ያልፉታል። ነገር ግን አሜሪካም ሆነች ሌሎች ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚሹ ሃይሎች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014