የምአራብ ዓለም መንግሥታትና በነሱ የሚዘወሩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ከዓለም አቀፍ መርሆችና ከሙያ ሥነ ምግባርን በተጻረረ መልኩ በኢትዮጵያና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ ከፍ ያሉ የተቀናጁ ዘመቻዎችን በስፋት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። አገሪቱ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ከማዛባት አንስቶ ፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትን መሳሪያ በማድረግ ጫናዎችን ለማሳረፍ የተቻላቸውን ሁሉ እየሰሩ ነው።
በአንድ በኩል ለአገሪቱ ሰላምና ደህንነት ጠንቅ የሆነው አሸባሪው ሕወሓት ተፈጥሯዊ ሞቱን እንዳይሞት ፤ በዚህም አገርና ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እንዳገኝ በትጋት እየሰሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ ጫናዎችን እያሳደሩ፤ እራሳቸውን የሰላም ሀዋሪያ ለማድረግ ከፍ ባለ ድምጽ እየጮሁ ነው።
እነዚሁ አንዳንድ የምዕራብ አገራት መንግሥታት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው የሰላም ጠንቅ የሆነውን የአሸባሪውን ሕወሓት የአደባባይ የሽብር ተግባራት ከማውገዝ ይልቅ ቡድኑ በሽብር ተግባሩ እንዲገፋበት የልብ ልብ የሚሰጡ ድጋፎችን እያደረጉለት ነው። ከቁሳቁስ ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃኖቻቸውም ለቡድኑ የተጠናከረ የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ እየሰጡ ነው።
ለዚህም ዋሽንግተን ፖስትን ጨምሮ ሲኤንኤ፣ ቢቢሲ፣ አልጀዚራና ሌሎች የምዕራብ ዓለም የመገኛኛ ብዙኃን ተቋማት በአገሪቱ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ በሚጻረር ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባር በጎደለውና አሳፋሪ በሆነ መልኩ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ስለ ኢትዮጵያ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ሞራል አልባ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ነው።
በየዕለቱ ዲስክ ላይ ቁጭ ብለው የሚፈበርኳቸውን የተዛቡ መረጃዎች ሰበር ዜና አድርገው ከማቅረብ ጀምሮ ፤ በሕዝብ ሙሉ እውቅና ወደ ሥልጣን የመጣውን የአገሪቱን መንግሥት ስምና ምግባር የሚያጠለሹ የተቀናጁ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ውስጥ ተጠምደው ይገኛሉ።
ሰሞኑን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው የአገሪቱን እና የሕዝቦቿን ሰለምና ደህንነት ለማስከበር ያለበትን ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ የጀመሩት የተለመደ ማላዘን የዚሁ መሰሪ መንገዳቸው አካል ነው።
“የዓለም ሰላም ኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጦርነት ለመምራት ወደ ግንባር ዘመተ” የሚሉና ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ዜናዎች በሰበር ዜናነት ሲያስተናግዱ ፤ በነዚህ ሰበር ዘገባዎቻቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ሀዋሪያነት ለማጠልሸት በስፋት ሲሰሩ እየታየ ነው።
እነዚህ የመገኛኛ ብዙኃን በዘገባዎቻችው ሁለት ነገሮችን ማስተዋል እንዳልቻሉ መገመት አይከብድም። አንደኛው
ለኢትዮጵያውያንና ለመሪዎቻቸው አገር እና የአገር ነጻነት የቱን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው፤ ዋጋውም በሕይወታቸው የሚወራረዱት እንደሆነ ፤ ይህም በትልቁ ታሪካቸው በደማቅ ቀለም የተጻፈ እና በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የታተመ መሆኑን አለመረዳታቸው።
ሌላው ደግሞ የሰላም ኖቤል ሽልማት የሚዘጋጅበትን ምክንያት በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ይህም ሽልማቱ ተሸላሚዎችን ለምዕራቡ ዓለም ሴራዎች የመዘጋጃ እውቅና ማሰባሰቢያ መድረክ አድርጎ ከማሰብና ይህንን የተዛባ አስተሳሰብ በተሸላሚዎች ላይ ለመጫን የሚደረግ ያልተገባ ጫና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚያስችል ቁርጠኛነት በኢትዮ-እርትራ መካከል የነበረውን ግጭት በድርድር በመፍታታቸው፤ በአካባቢው ሰፍኖ የነበረውን በጠላትነት የመፈላለግ ስሜት በወዳጅነት መቀየር በመቻላቸው ነው። ይህን ማድረጋቸው የፈጠረውን የሰላም አየር ከማንም ይልቅ የቀጠናው አገራት ሕዝቦች በመተንፈስ ያጣጣሙት ነው። ይህም ከእውቅናውም በላይ ነው።
በርግጥ ቀድሞውንም ቢሆን በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ግጭቶችን በመፍጠር ቀጠናውን የግጭት ቀጠና በማድረግ ተጠያቂ የሆነው አሸባሪው ሕውሓት መሆኑን ለመቀበል ነጻ ህሊና ላለው አካል፤ ይህንን ሃይል ለማስወገድ የሚደረግ ትግል የቀጠናውን ሰላም በጠንካራ መሰረት ላይ የማዋቀር ተልዕኮ እንደሆነ ለመረዳት የሚከብደው አይሆንም።
ይህ አሸባሪ ቡድን ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንግሥት እና በሕዝብ የቀረቡ የተለያዩ የሰላም ጥረቶችን ገፍቶ የጦርነት አሳት በእብሪት በመጫር የሕዝባችንን ሰላም ብቻ ሳይሆን የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ጨምሯል፤ ግጭቱን ቀጠናዊ ለማድግ የሚያስችሉ ሙከራዎችን አድርጓል። ወደ ኤርትራ ሚሳኤል በመተኮስ ፍላጎቱን በተግባር አሳይቷል።
ይህንን ከግጭት ማትረፍ የሚፈልግ፤ ስለ ሰላም ማዜም ማነስ መስሎ የሚታየውን ቡድን በለኮሰው እሳት ነድዶ እንዲቃጠልና አመድ እንዲሆን ማድረግና ይህንን እውን ማድረግ የሚያስችል ተልዕኮን መምራት ቀርቶ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ተሳታፊ መሆን ከፍ ያለ የሰላም ሀዋሪያነት ነው።
ይህን ደግሞ ስለ ሰላም በእውነተኛ ልብና መንፈስ የሚያዜሙ በቀላሉ የሚረዱት እና የሚደግፉት ነው። ሰላም ስለ ሰላም በማዜም ብቻ የሚገኝ ሳይሆን፤ ስለ ሰላም ማሰብ ማነስ ነው ብለው የሚያስቡ ኃይሎችን በተጨባጭ አለማነስ መሆኑን በማሳወቅ የሚገነባ እና የሚጠናከር ጭምር ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እያደረጉ ያሉትም ይህንኑ ነው። ይህም የሚያስወግዝ ሳይሆን ዓለም አቀፍ እውቅና የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/2014