‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡
አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም››
የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ
ይህ ታሪካዊ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ መላው ሕዝባችንን በአንድ መንፈስ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ፋና ወጊ የሆነውን የዓድዋ ድል እውን ያደረገ፤ የቀደሙት አባቶቻችንን የነፃነት የተጋድሎ ታሪክ በማደስ ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው የቱን ያህል ቀናኢ እንደሆኑ ለዓለም በተግባር ማስመስከር ያስቻለ ነው።
የክተት አዋጁ የኢትዮጵያውያንን መንፈሳዊ ልእልና፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች መሠረት ያደረገ ነው፤ ኢትዮጵያውያን መሪዎች ለአገር እና ለነፃነት ጉዳይ የቱን ያህል ጥንቁቅ እንደሆኑ በተጨባጭም ያሳየ ነው። የአገርን ጉዳይ የቱን ያህል ከፍ ባለ ጥበብና ማስተዋል እንደሚመለከቱት፤ ለዚህ የሚሆን የዳበረና ያደገ ባህል ባለቤቶች መሆናቸውንም ያስመሰከረ ነው።
ከዚህም በላቀ በኢትዮጵያውያንና በመሪዎቿ መካከል በአገር ሉአላዊነትና ነፃነት ጉዳይ ጥልቅ መናበብ እንዳላቸው ያሳየ፤ ውጤቱም ታላቁን የዓድዋ ድል ለዓለም የጥቁር ሕዝቦች በማብሰር የአልገዛም ባይነትን ጠንካራ መንፈስ መፍጠር ያስቻለ ነው። የተዛቡና ዘርን መሠረት ያደረጉ አስተሳሰቦችን በተጨባጭ ማረምና ማስተካከል ያስቻለም ነው።
ኢትዮጵያውያን መሪዎች በየዘመኑ ከአገራቸው የሚያስበልጡት ሥልጣንም ሆነ ሕይወት እንደሌላቸው በቀደመው ዘመን አጼ ዮሐንስ በመተማ፤ አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ አጼ ምኒልክ በዓድዋ በተጨባጭ ለዓለም
አስመስክረዋል። ይህም የመሪዎቻችን የመስዋእትነት ገድል የነፃነትና የአትንኩኝ ባይነታችን ታሪካችን ጉልህ ቀለም ነው።
ይህ የመሪዎቻችን ራስን ለአገር ነፃነትና ሉአላዊነት መስዋዕት አድርጎ የማቅረብ የጸና ቁርጠኝነቱ ቀናኢ የሆነ ትውልድ በየዘመኑ በመፍጠር አገራችን ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ነፃነቷ እና ሉአላዊነቷ ተጠብቆ እንዲኖር ከፍ ያለ አቅም ሆኗል። አገር የህልውና አደጋ ሲያጋጥማትም መሪውን ተከትሎ የሚተም ኃያል ሰራዊት መፍጠር አስችሏታል።
ዛሬም በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ እየሆነ ያለው የዚሁ ታሪክ ቀጣይ ምዕራፍ ነው። የአገር ህልውና በታሪካችን ባልታየና በማይታወቅ ደረጃ በባንዳዎች አደጋ ውስጥ ገብቷል። ጠላቶቻችን በጦር ሜዳ ተሰልፈው ሊያሸንፉን የሚችሉበት አቅም ስለሌላቸውና መቼም ቢሆን ይህንን ማድረግ ስለማይችሉ በአሸባሪው ሕወሓት በኩል የዘመናት መሻታቸውን እውን ለማድረግ ባላቸው አቅም ሁሉ እየተንቀሳቀሱ ነው።
በዓድዋ ወቅት ያደረጉትን ኢትዮጵያውያን በኃይል የማስገዛት፤ ነፃነታቸውን ገፎ አንገት የማስደፋት እኩይ ዓላማን ከፍ ባለ መልኩ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በሚያስችል ሴራ አደባባዮችን ሞልተዋል። ሴራቸውም የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አቅምና የተጋድሎ ሰብእና የጠየቀበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ታሪክ ሰሪውን ሕዝብ ለአዲስ ታሪክ ራሱን እንዲያዘጋጅም አስገድዶታል።
ከዚህ የተነሳ አገርን የመታደግና የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት የወደቀባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀደም ባለው ጊዜ ለመላው ሕዝባችን የክተት ጥሪ አቅርበዋል። ጥሪያቸውን ተከትሎም ሕዝባችን ከዳር እስከዳር ከፍ ባለ የእናት አገር ፍቅርና የታሪክ ሰሪነት መንፈስ ለማይቀረው ታሪካዊ ፍልሚያ ወደ ግንባር እየተመመ ይገኛል።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደ ዓድዋው ጀግና አጼ ምኒልክ ጦርነቱን በግንባር ሆነው ለመምራት መንቀሳቀሳቸውን በመግለጽ አይቀሬውን የሕ ዝባችንን ድል ለማብሰር ወደ ጦር ሜዳ አ ምርተዋል።
በጉዞ መልዕክታቸውም «ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የአሸናፊዎች ስም ነው፤ የነፃነት ምልክት ነው። አልጠራጠርም፣ የእኔ ትውልድ ለአሸናፊ ስሙና ለነፃነት ምልክቱ የሚጠበቅበትን ዋጋ ከፍሎ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በክብር መዝገብ ላይ በወርቅ ብዕር ያትማል» ሲሉም አብስረዋል።
በርግጥም ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ማንም ሊቆም አይችልም። በዘመናት ሂደት በመስዋዕትነት ደም የተገነባው ኢትዮጵያዊነት በአዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ህያው ሆኖ በአዲስ የድል ብስራት ከፍ ባለ ልእልና የሚታደስበት የሽግግር ወቅት ላይ ነን። ዳግማዊውን ዓድዋ በአንጸባራቂ ድል ዕውን ለማድረግ እንደ ሕዝብ ከመሪያችን ጋር ከትተናል።
ትናንት በዓድዋ አባቶቻችን በታላቅ የአገር ፍቅር መንፈስ ወደ ጦር ግንባር ተመው በከፈሉት መስዋዕትነት ባስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል መሆን እንደቻሉ፤ እኛ ልጆቻቸው ዳግም ዓድዋን በአንጸባራቂ ድል ዛሬ ላይ በመድገም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን የሚችሉበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንከፍታለን።
ይህ የታሪክ ምዕራፍ ለኢትዮጵያዊነት አዲስ ውበት፤ አዲስ ልእልና የሚያጎናጽፍ ነው፤ ይህንን ታሪክ ለመስራት ራሱን ያዘጋጀው ይህ ትውልድና ይህንን ትውልድ የአዲስ ታሪክ ባለቤት ለማድረግ ቀን ተሌት ከፍ ባለ ቁርጠኝነት እና የአገር ፍቅር ስሜት እየተጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታሪኩ እንቁዎች ናቸው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 15/2014