በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ጋዜጣው በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ይዟቸው የወጡ ወንጀል ነክና የፍትህ ዘገባዎችን እንዲሁም ወጣ ያሉ የሚያስገርሙ ዘገባዎች ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
1,370 ጥይት ቀረጥ ሳይከፈልበት ተያዘ
ቀረጥ ያልተከፈለበት ፩ሺ ፫፻፸ ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ጥይት ከጂማ ከተማ ተይዟል። ጥይቱን ከአዲስ አበባ ከፋ ጠቅላይ ግዛት ጂማ ከተማ ይዘው የገቡት አቶ አብጠው ዋሴ የተባሉ ሰው ናቸው።
ጥይቱ የኮንትሮባንድ መሆኑንና ህጋዊ ቀረጥ ያልተከፈለበት መሆኑ በጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ከተጣራ በኋላ ክሱ ጂማ ፪ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተከሳሹ ፶ ብር እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል። ጥይቱ በሙሉ ውርስ ሆኖ ለመንግሥት ገቢ ሆኗል።
ሚያዝያ 19 ቀን 1956 አ.ም
ወንበዴው በጭቁን ገበሬ ተደመሰሰ
ደብረ ብርሃን (ኢ-ዜ-አ-)በመንዝና ግሼ አውራጃ በውንብድና ተግባር ተሰማርቶ የብዙ አርሶ አደሮችን ሕይወት ሲያጠፋና ንብረት ሲያወድም የነበረ አንድ ወንበዴ ታኅሳስ ፲፩ ቀን ፸ ዓ.ም በአንድ ጭቁን ገበሬ የተገደለ መሆኑን የአውራጃው አስተዳዳሪ ገለጡ።
ይኸው ንጉሤ አየለ የተባለው ከለየላቸው አድኃሪያን ከነመርዕድ ብሩ ጋር በማበር ለብዙ ጊዜ ፀረ አብዮት ድርጊት ይፈጽም እንደነበር ታውቋል።
ሆኖም ከሰፊው ሕዝብ ተደብቆ መኖር ስለማይቻል አቶ ደጀኔ ማሞ የተባለው ጭቁን ገበሬ ከተደበቀበት ሥፍራ ድረስ በመሄድ በጥይት ተኩሶ ሊገድለው የቻለ መሆኑን አስተዳዳሪው ገልጠዋል።
ወንበዴው በተገደለበት ወቅት አንድ ካርቫይ ጠመንጃ ከ፵ መሰል ጥይቶች ጋር ተገኝቶበታል። አብዮተኛው አርሶ አደር ስለወሰደው ቆራጥ ርምጃ ከአውራጃው የአብዮትና ዘመቻ አስተባባሪ ከፍተኛ ምስጋና ከማግኘቱም በላይ አንድ ምንሽር ጠመንጃ ከ፶፭ መሰል ጥይቶች ጋር ተሰጥቶታል።
(ታኅሳስ 6 ቀን 1970 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ታማኙ ሾፌር ቦርሳውን አስረከበ
ሐረር (ኢ-ዜ-አ-) አቶ ብሥራት መንገሻ የተባለው በሐረር ከተማ ፈረስ መጋላ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ማቆምያ ፴፭ ብርና ልዩ ልዩ ጽሁፎች የሚገኙበትን የሴት ቦርሳ ወድቆ በማግኘቱ የካቲት ፳፭ ቀን ሐረር ከተማ ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ አስረክቧል።
የቦርሳው ባለቤት ባመገኘቱ ንብረቱ በጣቢያው የሚገኝ መሆኑን የጣቢያው አዛዥ ሻምበል ውብሸት ፋንታ ገለጡ።
(መጋቢት 4 ቀን 1960 የታተመው አዲስ ዘመን)
ሐሰተኞቹ ዳኞች ተቀጡ
አርባምንጭ (ኢ-ዜ-አ-) በገሙጎፋ ጠቅላይ ግዛት በገሙ አውራጃ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ በሸንገሌ ቀበሌ የዳኝነት ሥልጣን ሳይኖራቸው ዳኝነት እየተሰየሙ ህዝቡን ሲያጭበረብሩ የተገኙት አራት ሰዎች ምዕራብ ዓባያ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሰው ቀርበው አድራጎታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው በ ፮ ወር እሥራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል።
እነዚህም ሐሰተኞች መኩሪያ በልአ አቦዬ አይካ ቶሃ ቶምባርና ቴራ ቀልሐ የተባሉ መሆናቸውን የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መኮንን አበበ ገልጠዋል።
(መጋቢት 4 ቀን 1960 የታተመው አዲስ ዘመን)
ኮብልለው የነበሩ 44 ሰዎች ከነመሣሪያቸው ገቡ
ዲላ(ኢ/ዜ/አ/) በአድኃሪያን ስብከት ተታለው በጌዴኦ አውራጃ በፍስሃ ገነት ወረዳ በገለና ሸለቆ ጫካ ገብተው የነበሩ ፵፬ ሰዎች ለፀረ አብዮት ድርጊት ይገለገሉባቸው የነበሩትን ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች እንደያዙ ባለፈው ሐሙስ ምህረት ጠይቀው እጃቸውን ለአውራጃው አስተዳዳሪ ሰጥተዋል፡፡
የአውራጃው አስተዳዳሪ በዚሁ ጊዜ በሰጧቸው ምክር በአብዮቱ አፈንግጠው ጫካ ገብተው የነበሩ ሁሉ ምህረት ጠይቀው ከተመለሱ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በወጣ ዓዋጅ መሠረት ምህረት የተደረገላቸው መሆኑን ገልጠው አሁንም ወደየሰፈራቸው ተመልሰው ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል ያለ ሥጋት መኖር የሚችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የወንበዴዎቹ መሪ የነበረው በበኩሉ በተናገረው ቃል በአንዳንድ አወናባጆች ስብከት ተታለው የፈጸሙት ፀረ አብዮት ድርጊት የፀፀታቸው መሆኑን አረጋግጧል።
ጦጣ ሕፃን ገደለች
ደብረዘይት (ኢ-ዜ-አ) ከተወለደች 22 ቀናት የሆናት የአቶ በቀለ ነገዎ አንዲት ሴት ሕፃን በጦጣ ተነክሳ ሞተች። ሕፃኗ ተነክሳ የሞተችው በአድአ ወረዳ በደንካካ ቀበሌ ነው።
ይህ ለማዳ የሆነው የአቶ ለገሠ ገብረመስቀል ጦጣ ከታሰረበት ቦታ አምልጦ ሕፃኗ ወደ ምትገኝበት ቤት በመግባት ሕፃኗን ነክሶ የገደላት መሆኑ ታውቋል።
የጦጣውም ባለቤት አቶ ለገሠ ገብረመስቀል በፖሊስ ተይዘው ለምርመራ ከጣቢያ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
(መጋቢት 3 ቀን 1960 የታተመው አዲስ ዘመን)
ላሟ ፲ ጥጃዎች ወለደች
አሰላ(ኢ-ዜ-አ) አንዲት ላም በአንድ ጊዜ አሥር ጥጃዎች ወለደች። ከተወለዱት አስር ጥጆች መካከል አንዱ በተፈጥሮው ትክክለኛ ጥጃ ሲሆን፤ ፱ኙ ደግሞ መጠናቸው በጣም ትናንሽ ነበር። እነዚሁ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑት ጥጆች ወዲያውኑ ሲሞቱ መጠኑ ከነርሱ ከፍ ይል የነበረው ፲ኛው ጥጃ ደግሞ ፮ ቀን ቆይቶ ሞቷል።
የላሚቱ ባለቤት አቶ ወትዩ ድልበቶ የሚባሉት ሲሆኑ፤ በአርሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላ አውራጃ ኮፈሌ ወረዳ ቆሬ መደጋ በሚባለው ቀበሌ የሚኖሩ መሆናቸው ተገልጧል።
(መጋቢት 15 ቀን 19 60 የታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014