አሸባሪው ሕወሓት በእናት አገሩ ላይ የክህደት ጥቃት ከሰነዘረበት ወቅት አንስቶ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ግፎችን መፈፀሙ የሚታወቅ ነው። በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶች የማውደም፣ ሴቶችና ሕጻናትን አስገድዶ የመድፈር፣ ንጹሐን ዜጎችን በግፍ የመጨፍጨፍ ስልት በመቀየስ በተግባር ሲፈፅመውም ተመልክተናል። እነዚህን ጸያፍና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ማድረጉ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጥሎም አልፏል።
አሸባሪው ሕወሓት እነዚህን የሽብር ሥራዎቹን ሲያካሂድባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል የአፋር ክልል አንዱ ነው። የአፋር ክልል የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጪ ንግድ የሚቀላጠፍበት ወሳኝ ስትራቴጂክ ስፍራ መሆኑን ያወቀው ይህ አሸባሪ ቡድን ይህንን ክልል በመቆጣጠር ከአቅሙ በላይ ተወጥሮ ለመገኘትና የመደራደር አቅም ለመፍጠር ካለው ከንቱ ምኞት የተነሳ ብዙ የጥቃት ዒላማዎቹን ሰንዝሯል። በአፋር ሕዝብ ላይ የፍርሃት መንፈስ ለመፍጠር በማሰብም ህጻናት ሳይቀር የተጨፈጨፉበትን የጋሊኮማ የጅምላ ግድያ በፍጹም የአረመኔያዊነት መንፈስ ተግብሯል።
ይህን ሴራ የተረዳው አገር ወዳዱ የአፋር ሕዝብ የአገሪቷን ዳር ድንበር የማስጠበቅ የቀደመ ታሪኩን በማስታወስ በአገር ጥቅም ላይ የማይደራደረው የአፋር ሕዝብ ኮሽታውን ሳያሰማ አሸባሪው ሕወሓት ያሰለፈውን ወራሪ ኃይል ደጋግሞ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ወደተመኘው ሲዖል ሸኝቶታል። ስለሆነም ለእነዚህ ለአገራቸው ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ላሉት የአፋር ልጆች ትልቅ ክብር መስጠት ተገቢም አስፈላጊም ይሆናል።
የአገራችን በኢኮኖሚ መበልጸግ ብሎም የሕዝቦች አንድ መሆን የማይመቸው አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለመበተን ከአፋር ክልል ሕዝብ ሲጀምር የሀፍረት ማቁን ለመከናነብ በቅቷል። አገር ለማፍረስ የሚቅበዘበዘውን አሸባሪ ሕወሓት በመቅበር ረገድ የአፋር ሕዝብ አሻራውን አሳርፏል፤ አሁንም እያሳረፈ ይገኛል። በጀግንታቸውና በጽናታቸው “ምድራዊ ድሮን” የሚል ቅጽል ስም እስከማግኘት የደረሱት የአፋር ጀግኖች ሕወሓት በከፈተባቸው ጦርነት ሳያፈገፍጉ ወደፊት በመግፋት የተለያዩ ከባድ መሳሪያዎችን ማርከዋል ፤ ጠላትን ማንበርከክም ልምዳቸው አድርገዋል።
የአፋር ሕዝብ ጀብዱ በዚህ አያበቃም። የአፋር ሕዝብ አስቸጋሪውን መልክዓምድር በጥበቡ ተጋፍጦ ኑሮውን የሚመራ፣ ከተፈጥሮ የተሰጠውን የአዋሽ ወንዝን በመጠቀም በረሃውን ወደ ልምላሜ መለወጥ የቻለ ሕዝብ ነው። ከአፋር ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ የሚወድ፣ እንግዳ ተቀባይና በጋራ የሚኖር፣ በአገሩ ክብር ላይ ለሚመጣበት ጠላት ደግሞ የማይበገር ኩሩ ጀግና ሕዝብ መሆኑን አስመስክሯል።
የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በማንነቱ ለመጣ ወራሪ ኃይል ምህረት እንደሌለው በዚህ ጦርነት ደጋግሞ በማሳየት የማይረሳና የማይደበዝዝ የታሪክ ገድል ፅፏል። አፋርን ከኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ከአፋር ውጭ ማሰብ የማይቻል መሆኑን እንኳን ”እኛ ግመሎቻችን ዳር ድንበሯን ያውቁታል” በማለት ለአገራቸው ያለቸውን ክብርና አይደፈሬነት ለሽብርተኛው ቡድን በሚገባው ቋንቋ ነግረውታል።
የአፋር ሕዝብ አሸባሪው ቡድን በአፋር ክልል የፈጸመው ወረራ በአንድ ክልል ሕዝብ ብቻ ላይ ያተኮረ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የመዳፈር ድርጊት መሆኑን በመረዳት ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት መድረሻ አሳጥቶታል፤ አሸባሪው ቡድንም በመጣበት ልክ በተደጋጋሚ ተደምስሶ አፋር መቀበሪያው ሆኗል።
የአፋር ሕዝብ ከመንግሥት የተቀበለውን የሕልውና ጦርነት በመቀላቀል፣ ወረራ የፈፀመበትን አሸባሪ ሕወሓት ለማንበርከክ የተጣለበትን ሕዝባዊና ታሪካዊ አደራ በሚገባ ተወጥቷል። ለዚህም የጠላቶቹን ዓላማና ሴራ በአግባቡ ተገንዝቦ፣ ነጻነቱንና ክብሩን ለማረጋገጥ አጥብቆ በመፋለም፣ ለአንድ አገሩ ኢትዮጵያ ውለታ የዋለ ሕዝብ ነው። የአገር ጠላት የሆነውን የሽብር ቡድን ተገቢውን አጸፋ በመስጠቱም ምንግዜም ታሪክ የሚያስታውሰው ነው።
በአጠቃላይ የአፋር ሕዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬም ለሰንደቅ ዓላማው ክብርና ለአገሩ ሉዓላዊነት ዋጋ እየከፈለ ሲሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለአገራቸው ፍቅር ሲሉ አገር ለማፈራረስ የተነሳውን የአሸባሪውን ሕወሓት ጥቃት ለማክሸፍና አንጸባራቂ ድል ለመጎናጸፍ ከምንጊዜውም በላይ በጠነከረ አገራዊ ስሜት በፅናት ቆመዋል። ስለሆነም የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጫ የሆነውን ይህንን የሕዝቦች አንድነት፣ የአገር ፍቅር፣ አትንኩኝ ባይነትና አይበገሬነት በተግባር ለተረጎመው የአፋር ህዝብ ላቅ ያለ ምስጋና ሊቸረው ይገባል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2014