ኢንጂነር ግደይ ዘርዓጽዮን ከ1960ዎቹ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምረው ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ ቆይተዋል። በኖርዌይ የሚኖሩት እና በሕወሓት መስራችነት የሚታወቁት ኢንጂነር ግደይ ‹‹ ዝምታዬን ሰብሬያለሁ፤ ዝምታው ይብቃ›› በማለት የሕወሓትን ተገቢ ያልሆነ አካሔድን ለዓለም አጋልጠዋል። አሁንም ትግራዋይ ሕወሓት ይብቃህ ብለው እንዲያስቆሙት በመጎትጎት ላይ ይገኛሉ። ከእኚሁ ፖለቲከኛ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- ‹‹ዝምታዬን ሰብሬያለሁ፤ ዝምታው ይብቃ›› የሚል ጽሑፍ ጽፈዋል። የጽሑፉ አንድምታ ምንድን ነው? በፊትስ ለምን ዝም አሉ?
ኢንጂነር ግደይ፡- እስከ አሁን ድረስ ዝም አላልኩም። ጽሑፉ ከተፃፈ አንድ ዓመት አልፎታል። ያኔ ጦርነቱ እንደተጀመረ ሕወሓት ነገሩን በማቀጣጠል የዓለምን ሚዲያ የተጠቀመበት መንገድ ፈጣን ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይን ዘር ለማጥፋት የሚሠራ አስመስሎ በማቅረብ ወቀሳ አካሂዷል። ይህ የሆነው ከእርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው አጥኚዎች ነን የሚሉ ታዋቂ ሰዎችን እንዲሁም በየአገራቱ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ወይም በመንግሥት ውስጥ ስልጣን ያላቸው ሰዎችን ሁሉ ተጠቅሞ በአንድ ጊዜ የሐሰት ፕሮፖጋንዳውን በማሰራጨቱ ነበር።
ከሕወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ‹‹የኖቤል ተሸላሚው ጦርነት ውስጥ ገባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን መነጠቅ አለበት›› ብለው ለሕወሓት አንቂ (አክቲቪስት) ሆነው ሲሰሩ ነበር። እኔ ደግሞ ወዲያውኑ ይህንን ውሸት አልቀበልም በማለት ጦርነቱ በተጀመረ በስምንተኛው ቀን ይህንን ፅፌያለሁ። በዛ ወቅት የአውሮፓ ሕብረት አባላት በፓርላማቸው ጉዳዩ ተነስቶ ‹‹የዘር ማጥፋት ነው። ›› ብለው ሲከራከሩ ነበር። በጊዜው ሕብረቱ ላይ ጉዳዩ የዘር ማጥፋት ነው ከማለት ውጭ የጦርነቱን መንስኤ የሕወሓት ሃይል የሰሜን ዕዝን በማጥቃቱ መሆኑን አያነሱም ነበር። እናም ውሸት ላይ ተመስርተው ውሳኔን ያሳልፉ ነበር። ዩናይትድ ኪንግደም ላይም በተመሳሳይ መልኩ ነበር። ስለዚህ ይህ ውሸት ነው በማለት ጦርነቱ በምን ምክንያት እንደተነሳ፤ በመንግሥት በኩል የተደረጉ ሙከራዎችን በሚመለከት ፅፌያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አዎ! እዛው ጽሑፉ ላይ ሰላም መደፍረሱን በሚመለከት የሕወሓት ሚና ምን እንደነበር አጉልተው አሳይተዋል። ሕወሓቶች የመንግሥትን የሠላም አማራጮች እና ጥሪዎችን ጥሰው አገር የማፍረስ አንድምታ የነበራቸው እንቅስቃሴዎች ማድረጋቸውን በጽሑፎት አካተዋል። ከአመሠራረቱ ጀምረው የሚያውቁት ድርጅት በመሆኑ እርሱን የሚገልጹት እንዴት ነው ?
ኢንጂነር ግደይ፡– ሕወሓት ለ27 ዓመታት በምን ዓይነት መልኩ ኢትዮጵያን እንደገዛ አይተናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያውቃል። አምባገነን፣ አፋኝ፣ ጨቋኝ በመሆኑ ሕዝቡ ተነሳስቶ ሥርዓቱ ከሥልጣን አባርሯል። ወዲያው ከስልጣን እንደተባረሩ ወደ ትግራይ ሔደው ሕዝቡን ለማታለል ሞክረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕወሓት በፈጠረው የዘር ሽኩቻ ሕዝቡ እርስ በእርስ የሚጨፋጨፍበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ስልጣን እንደለቀቁ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ታይቷል። በየክልሉ የተለያዩ ግጭቶች ታይተዋል። በሶማሌ እና ኦሮሞ፤ በሶማሌ እና አፋር ፤ በአማራ እና በኦሮሞ እየተባለ ስንት ሰው እንደተፈናቀለ ይታወቃል። እነርሱ ይህንን ሁሉ ያመጣው ዐቢይ ነው ይላሉ። ነገር ግን እነርሱ የፈጠሩት ችግር ነው።
ሌላው ሕዝብ ብቻ አይደለም፤ የትግራይ ሕዝብም ተመቷል። ከተለያዩ አካባቢዎች እንዲፈናቀል ተደርጓል። ከአማራ፣ ከኦሮሚያ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ፣ ንብረታቸው የወደመባቸው እና የተገደሉም አሉ። ሕወሓት ፈጥሮት በሔደው ጉዳይ ትግራዋዮችን እንደልዩ ተጠቂዎች አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል።
አዲስ ዘመን፡- ብሔርን ተጠቅሞ ከሌላው ሕዝብ ለመነጠል ማለት ነው?
ኢንጂነር ግደይ፡- አዎ! ትግራዋይ በየአካባቢው እየተጠቃ እና እየተመታ ነው በማለት ሕዝቡን በስሜት ለማነሳሳት እና ለመያዝ ሞክሯል። አንደኛ የትግራይ ሕዝብን ለመብትህ ታገል፤ መክት እያለ ሕዝቡ በትጥቅ እንዲታገል በማድረግ ወደ ሥልጣን ለመመለስ አስበዋል። የጎደለባቸው ነገር የለም። እንደሌላው ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሳተፉ፣ ፖለቲካል አቋማችሁን ግለፁ ቢባሉም በሃይል ወደ ስልጣን እንመጣለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ላይ እንዳነሱት በኃይል ወደ ሥልጣን መመለስ ሲባል ሕወሓት ፈቀቅ ካለ በኋላ ከፍተኛ የጦር ኃይል ማዘጋጀት፤ ልዩ ኃይሉን በደንብ አስታጥቆ ማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስመልክቶ ያሎትን ሃሳብ እስኪ በደንብ አብራሩት ?
ኢንጂነር ግደይ፡- የትግራይን ሕዝብ የብሔራዊ ስሜቱን በማነሳሳት መክት የሚል መርህ በመያዝ ሕዝቡን ሚሊሻን እንዲሁም ልዩ ኃይሉን በማስታጠቅ እና በብዛት በማሰልጠን የኢትዮጵያን መንግሥት አፈርሳለሁ ብሎ ተነስቷል።
በተደጋጋሚ በስታዲየም እየወጣ በወታደራዊ ትርኢት ሃይሉን አሳይቷል። በቪዲዮም ሃይላቸውን እና ጉልበታቸውን የሚያሳዩበት ሁኔታ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የትግራይ እናቶች ጦርነት አይፈልጉም›› ሲሉ እነርሱ ግን ‹‹ይህን ያለው እንዴት ቢንቀን ነው›› ብለው ሊወጋን ነው እያሉ ሕዝቡን ወደ ጦርነት ለማስገባት እየገፉ ቆይተዋል። ሌላውን አካባቢ ደግሞ እነርሱ ተቃዋሚ የሚሏቸው ሃይሎችን እየደገፉ የብሔር እንቅስቃሴ እንዲነሳ እና ብጥብጥ እንዲኖር በየአካባቢው ሰርተዋል። ኦሮሚያም፣ አማራ ክልልም፣ ሁሉም ጋር እየገፉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላም እንዳይኖር ሰርተዋል።
ሕወሓቶች በተግባር ያሳዩትም ነገር ነበር። የተከሰሱ ሰዎችን አናስረክብም በማለት የኢትዮጵያ መንግሥትን ሕግ አናከብርም ሲሉ ታይተዋል። የማንነት እና የወሰን ኮሚሽን ሲቋቋም እኛን ለማጥቃት የተፈጠረ ነው በሚል በፓርላማ ሳይቀር አንቀበልም በማለት ሕዝቡን ለማነሳሳት ሞክረዋል። የድንበር ጉዳይ ያለው በትግራይ ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ የድንበር ጥያቄ እየተነሳ ውዝግብ እየተፈጠረ ስለነበረ ጥናት ተደርጎበት መፍትሔ እንዲመጣ ማድረግ ጥሩ ውጤት ከማምጣት ውጭ ምንም የማያደርገውን ነገር ፖለቲካዊ አድርገው ሕዝቡን ለማነሳሳት ሞክረውበታል።
በኢትዮጵያ የሚደረገውን ምርጫ በማውገዝ የራሳቸውን ምርጫ አድርገዋል። ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት አይኖርም ብለው ሕዝብን ለማነሳሳት ሞክረዋል። አልፈው ተርፈው ለሰሜን ዕዝ መከላከያን ለመምራት በኢትዮጵያ መንግሥት ተሹሞ የሔደውን መሪ አንቀበልም ብለው እንደመለሱት ታይቷል። በመጨረሻም በትዕቢት እና በትምክህታቸው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል። አንድ ክፍለ ጦርን በመብረቃዊ ጥቃት ተቆጣጠርነው፤ አስፈላጊውን መሳሪያ በእጃችን አስገብተናል፤ ከእንግዲህ ማንም አይነካንም ብለዋል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሥርዓት ካላስያዛቸው ምን ያደርጋል? ማንኛውም መንግሥት እንኳን አንድ ክፍለ ጦር ተመቶበት ትንሽ ንዑስ ክፍል እንኳ ቢነካበት አፀፋው ከባድ ነው። አውሮፓውያን የራሳቸውን ጥቅም አስበው እንጂ መጀመሪያውኑ በዚህ ተግባሩ ሕወሓትን ማውገዝ ነበረባቸው። ቢያንስ እንደዚህ ተደርጓል ስህተት ነው። ከዚህ በላይ እንዲህ እንዳይደረግ መጠንቀቅ አለባችሁ አላሉም። ይልቁኑ ያደረጉትን ሸፋፍነውላቸው ሕወሓት የሚፈልገውን የዘር ማጥፋት እንደተካሔደ ለማስመሰል ሞክረዋል።
የዘር ማጥፋት ጉዳይ ከሆነም መጠየቅ የነበረበት ሕወሓት ነበር። በዕዙ ከታች ወታደር እስከ ከፍተኛ አዛዥ የነበሩትን ትግራዋይ ያልሆኑትን አጥቅቷል። መጠየቅ የነበረበት ይህ ነበር። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ እንጂ ትልቅ ነገር የሚያስነሳ ነበር። ከዚህ አለፍ ብሎ ማይካድራ ላይ የአማራ ሕዝብ ተለይቶ በተጋሩ እንዲጨፈጨፍ አስደርጓል። እነዚህ ጨፍጫፊዎች ደግሞ ሱዳን ገብተው አማራ ትግሬን ጨፈጨፈ ብለው ያወራሉ። እንዲህ ዓይነትን ፖለቲካ የሚጠቀም ድርጅት ዓላማው ምንድን ነው? በሠራው ሥራ ብዙ የትግራይ ሕዝብ ይጨረስ ነበር። አልተደረገም የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ የኢትዮጵያውያን ሞራል በጣም የሚገርም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሕወሓትን በደንብ ስለሚያውቁት የሄደባቸውን መንገዶች ቢያብራሩልኝ?
ኢንጂነር ግደይ፡- እንዳያችሁት ዓላማው አለመቀየሩን የሚቆጥሩት እንደ ትልቅ ጀብድ ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲን አንቀይረውም ይላሉ። ነገር ግን ዓለም በብዙ ነገር ተቀይሯል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም። ይህንን የሚጠቀሙት እንደሽፋን ነው።
ሌላው ሕወሓት በፖለቲካ ማሸነፍ ስላልቻለ በሃይል ሁሉንም ነገር ማድረግ አለብኝ የሚል እምነት አለው። ጌታቸው ‹‹አገር ትበጣበጥ ትፍረስ ጉዳዩ አይደለም። ›› ብሎ ተናግሯል። ጉዳያችን ራሳችንን እና ሕዝባችንን መከላከል ነው ብሏል። አሁንም ሕወሓት በሔደበት እና በገባበት ሁሉ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ተግባር እየፈፀመ ነው። ስትራቴጂውም ይኸው ነው። ወልቃይት ሔዶ ተጋሩን አጣላ፤ ማይካድራ ላይ የሠራው ታይቷል። አማራ ውስጥ ገብቶ ቅማንት እና አገው እያለ ሊበጣጥስ ሞክሯል። አካሔዱ ብጥብጥ በመፍጠር ሥልጣን ላይ ለመውጣት እና ለመቆየት ብቻ ነው። ተግባሩ ለአገር የሚበጅ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በሐሰት መረጃዎች ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚደረግ ጥረት እንዴት ይገለፃል?
ኢንጂነር ግደይ፡- አዎ! በዚህ አካሔድ በጣም የተካኑ ናቸው። ድራማ ሰርተው ሳይቀር ለሚዲያ ያቀርባሉ። እንዳያችሁት የዘር ማጥፋት ተካሄዷል በማለት ያላቀረቡት ነገር የለም። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት የጣምራ የምርመራው ውጤት እንዳሳየው የዘር ማጥፋት የሚባል ነገር የለም። በመንግሥት ርሃብን እንደጦር መሣሪያ መጠቀም አለ ቢሉም እንደዚህ ዓይነት ነገር አልተደረገም ተብሏል። ይህንን ዕርዳታ ሰጪዎችም ሆኑ የአውሮፓ አገሮች ሲያራግቡት የነበረ ቢሆንም እውነት እንዳልሆነ ተረጋግጧል። ነገር ግን ሕወሓት መረጃ የሚመስል ነገር ለማቅረብ የማይሠራው ሥራ የለም። አዴት አካባቢ ሬሳ እየጣለ ወታደሩ እንዲህ እያደረገ ነው ሲል ነበር። ራሱ አስገድዶ መድፈር እያስፈፀመ በሌላው እንደተደረገ አስመስሎ ያስነግራል። እንደዚህ እንደሒሊኮፕተሩ የተሳሳተ ወሬ ማራገብ ማቅረብ የተለመደ ነው።
የድምፅ ማታለያ አቀናብረው ዐቢይ ያላለውን ብሏል ብለዋል። ይህንን የዓለም ሕዝብ እንዲገነዘበው ከነምሳሌዎቹ ለሚዲያ ሰዎች ማጋለጡ ጥሩ ነው። ብዙ ማሳያዎችና ምሳሌዎች አሉ። የሒሊኮፕተሩ ወሬ የዓለምን ሕዝብ ለማወናበድ ብቻ አይደለም፤ ለትግራይ ሕዝብም ጭምር ነው። አሁን ሕወሓት የድል ዜና ጠፋበት ስለዚህ የራሱን ሠራዊት እና ሕዝቡን ለማወናበድ የሐሰት ወሬውን አወራ። እነዚህን ውሸቶች ማጋለጥ ይገባል። በፊትም ብዙ የውሸት ወሬ በማውራት ሕዝብን አነሳሳ፤ ብዙ መሰዋእትነት ተከፈለ፤ አሁንም መስዋትነት እያስከፈለ ነው። ነገር ግን በውሸት ላይ የተመሠረተ ቤት አፍራሽ ነው። እውነት መውጣቱ አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፍ ተዓማኒነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በዚህ ሥራ ላይ ተሰማተርተዋል። በእርሶ ዕይታ ፍላጎታቸው ምንድን ነው?
ኢንጂነር ግደይ፡– በእርግጥ በዚህ ሒደት ትልቅ ሴራ እንዳለ የሚመስል ሒደት አለ። ሴራው ከዚህ ተነስቶ ወደዚህ ሄደ ብሎ ለመግለፅ ቢያስቸግርም አሜሪካን ውስጥ
ያሉት ባለሥልጣኖች የእነርሱ የጥቅም ተጋሪ የሆኑ ኃይሎች በዛው ሕወሓት እንዳይጠፋባቸው ይፈልጋሉ። ሕወሓት ለእነርሱ ታዛዥ ነበር። አሁን ደግሞ የማይታዘዝ ሲመጣ ሴራ ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው። እንግሊዝ፣ በአጠቃላይ ምዕራባውያን በሙሉ የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። ከዚህ ጀርባ የተቀናጀ የሚዲያ ቅስቀሳ አለ። አንዱ ከአንዱ እየተቀባበለ ለሕዝብ እውነተኛው መረጃ እንዳይተላለፍ የማድረግ ሥራ ይሠራል።
የአውሮፓ ሕዝብ ጦርነቱ የዘር ማጥፋት ነው ብሎ እንዲያምን፤ ማዕከላዊ መንግሥት ከመሃል ሔዶ ትግራይን እያጠቃ እንደሆነ አስመስሎ ዘገባ ማቅረብ አለ። ነገር ግን እዚህ ላይ ጦርነቱ ለምን ትግራይ ውስጥ መካሔድ ጀመረ ለሚለው ግን መረጃ አይሰጡም። በእርግጥ ከምዕራባውያን ብዙ ቀና የሆኑ ሰዎች ምሁራን እና ተመራማሪዎች ይህንን እያጋለጡ ነው። በጣም የታወቁ ሰዎች ጋዜጠኝነት ማለት ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄን እያነሱ ነው። እንደነሲ ኤን ኤን ኒዎርክ ታይምስ ዓይነቶቹ ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀምረዋል።
ኒዎርክ ታይምስ ህፃን ልጅ ጠመንጃ ይዞ “ለነፃነታቸው የተነሳሱ” በማለት ለመብታቸው የሚታገሉ ቆራጦች ብለው ዘግቧል። ይህ በጋዜጠኝነት ሥነምግባር መርህም ተቀባይነት የለውም። እርግጥ አሁን እነርሱም ራሳቸውን ችግር ውስጥ እያስገቡ ነው። አሁን ሕወሓት ወደ አዲስ አበባ ተጠጋሁ ሲል አዲስ አበባ ተከባለች ብለው ዜጎቻቸው እንዲወጡ የሚያደርጉት ሆን ብለው ጫና ለመፍጠር ነው። እንደዚህ ዓይነት ሴራ መኖሩ ታይቷል።
በአጠቃላይ በሰብዓዊነት ሥም እየነገዱ ነው። ‹‹ወደ ትግራይ እርዳታ አልገባም›› እያሉ ሲጮሁ ነበር። መኪናዎች ታገቱ ሲሉም ነበር። አሁን ደግሞ ሕወሓት መኪናዎቹን እየተጠቀመበት ነው የሚል ነገር አያነሱም። 800 መኪና ገብቶ የማይመለሱ ከሆነ ተጠያቂው ማን ነው? መኪናዎቹ መንገድ ላይ ሲሔዱ ጦርነት ከፍቶ ካደናቀፈ ተጠያቂው ማን ነው? ሞራል ቢኖራቸው ኖሮ በአፋር እና በትግራይ ክልል ገብቶ ሕዝቡን እያፈናቀለ ያለውን ሕወሓትን ይቃወሙ ነበር። በተመሳሳይ በኩል በኢትዮጵያም ርሃብ አለ። ለእነዚህም ምግብ ይደረስ ሲባል አይደመጥም፤ ይህ እነርሱ የሞራል ችግር እንዳለባቸው ያመለክታል። በእርግጥ ሰብዓዊነት አላቸው ወይ ከተባለ ያጥራጥራል።
አዲስ ዘመን፡- ሕወሓት በከፍተኛ መጠን ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን ህፃናትን እና ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎችን ወደ ጦር ግንባር እያሰለፈ ነው። ትግራይ ወጣት አልባ እንዲሆን ትውልድ የመጨረስ ሥራ እየሠራ መሆኑን በየጦር ግንባሩ እየተስተዋለ ነው። ይህንን በተቀናጀ መልኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ እንዴት ሊከላከለው ይገባል?
ኢንጂነር ግደይ፡– አዎ! በጣም ያሳዝናል። የትግራይ ሕዝብ ይህንን በወቅቱ ሊረዳው አልቻለም። በእርግጥ ትግራይን ራሳቸው ውስጥ አስገብተው ፕሮፖጋንዳ ሲሰሩበት ቆይተዋል። የትግራይ ሕዝብ ሌላ መረጃ ማግኘት የሚችልበት ዕድል የለም። ነገር ግን በውጭም ያለው መረጃ ለማግኘት እየቻለ በድንብርብር ውስጥ የገባ ዘረኛ ሆኖ በትምክህት እየሔደ ነው። ችግሩ የሕወሓት አካሔድ ዘረኝነት ነው። ትግራዋይ የተለየ ጦረኛ እና የራሱን መብት በሃይል የሚያስከብር ሕዝብ ነው የሚል ስሜትን ፈጥረዋል። አንዳንዴ ‹‹የራሴን መንግሥት ልመሠርት ነው›› ይላሉ። አንዳንዴ ደግሞ ማዕከላዊ መንግሥትን አፍርሶ ፌዴራል ሥርዓት ይመሰርታል ይላሉ። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ይዞ ከፋሽስት የሚለይበት ሁኔታ የለም። ውጭ ያለው ስሜት እየተጓዘ እየተነዳ ነው። ከዚህ ወጣ ብሎ ተረጋግቶ ማሰብ አለበት ብዬ አምናለሁ። እርግጥ አሁን በድል ስካር ውስጥ ስላለ ማየት አልቻለም። ነገር ግን ኪሳራው ሲደርስ ያጠፋነው ምንድን ነው? ለምን እንዲህ ሆንን የሚል ጥያቄ ይመጣል። ይሔ የሄዱበት ጉዞ ለትግራይ ሕዝብ የጥፋት ጉዞ ነው።
አሁንም የሔዱበት የጥፋት መንገድ ነው። አማራ ትግራይ ሔዶ ያጠፋው ሳይሆን፤ ራሳቸው ሕወሓቶች ሔደው የሚያጠፉት ብዙ ነው። ይሕ ትልቅ ኪሳራ ነው። እንደሚታየው የገቡበት ቦታና ስፋት ሲታይ እንዲህ ዓይነት ቦታ መርጠው መግባታቸው ራሱ ዕብደት ነው። ሁኔታው መገልበጡ አይቀርም። እነርሱ ሌላውን ሕዝብ ገልብጠው ሥልጣን ላይ እንወጣለን የሚል አስተሳሰብ ካላቸው ተሳስተዋል። ማንም ማንንም ሕዝብ ማንበርከክ አይችልም። ይህንን በተግባር እያየነው ነው። እኔ የምለው የትግራይ ሕዝብ ራሱን መጠየቅ ያለበት ጊዜ ነው። ተበደልኩ ብቻ ሳይሆን እኔስ ምን ስሜት ይዤ እየሔድኩ ነው ብሎ ከዚህ ስሜት መውጣት አለበት። እኛስ ምን ስላደረግን ምን ስለተደረግን እንዲህ ሆንን? መባል አለበት። ሁሉም ታሪክ አለው። የራሱን ታሪክ ይዞ መጥቷል። ይህንን ማየት መቻል አለባቸው።
አሁን መጥፎ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ይታየኛል። ሕዝቡ እስኪደራጅ ድረስ የደቦ ውጊያ ይዞ የፈለጉበት መግባት ይቻላል። ነገር ግን ሕዝቡ ከተደራጀ ጊዜ የሚወስደበት ሁኔታ የለም። እስከ አሁን ድረስ እንቅስቃሴያቸውን ያገዛቸው ሕዝቡ ነው። ጊዜ በወሰደ ቁጥር ሕዝቡ በደንብ እየተደራጀ የራሱንም መሪዎች እያሰለጠነ የሚሔድበት ሁኔታ ይኖራል። ለጊዜው የሚታየኝ ይህ ነው። አሁን በትክክል ሒደታቸው እየተቀለበሰ ነው። የትግራይ ሕዝብ ይሔ ነገር አያዛልቀንም። የሚያዋጣን ከጎረቤቶቻችን ጋር በሠላም መኖር ነው ብሎ ከጎረቤቶች ጋር በሠላም የሚኖርበትን መንገድ መቀየስ ይኖርበታል።
ከኤርትራ፣ ከአፋር እና ከአማራ ጋር ተጣልቶ ከማን ጋር ሊኖር ነው? አካባቢህን በሙሉ በጠላት ከበህ እንዴት ትኖራለህ? ሁሉንም ነገር በሃይል ማድረግ አይቻልም። የትግራይ ሕዝብ እዚህ ላይ ማሰብ አለበት። ከአሁን በኋላ የሚመጣውን ጉዳት በማየት ሕዝቡ ራሱ መንቃት ይኖርበታል። እኛ እስከ አሁን ድረስም ይህ ሁሉ ከመድረሱ በፊት ስናስጠነቅቅ ነበር። አሁን ግን ሁኔታ እዚህ ላይ ደርሷል። አማራጩ ምንድን ነው? ውጪ ያሉት እኮ ኢትዮጵያ አገራችን አይደለችም እስከማለት ደርሰዋል። ኢትዮጵያ አገራችን ነች። ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረን የምንኖርበትን ቀመር ማምጣት አለብን። በሃይል አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ አገሪቱን የማፍረስ ዕቅድ አለ። ወደ መሃል አገር ሰርጎ የመግባት ጥረቶች አሉ። አገር ቀጣይነት እንዲኖራት ምን መደረግ አለበት። ከማን ምን ይጠበቃል?
ኢንጂነር ግደይ፡- አሁን እንግዲህ የሕወሓት አካሔድ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት ለመኖር እየሞከሩ ነው። በሕዝቡ ላይ ጥላቻን በመፍጠር ለመኖር አስበዋል። የትግራይ ሕዝብ ግን ከዚህ መውጣት አለበት። የትግራይ ሕዝብ የሚኖረው ትግራይ ውስጥ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢው የሚኖር ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከግማሽ ሚሊየን ያላነሰ ሕዝብ አለ። አማራ ጠላታችን ነው ይላሉ። ነገር ግን በአማራ ክልል ከ100 ሺህ በላይ ትግራዋይ ይኖራል። እንደዚህ ሲኖር የነበረን ሕዝብ አለያይተህ እርስ በእርስ አጋድለህ መኖር አትችልም። ከዚህ ዕብደት መውጣት አለብን።
የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ ሕዝብ እንዲጋደል ነው። የአማራ ሕዝብ ወይም የማዕከላዊው ሕዝብ ትግራይ የገባው ሕዝቡን ለማጥፋት አይደለም። ትግራይን ማውደም ከፈለገ ከአዲስ አበባ ወይም ከትግራይ ክልል ነዋሪዎች መጀመር ይችላል። እንደርሱ እንዲሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ አይፈቅድም። እነርሱ ግን የሚፈልጉት እርሱን ነው። ሕዝቡ በጥላቻ ከእነርሱ ጋር እንዲሰለፍ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው። አሁንም በየሔዱበት ወደ ደሴ ኮምቦልቻ አማራ አገር ሲገቡ እዛ የነበረው የትግራይ ነዋሪ እንዲጎዳ ያደርጋሉ። ሰርገው ገብተው ከሕዝቡ ጋር የነበረው ጠቋሚ አስገዳይ ገዳይ እንዲሆን አድርገዋል። ሕዝቡ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርገዋል። ይህንን መቀልበስ አስቸጋሪ ነው። ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ። አሁን ቢቻል መፍትሔው በሠላም ቢያልቅ ነው። የሕወሓት ሃይል ወደ ሰላም የሚሔድበትን መንገድ መፈለግ አለበት።
የሕወሓት ሃይል ከያዘው ከአማራ ክልልም ሆነ ከአፋር ክልል ወጥቶ በሠላም ወደ ትግራይ መመለስ አለበት። ተኩስ ማቆም እና ለድርድርም ዝግጁ መሆኑን ማሳየት አለበት። የኢትዮጵያ መንግስትም በበኩሉ ለሠላም በር መክፈት አለበት። አሁንም አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነው። እንዲህ ቢጀመር መልካም ነው። እንደዚህ ካልሆነ የጦርነቱን አካሔድ እያየነው ነው። ወዴት እንደሚሔድ የሚያመላክት ፍንጭ አለ። አሁን ሕወሓቶች እየገፉ ብዙ መጥተው ለመውጣትም የሚቸገሩበት ሁኔታ ላይ መድረሳቸው ይታየኛል። ከዚህ በኋላ ከገፉም የትግራይ ሰው ጦርነት ውስጥ የገባው ትንሹም ትልቁም ብዙ ሰው ያልቃል። በመንግሥት ደረጃ ጥሩ ምልክት አለ። ሕዝቡም ወደዛ መግፋት አለበት። ሌላ አማራጭ የለም።
ሌላ የምለው በየአካባቢው ያሉ ትግራዋይ ሽማግሌዎች ተነስተው ከሕዝቡ ጋር የሚታረቁበትን መንገድ መፍጠር አለባቸው። በኅብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት ትልቅ ነው። ይህንን ክፍተት ለመዝጋት የትግራይ ሽማግሌዎች በየአካባቢው ተነስተው ከሽማግሌዎች ጋር የሚታረቁበትን እና የሚስማሙበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። አሁን በትግራዋይ ላይ ብዙ ጥርጣሬ አለ። ትግራዋይ ታሰሩ የሚለው ነገር እየተሰማ ነው። እነሕወሓት ይህንን ለፖለቲካ እየተጠቀሙበት ነው። ነገር ግን እውነታው እንደዛ ቢሆንም ምክንያት አለው። ልናመልጠው የምንችለው ጉዳይ አይደለም።
ተጋሩዎች በብዙ የሥልጣን ቦታ ሆነው ያሳዩት ክህደት ታይቷል። ይሔ የሚደበቅ አይደለም። አንድ ክፍለ ጦር ሲጠፋ ከታች ጀምሮ እስከላይ ስንት ትግራዋይ እንደነበረበት ይታወቃል። ይህን ሚስጥር ይዘው በሌሎች ላይ አደጋ ለመፍጠር መቻል በራሱ ትልቅ ነገር ነው። የተሰጣቸውን ሃላፊነት ችላ በማለት ብዙ ሹፌሮች ጅቡቲ ሔደው እጃቸውን እንደሰጡ እና መኪናዎችን ለጅቡቲ እንዳስረከቡ አይተናል። ለሥራ የተመደቡ የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች በዛው እንደቀሩ ተመልክተናል። እዚህ ውጭ ኢትዮጵያ አገሬ አይደለችም የሚሉም ታይተዋል። እንደዚህ ዓይነት ነገር መፈጠሩ የሚካድ አይደለም። ከዚህ ሁሉ በኋላ አትጠርጥሩኝ ማለት አይቻልም። ይህንን በትክክል ማስቀመጥ ይገባል።
እኔ የምለው አትፈተሹ አይደለም። ሲፈተሽ ሕጋዊ መሆን አለበት። ሠላማዊ ሰው እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በመንግሥት በኩል ሕጋዊ በሆነ መልኩ መካሔድ አለበት። አንዳንዱ ይህንን ያለአግባብ የሚጠቀምበት ይኖራል። አንዳንዱ ጉቦ የመውሰጃ መንገድ ያደርገዋል። ግማሹ ቂም የሚወጣበት ይሆናል። ከዚህ ሁሉ ነፃ የሚወጣበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። ሕወሓት ራሱ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ሊያስጠቁም ይችላል። ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ለመዳን ሕዝቡም ይህንን ከግምት አስገብቶ እንዲተባበር እና ጉዳዩ ወደ መጥፎ እንዳይሔድ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለእነአሜሪካም ሆነ ለእነእንግሊዝ የሚሉት ነገር ካለ?
ኢንጂነር ግደይ፡- ሳያውቁ ያደረጉት ከሆነ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ከሁሉም በላይ እነዚህ መንግሥታት ዕውቀት አላቸው። ኢምባሲ አላቸው፤ ከእኛ በላይ መረጃ አላቸው። እያደረጉት ያለው ሆን ብለው ነው። ከሆነ ደግሞ እዚህ ላይ ምንም ልትወጡት የምትችሉት አይደለም። እንደውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ እንዲጠነክር እና እናንተን እንዲቃወም ከማድረግ ውጪ ብዙ የሚያስኬዳችሁ አይደለም እላለሁ።
ተሳስተን አላየነውም የሚሉት ነገር ካለ ኢምባሲዎቻቸው አሉ ማየት ይችላሉ። እኔም በጣም ያበሳጨኝ ነገር እነርሱም ተከትለው ዘር ማጥፋት ነው ሲሉ ለምን ኢምባሲዎቻቸውን አይጠይቁም ብዬ ለመፃፍ ተነሳስቻለሁ፤ በአጠቃላይ አውቀው ከሆነ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ማንሳት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የውጪ አካላት አያውቁትም የሚል እምነት የለኝም ብለዋል። ነገሩ ኢትዮጵያውያንን ይጎዳል። ነገር ግን ለእኛ ጥቅማችንን ያስከብራል ብለው ከሆነ ምሥራቅ አፍሪካ ከተተራመሰ ያሰቡትን ውጤት እንዴት ያገኛሉ? ከስደት እንዲሁም ከራሳቸው ሠላም እና ደህንነት አንፃር መልሰው እነርሱ የሚጎዱበት ሁኔታ አይፈጠርም? ይህንንስ እንዴት መገንዘብ አቃታቸው?
ኢንጂነር ግደይ፡– አዎ በእርግጥ አንዳንዴ ብዙ የሚያውቁ ይመስለናል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አያውቁም። የሚሰሩት ሥራ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያበላሽ መሆኑን በብዙ ቦታ ታይቷል። ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ ገቡ ነገር ግን የትኛውንም ውጤት አላገኙም። አሁንም ዕውቀታቸው ውስን ነው። የሕወሓት ነገር ያዛልቀናል ብለው ካሰቡ ስሕተት ነው። ምክንያቱም ሕወሓት አገር በማበጣበጥ እገዛለሁ የሚል ድርጅት ነው። ይሔ አካባቢ ከተበጣበጠ አሜሪካ ልትይዘው አትችልም። አይተውታል። ሶማሊያ በነበረው ብጥብጥ ምን ያህል አካባቢውን እንዳመሰው ያውቃሉ። ሶማሌን እንኳ መቆጣጠር አልቻሉም። በምስራቅ አፍሪካ እንዲህ ዓይነት ነገር ከመጣ መቆጣጠር አይችሉም። ይህንን ነገር ማየት ነበረባቸው። ፍላጎታቸው በዚህ የሚጠበቅ አይደለም።
ኢትዮጵያ ትልቅ አንድነት ካላት አስተማማኝ ሠላም ለማምጣት ሚና ያላት አገር ናት። ሠላም ሆና ስትቀጥል የእነርሱም ጥቅም ሊጠበቅ ይችላል። ነገር ግን ይህንን ማየት አልቻሉም። ለዚህ ምንም ማድረግ አይቻልም። በእርግጥ ይህንን እየተወያዩበት ነው። አንዳንዶቹ ይህንን ጥያቄ እያነሱት ነው። ነገር ግን የፖለቲካ ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ይህንን ጥያቄ ይሰሙታል አይሰሙትም የሚለው ጉዳይ ያሳስባል። ነገር ግን የተጠየቀው ትክክል ነው። ሶማሌ ብቻዋን እንኳ እንዴት እንዳስቸገረቻቸው ይታወቃል።
እነአሜሪካ ኢትዮጵያን በገፏት ቁጥር ወደ ራሺያ እና ቻይና እየወሰዷት ነው። የራሳቸውን ጥቅም እያጡ ነው። ይህ ከጥቅማቸው አንፃር አስበው እያደረጉት ያለ ቢመስላቸውም፤ ከጥቅማቸው አንፃር ያግዛቸው እንደሆነ እናያለን እንጂ ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጫና ለማድረግ ሲሞክሩ አይተናል። ደህና ዕውቀት ያላቸው ይህንን ይቀይሩታል ብለን እናስብ፤ እኛ ማድረግ የምንችለው የአቅማችንን ነው። እኛ ለማንም ለእንደዚህ ዓይነት ሳንበረከክ ሕዝባችንን በአንድነት ነፃነቱን እና ክብሩን ጠብቆ እንዲኖር ትግል ማድረግ አለብን እንላለን።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም እጅግ የከበረ ምስጋና አቀርባለሁ።
ኢንጂነር ግደይ፡– እኔም አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሃሳቤን እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014