ያለንበት ዘመን መረጃን በቅጽበት መለዋወጥ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ የዋሉበት ነው። አብዛኛው ሰው ግንኙነቱ ከኢንተርኔት እና ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር እየሆነ በመምጣቱ መጻሕፍትን የማንብብ ፍላጎቱ አናሳ እንደሆነ ይነገራል። በዚህም የተነሳ የንባብ ባህላችን አደጋ ላይ ወድቋል በሚል ምሁራን ሲከራከሩ ይሰማል። ከዚህ አንጻርም መጻሕፍትን ከሚይዙ ይልቅ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሞባይላቸው ላይ የሚያቀረቅሩ ሰዎችን መመልክትም የተለመደ ሆኗል።
ከሊቅ እስከ ደቂቅ ትኩረቱን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳደረገም በየሰዓቱ የምንመለከተው ነው። በተለይም ወጣቱ ከንባብ በመራቁ ምክንያት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ሲያንጸባርቅ አይታይም፤ ምክንያታዊ አስተያየት አይሰጥም የሚሉ ትችቶችም ይሰማሉ።
የችግሩ ጥልቀት በዚህ ልክ እየተገለጸ ትውልዱ ያለበትን ክፍተት ለመሙላት የሚደረገው ጥረት ግን አናሳ ነው። ‹‹ንባብ ሙሉ ሰው ያደርጋል›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ተረድቶ ትውልድን ከመገንባት አንጻር አመርቂ ሥራ ተሠርቷል ማለት አይቻልም። ከቤት እስከ ሰፈር ፤ ከትምህርት ቤት እስከ ተቋም ለንባብ የተሰጠውን ትኩረት ሁላችንም የምናውቀው ነው።
የዛሬው የአስኳላ አምዳችን የአካባቢውን ማህበረሰብ የንባብ ባህል ለማሳደግ በአንድ ግለሰብ ተነሳሽነት ተቋቁሞ የነጻ ንባብ አገልግሎት የሚሰጠውን አነስተኛ የጎዳና ላይ ቤተመጻሕፍት ያስጎበኘናል። ቦታው ልደታ ክፍለ ከተማ ፤ ከአምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ቁልቁል ወደ በግ ተራ ሲኬድ በስተግራ በኩል፤ በአረቄ ፋብሪካ መውጫ መንገድ ዳር የሚገኝ ነው። አነስ ያለች ቤተ መጻሕፍት ብትመስልም ውስጧ ግን ብዙ ነገር ይዟል። ለብዙዎች ብርሃን ለመስጠትም ተዘጋጅቷል። በሸራ በተወጠረችው ዳስ መሰል መጠለያ ውስጥ በርካታ መጻሕፍት ተደርድረውባትም ትታያለች። ዙሪያዋ በችግኞች የተከበበ ነው። ትንንሽ መቀመጫዎችና ጠረጴዛዎች ተኮልኩለውባታልም። ሰዎች እዚህና እዚያ ቁጭ ብለው በተመስጦ ያነባሉ። ሌሎችም መታወቂያቸውን እያስያዙ መጻሐፍ ይዋሳሉ። ጎዳና ላይ መጽሐፍ ሲሸጥ እንጂ የቤተመጻሕፍት አገልግሎት ሲሰጥ ባለማየቴ ሁኔታው አስደምሞኝ ጥቂት ስመለከት ከቆየሁ በኋላ አስተናጋጁ ስለ አገልግሎቱ እንዲያስረዳኝ ጠየኩትና ሁኔታውን ያወጋኝ ጀመር።
ቦታው ከዚህ ቀደም ወጣቶች ተሰብስበው ጫት የሚቅሙበት፤ የሰፈሩ ሰዎችም ፈሳሽ ቆሻሻ የሚደፋበት ነው። በአንድ ግለሰብ ተነሳሽነት ቦታው ከጸዳና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃውም በአርማታ ከተሸፈነ በኋላ ቦታው ላይ ማንኛውም ሰው የነጻ ንባብ አገልግሎት የሚያገኝበት ቤተመጻሕፍት ተሠራ።
የቤተመጻሕፏ መስራች ካሌብ ታደሰ ይባላል። የዚያው አካባቢ ነዋሪ ነው። የአካባቢው ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ነገሮች ሲያሳልፉ እያየ የሚቆጭ ነው። ካሌብ ለወጣቶች የንባብ ማዕከል፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ወዘተ ሳይቀርብላቸው የዚህ ዘመን ትውልድ እያሉ መተቸት ተገቢ አይደለም ይላል። በዚህ የተነሳ ነበር ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ለወጣቶች ነጻ የንባብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቤተመጻሕፍት ለመክፈት ያሰበው።
‹‹ሕጻናት የሚቀረጹት ባሳየናቸው መንገድ ነው›› የሚለው ካሌብ፤ ወደዚህ ሥራ የገባው አንባቢ፣ ምክንያታዊ፣ ተመራማሪና ጠያቂ ትውልድ ለማፍራት ካለው ጉጉት የተነሳ እንደሆነ ይገልጻል። የኮሮና ቫይረስ መከሰት ሐሳቡን እውን ለማድረግ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለት ይናገራል።
ቤተ መጻሐፉን ከማቋቋሙ በፊትም ቢሆን ‹‹ሰው ክቡር በጎ አድራጎት ማህበር››ን በማደራጀት ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን የተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበር ያስታውሳል። በ2013 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ደግሞ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሲስተጓጎልና ተማሪዎች እቤት ሲውሉ መጻሕፍትን እየተዋሱ እንዲያነቡ በማሰብ ሥራውን ጀመረ።
መጀመሪያ የሰፈሩን ወጣቶች በማስተባበር አካባቢውን አጸዳ። ቀጥሎም መጠለያውን ለመሥራትና መጻሕፍት ለመግዛት የሰዎችን ድጋፍ ጠየቀ።ሰዎች ባደረጉለት ድጋፍ ላይ ከራሱ አስራ ስድስት ሺ ብር በመጨመር ቤተመጻሐፉን አቋቋመ። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በርካታ ደንበኞችን በማፍራት አገልግሎት መስጠቱን ጀመረ። ከተማሪዎች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ በተጨማሪ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅርንጫፍ የካንሰር ህሙማን ማዕከል ባለሙያዎች፣ ታማሚዎችና አስታማሚዎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አደረገ።
ቤተመጻሐፉ ሲዘጋጅ ይህንን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ እንደነበር የሚናገረው ካሌብ፤ ዓላማውን በሚገባ እያሳካ መሆኑን ይናገራል። የነጻ አገልግሎት የሚሰጥ እንደመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተጠቃሚው ቁጥር እያደገ መምጣቱን ይገልጻል። በተለይም ተማሪዎች አጋዥ የሆኑ መጻሕፍትን በሚገባ እየተጠቀሙባቸው ናቸው ይላል።
መታወቂያ በማስያዝ የሚፈልጉትን መጽሐፍ በኃላፊነት ወስደው የመመለስ ልምድ እያዳበሩ መምጣታቸውን የሚናገረው ካሌብ፤ ቢያንስ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሥራ በመሥራቱ እና የነበረውን ገጽታ በመቀየሩ ደስተኛ እንዳደረገው ያስረዳል።
ካሌብ የገዛቸውን መጻሕፍት ጨምሮ አሁን ላይ ከሁለት ሺ አራት መቶ በላይ የታሪክ፣ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የፖለቲካ፣ የአካውንቲንግ፣ የቢዝነስ፣ የማኔጅመንት፣ የሜዲካል፣ የፍልስፍና፣ የልቦለድ ወዘተ መጻህፍት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግሯል። በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በጉራጊኛ በእንግሊዝኛ የተጻፉ መጻሕፍት እንዳሉና በቀጣይ የተለያዩ ቋንቋዎችን ለማካተት መታሰቡንም ይገልጻል።
ካለው አጠቃላይ መጽሐፍ ውስጥ ወመዘክር ከአንድ ሺህ በላይ መጽሐፎችን ድጋፍ አድርጎለታል።፡ ግለሰቦችም አስፈላጊ የሆኑ መጻሕፍትን እየገዙ አበርክተውለታል። አብዛኛዎቹ መጻሕፍት ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ኮሌጅ ባሉ የትምህርት እርከኖች በማጣቀሻነት የሚያገለግሉ ናቸው።
ካሌብ በቤተ መጻሕፍቱ ለሚያስተናግድ ሠራተኛ የምግብና የማረፊያውን ችሎ በወር መጠነኛ ገንዘብ በመክፈል የሥራ እድል ፈጥሯል። የሚያግዙት ሰዎች ቢኖሩ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻልም ይገልጻል። በተለይም ቤተመጻሕፍቱን የማስፋት እቅድ ስላለው ለዚህም የቀበሌው መስተዳድር የቦታ ጥያቄውን ቢመልስለት ደስተኛ እንደሚሆን ይናገራል። እስካሁንም መልስ እስኪሰጠው በተስፋ እየተጠባበቀ ይገኛል። አመራሮች በወቅታዊ የአገር ጉዳይ የተጠመዱ መሆናቸው እንጂ ጥያቄው እንደማይዘገይበት ያምናል።
ከቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለፈ ወጣቶች የሥነ ጽሑፍ ችሎታቸውን ሊያዳብሩ የሚያስችሉ ዝግጅቶችንም ለማድረግ ሞክሯል። ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችን በማሳተፍ ለሁለት ጊዜ ያህል በዚያው በቤተመጻሕፉ ውስጥ የግጥም ምሽት አካሂዷል። ካሌብ ወደፊትም ቋሚ ፕሮግራም በማዘጋጀት የሥነጽሑፍ ምሽቶችን የማዘጋጀት ሀሳብ እንዳለው ተናግሯል።
የአካባቢው ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ነገር እንዳያሳልፉ እና መጻሕፍትን በማንበብ እንዲደመሙ የተቻለውን ሁሉ እንደሚደርግ የሚናገረው ካሌብ፤ ወጣቱ በመረጃና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ንግግር ለማድረግ መጀመሪያ ማንበብ እንዳለበት ያስረዳል። ማንበብ የአስተሳሰብ፣ የንግግር፣ የማዳመጥ፣ የመጻፍ ችሎታን እንደሚያዳብርና ብዙ ያነበበ ሰው ብዙ እውቀት እንደሚኖረው እምነቱን ይገልጻል። ስለዚህም ማንኛውም ሰው ይህንን እንዲያደርግ ይመክራል። መንግሥት እንደዚህ አይነት ጥረቶችን ማበረታታት ከቻለ በትውልድ ስብዕና ቀረጻ ላይ ኃላፊነቱን መወጣት ይችላልም ይላል።
በቤተ መጻሕፍቱ ሲጠቀሙ ያገኘናቸው ደንበኞችም የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። ከእነዚህ መካከል ተማሪ ሰርክዓለም አስረስ አንዷ ነች። ሰርካለም የተዋሰችውን መጽሐፍ ስትመልስ ያገኘናት ደንበኛ ነች። በሰፈሯ ውስጥ ነጻ የቤተመጻሕፍት አገልግሎት ማግኘቷ ከፍተኛ ጥቅም እንደሰጣት ትናገራለች። ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ልምድ እንዳልነበራት የምትናገረው ሰርክዓለም፤ ይህ ቤተመጻሕፍት ሥራ ከጀመረ ወዲህ በርከት ያሉ መጻሕፍትን ተውሳ ማንበቧን ገልጻለች።
ቤተመጻሕፉ መውጫና መግቢያ መንገድ ላይ መሆኑ እርሷን ጨምሮ የብዙ ጓደኞቿን ትኩረት በመሳብ እንዲያነቡ ምክንያት እንደሆናቸው ታስረዳለችም። መጽሐፍ የመግዛት አቅም ለሌላቸው የአካባቢው ተማሪዎች ትልቅ እገዛ እያደረገ ነውም ትላለች። የተለያየ ይዘት ያላቸው በርካታ መጽሐፎች መገኘታቸውና ነጻ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑም የተጠቃሚውን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳዳገው እንደሚገኝ ትገልጻለች። እንዲህ አይነት አገልግሎት በሁሉም ቦታ ቢኖር የተማሪዎችን ችግር እንደሚፈታና አንባቢ ትውልድን ለማፍራት እንደሚያግዝ እምነቷ ነው። ወጣቱ እንዲህ አይነት የማንበቢያ ቦታዎችን ቢያገኝ እራሱን ከአልባሌ ተግባራት ሊገታ ይችላልም ትላለች።
ሌላው በቤተመጻሕፉ ሲጠቀሙ ያገኘናቸው አቶ ሳምሶን ደንድር ይባላሉ። ወደ አካባቢው ለግል ሥራቸው በሄዱ ቁጥር ጎራ እያሉ አንዳንድ መጻሕፍትን አንብበው እንደሚመለሱ ይገልጻሉ። መጽሐፍ የሚያነቡ ወጣቶችን ማየታቸውም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። የጫት መቃሚያ የነበረው ቦታ ጸድቶ የማንበቢያ ቦታ መሆኑ ብዙ ወጣቶችን መታደግ የሚያስችል መልካም ሥራ እንደሆነ ይገልጻሉ።
‹‹ማንበብ ሙሉ ሰው ያርጋል›› ያሉት አቶ ሳምሶን፤ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ኢተአማኒ ጽሑፎችን ከማንበብ ይልቅ መጻሕፍትን ቢያነብ ጥልቅ እውቀት ሊያገኝ ይችላል ባይ ናቸው። እንዲህ አይነት ተሞክሮዎችን በየሰፈሩ ማስፋፋት ቢቻል አንባቢ ትውልድን እንደሚፈጠር የሚያነሱት አቶ ሳምሶን፤ ምግብ ለሆዳችን እንደሚያስፈልግ ሁሉ መጻሕፍትን ማንበብም ለአዕምሯችን አስፈላጊ ነው። እናም ወጣቱ ጊዜውን በንባብ ማሳለፍ አለበት ይላሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራት ኪሎ አካባቢ እያስገነባ ስላለው ግዙፍ ቤተ መጻሕፍት ያለንን መረጃ ማካፈል ወደድን። በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲስ አረጋይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተከታዩን መረጃ ሰጥተዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ‹‹አብርሆት›› የተባለ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት አስገንብቶ በማገባደድ ላይ ነው።
ንባብን ባህሉ ያደረገ ሕብረተሰብን ለመፍጠር ብሎም ጠያቂ ትውልድን ለማነጹ ልጆች እያነበቡ፣ እየጠየቁ፣ አካባቢያቸውን እየተረዱ እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል። ማንበብን የሕይወታቸው መሠረትና ልማድ እንዲደርጉም ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል። በዚህም በከተማ አስተዳደሩ በኩል አቅጣጫ ተይዞ ዜጎች በአዕምሮና በሥነልቦና እንዲጎለብቱ፤ አዳዲስ ሀሳቦችን እንዲያፈልቁ፤ መማማርና መመራመር፣ መደማመጥን እንዲጎለብቱ የንባብ ቦታዎች እየተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
መመራመርና ማንበብ እየፈለገ መጻሕፍትን ባለማግኘት ወይም ምቹ ቦታን ከማጣት አንጻር የሚባክነውን ትውልድ ለመታደግ ታስቦ አብርሆት ቤተ መጻሕፍትን ማቋቋም እንዳስፈለገም የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ቤተ መጻሐፍቱ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ተመድቦለት የተሠራና ሰፊ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል። የመንግሥት ተቋማትንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ባማከለ ቦታ ላይ የተሠራም ነው ብለዋል።
ዲጂታልና ማኑዋል አገልግሎቶችን መስጠት ይችላል የተባለለት ይህ ቤተመጽሕፍት፤ በአንድ ጊዜ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ተጠቃሚዎችን ያስተናግዳል። ማንበብ እየፈለጉ በልጆች ምክንያት ታስረው ለሚቀመጡ የልጅ እናቶችንም የሚጠቅምና ለልጆች ጭምር የተዘጋጁ መጻሕፍት ማካተቱን ተናግረዋል። ቤተመጻሕፉ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ተጠናቋል። በቀጣይ የምርቃ መርሃ ግብሩ ከተከናወነ በኋላ ሥራ ለመጀመር እየተንደረደረ መሆኑን አቶ አዲስ ገልጸዋል። ቀደም ሲል ከጠቃቀስናቸው ችግሮች አንጻር ከተማ አስተዳደሩ ለቤተመጻሕፍት በዚህ ልክ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ሳንጠቅስ አናልፍም።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደአብርሆት ያሉ ቤተመጻሕፍትን በየቦታው መገንባት ባይችልም አነስተኛ ቤተመጻሕፍትን እየገነባ ወይም በግል የሚንቀሳቀሱ በጎ አድርጊዎችን እየደገፈ ነዋሪውን በያለበት ተደራሽ የሚያደርግበትን አሠራር ቢዘረጋም የበለጠ የጀመረውን ሥራ ያጠነክርለታልና ይህንንም ቢያያው ማለት እንፈልጋለን። እንደካሌብ አይነት ቅን ልቦና ያላቸውን በመደገፍ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዝም ሌላው አማራጭ መሆኑን ለከተማ አስተዳደሩ ጠቁሞ ማለፍ ጠቃሚ ነው።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014