አገር በማትፈልገው የሕልውና ጦርነት ውስጥ ከገባች አንድ ዓመት አስቆጥራለች። በዚህም ጦርነት ሕዝባችን እንደ ሕዝብ ከፍ ያለ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል። በዚህም በአገር ላይ ተደቅኖ የነበረውን የሕልውና አደጋ መቀልበስ የሚያስችል ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር እና ማንቀሳቀስ ተችሏል።
አሸባሪው ሕወሓት መንግሥት በነበረባቸው 27 የሥልጣን ዘመኑ በሕዝብ ሀብት የጦር መሳሪያዎችን በብዛት ገዝቶ በስውር የማካማቸቱ ሁኔታ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘራው መርዘኛ ልትጠፋ ነው ፕሮፓጋንዳ ከዚያም በላይ የምዕራቡ ዓለም ለቡድኑ ሕይወት ለመስጠት እየሄደበት ያለው ያልተገባ መንገድ የሕልውና ዘመቻውን ውስብስብ አድርጎታል።
የሽብር ቡድኑ ገና ከውልደቱ ጀምሮ ይዞት ሲንቀሳቀስ የኖረው አገርን የማፍረስ ተልዕኮን በሥልጣን ዘመኑ ሳይቀር በተደራጀ እና በተጠና መንገድ ተግባራዊ ሲያደርገው ቆይቷል። ሕዝቡን በዘር ከመከፋፈል ጀምሮ አገራዊ እሴቶችን በማጥፋት በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የነበረውን የአገር ፍቅር ስሜትና አገራዊ እሴቶችን ለማጥፋት ብዙ መንገድ ተጉዟል።
በተለይም የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማዳከም በማኔፌስቶ የተደገፈ ተልዕኮ ቀርጾ ሲንቀሳቀስ ነበር። በዚህም ለሞት፣ ለአካል ጉድለት፣ ለስደትና ከፍ ላሉ ለስነልቦና ቀውሶች የተዳረጉ የብሄሩ ተወላጆች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ። ብሄሩን ከሌሎች የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ለማጋጨትም ብዙ የጥፋት ትርክቶችን ፈጥሮና የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎም ተንቀሳቅሷል።
ለዚሁ ዓላማው ስኬትም ተለጣፊ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ቡድኖችን በመፍጠር በአማራ ሕዝብ ላይ ግልጽ የሆኑ የጥፋት ተልዕኮዎችን በነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ቡድኖች በኩል ሲተገብርና ሲያስተገብር፤ የአማራው ሕዝብ በገዛ አገሩ በሰላም መኖር የማይችልበትን የፖለቲካ ሥርዓት ፈጥሮ ቆይቷል።
የአማራን ሕዝብ ማዳከም ብሄራዊ አንድነትን ለማዳከምና ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስ ወሳኝ አቅም ነው ብሎ የሚያምነው አሸባሪው ሕወሓት፤ በሕዝቦች የተባበረ ክንድ ከሥልጣን ከተባባረ በኋላም ቢሆን ይህንን ሀሳቡን እውን ለማድረግ ከመቀሌ በሚሰጡ ተልዕኮዎች በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍ ያሉ ግፎችን ፈጽሟል፤ አስፈጽሟል።
አሸባሪ ቡድኑ ጥቅምት 14 ቀን በሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት እንኳን በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ የአማራ ተወላጆችን ለይቶ የፈጸማቸው ግፎች የቅርብ ጊዜ መጥፎ ትዝታዎች ናቸው። በዚህም ለአገራቸው ክብር መስዋዕት ለመሆን የቆረጡ የብሔሩ ተወላጆች የግፍ ሞት እንዲሞቱ ሆኗል።
መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ከወጣ ማግስት አንስቶም ቡድኑ ሕዝባዊ የጥፋት ኃይል በመፍጠር በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባካሄዳቸው ወረራዎች በንጹሀን የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ያደረሳቸው ዘርን መሠረት ያደረጉ ግልጽ የጅምላ ግድያዎች፤ አስገድዶ መድፈሮች እና ዝርፊያዎች ቡድኑ በአማራ ሕዝብ ላይ ያለውን የጥፋት ተልዕኮ ከመቼውም ጊዜ በላይ አደባባይ ያወጡ ሆነዋል።
የአማራ ሕዝብ አገሩን እንደሚወድ ዜጋ የቡድኑን ሴራ በመረዳት በቡድኑ የሚደርሱበትን በደሎች ተሸክሞ ረጅሙን የትዕግሥት ጉዞ ከፍ ባለ ጽናት መጓዝ ችሏል። በዚህም ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል ተገዷል። ይሁንና ሁሉም ነገር ጅማሬ እንዳለው ፍጻሜም የሚኖረው በመሆኑ በአሁን ወቅት ግን “ሁሉም ይብቃ በቃ” በሚል ከፍ ወደ አለ ራስንና አገርን የመታደግ የሕልውና ዘመቻ ውስጥ ገብቷል።
ይህ የጀመረው የሕልውና ዘመቻ አንድም የራሱን ሕልውና የማስጠበቅ ተልዕኮ ያለው ሲሆን ከዛም በላይ አገርን በጠንካራ መሠረት ላይ የማዋቀርና አገርን እንደ አገር የማስቀጠል ከፍ ያለ ተልዕኮ የተሸከመ ነው። የአማራን ሕዝብ የአገር ግንባታ ታሪክ ማደስ የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው።
በዚህ የሕልውና ዘመቻ የአማራ ሕዝብ እንደ አማራ እየከፈለ ያለው መስዋእትነት የቀደመውን የሕዝቡን የጀግንነት፣ የአትንኩኝ ባይነት እና የነጻነት ቀንዲልነት ታሪክ የሚያድስ፤ ዳግም በደማቅ ቀለም መጻፍ የሚያስችል ነው። መጪው ትውልድ የአገር ባለቤት እንዲሆን የሚከፈል የክብር መስዋዕትነትም ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014