
አዲስ አበባ፡- በተለያዩ የዓለማችን ክፍለ አህጉራት የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የአሜሪካንና የሌሎች ምዕራ ባውያን ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሠላማዊ ሠልፍ አካሂደዋል።
የሠላማዊ ሠልፉ መርሐ ግብር በአሜሪካ ዋሽንግተንን ጨምሮ በተለያዩ ግዛቶች፤ በካናዳ ኦታዋና በሌሎች አነስተኛ ከተሞች፤ በእስራኤል፤ በአውሮጳና በአፍሪካ ክፍለ አህጉራት እንደተካሄደ ለማወቅ ተችሏል።ሰልፎቹም ከ27 በላይ በሚሆኑ በተለያዩ አህጉራት በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ተካሂደዋል።
በሠላማዊ ሠልፉ ላይ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የተገኙ ሲሆን የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በሠላማዊ ሠልፎቹ የተሳተፉት ትውልደ ኢትዮጵያውን ኤርትራውያን የአሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያ ከብሩ አሳስበዋል። አሜሪካና አውሮፓውያን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መከራ ሲዘራ የኖረውን አሸባሪውን ሕወሓት ከመደገፍ እንዲቆጠቡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለውን ሁለንተናዊ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚያወግዙ፤ መገናኛ ብዙሃኖቻቸውም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያቀርቡትን ለአንድ ወገን ያደላ ዘገባና የሀሰት መረጃ የሚቃወሙ የተለያዩ የተቃውሞ ድምፆች ተሰምተዋል።
ከመርሐ ግብሩ አስተባባሪዎች ከሆኑት አንዷ የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የሲቢኤስ ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ እንደተናገረችው ሠላማዊ ሠልፉ “Black Alliance for peace” እና “@answercoalition” በተሰኙ ድርጅቶች እንደተሰናዳና የምዕራባውያንን ሁለንተናዊ ተፅዕኖ የመቃወም ዓላማ ያነገበ ነው ስትል አስታውቃለች።
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ለመቃወም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠራው ‘#NOMORE’ ዘመቻ ሰልፍ በካናዳ ኦቶዋ የተካሄደ ሲሆን በሰልፉ ላይ በካናዳ ኦቶዋ፣ ቶሮንቶ፣ ሞንትሪያል፣ ኩቤክ፣ ስካርብሮ፣ ኪንግስተን እና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና የኤርትራ ዜጎች ተሳትፈዋል።
የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና የሚያወግዙና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እየሰሩ ያሉትን ግጭት አባባሽ ሀሰተኛ መረጃዎችን እንዲያቆሙ ጥሪ የሚያደርጉ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ ተላልፈዋል።
ለካናዳ ፓርላማ እና በኦቶዋ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዲያቆሙና እጃቸውን እንዲያነሱ የሚያስገነዝብ ደብዳቤ መሰጠቱን ከሰልፉ አስተባባሪዎች ለማወቅ ተቸሏል።
የምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና በመቃወም በመላው ዓለም በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ከሚከናወኑ ሰልፎች መካከል አንዱ የሆነ ሰልፍ በእንግሊዝ ተካሂዷል።
በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃገብነት የሚቃ ወም ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ የእንግሊዝ መንግሥት በኢትዮጵያውያን የተመረጠው መንግሥት ላይ ጫና ከማድረግ እንዲቆጠብ እና እንግሊዝም ሆነች አሜሪካ ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ ጠይቀዋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምርጫችን ነው፤ ሕዝባችንን ለዘመናት ሲያሰቃይ የቆየውን አሸባሪውን ሕወሓት ‘ፈፅሞ አይሆንም’ እንለዋለን፤ የአፋር እና የአማራ ሕዝብ በሽብር ቡድኑ መሞት ይብቃ” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችንም አሰምተዋል ።
በተመሳሳይም የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በእስራኤል ተካሂዷል።
በእስራኤል የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና እንዲያቆሙ፣ እስራኤል ለኢትዮጵያ መንግሥት የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2014