ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ትገኛለች። በአንድ በኩል የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ከማህፀኗ ወጥተው መልሰው ራሷን የሚያደሙ የውስጥ ጠላቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተገዳደሯት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከኋላ በመሆን ይህንን የሚያስተባብሩና የውስጥ ባንዳዎችን እየደገፉ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቆርጠው የተነሱ የውጭ ጠላቶች ትልቅ ፈተና ሆነውባታል።
በርግጥ የኢትዮጵያ የውስጥ ጠላቶች በዚህ ደረጃ ለኢትዮጵያ ፈተና የሚሆኑበት አቅም አነስተኛ ነው። ይህ ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ ቡድኑ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተፍረክርኮ መበታተኑና በርካቶችም ተደምስሰው ከፊሎቹም እጅ መስጠታቸው አንድ ማሳያ ነው። ነገር ግን በሳተላይት እና በልዩ ልዩ መሳሪያዎችና ፕሮፓጋዳዎች ድጋፍ ቡድኑ እንዲያንሰራራ ያደረጉት የውጭ ሃይሎች ናቸው።
በአንጻሩ በአሜሪካ የሚመራውና በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት የውጭ ሃይሎች ቡድን ኢትዮጵያን ለመከፋፈል አልሞ እየሰራ ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት እና ጥቂት የአውሮፓ አገራት ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ የሲኤንኤን፣ ቢቢሲ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሬውተርስ፣ አልጀዚራና መሰል የምዕራባውን ሚዲያዎች የሃሰት ትርክቶችና ዜናዎችን ጭምር በተከታታይ በመስራትና በማሰራጨት ጫናውን እያጠነከሩ ሲሆን፣ በርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱት የምዕራባውያን ተቋማትም በልዩ ሁኔታ የነሱን አጀንዳ ለማስፈፀም ሲሯሯጡ ታይቷል።
ለምሳሌ በሰብአዊ ድጋፍ ስም የሚሰራው የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት ሃላፊ ሳማንታ ፓወር በግልጽ ከድርጅታቸው ዓላማ ውጭ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሄዱበት ርቀት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ያልቆመ ተግባር ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞች በሰብአዊ ድርጅት ስም ወደአገራችን ገብተው አሸባሪውን ሕወሓት በመደገፍ ስራ ላይ መሰማራታቸውና ጥቂቶቹም ከአገር እንዲወጡ መደረጉም የሚታወስ ነው። በቅርቡም በሰብአዊ እርዳታ ስም እየተንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኑን ሲደግፉ የተገኙ ድርጅቶችንም መንግስት ደርሶባቸው ምርመራ ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ ውጭ ደግሞ አሜሪካና አጋሮቿ በተለይ በኢትዮጵያ ላይ የጀመሩት የስም ማጥፋት ዘመቻ ወደከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ኢትዮጵያውያንን የሚያሸብሩ ተግባራትን ወደማከናወን ገብተዋል። ከነዚህ ተግባሮቻቸው ውስጥ አንዱ አሸባሪዎቹ “ሕወሓትና ሸኔ ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ከጫፍ ደርሰዋል” ከሚለው ትርክት ጀምሮ ዜጎቻቸውን ውጡ እስከማለት የደረሰው ውሳኔያቸው እና ሰሞኑን ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚነሱ በረራዎች ከመሬት ላይ በሚነሱ ጥቃቶች ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተነጣጠረው ዘመቻ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።
ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከትግራይና ከጥቂት የአማራ ክልል አካባቢዎች ውጭ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ባለበት ሁኔታ እነዚህ ኃይሎች በአገሪቱ ሽብር ያለ ለማስመሰል የሚሄዱበት ጥረት አገሪቱ በሽብር ውስጥ እንዳለች ለማስመሰልና በዚህ አለመረጋጋት ሰበብ አሸባሪውን ቡድን በድርድር ሰበብ ወደስልጣን ለማምጣት የሚደረግ ሩጫ ነው።
በሌላ በኩል አሸባሪው ቡድን ያሰማራቸው ሰርጎገቦችና ጋሻጃግሬዎቻቸው በህዝብ ውስጥ በመሰግሰግ በሚያናፍሱት የሃሰት ፕሮፓጋንዳና የወሬ ዘመቻ አገሪቱን እና ህዝቦቿን ስጋት ውስጥ በመክተት በቀላሉ ለማንበርከክ የሚሄዱበት ጥረት ከፍተኛ ነው። በተለይ በተለያዩ ቦታዎች ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙ ደጋፊዎቻቸውና ተቀጣሪዎቻቸው የሽብር ቡድኑ ዛሬም አቅም እንዳለው ለማስመሰል እና ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ እንደሆነ በማሳየት የደጋፊዎቻቸውን ሞራል ለመገንባት በህዝብ ውስጥ የውሸት ዜና ሲያሰራጩ እና ህዝቡን ለማሸበር ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። ከዚህም አልፎ ጥቂቶቹ ደግሞ በህገወጥ መንገድ መሳሪያዎችን በማከማቸት ለሽብር ቡድኑ ለማቀበል፤ እንዲሁም ህዝቡን ሰላም ለመንሳት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖሊስ ያወጣው መረጃ አመላካች ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ልክ በዓድዋ ድል እንደተጎናፀፉት ሁሉ በዚህ ቡድንም ሆነ በአሜሪካ መራሹ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን ላይ የሚያደርጉትን ትግል ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ለመመከት በተጠናከረ ወኔ ተነስተዋል። ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከጎናችን ለመሆናቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለፁና በተግባርም እያሳዩ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂ ሰላማችንን ለማረጋገጥና አፍሪካንም ዳግም ከምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ለማውጣት የጀመርነውን ትብብር አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።
በተለይ በውስጥ ሆነውና ወዳጅ መስለው ከጠላት ጋር የሚያብሩ የውስጥ ባንዳዎች የሚያደርሱት ጥፋት የከፋ በመሆኑ እነዚህን ኃይሎች የመከላከሉ ሚና በዋናነት የእያንዳንዱን ዜጋ ትብብር የሚጠይቅ ነው። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መንግስት ጉሮሮ ለጉሮሮ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር በሚያደርገው ትግል ለጊዜው በቀጥታ በግንባር በሚካሄደው ጦርነት ላይ ለመሳተፍ እድሉን ያላገኘው ዜጋ ሁሉ ኃላፊነቱን ለመወጣት ባለበት ስፍራ እነዚህን የውስጥ ጠላቶች ነቅቶ በመጠበቅ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በውስጥ ሰርገው በመግባትና ወዳጅ መስለው ለጠላት መሳሪያ የሚያቀብሉ አስመሳይ ጠላቶችን ነቅቶ በመጠበቅ ሰላሙን መጠበቅ ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ሰላማችን ቅርብ፣ ድላችንም አስተማማኝ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2014 ዓ.ም