በሹፌርነት የሥራ መስክ ተሰማርተው ነው የሚገኙት። በሙያው ለመሰማራት የበቁት የ12ኛ ክፍል ፈተና (ማትሪክ) ውጤታቸው ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባቸው ስላልቻለ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ምናልባትም ዛሬ በሥነ ጽሑፉ ዓለም አንቱ በተባሉ፤ ስንትና ስንትም የድርሰት ሥራዎቻቸውን ባስነበቡን ነበር።
ወረቀት መዘርጋትና ብዕርን መወደር ሳይጠብቅ የሚደረደር፤ ገና አንድ ነገር ሲያስተውሉ እንደ አባይ ፏፏቴ ወዲያውኑ፤ በዚያው ፍጥነት፣ በቃል ብቻ የሚንፎለፎል (አንዳንዴም የሚዥጎደጎድ) አስገራሚ የመግጠም ችሎታ አላቸው። ይሄን ተሰጥኦም እንበለው ችሎታ ያገኙበት መንገድ እጅግ የሚያስገርም ተአምራዊ ምትሃት ነበር ማለት ይቻላል። ጉዳዩን ምትሃት የሚያሰኘው መጋቢት 1995 ዓ.ም መሬት ላይ ወድቆ ያገኙት “ኮስትር” ስክሪፕቶ ነው። ስክሪፕቶው ደረት ኪሳቸው ላይ ተሽጦ እንደ ሰው “ግጥም ጻፍ … ጻፍ …” ብሎ ነው ወደ ሙያው ጎትቶ ያስገባቸው። ይህ “ምትሀታዊ” ተግባርም የሰይፉ ፋንታሁንን ጥያቄ በፍጥነት በስልክ በመመለስ አንድ ሺህ ብር ተሸላሚ አድርጓቸዋል።
ግጥማቸው በባልደረቦቻቸው ተወድዶና አድናቆት አስገኝቶላቸዋል። በተለይም በዚሁ በሹፍርና ሙያ በሚሰሩበት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባልደረቦቻቸውና የተሽከርካሪ አገልግሎት በሚሰጧቸው ጋዜጠኞች ዘንድ ‹ከማይረባ ቁርስ አንድ የሽሜ ግጥም ይሻላል” ተብሎላቸዋል። ሆኖም አሁን ድረስ በልጅነታቸው የተመኙትን ዓይነት ሰው መሆንና በዚህ ችሎታቸው መስራት አልቻሉም። ግን ደግሞ ተስፋ ሳይቆርጡ ያሰቡትን የማሳካት ጥረታቸው ዛሬም አልተቋረጠም።
እኚህ፣ የፈጣን ቃል-ግጥም ባለሙያ አቶ ሽመልስ ሙሉጌታ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት ልደታ ክፍለ ከተማ፣ በተለምዶ ዳርማር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ያሳደጓቸው የእናታቸው ወንድም፣ አጎታቸው ናቸው። ትምህርት የጀመሩት ከቄስ ትምህርት ቤት ነው። ወንጌልና ዳዊት እስከ መድገም ደርሰዋል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባልቻ አባ ነፍሶ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በ1978 ዓ.ም በተከፈተውና ‹‹ከፍተኛ ሰባት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት›› በተሰኘውና መሳለሚያ አካባቢ በሚገኘው ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል።
አቶ ሽመልስ ከትምህርት ቤቱ የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ናቸው። በ1981 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እስካስፈተናቸው ድረስም ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ጥሩ ውጤት አምጥተውና ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሚፈልጉት የሙያ መስክ ተሰማርተውና ጥሩ ደመወዝ ተከፋይ ሆነው ቤተሰባቸውን የመርዳት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸውም አይዘነጉትም። ‹‹ወጡ ሳይወጠወጥ የወስከንባው ቂጢጥ›› እንዲሉ ጉጉቱን እንደ እቅድ ይዘውት እንደነበረም ይገልፃሉ። አንድ ወንድማቸውና አምስት እህቶቻቸው ከአባትና እናታቸው ጋር “ይደርስልናል” የሚል ተስፋ ጥለውባቸው እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
ጠንቃቃው ሾፌር አቶ ሽመልስ እንዳጫወቱን በዚህ ሁሉ ምክንያት በትምህርታቸው ዋዛ ፈዛዛን የሚያውቁ አልነበሩም። የክፍልም ሆነ የቤት ሥራ ፈጥነው በመሥራትና ፈተናዎችን በመድፈን በክፍል ጓደኞቻቸውና መምህራኖቻቸው ዘንድ ጎልተው ይታወቃሉ። በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት ይከታተሉ የነበረው በጽሞና ነው። እሳቸው ጎን ተቀምጦ ክፍል ውስጥ አስተማሪ ሲያስተምር የሚያሾፍ ተማሪ የለም። አንድ መምህር ምላሽ ሲፈልግ መጀመሪያ የሚጠይቀው እርሳቸውን ነበር።
ይሁን እንጂ፦
‹‹ማትሪክና ቀበሌ የሰራለትን አያውቅም›› የሚሉት አቶ ሽመልስ ‹‹1ኛ የምወጣ የደረጃ ተማሪ ነበርኩ። ለ12ኛ ክፍል ፈተና ይበልጥ ዝግጅት በማድረጌ አራት ነጥብ አመጣለሁ ብዬ አስቤም ነበር›› ሲሉም ውጤታቸው እንደጠበቁት እንዳልሆነላቸው በቁጭት ደጋገመው ይናገራሉ።
አቶ ሽመልስ እንደሚያስታውሱት ከዛ በፊት ዓይናቸው እንኳን ሊያለቅስ እንባ አቅርሮ አያውቅም። ‹‹ውጤት እንዳልመጣልኝ የሰማሁ ቀን ግን የእንባ ከረጢቴ ተቀደደ። ግድግዳ ተደግፌ የእናቱንና የአባቱን ሞት እንደሰማ ሰው ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ›› ይላሉ። ውጤታቸው 1 ነጥብ 8 በመሆን ሲበላሽባቸው በአራቱ ዓመት የትምህርት ቤት ቆይታቸው አድናቆታቸውን ሲቸሯቸው የነበሩ መምህራኖቻቸው ከእሳቸው የበለጠ ማዘናቸውንም አልሸሸጉንም። የመጣላቸው ውጤት የእሳቸው ሊሆን አይችልም የሚል ግምት በማሳደሩም እንዲያስመረምሩ ሁሉ መክረዋቸው እንደ ነበር ሽሜ አልረሱትም።
(በዛን ወቅት የትምህርቱን ጠጣርነት፤ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብን ከፍተኛነት (ጥብቅነት) ለተገነዘበ ወይም ላስታወሰ ወይም በውስጡ ላለፈ የአቶ ሽመልስ አስተያየት ግልጽ ይሆንለታል። የድሮ ተማሪ የሚለውንም ያስታውስ ዘንድ ያግዘዋልና ሽሜ ወጋቸውን ይቀጥላሉ።)
ሆኖም የጠበቁት ውጤት ስላልመጣላቸውና በወቅቱ ትምህርት የመቀጠል ፍላጎታቸውን “ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ ገድሎት” ስለነበር ፈቃደኛ አልነበሩም። ቤተሰባቸውን ለመርዳት በተገኘው አቅጣጫው ሁሉ ሩጫቸውን ጀመሩ። በ1981 ዓ.ም በአጎታቸው አማካኝነት ሁለተኛ፤ በ1983 ዓ.ም ሦስተኛ መንጃ ፈቃድ በማውጣት በ1984 ዓ.ም አሁን ድረስ እየሠሩት ወዳለ ሹፍርና ሙያ ገቡ። ሥራውን በቤተሰብ ታክሲ ነው የጀመሩት። እስካሁንም እያሽከረከሩት የሚገኙት በዚሁ (በ3ኛ) መንጃ ፈቃድ እንደሆነም ነግረውናል።
ተጫዋቹ ሽሜ ‹‹በታክሲዋ የተወሰነ ዓመት ከአጎቴ ልጅ ጋር እየተፈራረቅን ከሰራን በኋላ በመሸጧ ተቀጥሮ ወደ መሥራት ገባሁ›› ይላሉ። በዚህ መካከል ሁሉ የሳቸውን የትምህርት ደረጃ የሚመጥንና የተሻለ ሥራ ለማግኘት ከመጣር አልቦዘኑም ነበር። እስከ 1990 ዓ.ም ጣና ዙሪያ፣ መገናኛ፣ ፍልውሃ፣ ካዛንቺስ መስመር ላይ በታክሲ ሹፌርነት የግለሰብ ተቀጣሪ ሆነው ሰርተዋል።
በዚህ መካከል አክስቷን ለማገዝና ማታ ማታ ለመማር አጎታቸው ቤት ከምትሰራ አንዲት ልጅ ጋር በፍቅር በመውደቃቸው ከድህነቱ በላይ ብዙ መሰቃየታቸውን ይገልፃሉ።
‹‹ገና እንዳየኋት ልቤ ደነገጠ›› የሚሏትን ወጣት ሰርክ ማየት ነበረባቸው። ይሄን ማድረግ ደግሞ በእጅጉ ያስደስታቸዋል። ለዚህ ሲሉም በየዕለቱ ልጅቷ ምግብ እንድታቀርብላቸውና ቡና ስታፈላ ለማየት ለምሣ ወደ ቤት ይሄዱ ነበር። ካላገኟት ቅር ይላቸውና ይበሳጫሉ። ትዳር ለመመሥረት የሚያስችል፣ ይሄ ነው የሚባል ገቢ ባይኖራቸውም ፍቅሯ ሲፀናባቸውና ከእጃቸው እንዳትወጣ በመስጋት ሊያገቧት እንደሚፈልጉ ደፍረው ነገሯት።
“’እኔ ለሥራ ነው የመጣሁት’ በማለት ተናዳ ጠፋችብኝ” የሚሉት አቶ ሽመልስ እሳቸው ደሃ በመሆናቸው ገንዘብ ያለው ሰው ልታገባ ነው በሚል ፍለጋቸውን ተያያዙት። በራሳቸው የፈጠሩት “ሌላ ሰው ልታገባ ነው” የሚል ሀሳብ ቅናት አሳደረባቸው። ቅናታቸውን ዋጥ አድርገው ከታክሲ ሹፌርነት ባሻገር የተሻለ ሥራ ፍለጋቸውንም አጣደፉት። እሷን ሲያገቡ ለሰርግና ትዳር የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማጠራቀም በማሰብና ቤተሰባቸውን ለመርዳት እጅግ ረጃጅም መንገዶችን በእግራቸው ተጉዘዋል። በመሀል ልጅቷን በማግኘታቸው በአክስቷ በኩል አሳምነው በሚያገኝዋት 300 ብር የታክሲ ሹፌርነት ደመወዝ ቤት በመከራየት ወደ ትዳር ዓለም ገቡ። ዘንድሮ ጥር ሲመጣ ትዳር ከመሰረቱ 29 ዓመታቸውን ይይዛሉ።
ዛሬ ሽሜና ባለቤታቸው ሦስት ሴት ልጆችንም አፍርተዋል። ሁለቱ ሴቶች በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው በጎሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ የመጨረሻዋ ልጃቸው ደግሞ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነች።
ገጣሚው ሽሜ እንደነገሩን ከሆነ ተአምረኛውን የቃል-ግጥም ችሎታቸውን ያገኙት ከአንዲት በአስመጪና ላኪነት ንግድ ዘርፍ ከተሰማራች ታዋቂ ነጋዴ ጋር ሲሰሩ በነበረበት ወቅት ነው። የሶማሌ ዜግነት ያላት ይህቺ ነጋዴ አንድ የሥራ ቀን ማማ ወተት ግዛ ብላ 10 ብር ትሰጣቸዋለች። ዕለቱ 1995 መጋቢት 19 ነበር። ቦታው ከቦሌ ወደ ወሎ ሠፈር፤ ከወሎ ሰፈር ወደ ቦሌ የሚያስኬደው ሁለት አካፋይ መንገድ ላይ ነው። ታክሲውን እዚህ መንገድ አስፋልት ዳር አቁመው “ኖቪስ” የተሰኘው ሱፐር ማርኬት ወተት መኖሩን ይጠይቃሉ። ሾላ እንጂ ማማ ወተት እንደሌለ ይነገራቸዋል። ሁለቱ አካፋይ የአስፋልት መንገዶች ተሻግረው ማዶ ወዳለው “አብሪኮ ሱፐር ማርኬት” በመሄድ ወተቱን መግዛት እንዳለባቸው ያስባሉ። አስፋልቶቹን ለመሻገር ዳር ላይ ቆመው መኪና ሲያሳልፉ አንዲት ስክሪፕቶ ዓይናቸው ትገባለች። ስክሪፕቶዋ ከሁለት አስፋልት ማዶ ለእሳቸው የታየችበት ሁኔታ እየገረማቸው ለመሻገር መኪናዎችን ሲያሳልፉ ይቆያሉ። ከአስፋልቱ ዳር ቆመው መኪና በማሳለፉ ወቅት ብዙ ደቂቃዎች ቢቆጠሩም፣ ብዙ ተላላፊ ሰዎች ቢኖሩም ስክሪፕቶዋ በእግር አልተረገጠችም፤ ያነሳትም የለም ነበር። ያልተነሳችው ቀለሟ ስለደረቀ ወይም ስለገነፈለ መስሏቸው ነበር። አስፋልቶቹን ተሻግረው ሲያነሷት ግን “ኮስትር” የምትባል አዲስ ስክሪፕቶ ከነ ክዳኗ ነበረች። እናም አንስተው የደረት ኪሳቸው ውስጥ ሻጥ ያደርጓታል። አሰሪያቸው በሰጠቻቸው በ10 ብርም አምስት ወተት ገዝተው ታክሲያቸውን ወዳቆሙበት ይመለሳሉ። አሠሪያቸው ሊሄዱ የነበረው መርካቶ ቢሆንም “የረሳሁት ዕቃ ስላለ ወደቤት እንመለስ” ትላቸዋለች። ተመልሰው ወተቱን ለወጥ ቤት ሠራተኛዋ እንድታቀብላት ግቢ ውስጥ ለነበረችው የጽዳት ሠራተኛ ይሰጡና እደጅ ከጥበቃው ጋር ቁጭ ይላሉ። ጨዋታም ይጀምራሉ።
በዚህ ወግ መካከል ከበስተኋላቸው ‹‹ጻፍ ጻፍ የሚል ድምጽ ተደጋግሞ ተሰማኝ›› ሲሉ ይገልፁታል የመግጠም ችሎታቸውን መሠረታዊ መነሻ። ድምፁ ከጥበቃው የወጣ መስሏቸው ነበር። ሆኖም ቀና ብለው ሲያይዋቸው ጥበቃው እያወሩላቸው የነበረው ሌላ ወግ ነው። ወደ ውስጣቸው ሲያዳምጡ መንፈስ ስለመሰላቸው በሆዳቸው 10 ጊዜ ያህል በስመአብ … ብለዋል። ሆኖም ድምፁ ባለማቋረጡ “ምንድነው የምፅፈው?” ብለው በልባቸው ራሳቸውን ጠየቁ።
‹‹መንፈሱ ‘ግጠም’ ሲለኝ ከት ብዬ ሳቅሁ። የሳኩት ከዚህ ቀደም ግጥም እንኳን ልጽፍ አንብቤ እንኳን ስለማላውቅ ነበር›› የሚሉት አቶ ሽመልስ በወቅቱ በተገለጠላቸው ተስጥኦ ፊታቸው በደስታ በርቶና 36ቱም ጥርሶቻቸው ፈክተው እጅግ ተደስተው ነበር። በሽሜ ሳቅም ጥበቃው እጅግ ይደነግጣሉ። እያወጓቸው የነበረው ወግ የሚያስቅ ስላልነበረም ያመማቸው ሁሉ መሰሏቸዋል። “ልጄ ምን ነካህ፣ ምን ሆነህ ነው የምትስቀው? እኔ እያወራሁልህ ያለሁት ወሬ የሚያስቅ አይደለም።” ሲሉም በአግራሞት እያዩ ጠይቀዋቸዋል። ቢነግሯቸው እንደማይገባቸው የተረዱት አቶ ሽመልስ፣ በዚሁ ቅጽበት ከመሬት ያገኝዋትን ስክሪፕቶ ያወጡና ወተት ሲገዙ በተሰጣቸው ቢል ጀርባ፦
ትምህርት በጨረስኩ በ14 ዓመት፣
አዲስ ሥራ ያዘ የኔ ጭንቅላት፣
ወዳቂዋን ብዕር አርጎ ምክንያት።
ሲሉ ስለ ተስጥኦቸው የመጀመሪያውን ግጥም ጻፉ። ግጥሙን ሲጽፉ የመጣላቸውን ሀሳብ በቃላቸው እያነበነቡ መሆኑ ደግሞ ጥበቃውን አስገርሟቸው አእምሯቸው የተነካ መስሏቸውም ነበር። ለጠቅ አድርገውም፦
በትምህርት ውጤቴ ዕድሌ ተጣሞ፣
መቋቋም አልቻለም ኑሮዬን ፈፅሞ፣
ለካስ አምላክ እኔን ያየኝ ነበር ቆሞ።
ዓይቶ እስከ ዛሬ ያልሰጠኝን መላ፣
ዛሬ በጥበቡ አመጣው ከኋላ፣
በወደቀው ብእር አድርጎ ከለላ።
ይሄን ምክንያት አድርጎ መወጣጫ ዛፍ፣
ሊያገባኝ ነው መሰል ወደ አዱኛ ቤት።
ፈጣሪን መለመን እንዳትሰለቹ፣
የእሱ በረከት ነው በምድር ላይም ምቹ
ከምስጋና በቀር አይፈልግም ጉቦ፣
ማንም በንፁህ ልብ ቢጠይቀው ቀርቦ፣
ማውጣቱን ይችላል ከችግሩ ስቦ።
ብለውም ለፈጣሪያቸው ምስጋና አቅርበውበታል።
ጥበቃው በዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዩት ችሎታቸው ደጋግመው ያማትቡ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሽሜ እንዳወጉን ከዚህ በኋላ ንግግራቸው ሁሉ ግጥም እስኪሆን ድረስ ባዩት አጋጣሚ ሁሉ ያንቆረቁሩት፣ ይቀኙት ጀመር።
አሁን ላይ ባዩት አጋጣሚ በቃላቸው የሚያነበንቡትን ጨምሮ በወረቀት የፃፏቸው አያሌ ግጥሞች አላቸው። ‹‹እግዚአብሔር የፈቀደ ዕለት አሳትማቸዋለሁ የሚል ተስፋ አለኝ›› ይላሉም። ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሹፌርነት ለመቀጠር የፈለጉበትም ምክንያት አንድ ቀን በሙያው ለመሥራትና ኑሮዬን ለማሻሻል የሚያስችለኝ ገቢ ያስገኝልኛል ብለው በማሰብ እንደነበርም ይጠቅሳሉ። በተለይ ተስጥኦው የተገለጠላቸው ሰሞን በልጅነቴ መሆን የምፈልገውንና የ12ኛ ክፍል ውጤቴ ያደናቀፈብኝን ምኞት ያሳካልኛል ብለው አስበው እንደነበርም ነግረውናል። የገቡ ሰሞን በነበሩት ዓመታት ግጥማቸው ድርጅቱ በሚያሳትመው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ይወጣላቸው ነበር። በድርጅቱ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲኖሩም መድረክ ላይ ወጥተው ሠራተኛውን በግጥማቸው ፈታ፣ ዘና ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ደሞዛቸው ስምንት ሺህ (8‚000.00) ብር የደረሰ ሲሆን፤ ሲቀጠሩ ያገኙት የነበረውን የ500 ብር ደመወዝ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይደጉሙ ዘንድ አስችሏቸዋል። ግጥሙ ከአእምሯቸው ይጠፋል የሚል ስጋት ባይኖርባቸውም “ግጠም … ግጠም …” የሚል ፍላጎታቸውን ለማርካት በየዕለቱ ልምምድ ያደርጋሉ። በተለይ ለሥራ ሠራተኞችን ጭነው ሲወጡና ሲመለሱ የጨዋታ መዳረሻቸው ግጥማቸው ነው። ግጥማቸው ማልደው በሚያመላልሷቸው ጋዜጠኞች ይወደዱላቸዋል። “ከማይረባ ቁርስ አንድ የሽሜ ግጥም …” ተብለው ይሞካሹ ዘንድም ምክንያቱ ይኸው ነው።
ሾፌር ጋዜጠኛው አቶ ሽመልስ ‹‹የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ እዚህ ድርጅት ውስጥ ነው የሚሰሩት። በተደጋጋሚ ወደ ማህበሩ ብቅ እንድልና ተስጥኦዬን እንዳዳብር መክረውኛል›› ይላሉ። ሆኖም የተሰማሩበት የሹፍርና ሙያ ለዚህ የሚሆን ጊዜ ሊሰጣቸው አልቻለም። በጣም ሥራ ስለሚበዛባቸው እዚህም ሆነ ሌሎች የግጥም መርሐ ግብር ዝግጅቶች ላይ መሄድ፣ ሥራቸውን ማቅረብ፣ እንዳሰቡትም ሙያውን የገቢ ምንጭ ማግኛ ማድረግ አልቻሉም። አሁን ላይ እየሰሩት ያለውን የሹፌርነት ሥራ ባይጠሉትም መሆን የሚፈልጉትን መሆን ባለመቻላቸው ግን ዛሬም ይቆጫሉ። ያኔ በወዳጆቻቸውና መምህራኖቻቸው “ውጤትህን አስመርምር” ሲባሉም ባለማስመርመራቸው በእጅጉ ይፀፀታሉ።
አቶ ሽመልስ ቁጭቱና ፀፀቱ ዛሬም ከሆዳቸው የወጣ አይመስልም። ያኔ ምን መሆን ነበር የፈልጉት ስንላቸው ‹‹አታምኑኝም፣ በፍፁም ሹፌር ሆኜ እቀራለሁ ብዬ አላሰብኩም። ዓላማዬ እስከ መጨረሻው በትምህርት መግፋትና የሕክምና ባለሙያ መሆን ነበር። ያውም ደግሞ ስፔሻሊስት ባለሙያ›› በማለት የመለሱልን ሲሆን፤ ዛሬም የፈለጉትን ባለመሆናቸው ዓይናቸው እንባ እንዳቆረዘዘ ትክዝና እዝን ብለው አጫውተውናል።
አቶ ሽመልስ እንደ ብዙዎቻችን ያሰቡት ባለማሳካቱም ዓይናቸው እንባ አቆርዝዞ ሲታዩ ያሳዝናሉ። በእጅጉም አንጀት ይበላሉ። ነገር ግን ያሰቡትን ለማሳካት የሚያደርጉት ሩጫና ጥረት ከእሳቸው አልፎ ለሌላውም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ ያስደስታል።
ግጥምን እንደ ቀላል ባፉ እሚነሰንስ፤
የፕሬሱ ሹፌር ጠይሙ ሽመልስ፤ ሲሉም ያሞካሹታል።
ደሞስ ማን ያውቃል፣ የጥበብ ጥሪ’ኮ ድንገቴ እንጂ አዋጅ አይነግርምና አቶ ሽመልስ ያሰቡት ሁሉ ሆኖ የምናይበት ቀን ቅርብ ይሆን ይሆናልና፤ ለቃል-ግጥም ገጣሚው ሽሜ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን!!!
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014